የአልጀርሱ “የሰላም” ስምምነት፤ የኢትዮጵያና ኤርትራ 1600 ኪሎ ሜትር ድንበር እንደገና የመካለል ጉዳይና የወልቃይት ታሪካዊ ጥያቄ!

የወያኔ የበታችነት ስሜትና የሻዕብያ የበላይነት ስሜት የወለደውን የባድመውን ጦርነት ተከትሎ «የኢትዮጵያ እና የኤርትራን የድንበር ላይ ጦርነት» በሚል በአለማቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ የሚጠራው በኢትዮጵያና በመለስ ዜናዊ ደብዳቤ አገር ሆና እውቅና በተቸራት በኤርትራ መካከል የተፈጠረውን በጠላትነት የመፈላለግ ስሜት ለማስወገድ በሚል በ1993 ዓ.ም. በአልጄሪያ መዲና አልጀርስ ላይ በሁለቱ አገዛዞች መካከል «የአልጀርስ የሰላም ሥምምነት» ውል መፈረሙና የመለስ ዜናዊ አገዛዝ ስምምነቱን ሙሉ በሙሉ መቀበሉ ይታወቃል። ሆኖም ግን ስምምነቱ እስከዛሬ ድረስ ተግባራዊ ሳይሆን ቆይቷል።

የአልጀርሱ የመለስ ዜናዊና የኢሳያስ አፈወርቂ ስምምነት ለኢትዮጵያ የማይጠቅም፤ ይልቁንም በታሪካችን ከሁለተኛ አገር ጋር ተካሄዱ ስምምነቶች ሁሉ ኢትዮጵያን እጅጉን የሚጎዳ ቢሆን ቅሉ እስከዛሬ ድረስ ግን ተግባራዊ ያልሆነበት ምክንያት ኢትዮጵያን ስለሚጎዳ ሳይሆን ትግራይን በሚጠቅምበት መንገድና አማራን በሚጎዳበት አኳኋን እንዲተገበር ቅድመ ሁኔታ ስለተቀበጠበት ነው። በዚህ ጽሑፍ የአልጀርሱን ስምምነት ምንነት፣ ከስምምነቱ ውጭ ወያኔ ያስቀመጠው ቅድመ ሁኔታና ከአማራ አንጻር በተለይም ከወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምትና ሑመራ ታሪካዊ ይዞታ አኳያ የደቀነውን ፈተና እንፈትሻለን።

የአልጀርስ የሰላም ስምምነት እየተባለ የሚታወቀውና የኢትዮጵያ ፍላጎት ሳይካተትበት መለስ ዜናዊና ኢሳያስ አፈወርቂ በታህሳስ 3 ቀን 1993 ዓ.ም. በአልጀርስ ከተማ የተፈራረሙት ውል ጠቅለል ተደርጎ ሲታይ የከፋ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ጥፋትን ለማስቆምና የኢትዮጵያ እና ኤርትራ የድንበር ጦርነትን ለመቋጨት ተብሎ የተፈረመ ሲሆን ዝርዝር ውሉ ግን 6 አንቀጾችና አራት መሰረታዊ ግቦች ነበሩት። የስምምነቱ አራቱ መሰረታዊ ግቦች፤

1. በሁለቱ ሀገራት መካካል የነበረውን የባላንጣነት መንፈስና በጠላትነት መፈላልግ ማቆም፤ ሀገራቱ ከዛቻ እና የሃይል እርምጃ እንዲቆጠቡ ማድረግ፤

2. ከአልጀርሱ የሰላም ስምምነት ቀደም ብሎ በሰኔ 1/1992 ዓ.ም. የተደረሰውን በባለንጣነት ያለመተያየት ስምምነት እንዲከበር እና ወደፊትም በተግባር እንዲፈጸም ዋስትና መስጠት፤

3. በእስር ያሉ የጦር ምርኮኞች እና ግለሰቦች ተለቀው ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ማስቻል፤

4. ሁለቱ ሀገራት በግዛቶቻቸው ውስጥ ላሉ የሌላኛው ወገን ዜጎች ሰብአዊ እንክብካቤ እንዲያደርጉ ድልድልይ መሆን ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪ የአልጀርሱ ስምምነት ከፍ ሲል የተጠቀሱትን ግቦች በየተራ ለማሳካት ስምምነቱ «ነጻ» የድንበር እና የካሳ ኮሚሽኖች እንዲቋቋሙ አቅጣጫ አስቀምጧል። ይህን ተከትሎም 5 አባላት ያሉት የኢትዮ ኤርትራ የድንበር ኮሚሽን ተቋቁሞ የራሱን ምርመራ በማድረግ አለመግባባት የፈጠሩ የድንበር ቦታዎች ቢኖሩ ለየትኛው ሀገር እንደሚገቡ ለመወሰን እንዲችል ተደርጎ በወቅቱ ከስምምነት ላይ መደረሱን የአልጀርሱ ስምምነት ያወሳል።
ሁለቱ አገራት ለድርድር ሲሰየሙና ተወካዮችን ሲሾሙ ኢትዮጵያ 14 ተወካዮችን የሾመች ሲሆን 11ዱን ተወካዮች ግን እጅግ ብዙ ገንዘብ በማውጣት ከውጭ አገራት የቀጠረታቸውና [በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ለድርድሩ 9 ሚሊዮን ዶላር የድሃ ገንዘብ አባክናለች] ተቀጣሪዎቹ ከመለስ ዜናዊ በተሰጣቸው አቅጣጫ መሰረት በመንቀሳቀሳቸው ለኢትዮጵያ ተቆርቋሪነት ሆነው እንዳይከራከሩ ብቻ ሳይሆን ሞያቸውን እንኳ በትክክል እንዳይሰሩ አግዷቸዋል።

በስምምነቱ ኢትዮጵያን የወከሉት ሶስቱ አባላት ደግሞ የትግራይ ተወላጆች ሲሆኑ እነዚህ ነውረኞች ባብዛኛው ይከራከሩ የነበረው ለኤርትራ ነበር። እነዚህ ጉዶች የኢትዮጵያን ድንበር ከተሰረዘው የቅኝ ግዛት ውል መቅዳታቸው ሳያንስ የቅኝ ግዛቱ ውል የኢትጵያን ድንበር ከምስራቅ 60 ኪሜ ገባ ብሎ ቢደነግግም እነሱ ግን የምስራቅ ጠረፍ የሚባለውን ከደሴቶቹ ሳይሆን ባሕሩ ከሚያልቅበት የየብሱ ጫፍ እንዲጀምር ተከራክረዋል፣ ከዚህም በላይ ቡሬን ድንበር አድርጎ በማካለል ከ60ኪሜ በላይ ወደ ኢትዮጵያ ዘልቀዋል። የነዚህ ነውረኞች ጉድ በዚህ አያልቅም። ኢትዮጵያን የወከለው የነዚህ ነውረኞች ቡድን «ጾረና የኤርትራ ነች» ብሎ ድርቅ በማለቱ የኢትዮጵያ ካርታ ብቻ ሳይሆን የኤርትራ ካርታም ልዩ ቅርጽ ሠርቶ እንዲታይ አድርገዋል። በዚህም የተነሳ ከኢጣልያ በኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ተጋድሎ የተቀላቀለችው ኤርትራ በነ መለስ ዜናዊ ‹‹የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት›› ተብላ ስትገነጠል ‹‹ባለህበት እርጋ›› የተሰኘው የድህረ ቅኝ ግዛት መርሕ እንኳ አልተከበረም። ለዚህም ነበር ፕሮፌሰር ክርስቶፎር ክላፋም ‹‹ኢትዮጵያ ሽንፈትን ከድል መንጋጋ ፈልቅቃ አወጣች›› ሲሉ ወቅቱን የገለጹት።

እነ መለስ ዜናዊ ኤርትራን ያስገነጠሏት «የራስን ዕድል በራስ መወሰን እስከመገንጠል» በሚለው የጸረ ቅኝ ግዛት ትግል መመሪያ እየተነዱ ነው። የራስን ዕድል በራስ መወሰን እስከመገንጠል የሚባለው መብት በሕግ የሚረጋገጠው በሦስት መንገዶች እንደሆነ የሕግና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን ይገልጻሉ። የመጀመሪያው አገሪቷ በቅኝ ግዛት ተይዛ ከነበር፣ ሁለተኛ፡- በባዕድ ጦር ትተዳደር ከነበር እና ሦስተኛ፡- ብዙ ዘሮች ያሉበት አገር ውስጥ አንዱን ዘር ካገለለና ከጨቆነ – ተጨቋኟ አገር መገንጠል ሲሉ ይሞግታሉ። ኤርትራም የተገነጠለችው ሕወሓት ኤርትራን የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ናት ብሎ በመመስከሩ ነው።

አገርና መንግሥት ቢኖር ኖሮ ግን እውነታና ሕጋዊነት የጎደለውን ይህን ነውረኛነት እስከ አለማቀፍ ችሎት ማቅረብ ይቻል ነበር። ሌላው ቀርቶ ኤርትራ በተገነጠለችበት ወቅት አገልግሎት ይሰጥ የነበረውን የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ቁጥር 253 እና የአፍሪካ አንድነት ቻርተር አንቀጽ ሁለትን በመጣስ በኢትዮጵያ በመንግሥትነት በተሰየመው ነውረኛ ቡድን ያላሰለሰ ጥረት የአፍሪካ አንድነትና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅቶች የኤርትራን መገንጠል ማጽደቅ ሳያስፈልጋቸው ተቀብለውታል።

የድንበር ውዝግቡ በወያኔ አለመፈለግ የተነሳ የኢትዮጵያን የባሕር በር እንዲዘጋ ቢደረግም፤ ጦርነቱ የተካሄደባቸውን የባድመን፣ የኢሮብን፣ የጾረናን፣ ከፊል አፋርንና ሌሎችም የኢትዮጵያ ግዛቶችን ለኤርትራ አሳልፎ የሚሰጥ ውዝግብ እንደመሆኑ ወያኔ ዘጠኝ ሚሊዮን ዶላር ከፍሎ እንዲካሄድ ያደረገው በ285 ቀናት ውስጥ የተጠናቀቀው ሙግትና የጊዜ ሰሌዳው ራሱ የስምምነት ተብዮውን ጤነኛነት አጠያያቂ ያደርገዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ድርድሩ የተካሄደባት አገር አልጀሪያ የኤርትራን መገንጠል ከጥንስሱ ጀምሮ ትደግፍ የነበረች ከመሆኗም ባሻገር የድርድሩ አጋፋሪ የነበረው የወቅቱ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሊቀመንበር የነበረው ሚስተር አብዱል አዚዝ ቡተፍሊካ ለኤርትራ መገንጠል የሀገሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በነበሩበት ጊዜ እግሩ እስኪላጥና ወገቡ እስኪጎብጥ የሰራ ጸረ ኢትዮጵያ ነው። ሌላው ቀርቶ እነ አሕመድ ቤን ቤላ ጭምር አብረው አዲስ አበባ ውስጥ እንዲቋቋም ያደረጉትን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ከኢትዮጵያ እንዲነሳ ባይሳካለትም ጥሪ አቅርቧል።

በሕግ አንድ ሕግ ወይንም ስምምነት የሚዘጋጅበት መንገድ ሕጉ ወይንም ስምምነቱ ከሚኖረው ዋጋ ጋር እኩል ይሆናል የሚል ታዋቂ መርሕ አለ። የአልጀርሱ ስምምነት ግን ይህን መሰረታዊ የሕግ መርሕ ጥሶ በስምምነቱ አንቀጽ ሁለት ላይ ጥሊያን ራሱ አምስር ጊዜ ያፈረሰውን ውል በመተላለፍ የቅኝ ግዛት ሕጎችን ተመስርቶ ኮሚሽኑ ውሳኔውን እንደሚያስተላልፍ በአልጀሪያ ኮሚሽኑ ተሰየመ። ለአገር አሳቢ ትውልድ ቢፈጠር ይህን የዘቀጠ ኢሕጋዊነት እንዳያስተካክል በስምምነቱ አንቀጽ 2 (15) ላይ ኮሚሽኑ የሚሰጠው የወሰን እና ማካለል ውሳኔ የመጨረሻ እና ገዢ እንደሚሆን ተደነገገ። በዚህ ኢሕጋዊነት ላይ ተመስርቶ የተደረሰው የአልጀርስ ስምምነት የወለደው የድንበር ኮሚሽን በ1996 ዓመተ ምሕረት የተሰየመበትን ውሳኔ አስተላለፈ። በዚህም ውሳኔው ሁለቱ ቡድኖች በይገባኛልነት ይከራከሩባቸውን በነበሯቸው ቦታዎች ላይ ብይኑን ሰጠ።

እንደሚታወቀው ሁለቱ ቡድኖች በይገባኛልነት ከተፋለሙባቸው ቦታዎች መካከል አንዷ የነበረችው ባድሜ በኮሚሽኑ ውሳኔ የኤርትራ ግዛት እንድትሆን ተፈረደ። ይህ በተወሰነበት ጊዜ ወያኔ ያለ ይግባኝ የተቀበለውን ስምምነት በመርሕ ደረጃ ተቀብየ በቅድሚያ 1600 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የኢትዮጵያና የኤርትራ ድንበር ይካለል፤ ተጨማሪ ውይይትም በሁለቱ ሀገራት መካከል እንዲደረግ እሻለሁ አለ። ሻዕብያ ግን የወያኔን ጥያቄ ሳይቀበለው በመቅረቱ፣ የሁለቱ ቡድኖች ድንበር ለተጨማሪ 16 ዓመታት የፍጥጫ ስፍራ እንዲሆን ሰበብ ሆነ። ወያኔ ባለፉት 16 ዓመታት ውስጥ ከኤርትራ ጋር 1600 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውን ድንበር ለማካለል ሀምሳ ጊዜ ያህል ለኤርትራው አገዛዝ ጥሪ አቅበን ቢለንም ሻዕብያ ግን የአልጀርሱን ስምምነት ተከትሎ የተሰጠው ውሳኔ እንዲከበር በመፈለጉ የወያኔ ፍላጎት ሳይሳካ ቀርቷል።

ከዚያ በኋላ የተለወጠው ነገር ባለፉት አራት ወራት ውስጥ የተከሰተው ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኢሕአዴግ ፓርላማ ፊት ቀርቦ መንበረ ሥልጣኑን በተቆናጠጠ ዕለት አጀንዳዬ ብሎ ካወጃቸው ጉዳዮች መካከል ከኤርትራ ጋር ሰላም ማውረድ አንዱ እንደሆነ ጠቅሶ ነበር። ለዚህ የዐቢይ አሕመድ ግብዣ ለሳምንታት የዘለቀ ምላሽ ከኤርትራ በኩል ጠፍቶ ከሰነበተ በኋላ የኤርትራው መረጃ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል ለአንድ የውጭ ሜዲያ የዐቢይ አሕመድን ግብዣ አስመልክቶ ለቀረበለት ጥያቄ «ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን አለመግባባት ልትፈታ የምትችለው የአልጀርሱ ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን ስትፈቅድ ብቻ!» ሲል የሰነበተውን የሻዕብያን አቋም አሳወቀ። ይህ የኤርትራ ግብረ መልስ በተሰማ በቀናት ውስጥ መደበኛ ስብሰባው ላይ ከትሞ የሰነበተው የዐቢይ አሕመድ የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ፤ ኢትዮጰያ ለሁለቱ ሀገራት መፃኢ -ሰላም ሲባል የአልጀርስ ስምምነትን እንደምትቀበል መወሰኑን በሰበር ዜና አበሰረ። በዚህ ጊዜ ነው እንግዲህ ከአስመራው አገዛዝ ለዐቢይ አሕመድ ጥሪ አዎንታዊ ምላሽ የተሰማው።

የዐቢይ አሕመድ የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የሆነው ወያኔ አዲስ አበባ ላይ የአልጀርሱን ስምምነትን ሙሉ ለሙሉ እንደሚቀበል አብሮ ወስኖ ወደ ምሽጉ መቀሌ ከገባ በኋላ ግን አዲስ አበባ አብሮ ያወጣውን መግለኛ ተቃርኖ አዲስ መግለጫ አወጣ። ይህ የቅሚያና ግድያ ድርጅት ከምስረታው ጀምሮ ከበርካታ ግራ አጋቢ ነገሮች ጋር የተወሳሰበ ነውረኛ ድርጅት ነው። ነው ጌጡ የሆነውና ከሽፍትነት ወደ «መንግሥትነት» የተለወጠው ወያኔ ባለም ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚባል አኳኋን ከቀናት በፊት ያወጣውን የራሱን ድርጅታዊ ውሳኔ ከቀናት በኋላ ራሱን ተቃውሞ መግለጫ ያወጣ ብቸኛው ድርጅት ለመሆን በቅቷል። በዚህ የተቃውሞ መግለጫቸው ከስልጣን እንደተገለሉም አንስተዋል።

አንድ እውነት አለ። የትኛውም ኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄድ ለውጥ [ጥገናዊም ሆነ መሰረታዊ] ከሚገባው በላይ ኢትዮጵያን የተቆጣጠረውና የመከላከያውን፣ ደህንነቱን፣ ኢኮኖሚውን፣ ውጭ ጉዳዩንና ባጠቃላይ የአገራችንን ሥልጣን ሁሉ የሰበሰበውን ወያኔን የሚጎዳ ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያን ለኢትዮጵያውያን ለማድረግ የሚደረግ የትኛውም እንቅስቃሴ የወያኔን ቅጥ ያጣ ዘረፋና ቅሚያ፣ ግድያና ስቃይ ስለሚቀንስ የትግራይ ፋሽስቶች ለግል ጥቅማቸው የመሰረቱት የቅሚያና የስርቆት ድርጅት፤ ኢትዮጵያን ረግጠውና አደንቁረው ሊገዙበት፤ ሐብቷን ሊበዘብዙበት፤ እንቦቀቅላ ልጆቿን ሊረሽኑበት በወንጀል ያቋቋሙት የሌብነት፣የግድያና የሙስና ማሕበር የሆነውን ሕወሓት ቢያስከፋ የሚያስደንቅ አይደለም።

ሌላውና ገራሚው የነነውር ጌጡ መግለጫ ሲገድሉንና ሲዘርፉን የኖሩት ነውረኞቹ እነ አባይ ፀሐዬና ስብሓት ነጋ በክብር እንዲሸኙላቸው የጠየቁበት መግለጫቸው ነው። አባይ ፀሐዬ የሩቁን እንኳ ብንተወው በቅርቡ ከድሃው የኢትዮጵያ ሕዝብ 77 ቢሊዮን ብር የዘረፈ ገፋፊ ነው። ስብሓት ነጋም የሩቁን ብንተወው የቅርቡን ብናይ በልጁ ስም ግዙፉን የጎተራ አደባባይ ለአምስት አመት ኮንትራት በ600 ሺህ ብር እንደወሰደው ፎርቹን ጋዜጣ ይፋ አድርጎታል። የ«አክሊል ክሬቲቭ ኤጄንሲ» ባለቤት የሆነው የስብሓት ልጅ [ተከስተ ስብሀት ነጋ]፤ በአካባቢው ያለን 4000 ስኩዌር ሜትርና በቢሊዮኖች የሚገመት መሬት እንደ ስጦታ ነው የወሰደው።

አገርና ሕግ ቢኖር ኖሮ እነዚህ ወያኔ በክብር እንዲሸኙለት የሚጠይቃቸው ሁለት ነውረኞች ለሀያ ሰባት አመታት ሙሉ የትግራይ ወታደሮችን እያሰማሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሐን ደም ባፈሰሱበት፣ በየማጎሪያ ቤቱ ሲፈጸም ለኖረው ሰቆቃ፣ በአገራቸው ውስጥ ስደተኛ እንዲሆኑ ለተደረጉ ሚሊዮኖች ስቃይና በስናይፐር ለተገደሉ የአማራና ኦሮሞ ወጣቶች ሕይወትና ኢትዮጵያን ሲገፏት ለኖሩት የጭካኔ ተግባር ተጠያቂ እንዲሆኑ እጃቸው የኋሊት በመጫኛ ታስሮ እውነተኛ ችሎት ፊት ቀርበው ለፈጸመው ወንጀል ይቀጡ ነበር።

ሕወሓት በክብር እንዲሰናበቱለት የሚጠይቃቸው እነዚህ በኢትዮጵያ ኪሳራ የአገር ካዝና አራቁተው የኢትዮጵያን ድሃ አጥንት የጋጡ ጨካኝ ወሮበሎችን ነው። ለነገሩ በቤተ ወያኔ አባይና ስብሃት ኢትዮጵያን ቢዘርፉ ገንዘቡ በመዋለ ንዋይ ስም ወደ ትግራይ እንደሚተላለፍ ስለሚቆጠር ኢትዮጵያን የሚጋጥጡ የሕወሓት ዘራፊዎች ለትግራይ እንደ ባለውለታ ቢቆጠሩ አይፈረድባቸውም፤ የታገሉትና እየታገሉ ያሉት ኢትዮጵያን ገፈው ትግራይን ለማልበስና የተስፋይቱን ምድር ለመመስረት ነውና።

መቀሌ ሄዶ መግለጫ በማውጣትና የአልጀርሱን ስምምነት የዐቢይ አሕመድ መንግሥት እንዳይተግብ ሲቃወም የሰነበረው ወያኔ ከሰሞኑ ደግሞ አልሸሹም ዘወር አሉ ሆኖ «የአልጀርሱን ስምምነት ከነሙሉ ማዕቀፉ ተግባራዊ ለማድረግ መወሰኑ በሁለቱ ሃገራት ድንበር መካከል የቆየውን ዝምታ የሰበረ ነው» ሲል ሌላ መግለጫ አወጣ። ወያኔ «የአልጀርሱን ስምምነት ከነሙሉ ማዕቀፉ ተግባራዊ እንዲሆን» የሚለን እስካሁን ድረስ ሲጠይቁት የኖሩትን የ1600 ኪሎ ሜትር የኢትዮጵያና የኤርትራ የድንበር ማካለል ተግባር ነው።

ሻዕብያና ጀብሐ ጫካ በገቡ ወቅት ባሰመሩት መስመርም ሆነ በመለስ ዜናዊ ቡራኬ ኤርትራ አገር ስትሆን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በተመዘገበው የኤርትራ ካርታ መሰረት ኤርትራ በደቡብ በኩል ድንበር የምትጋራው ከበጌምድር/ጎንደር ጋር ሲሆን የሰቲት/ተከዜ ወንዝ ኡምሀጀርን ከሚነካበት [የሁመራ ሰሜናዊ ጫፍ] አንስቶ የሰቲት/ የተከዜ ወንዝ የጋሽ ባርካን ደቡባዊ ጫፍ እየታከከ ሄዶ የባርካንን ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ የሚነካበትን ስፍራ በማካለል፤የተከዜ ወንዝ ጋሽ ባርካን ለመጀመሪያ ጊዜ እስከከሚነካበት ቦታ ድረስ ሲዘረጋ፤ በትግራይ በኩል ደግሞ የመረብ/ የጋሽ ወንዝ ወደ ጋሽ ባርካ ምድር እስከሚገባበት ድረስ በተሰመረው ቀጥተኛ መስመር እየተካለለ ሄዶ ምስራቅ ትግራይንና ደጋማውን የኤርትራ ክፍል እስከሚለየው የመረብ ወንዝ ይዘረጋና በመጨረሻም በደቡብ ምስራቅ በኩል እስከ ደናክል ሰርጥ ድረስ ይደርሳል። ይህ ድንበር 1600 ኪሎ ሜትር ያህል ይረዝማል ተብሎ ይገመታል።

ከ1990-92 ዓ.ም. የተካሄደው በሻዕብያና በወያኔ መካከል የተነሳው ጦርነት የተቀሰቀሰው 260 ኪሎ ሜትር በሚሸፍነው የተከዜ ወንዝ ጋሽ ባርካን ለመጀመሪያ ጊዜ ከሚነካበት ቦታ የመረብ/ የጋሽ ወንዝ ወደ ጋሽ ባርካን ምድር እስከሚገባበት ድረስ በተዘረጋው ቀጥተኛ መስመር በሚካለለው የባድሜ የይገባኛል ጥያቄ ነው። ከባድመ ጦርነት በኋላ ግን የወያኔ ቀዳሚ አጀንዳ የነበረው ጦርነቱን ለመቋጨት የተሰየመው የአልጀርሱ ስምምነት የደረሰበትን ብያኔ የመፈጸም ጉዳይ ሳይሆን ከጦርነቱ መነሻና ከአልጀርሱ የድንበር ኮሚሽን ጋር ምንም ግንኙነት የሌለውን 1600 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውን የኢትዮጵያንና የኤርትራን ድንበር የማካለል ጉዳይ ነበር። የባድመ የይገባኛል ጥያቄ ወለደው የተባለውን ደም አፋሳሹን ጦርነት ከመቋጨት ይልቅ ከጦርነቱ ጋር ምንም ግንኙነት የሌለውን 1600 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የኢትዮጵያንና የኤርትራን ድንበር ወያኔ እንደገና ማካለል የፈለገበትን እንቆቅልሽ ብዙ ሰው የተገነዘበው አልመሰለኝም።

ወያኔን እንደ እጁ መዳፍ የሚያውቀውና ሱሪ ያስታጠቀም ባንድ ወቅት ብዙ ያልተመነዘረ አንድ ጥቅል ሀሳብ ሰንዝሮ ነበር። የሻዕብያው አምበል ኢሳያስ አፈወርቂ በጦርነቱ ወቅት እ.ኤ.አ. ፕሪኒስተን ዩኒቨርሲቲ ተገኝቶ ባደረገው ንግግር ወያኔ ከሻዕብያ ጋር ጦርነት ውስጥ ከገባባቸው ምክንያቶች አንዱ የትግራይን ድንበር እንደገና ለማካለልና አለማቀፋዊ እውቅና የማሰጠት አላማን ጭምሮ አንግቦ መሆኑን ነግሮን ነበር። ይህ ኢሳያስ ስለጦርነት የተናገረው አስተያየት ሚዛን የሚደፋው ከጦርነቱ በኋላ በተሰየመው የአልጀርስ የድንበር ኮሚሽን ወያኔ እንደ አሰብ አይነት የኢትዮጵያን ጥቅሞች ከማንሳት ይልቅ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር የምትዋሰነው 1600 ኪሎ ሜትር ድንበር እንዳላትና ይህ 1600 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው ድንበርም እንዳዲስ እንዲካለል ጦርነቱን ካስነሳው የባድመ ጉዳይ በላይ አብዝቶ ጠየቁን ስናጤን ነው። ወያኔ የባድመ ጥያቄ ወለደው የተባለውን ጦርነት ለመዳኘት የተሰየመው አለማቀፉ የድንበር ኮሚሽን 1600 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውን የኢትዮጵያንና የኤርትራን ድንበር የማካለል ስራ እንዲሰራ ለማግባባት ደጅ ያልጠናው የምዕራብ አገር የለም።

ከፍ ሲል ሻዕብያና ጀብሐ አገራችን የሚሉት፤ ወያኔም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስጸድቆ አገር ያደረጋት ኤርትራ የደቡብ ምዕራብ ድንበሩ የሰቲት/ተከዜ ወንዝ የኡምሀጀር ሸለቆን ከሚያዋስንበት [የሑመራ ሰሜናዊ ጫፍ] አንስቶ የሰቲት/ የተከዜ ወንዝ የጋሽ ባርካን ደቡባዊ ጫፍ እያካለለ ለመጀመሪያ ጊዜ የባርካንን ምድር እስከሚነካበት ድረስ ነው ብለናል። ይህ አዋሳኝ ቦታ ደግሞ እስካሁን ድረስ በሻዕብያ/ጀብሐዋ ኤርትራም ሆነ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በታወቀችዋ ኤርትራ ካርታ ላይ የሚገኘው በጌምድር/ስሜን ጠቅላይ ግዛት ወይንም በጎንደር ክፍለ ሀገር ስር ነው። ይህ ቦታ ወያኔ በ1983 ዓ.ም. ተከዜን ተሻግሮ በወረራ የያዘውና «ምዕራብ ትግራይ» ሲል የፈጠረውን የወልቃይት፣ የጠገዴ፣ የጠለምትና የሑመራን ምድር ያቀፈ ነው።

እነዚህን በጌምድር/ስሜን ጠቅላይ ግዛት ወይንም በጎንደር ክፍለ ሀገር ስር እንደሆኑ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጭምር የሚታወቁ የወልቃይት፣ የጠገዴ፣ የጠለምትና የሑመራ መሬቶች የትግራይ ማድረግና የትግራይ ሪፑብሊክ ሲመሰረት አካሉ የሚሆኑት በባድመ ጦርነቱ አሳቦ ሙሉውን 1600 ኪሎ ሜትር የሚረዝመውን የኢትዮጵያና የኤርትራ ድንበር በተባበሩት መንግሥታት ማዕቀፍ ስር እንደገና በማካለል ከቀድሞ ይዞታቸው ከጌምድር/ስሜን ጠቅላይ ግዛት ወይንም የጎንደር ክፍለ ሀገር ከ1983 ዓ.ም. በኋላ በተፈጠረው ትግራይ ክልል ተካተው የኤርትራ ደቡብ ምዕራባዊ ድንበር ሙሉ በሙሉ በግፍ ከተፈጠረው ምዕራብ ትግራይ ጋር ብቻ ከተዋሰነ ነው። ለዚህ አላማ ነበር የባድመ ጥያቄ ወለደው የተባለውን ጦርነት ለመዳኘት የተሰየመውን የድንበር ኮሚሽን ያልተሰየመበትን 1600 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውን የኢትዮጵያንና የኤርትራን ድንበር እንዲያካልል አብዝተው የጠየቁትና አሁንም ድረስ እየጠየቁ የሚገኙት።

እነሱም እድለኛ ናቸው የጦርነቱ መነሻ 260 ኪሎ ሜትር በሚሸፍነው የኢትዮጵያና የኤርትራ ድንበር ላይ በተፈጠረ የይገባኛል ጥያቄ ሆኖ ሳለ «የአልጀርሱን ስምምነት በመርህ ደረጃ ተቀብለናል» እያሉ ከስምምነቱ ጋር ምንም ግንኙነት የሌለውን 1600 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውን፤ ምንም ጥያቄ ያልተነሳበትንና ኢሳያስ እንዳለው በደንብ የሚታወቀውን የኢትዮጵያንና የኤርትራን ድንበር እንደገና የማካለል ጉዳይን ከሁሉ በፊት ከኤርትራ ጋር ያላቸውን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸው አልፋና ኦሜጋ ለምን አደረጉት ብሎ ያጠየቃቸው ሰው የለም።

ዐቢይ አሕመድ ዛሬ ከኢሳያስ ጋር እያደረገው ባለው ወዳጅነትም ለወያኔ ወያኔ የተገባለት ቃልም ጦርነቱን የወለደውን የአልጀርሱን ስምምነት ተግባራዊ ከማድረግ ይልቅ ከሁመራ/ኡምሀጀር እስከ ደናክል ሰርጥ ያለው 1600 ኪሎ ሜትር የኢትዮጵያያ የኤርትራ ድንበር እንደገና እንዲዋሰን ከጦርነቱ በፊት ኤርትራ በደቡብ ምዕራብ በኩል ከበጌምድር/ሰሜን ጠቅላይ ግዛት ወይንም የጎንደር ክፍለ ሀገር ጋር ትዋሰን የነበረው ተደምስሶ ከምዕራብ ትግራይ ጋር እንድትዋሰን ተደርጎ ከአፋር ወደ ትግራይ የተካተተው መሬትም ጭምር ተካቶ በድንበር ማካለል ስም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተመዘገበ የትግራይ አካል እንደሚሆን ነው። ይህም የተስፋይቱ ምድር ስትመሰረት የትግራይ አለማቀፍ ድንበር ይሆናል።

እንደሚታወቀው የወያኔ ሕገ መንግሥት የኢትዮጵያን ድንበር ሲደነግግ ክልሎች የተባሉት ከጎረቤት አገሮች ጋር የሚዋሰኑበት ቦታ እንደሆነ ይነግረናል። በሌላ አነጋገር ኤርትራ በደቡብ ምዕራብ በኩል ከበጌምድር/ሰሜን ጠቅላይ ግዛት ወይንም ከጎንደር ክፍለ ሀገር ጋር ትዋሰን የነበረው ተደምስሶ 1600 ኪሎ ሜትሩ የኢትዮጵያያ የኤርትራ ድንበር እንደገና ሲዋሰን በደቡብ ምዕራብ በኩል ከኤርትራ ጋር የሚዋሰነው የበጌምድር/ሰሜን ጠቅላይ ግዛት ወይንም የጎንደር ክፍለ ሀገር በምዕራብ ትግራይ ሲተካ የትግራይ ክልል ከኤርትራ ጋር እስካሁን በአለም አቀፍ ደረያ ያልነበረው የደቡብ ምዕራብ አዋሳኝ ሆኖ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተመዘገበ አለማቀፍ ድንበርተኛ ይሆናል ማለት ነው።

ስለዚህ ወያኔ «የአልጀርሱን ስምምነት ከነሙሉ ማዕቀፉ ተግባራዊ እንዲሆን» የሚለው 1600 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የኢትዮጵያንና የኤርትራን ድንበር የኤርትራን ድንበር የማካለል ሥራ ከመጀመሩ በፊት ወልቃይት ወደ ቀድሞው በጌምድር/ስሜን ጠቅላይ ግዛት ወይንም ጎንደር ክፍለ ሀገር መመለስ ይኖርበታል፤ አልምያም የኢትዮጵያና የኤርትራ ድንበር እንደገና ይካለል ከተባለ መካለል ያለበት የድንበር ጦርነቱ የተቀሰቀሰበት 260 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የተከዜ ወንዝ የጋሽ ባርካን መሬት ለመጀመሪያ ጊዜ ከሚነካበት ቦታ አንስቶ የመረብ/ የጋሽ ወንዝ ወደ ጋሽ ባርካን ምድር እስከሚገባበት ድረስ የተዘረጋው ባድመ የሚገኝበት ቀጥተኛ መስመር መሆን ይኖርበታል።

አማራ ሁሉ ወያኔ ተከዜን ተሻግሮ በወረራ የያዘውና «ምዕራብ ትግራይ» ሲል የፈጠረው የወልቃይት፣ የጠገዴ፣ የጠለምትና የሑመራ ርስቱ ወደ ነባር ይዞታቸው ሳይመለሱ የኢትዮጵያና ኤርትራ 1600 ኪሎ ሜትር ድንበር እንዳይካለል መታገልና በወረራ የተወሰደውን መሬት ለማስመለስና ሕልውናውን ለማስጠበቅ በነቂስ ታጥቆ መነሳት አለበት።