በበርካታ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ተጠያቂ የሆነው የህወሓት ሹመኛው የሶማሊ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አብዲ ኢሌ የጠ/ሚ/ር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር በቁጥጥር ሥር አውሎት ለፍርድ ካላቀረበው በዓለምአቀፍ ፍርድ ቤት ሊጠየቅ እንደሚችል ጎልጉል ጥቆማ ደርሶታል።

ሰሞኑን ከህወሓት ጀነራሎች የተሰጠውን የሥራ ተግባር ሲወጣ የነበረው አብዲ ከሥልጣኑ የሚለቅበትና እጁን የሚሰጥበት ቀን ዛሬ ሰኞ እንደሚሆን አንዳንድ የሶማሊ አክቲቪስቶችና የማኅበራዊ ሚዲያ ተሳታፊዎች ሲገልጹ ቆይተዋል። በርካታዎች ጤንነቱን የሚጠራጠሩትና ከዕውቀት የጸዳው አብዲ በምክትል ጠ/ሚ/ር ደመቀ መኮንን ለተመራው ቡድን ሥልጣኑን እንደሚለቅ ቃል ገብቷል የሚለው በስፋት እየተወራ ነው። ሆኖም አረፋፍዶ ይህንኑ ሊቀለብስና በፈለገው አቅጣጫ ሊሄድ ይችላል የሚለውም ከውሳኔው ጋር አብሮ ከግምት ውስጥ የገባ ነው።

የአብዲ ኢሌይ መጨረሻ ሲጀምር በሚል ርዕስ ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ ሒውማን ራይትስ ዎች “We are Like the Dead’: Torture and other Human Rights Abuses in Jail Ogaden, Somali Regional State, Ethiopia” በሚል ርዕስ ያወጣውን የ88 ገጽ ዘገባ በመንተራስ በዘገበበት ወቅት የሚከተለውን ማለቱ ይታወሳል።

“ይህ የግፍ ቁልል የተከማቸበት ዘገባ፤ በኦጋዴን እስር ቤት ግፍና ስቅየት በመፈጸምና በማስፈጸም ተዋናኝ የሆኑትን የፌዴራሉ መንግሥት የሶማሊ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አብዲ ኢሌንና ሌሎች ከፍተኛ የሶማሊ ክልል ባለሥልጣናትን ተጠያቂ እንዲሆኑ ጥሪ የሚያደርግ ነው”።

ከዚህ ጋር በተያያዘ የጠ/ሚ/ር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር በአብዲ ኢሌ ላይ ፈጣን እርምጃ እንዲወስድ የግፉ ገፈት ቀማሾችና የሶማሊ ክልል ወገኖች እየወተወቱ ነው። ጉዳዩን በቅርብ ከሚከታተሉ ጎልጉል ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ ደግሞ አብዲ ኢሌ በአገር ውስጥ ለፍርድ ቢቀርብ የተሻለ ይሆናል። ሆኖም በተለያዩ ምክንያቶች የዐቢይ አስተዳደር ቸልተኝነት ካሳየ ወይም የፖለቲካ አካሄዱን መስመር ለማስያዝ በሚል በሌላ አቅጣጫ ከሄደ አብዲ ኢሌ በውጭ አገር ለፍርድ እንዲቀርብ ዓለምአቀፍ የእስር ማዘዣ ሊወጣበት ይችል ይሆናል። ይህንንም ለመተግበር የቆረጡ ወገኖች እንዳሉ መረጃው ያመለክታል። የዛሬው ውሎና ውሳኔ ወደ ዓለምአቀፉ መድረክ የመሄድ ወይም አለመሄድ ሁኔታን ይወስነዋል ተብሏል።

ይህንን ዘገባ እያዘጋጀን ባለበት ወቅት ጅጅጋ ውስጥ አብዲ ኢሌን ከሥልጣኑ ለማውረድ ስብሰባ መጀመሩንና አብዲ ሲወርድ በቦታው ይተካል ተብሎ የታሰበው የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ሚ/ር አህመድ ሺዴ በስብሰባው ላይ የሚገኝ መሆኑ በተለያዩ የማኅበራዊ ገጾች ላይ እየተዘገበ ይገኛል።


ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ