August 8, 2018ሐይሉ አባይ ተገኝ

የ”ልሣነ አማራ” ማስጠንቀቂያ አዋጅ – ከድጡ ወደ ማጡ! (ሐይሉ አባይ ተገኝ)

ስፔንሰር ጆንሰን እንዲህ ይላል::

  1. “ሃቀኝነት እውነትን ለራስ መንገር ሲሆን ታማኝነት እውነትን ለሌሎች መናገር ነው::” (Integrity is telling myself the truth. And honesty is telling the truth to other people.)
    (Spencer Johnson)

ለኔ በአማራው የአስተሣሰብ አድማስና የህልውና አደጋ (existential threat) ምከታ ላይ ሠርጎ የገባ ‘የራይላ ኦዲንጋና የትሮይ ፈረስ ቫይረስ’ (Raila Odinga & Trojan Horse Viruses) መኖሩ ይሠማኛል::

ከዚህ ቀደም በነሐሴ 1 ቀን 2018 ለአንዱዓለም አራጌ፣ ለታማኝ በየነና ግንቦት 7 አማራ ክልል እንዳይደርሱ ማስጠንቀቂያ ሰጡ::

እ.አ.አ. በነሐሴ 7/2018 ሌላ ማስጠንቀቂያ ስለ’ጎንደር ሕብረት’ አወጡ:: በቅርቡ የነርሱን ሃሣብ የማያራምድ ጎንደሬን ጎንደር፣ ጎጃሜን ጎጃም፣ ሸዋውን ሸዋና ወሎዬውን ወሎ እንዳይገባ ማስጠንቀቂያ እንደሚሰጡም አገምታለሁ:: ይህን የምቃወመው ስለ ግለሰቦቹና ድርጅታቸው ጥብቅና ቆሜ ወይም አባላቸው ሆኜ ሣይሆን መሠረታዊ የነፃነትና የዴሞክራሲ መርሆዎች ሲጣሱ በማየቴ ነው:: ሃሣቤንም ቤንጃሚን ፍራንክሊን እንዲህ ሲል ያጠናክረዋል:: “ሃሣብን በነፃነት የማሰብ ነፃነት ከሌለ ጥበብ፣ ህዝባዊ አርነትና የመናገር ነፃነት የለም” [Without freedom of thought there can be no such thing as wisdom & no such thing as publick liberty without freedom of speech] (Benjamin Franklin, 1722)

አዎ እውነትን እናገራለሁ:: እኔ የምፅፈው እውነት የመሰለኝን እንጂ ሌሎች እውነት ብለው ያመኑበትን ነገር ግን የማላምንበትን ሃሣብ አይደለም:: ሃሣቤን የማስበው በህሊናዮዬ እንጂ በአድናቂዎች ጭንቅላት አይደለም::

በእግር ኳስ ዳኛ ውሣኔ ላይ ሙሉ የስታዲየሙ ደጋፊ ጮኸ ማለት የዳኛው ውሣኔን የተሳሳተ አያደርገውም:: በአንፃሩ ይህ ደጋፊ ለዳኛው የተሣሳተ ውሣኔ ተገዢ ሆነ ማለት የዳኛውን ብያኔም ፍትሃዊም አያደርገውም:: በሁለቱም የውሣኔ ቅቡልነት ከሁለት አንዱን ብይን ፍትሃዊ ወይም ኢ-ፍትሃዊ የሚያደርገው የጨዋታው ሕግና የሕጉ አተረጓጎምና ተግባራዊነት ብቻ ነው::

ለእኔ የህለውና ጥቃትን (existential threat) መታደግና ፓለቲካዊ ፍረጃ የተለያዩ ናቸው::

ድርድርን (compromise) የማይጋብዝ የፍጥጫ (confrontational) ፓለቲካ ፍፃሜው አምባገነንነት ነው:: ከመላ ምድሩ ጋር የሚጣቆስ ፓለቲካም ለሽንፈትና ውድቀት እራሱን የሚጋብዝና መዘዝን በእራስ ላይ የሚጋብዝ (self inflicted wounds) ነው:: ፓለቲካ በመስጠትና በመቀበል ግብይይት ላይ የሚሰላ ጥበብ (wisdom) ነው::

ዴሞክራሲያዊ ፓለቲካ የተለያዩ አስተሣሰቦች ተፋጭተው በህዝብ ቅቡልነት፣ ይሁንታና ድምፅ አሸናፊ ለሆነው ሃሣብ እጅ መስጠት ነው:: የዴሞክራሲ እሴትና ባህልም በሚስማሙበት ብቻ ሣይሆን በማይስማሙበት ሃሣብ ጋር ተስማምቶ በመቻቻል ፓለቲካ መኖር ነው::

ድርጅቶችና ግለሰቦች ሃሣብና መርሆን ይነድፋሉ:: ነገር ግን አፅዳቂው ህዝብ እንጂ እነርሱ አይደሉም:: የራሱን ሃሣብ በራሱ የሚይፀድቅ አምባገነነት ብቻ ነው:: የማሰብ ነፃነትን በፈቀደውና ባመነበት መደራጀትን መጋፋት የለየለት ፀረ-ዴሞክራሲያዊነት ነው:: በአስተሳሰብ የማይስማሙትን አማራ “ደደብ አማራ”፣ “ዲቃላ አማራ”፣”ከሃዲ አማራ ዲያስፓራ”፣ “የደቡብ አማራ” ኢትዮጵያ የሚባል ማደንዘዣ” ወ.ዘ.ተ. የሚሉና የሌሎችን ሥምና ስብስብ በማህበር መንደፍ የስነምግባርና የሞራል ድቀትን የተላበሱ ስድቦች ሰዎችን በቡድን ስር ማምጣትና ማሰባሰብ አያስችልም:: ይልቅም በታኝና አግላይ ነው::

እነዚህ ዘግናኝ ስድቦችና ትችቶች ምንጫቸው ሁለት ነው:: አንድም በ’አብን’ ስም እንዲናገሩና እንዲያደናግሩ በፌስ ቡክ ላይ የተለቀቁ የወያኔ የሣይበር ሠራዊት ሲሆኑ እነርሱም አማራውን በአማራዊ ምንነቱና በኢትዮጵያዊ ማንነቱ እንዳይደራጅና ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድሞቹ ለማናቆር የተሰማሩ ናቸው:: ሌላው አማራ ሆነው ያልገባቸው ግን የገባቸው የሚመስላቸው አላዋቂዎች የሚፈጥሩት ጫጫታ ነው:: የመጀመሪያዎቹ የለየለት ለግል ጥቅም የቆሙ የጠላት መሣሪያ ናቸው:: እንደኔ ከወያኔ ሣይበር ሠራዊት ይልቅ ‘ከአማራ በላይ አማራ’ መስለው አማራንና ሌላውን ጥላሸት የሚቀቡ አላዋቂዎች ያስፈሩኛል:: ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር “በዚህ ዓለም ታማኝ ድንቁርና እና ጠንቃቃ ድንቁርና በላይ አደገኛ ነገር የለም” (Nothing in all the world is more dangerous than sincere ignorance and conscientious stupidity) ይላል:: 

‘አብን’ የአማራን የህልውና ጥቃት ለመታደግ የእራሱን ህልውና ጥቃት ከነዚህ ሃይሎች መጠበቅ፣ እራሱን ከነርሱ ማግለል (disassociate)፣ አመራሩን መፈተሽና በስሙ የሚፅፉና የሚናገሩትን በይፋ ማገድና ባለጌ ጥራዝ ነጠቆችን ከአመራርና ከአባልነት ማንሳት ይበጀዋል:: በድርጅቱና በስሙ በሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች መሃል መስመር ማበጀት ከጥፋት ያድነዋል:: እንኳን አማራን ከህልውና አደጋ ለመታደግ እራሱ ድርጅቱ በነዚህ አላዋቂዎችና ሠርገው በገቡ ግለሰቦች የህልውና አደጋ ተጋርጦበታል:: ፅዳት ያስፈልገዋል::

ችግሩ የት ላይ ነው?

ማንኛውም የጎሣ አደረጃጀት በጎሣ አስተሳሰብ ላይ ተመርኩዞ ሲመጣና የለየለት ጎሣዊ ፓለቲካን ሲላበስ መዝቀጥ ይጀምርና በቡድን ማሰብና መወሰን: ማንኛውንም ውሣኔ ያለ ግለሰቡ ፈቃድና እምነት በግለሰቡ ላይ መጫን ሲጀምር ዴሞክራሲን መጋፋት ይጀምራል:: አየን ራንድ እንደምትለው ” ምግብን በአንድ ገበታ መብላት ይቻላል:: ነገር ግን በአንድ ጨጓራ መፍጨት አይቻልም (We can share a meal among many friends, but we can’t digest it in a collective stomach “::

የጎሣ አደረጃጀት የተመሰረተበትን ዓላማ ሲስት ፍፃሜው አክራሪነት ይሆናል:: ይህ አክራሪነት ከሌሎች ጎሣዎች ጋር ‘እኛና እናንተ’ ከሚለው የንቁሪያና ፉክክር ሲጨርስ በራሱ ጎሣዎች ውስጥ ሌላ ጎጣዊ ልዩነትን ይወልዳል:: መጨረሻም ጉዳዩ እስከ ቤተሰብ ይዘልቃል:: በማህበር እንድናስብና በጎሣ እንድንደራጅ የሚያደርገን “የጎሣ ፌደራሊዝም” ነው:: የጎሣ አደረጃጀት በነባራዊ ሁኔታዎች ምክንያት የግድ ከሆነ፣ አደረጃጀቱ ብሄራዊና ወይም ሕብረ-ብሔራዊ የሚያደርገው የጎሣ አባላቱ አሰፋፈርና ስርጭትን ታሳቢ አድርጎ ነው:: ይህ አማራው ኢትዮጵያዊ መሆኑን ይናገራል::

መፍትሄውስ!

እራሱን ከማንነቱ ኢትዮጵያዊነት የነጠለ ጎሣዊ አደረጃጀትና ምንነት አንድነቱ የሚመሰረተው በዘር ሣይሆን በቋንቋ አንድነት ላይ በመሆኑ አደጋው የከፋ ነው::

ይህን እናስታውስ::
ኢራቆች አሜሪካንን ሲጋፈጡና በአሜሪካ ሲወጉ ኢራቃውያን ነበሩ:: ከጦርነቱ ፍፃሜ ማግስት ከእንቅልፋቸው ‘ሱኒ’ እና ‘ሺያ’ ሆነው ነቁ::

እራስን ከህልውና ጥቃትና አደጋ ለመታደግ ምክንያት አድርጎና በሁኔታዎች ተገዶ በጎሣ ዘቅጦ የሚደራጅ ኢትዮጵያዊነት እራሱንና ምንነቱን የሚከላከለው ኢትዮጵያዊ ማንነቱን ይዞ ነው:: እራሱን ነፃ ማውጣት ያስፈለገው ከማንነት ማህተም ሃገሩን ለማዳን ነው:: ሃገሩን እራሱን በመታደግ ካላዳነ እራሱም አይድንም:: ይህ ነው ከጠባብ ጎሰኝነት የሚለየው:: ደቡብ ሱዳን ከሰሜኑ ሱዳን በመለየቷ አልዳነችም:: በጎሣ ምንነት ተደራጅተው ሰሜኑን የተፋለሙ ደቡቦች ዛሬ በጎጥ ተከፍለው በእርስ በርስ ጦርነት ህዝባቸውን ያጋያሉ:: 

ከፓለቲካ አምባው እየራቁ ፓለቲካን መስራት አይቻልም:: ሁሉንም በጅምላ እያወገዙ የራስን ፓለቲካና አመለካከት ማግዘፍ አይቻልም:: የምንፈልገውን ነገርና ድርጅቶችን ማየት የምንችለው በራሳችን ህሊና እንጂ በፓለቲካ ምህዳር ውስጥ አይደለም:: እናስተውል!

በቃኝ!