ብሔር ከመታወቂያ ላይ ሊነሳ ነው
በቀበሌ መታወቂያ ላይ ብሔር እንዲጠቀስ ለምን ተፈለገ? የህጋዊነቱስ ጉዳይ?
Aerial view of the Addis Ababa
መስከረም 15/2010 ዓ.ም የእንግሊዙ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (BBC) በአማርኛ ዜና ትንታኔው ላይ እንዳቀረበው
የምስል መግለጫ መታወቂያ ላይ” ብሔር” የሚለውን ለማስተካከል ረጅም ጉዞ የተጓዘው ያሬድ ሹመቴ በሚል ርዕስ
ኢትዮጵያዊው የፊልም ባለሞያ ያሬድ ሹመቴ ያደረገውን ጥረት በሰፊው አትቷል፡፡
እንደ BBC ዘገባ ከሆነ ያሬድ ሹመቴ ይህንን ጥረቱን ከስምንት ወራት በፊት የጀመረው ቢሆንም
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት ለተወሰነ ጊዜ አቋርጦት ከቆየ በኋላ
አሁን ግን አቤቱታውን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ለማቅረብ በዝግጅት ላይ መሆኑንም ገልጧል፡፡
ይህም ከአንድ ያገባኛል ከሚል ዜጋ የሚጠበቅ ተግባር በመሆኑ ያሬድ ጥረቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ማበረታታት ይገባናል፡፡
የብሔር ጉዳይ በመታወቂያ ላይ መኖር አለመኖር ጋር ተያይዞ እኔም በውስጤ ይብላላ የነበረ ሀሳብን
ያሬድ ሹመቴ በግልጽና በድፍረት አንስቶ ለመገናኛ ብዙሀን እንዲደርስ ማድረጉ በእጅጉ ደስ ስላሰኘኝ
የእሱንም ሆነ የእኔን አተያይ ለፌስቡክ ወዳጅ ዘመዶቼ በማጋራት ይዞት የተነሳው ሀሳብ የውይይት ርዕሰ ጉዳይ እንዲሆን ፈለግሁና
ቀጥሎ በሚገኙት አንቀፆች ላይ እንደ አስፈላጊነቱ በ BBC ድረ ገጽ ላይ
የሰፈረውን የያሬድ ሹመቴን አስተያየት በማጣቀስ ጭምር ትንሽ ነገር ማለትን ፈለግሁ፡
እርግጥ ነው ባለፉት 26 ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ
ከቀድሞው በተለየ ሁኔታ በጥቅሉ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚለው አባባል ቀርቶ ብሔር፣
ብሔረሰብና ህዝብ ብሎ መጥራት በእጅጉ እየተለመደ መጥቷል፣
በሽግግር ወቅት ቻርተር እና በአዋጅ ቁጥር 7/1984 ላይ የተጀመረው የብሔር-ብሔረሰብ ጽንሰ ሀሳብ
በ1987 ዓ.ም ጸድቆ ስራ ላይ በዋለው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ህገ-መንግስት ከመግቢያው ጀመሮ
እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ሔረሰበቦችና ህዝቦች በማለት የብሔር-ብሔረሰብን ጉዳይ ትልቅ ቦታ ሰጥቶታል፡፡
ህገ-መንግስቱ ብሔሮች፣ ሔረሰበቦችና ህዝቦች ማለት ምን ማለት እንደሆነም በአንቀጽ 39 ንዑስ አንቀጽ 5 ላይ በግለጽ ለማመላከት ሞክሯል፡፡
ይሁን እንጂ የህገ-ምንግስቱ ትርጉም ለመብት አጠቃቀም አመቺነት ሲባል የተደረገ እንጂ
ሶስቱም መጠሪያዎች ተመሳሳይ የሆነ ትርጉም ስላላቸውና
በይዘትም ሆነ በቅርጽ አንድ ስለሆኑ እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባዋል፡፡
ይህን መሰረተ ሀሳብ ተከትሎም የክልል መስተዳድሮች በአብዛኛው በቋንቋ ላይ እንዲመሰረቱ ተደርጓል፣
በዚህም መሰረት ትክክል ነው ለማለት ቢከብድም ክልሎች በሚያዘጋጁት የቀበሌ መታወቂያ ወረቀት ላይ
ብሔር ወይም ብሔረሰብ የሚል መጠይቅ መካተቱ/መስፈሩ ብዙም አነጋጋሪ ጉዳይ ባልሆነ ነበር።
ምክንያቱ ደግሞ ግልጽ ነው፡፡
ይህም ማለት የክልል መስተዳድሮቹ አፈጣጠርና አደረጃጀት
በራሱ የዚህ አይነት ቅኝት እንዲኖራቸው ሊያደርግ ይችላልና ነው፡፡
በሌላ አነጋገር ብሔርን ወይም ብሔረሰብን በቀበሌ መታወቂያ ላይ መጥቀስ መንግሥት ከዘረጋውና
በዋነኛነት ማንነትን መሰረት አድርጎ ከተቋቋው የፌዴራል ስርአት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ በመሆኑ
ላለፉት 26 ዓመታት ሲያነታሪክ ቢቆይም አሁንም ጥያቄው እንደ አዲስ የሚነሳበት አጋጣሚ መፈጠሩን
በመግቢያየ ላይ ያነሳሁት የያሬድ ሹመቴ ጥረት አንድ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።
ሆኖም በዚህ ረገድ እጅግ ግራ አጋቢ የሚሆነው ጉዳይ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች
በሚያዘጋጁት የመታወቂያ ወረቀት ላይ ብሔር የሚል መጠይቅ መካተቱ/መስፈሩ ነው፡፡
ይህም ሁኔታ በአንድ በኩል በጥቅሉ ብሔር፣ ብሔረሰብና ህዝብ እየተባለ በሚጠራበትና
የትኛው ማህበረሰብ ብሔር፣ የትኛው የህብረተሰብ ክፍል ደግሞ
ብሔረሰብ ተብሎ በግልጽ ባልተለየበተ ሁኔታ
በየትኛውም ክልል የሚዘጋጅ መታወቂያ ላይ በአንድ ቃል ብሔር ብሎ መጠየቅ
ብዙዎቹን ግራ የሚያጋባ ጉዳይ ሲሆን በሌላ በኩል
ብሔር ማለት አገር ማለት ነው ብለው በጽኑ ለሚያምኑና ለሚያስቡ ወገኖች ደግሞ
እስካሁንም ድረስ በምንም መልኩ ሊዋጥ የሚችል አባባል ሆኖ አልተገኘም፡፡
ከሁሉም በላይ ግን ከተለያዩ ብሔር-ብሔረሰቦች የተወለዱ ዜጎችና በሚሊዮን የሚቆጠሩ የከተማ ነዋሪዎች
አንድ ብሔር ወይም ብሔረሰብ ብቻ ለይተው እንዲመርጡ መገደዳቸው
በምንም መልኩ ምክንያታዊ ብቻ ሳይሆን ህጋዊም አይደለም፡፡
ለዚህም ይመስላል የፊልም ባለሙያው ያሬድ ሹመቴ
ይህንን የተዛባ ሁኔታ ለማስቀረት ብዙ ርቀት ለመጓዝ የሞከረውና
“ብሔር ለሚለው ሀሳብ ለኔ ኢትዮጵያ የምትለው ትበቃኛለች።” በማለትም የተቃውሞ ሀሳቡን የሚገልጸው።
ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት ሀገሪቱ ላይ እየተስተዋሉ ባሉት
ብሔርን መሰረት ያደረጉ ግጭቶችና ውጥረቶች ምከንያት
መታወቂያው ላይ ብሔር ብሎ መስፈሩን ያሬድ በፍጹም ሊቀበለው እንዳልቻለ BBC ይገልጻል።
ሀሳቡን አጠናክሮ በመቀጠልም “በብሔር ምክንያት የወዳጆች ግንኙነት እየተበላሸ፤
ለብዙዎች በሰላም ከሚኖሩበት ቦታ ለመፈናቀል ምክንያት በመሆኑ አደገኛነቱ እየጎላ መጥቷል።”
በማለት የሚናገረው ያሬድ ሹመቴ ይኸ ጥረቱ ለራሱ ብቻ ሳይሆን ብሔርን መተው ለሚፈልጉ ዜጎች ሁሉ መነሳሳትን ሊፈጥር እንደሚችል ያምናል።
እንደ ያሬድም ሆነ ሌሎች በርካታ ኢትዮጵያዊያን እምንት ባለፉት ሀያ ስድስት አመታት
እየታየ ያለው ብሔርን መሰረት ያደረጉ ቡድኖች መጠናከር የኢትዮጵያ ብሔርተኝነትን በእጅጉ አዳክሟል፤
በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያዊ ማንነትን ከማቀንቀን ይልቅ ብሔር/ብሔረሰብ ላይ ማተኮ
ር የበለጠ ጎልቶ ይታያል፣ ይህም በመሆኑ አንድነታችን ከመቼውም ጊዜ በላይ አደጋ ላይ ወድቋል፡፡
ሆኖም “ብሔራቸውን በመጥቀስ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግራይ ተብሎ እንዲፃፍላቸው የሚፈልጉት ምርጫቸው ይጠበቅ፤
ማንም ኢትዮጵያዊ ላይ ብሔር እንዳይፃፍ የሚል ጥያቄ የለኝም።
ለኔ ግን የማይገልፀኝን ነገር፣ በህገ-መንግሥቱም የማልገደድበትን ማንነት ሊፃፍብኝ አይገባም።
ስለሆነም የኔም ጥያቄ ይመለስ መብቴም አይከልከል ነው እያልኩ ያለሁት።”
ይላል የፊልም ባለሞያው ያሬድ ሹመቴ በግሉ በዚህች አገር ላይ እንዲሆን የሚፈልገውን ሀሳብ ይበልጥ ሲያብራራ።
ይህንን እምነቱን መነሻ በማድረግም ከስምንት ወራት በፊት
ለሚመለከተው የመንግስት አካል ያቀረበው ጥያቄ በወቅቱ ተቀባይነት ባለማግኘቱ ወደ ወረዳው ሥራ አስፈፃሚ ተመራለት፣
በማህበራዊ ድረ-ገፁ ላይ በግልጽ እንደፃፈውም ብዙዎች ጉዳዩን እንዳልተረዱት ከመግለጹም በላይ
“ብሔርህ በእናትህ ተፅፎ ነው?” እና “ብሔር ሳይል እንዴት ዜጋ መሆን ይቻላል?
ብሔር የሚለው መገለጹ የግድ ነው።” የሚሉ ጥያቄ አዘል አስተያየቶች
የቀረቡለት መሆኑ ብቻ ሳይሆን መልሳቸውም “መመሪያው አይፈቅድም!” የሚል እንደሆነ ይገልጻል።
ከላይ ለተጠቀሱት አስተዳደራዊ መዋቅሮች ያቀረበው ጥያቄ ምላሽ ባለማግኘቱ
ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት እንደወሰደውና ፍርድ ቤቶችም ይኸ ጉዳይ እኛን ሳይሆን የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ነው የሚመለከተው ብለው እንደመለሱት ያስረዳል፡፡
እናም ስራ ላይ የሚገኘው መመሪያ በአውጭው አካል አሊያም
ከሱ በላይ በሆነው ህግ አውጭ አካል ተስተካክሎ ህጋዊ መልክ እንዲይዝና
የሁሉንም ዜጎች ፍላጎት በተለይም ከተለያዩ ብሔር-ብሔረሰቦች የተወለዱና
በእርግጠኝነት ይኼ ነው ብሔሬ ወይም ብሔረሰቤ ማለት ለማይችሉ ወገኖች
ምቹ ሁኔታ ይፈጠር ዘንድ ሁላችንም በያገባናል ስሜት መታገል ያለብን ይመስለኛል፡፡
ይኸ ጉዳይ በመታወቂያ ላይ ተወስኖ መቅረት እንደሌለበትና በህዝብና ቤት ቆጠራ ጊዜም
ግምት ውስጥ እንዲገባ ከወዲሁ ማስገንዘቡ ተገቢ ነው ብየ አምናለሁ፡፡