ድልድይ ሁለት ጎን ለጎን የሆኑ ቦታዎችን ያገናኛል። ድልድይ በሌላቸው ቦታዎች የሚገኙ ሰዎች፤ መገናኘት ያስቸግራቸዋል። ባንጻሩም፤ ከትናንት ወደ ዛሬ የሚያሸጋግር ድልድይ ከሌለ፤ ዛሬ ትናንት የተሠራውን እንደገና እንዳዲስ በመሥራት ይጠመድና፤ ዛሬ ሁልጊዜም ትናንትን እንደሆነ ይቀጥላል። ይህ ነው በኢትዮጵያ፤ ለሕዝብ ተቆርቋሪዎች የእንቅስቃሴ ሂደት፤ በተደጋጋሚ እያየን ያለነው። ከትናንት መማር እያቃተን፤ ዛሬም የትናንቱን መልሰን ስንዳክርበት እንገኛለን። ለምን? መማር ስለማንችል አይደለም። የትናንቱ ስላልተመዘገበም አይደለም። የማስተላለፉ ሥርዓት በትክክል ስላልተከናወነ ነው። የዚህ ጽሑፍ ማጠንጠኛ ይህ ነው።

ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ፤ “በአቸነፈ እና በአሸነፈ የተላለቃችሁ!” ብለው ያስቀመጡትና አዳራሹን የሞላው ያጨበጨበበት፤ ብዙ ሕይወት ያለፈበትን የሁለት የተለያዩ የፖለቲካ አሰላለፎችን ትግል አቅልለው በማስቀመጣቸው ቢሆንም፤ ይህ የግል ስህተታቸው ሳይሆን፤ በብዙኀኑ ተቀባይነት ያለው መሆኑ ነው። አጨብጫቢዎቹ ስለ ነበረው ትግል ያላቸው ዕውቀት አነስተኛ ነው። በስድሳዎቹ የነበርነው ተማሪዎች፤ ስለ ሀገራችን ታሪክ፣ ስለ አርበኞቻችን ተጋድሎ፣ ስለ መንግሥት ሂደት፣ ስለ ታሪክና ማንነት የነበረንን ዕውቀት በግሌ ስመለከተው፤ ጎደሎ ነበር። እንዲሆን የምንፈልገውን፤ ከሀገራችን ታሪክና ተጨባጭ እውነታ ጋር አላጋባነውም ነበር። እዚህ ላይ፤ እኔ ሁሉን ወክዬ ሳይሆን፤ በግሌ ሁን የማምንበትን ነው የማስቀምጠው። እናም በተማርነው መሠረት፤ ለሁሉም ነገር ፊታችንን ያዞርነው ወደ ውጪ ነበር። ከትናንታችን የወረስነው አጥተን ሳይሆን፤ በቀጣይነት ያስረከበን ድልድይ አልነበረውም። ይህ ትልቅ ስህተት መሆኑን አምናለሁ።

ደርግ፤ ከትናንት የኢትዮጵያ ሕዝብ ተቆርቋሪዎች ለዛሬዎቹ ምንም ዓይነት መወራረስ እንዳይኖር፤ ትውልዱን ጨረሰው። የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ አነጋገር፤ በዚያ ወቅት ደርግ ባደረገው የትውልድ መጨረስ፤ በተተካ የፈጠራ ትረካ ውጤት ነው። መተላለቁ፤ በአንድ ቃል ሁለት አጠራር ላይ የተመሠረተ አልነበረም። መግለጫውን እንደ ዋናው ቁም ነገር መውሰድ፤ ስህተት ነው። ከዚያ በኋላ የተከተለው የፖለቲካ ታጋይም ሆነ የተማሪ ተንቀሳቃሽ፤ ሀ ብሎ እንደገና መፍጠር ነበረበት። ልምዱም ሆነ ግኘቶቹ ለቀጣዩ ትውልድ አልተላለፉለትም። ጉድለቶቹም ሆነ ጥንካሬዎቹ በትክክል አልተነገሩትም። በዚያው በደርግ ጊዜ የተደረጉት ግድያዎችና የቀይ ሽብር ዕልቂቶች በትክክል ተመዝግበው አልተላለፉም። የትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባር ዙፋኑን ዘርፎ፤ ራሱ ያደረጋቸው ጭፍጨፋዎችና ግድያዎች፤ አሁንም ሳንማርባቸው ተድበስብሰው ወደፊት መቀጠሉ፤ እየተንደረደርንበት ስለሆነ፤ ትምህርት ሳናገኝ፤ ነገ እንዳይደገም ሰግቻለሁ።

አዲሱ ወጣት፤ አዲስ ትግል ብሎ፤ እንደገና ከ ሀ እየጀመረ መቀጠሉ፤ ወደፊት የሚባል ሳይሆን፤ ባለህበት እርገጥ የሚል ጉዞ ላይ ያስቀምጠናል። ከትናንቶቹ በጎ የሆኑና ግድለቶች አሉ። ያን መርምረን፤ ከዚያ መማር ካልቻልን፤ የዚያ ጊዜ ድከመቶችን ተሸክሞ መጓዝና መድገሙ አይቀሬ ነው። ለምን? የስድሳዎቹ ተማሪዎች እንቅስቃሴ መሪዎች ምን ጥሩ ነገር ሠሩ? ምንስ ድክመት ነበራቸው? ከነሱ በፊት የነበሩት ምሁራንስ? ደርግስ? የትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባርስ? ነገ የሚከተለውስ? ያን ማሰብና መመርመር ካልቻልን፤ በድክመቶቻቸው ተዘፍቀን፤ ያንኑ እያሸተትን፣ ከዚያው የማንወጣ እንሆናለን።