ዐቢይ ምንም የሆነው ነገር የለም! ይሄ ፎቶ (ምስለ አካል) የዛሬ ነው ዐቢይ የእንግሊዝ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት (D.F.I.D) ኃላፊዎች ከሆኑ ጋር ዛሬ በጽ/ቤቱ ተቀብሎ አነጋገሯል፡፡ “ታዲያ እንዴት እንዲህ ዓይነት ዘግናኝ የሰውና የንብረት ውድመት ሲፈጸም እንዴት አንድም ነገር ትንፍሽ ሳይል ቀረ?” ካላቹህ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡
ሰሞኑን በጅጅጋና በሌሎችም የሀገራችን ክፍሎች የተከሰቱና በቀጣይም ሰሞኑን ሊፈጸሙ የታሰቡ ቀውሶችን በሕዝብ ላይ ለመፈጸም ስለታሰበና አደጋው ከመከሰቱ በፊት መከላከል እንዲቻል ሕዝብ በተለያየ መልኩ በየደረጃው ለሚመለከታቸው አካላት እያመለከተ፣ እየጮኸ፣ እያሳሰበ እያለና ለዚህ የሕዝብ ጥያቄ ተገቢና አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት የደረሰውን ቀውስ ማስቀረት እየተቻለ በተፈጠረ የአመራር ክፍተት ምክንያት የተከሰተ ለማስመሰል ተፈልጎ ነው ዐቢይ የሆነ ነገር ሆኖ ሥራውን በአግባቡ መሥራት ባለመቻሉ ቀውሱ የተከሰተ ለማስመሰል “ከአሜሪካ በመመለስ ላይ እያለ አውሮፕላን (በረርት) ውስጥ የመግደል ሙከራ ተደርጎበት ነው፣ በሥራ ጫና ብዛት ድካም (stress) ለሕመም ተዳርጎ ተኝቶ ነው!” ምንትስ ቅብርጥስ የሚባሉ ትወናዎችንና ወሬዎችን ሆን ብለው እያናፈሱ የሚገኙት፡፡
ወገን ሆይ! ደኅንነትህ ያለው በእግዚአብሔርና በእጅህ ነው፡፡ ይህ አገዛዝ ጠላትህ እንጅ ወዳጅህ አይደለም፣ አጥፊህ እንጅ ጠባቂህ አይደለምና የፈለገ ነገር ቢሆን ፈጽሞ አትመነው፡፡ መሰንበቻውን ሶማሌ ክልል በሚሉት አስቀድሞ ሕዝብ እየጮኸ እያሳሰበ እያለ አገዛዙ ግን ምን እያለ እያላገጠ በወገኖቻችን ላይ የሕይዎትና የንብረት ውድመት እንዲደርስባቸው እንዳደረገና እንዳስፈጃቸው ልብ በል! ስለሆነም እራስህን ጠብቅ!!!
አገዛዙ “ሕግ፣ የሕግ የበላይነትና ተጠያቂነት አለ!” የሚለን ከሆነ ለዚህ ለደረሰው ዘግናኝ ጥቃትና ውድመት ተጠያቂ የሆኑ አካላት በሙሉ በአፋጣኝ ተጠያቂ መሆን ነበረባቸው፡፡ እንደምታየው ግን በሚያሳዝን መልኩ በሀገሪቱ የሕግ የበላይነትና ተጠያቂነት የለምና፣ በዚህ አገዛዝ ውስጥ በሕዝብ ላይ ግፍ የፈጸመ ማንም ተጠያቂ ሲሆን ዓይተን ሰምተን አናውቅምና በዚህ ቀውስም ተጠያቂ የሆነውን ሁሉ አገዛዙ ተጠያቂ ያደርጋል ብለህ አትጠብቅ!!!
ስለሆነም እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ደምህ ደመከልብ ሆኖ መቅረቱ ነው፡፡ አንድም ኃላፊነት እንዲወስድና ተጠያቂ እንዲሆን የሚደረግ የአገዛዙ ባለሥልጣን አይኖርም፡፡ ገና እንዲያውም በተመሳሳይ መልኩ ተመሳሳይ ድራማ (ትውንተ ኩነት) እየተወኑ በማስፈጀት በነፍስ በሥጋህ ይጫወቱብሃል!!! ምክንያቱም አስቀድሞ ክፍተቱ እንዲኖር የተደረገው ሆን ተብሎ ለዚህ ዕኩይ ዓላማ ነውና፡፡
በአንድ ሀገር ውስጥ ሕግ የሚቀረጸው የሕዝብን ደኅንነት፣ ህልውናና ሰላም ለመጠበቅ ነው፡፡ በ21ኛው መቶ ክ/ዘ የሕዝብን ወይም የዜጎችን ደኅንነት፣ ህልውናና ሰላም ለመጠበቅ የማያስችል የማይበቃ ጭራሽ እንዲያውም ሆን ተብሎ የሕዝብን ወይም የዜጎችን ደኅንነት ህልውናና ሰላም ለአደጋ የሚዳርግ ክፍተት ያለበት ሕገ መንግሥት ተቀርጾ በአንድ ሀገር ላይ ሥራ ላይ ከዋለና በዚህም ምክንያት የዜጎች ወይም የሕዝብ ደኅንነት፣ ህልውናና ሰላም ለአደጋ ከታዳረገ ይሄ ሕዝብ በወንበዴዎች፣ በጠላቱ እጅ እንጅ መንግሥቴ በሚለው እጅ አይደለም ያለው ማለት ነው፡፡ ወገን ሆይ! ባንተ ላይ የሆነውና የታየውም ሌላ ምንም ሳይሆን ይሄው ነው፡፡
ወገን ሆይ! ደኅንነትህ የሚያሳስብህ፣ የሚገድህና ይሄ በሸፍጥ የተከሰተ ቀውስ እንዳይቀጥል ከፈለክ ይሄን ቀውስ አሰቀድሞ መከላከል እየተቻለ ግን ሳይቻል ቀርቶ እንዴት ሊከሰት እንደቻለና ለዚህም ተጠያቂው ማን እንደሆነ አገዛዙን በተቃውሞ ሰልፍ አፋጠህ ጠይቅና ክፍተቶቹ ሌላ የከፋ ችግር ሳይፈጠርባቸው እንዲዘጉ አድርግ!!! ይሄንን ማድረግ ካልቻልክ በዝምታ እንደተሸበብክ በወያኔ ሸፍጥ መጫወቻ ሆነህ ማለቅህ እንደሆነ እወቅ!!!
ወገን ሆይ! በአሁኑ ሰዓት ከሀገር ውስጥ እስከ ውጭ ቀደም ባለው ጊዜ የተቃውሞ ሰልፍ ሲያስተባብሩ ሲቀሰቅሱ የነበሩ አክቲቪስቶች (ስሉጣን) ለወያኔ/ኢሕአዴግ አድረዋልና፣ ወያኔ/ኢሕአዴግ ገዝቷቸዋልና፣ የወያኔን ጫማ ስመዋልና፣ ዕድሜ ልካቸውን አገዛዙን ለማገልገል ምለዋልና፣ በዚህም ምክንያት ነውና ይሄንን ሰሞኑን የተፈጸመብህን ዘግናኝና ከፍተኛ ግፍ ዓይተው እንዳላዩ ሰምተው እንዳልሰሙ በዝምታ ያለፉትና እነሱን የሚተካ ሳተና እስክታገኝ ድረስ ማንንም በስቃሽ አስተባባሪ ሳትጠብቅ እራስህ ውጣና ተቃውሞህን ጩኸትህን አሰማ፣ አገዛዙን ፈጥርቀህ ያዝ!!!
ብትችልማ እንዲያውም በመሬት አንቀጥቅጥ ዐመፅ አገዛዙን ጠራርገህ ማስወገድ ብትችል ሁነኛ መፍትሔው እሱ ነበረ፡፡ ይሄ የሰሞኑ ግፍ የተፈጸመው በሌላ ሀገር ቢሆንኮ ኖሮ መንግሥት አስገልብጦ ነበረ፡፡ ባንተ ሀገር በመሆኑና ልብህ በወያኔ አጃጃይ ሸፍጥ ተተብትቦ ስለተያዘ ነው ኮሽታ እንኳ ሳታሰማ በዝምታ የተቀመጥከው፡፡ በዐመፅ ወያኔን ማስወገድ ካልቻልክ ደግሞ ቢያንስ ከዚህ በኋላ በተመሳሳይ ሕገመንግሥታዊ ሸፍጥ ሳታልቅ በፊት ቶሎ ብለህ ፈጥርቀህ ይዘህ ሆን ተብሎ የተደረገውን የሕግ ክፍተት በአዋጅ አዘጋ!!!
እግዚአብሔር ይሁንህ ወገኔ!!!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
amsalugkidan@gmail.com