ግልጽ ደብዳቤ ለወ/ሮ ሙፈሪያት ከሚል የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤና
የደኢህዲን ሊቀመንበር
ክፍል 4
ዋካ ከስውዲን
ለክብርነትዎ! በቅድሚያ የከበረ ሰላምታዬን አቀርባለሁ፡፡ ይህንን ጽሑፍ ያዘጋጀሁት ሰሞኑን በዳውሮ ዞን ተርጫና ዋካ ከተሞች የተፈጠረውን የሕዝብ ቁጣና አመጽ ምክንያቱን ከሕዝብ ተረድተው የመፍትሔ አቅጣጫ ለማመላከትና ችግሩን ለመቅረፍ ወደ አካባቢው ያቀናሉ የሚል ወሬ ስለሰማሁ ይህችን ደብዳቤ ልጽፍልዎት ወሰንኩ፡፡ በዚህች ጽሑፌ የችግሩ መነሻ ምክንያት ምን እንደሆነ ትንሽ ወደ ኋላ ሄድ ብዬ እጠቁምዎታለሁ፡፡ በዚህ አጋጣሚ በተፈጠረው ሁኔታ ህይወታቸውን ላጡት ወገኖቼ የተሰማኝን ጥልቅ ሀዘን እገልጻለሁ፡፡ ለቤተሰቦቻቸውም መጽናናትን እመኛለሁ፡፡
ለመግቢያ ያህል የዳውሮ ሕዝብ ላለፉት በርከት ያሉ ዓመታት ለመንግሥት የተለያዩ ጥያቄዎችን ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ ፍትህ ዴሞክራሲና በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የእኩል ተጠቃሚነት መብት አለመከበር፣ የወረዳ ማዕከል ወደ ሚያማክልበት ሥፍራ ይዛወርልኝ ጥያቄ፣ የተጨማሪ ወረዳ ጥያቄ፣ የመንገድና የሌሎች መሠረተ ልማት ጥያቄዎችን በየአስተዳደር እርከኑ ሲያሰማ ቆይቷል፡፡ መፍትሔ የሚሰጥ አቤቱታ ሰሚ አካል በማጣቱ ምናልባት እሰማ ይሆን ወይ በሚል የተከበሩ የሀገር ሽማግሌዎችንና የሐይማኖት አባቶችን መርጦ በመወከል ወደ ክልል አስተዳደርና ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በተደጋጋሚ በመላክ ጥያቄ አቅርቧል፡፡
ጥያቄው ምላሽ ባለማግኘቱ የተነሳ በተደጋጋሚ የዋካ ከተማ፣ ሎማ ወረዳ የዲሳ አካባቢ ሕዝብ፣ የጌና ወረዳ የወልደሃኔ አካባቢ ሕዝብ፣ በቶጫ ወረዳ የቶጫ ከተማ ሕዝብ በልማትና ከወረዳ ጋር በተያያዘ ሕዝባዊ አመጽና ትግል ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ታስሯል፡፡ ተንገላቷል፡፡ እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ድረስ ተከፍሎበታል፡፡
የተከበሩ አፈ ጉቤና የደኢሕዴን ሊቀመንበር ሆይ! ከሕዝብ ትግል ጋር በተያያዘ አንድ እጅግ ሲያሳዝነኝ የቆየ ነገር ላንሳልዎት፡፡ የዳውሮ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አለው፡፡ የማረሚያ ቤትም አለው፡፡ ይሁን እንጂ የልማት ጥያቄ አንስታችኋል የተባሉ ወንድሞቻችን ግፍ ተፈጽሞባቸዋል፡፡ ምንም ፍላጎታቸው ሳይጠየቅ ተገድደው በግዞት ወደ ሌላ ዞን / አካባቢ ፍርድ ቤት ቀርበው እንዲከሰሱና ወደዚያው ማረሚያ ቤት ተዛውረ እንዲታሰሩና በቅርብ ሆነው ከወዳጅ ዘመዶቻቸው ስንቅ እንዳያገኙ ተደርጓል፡፡ የሐስት ማስረጃ በገንዘብ እየተገዛ፣ ሕግ ወደ ጎን ተትቶ ዳኞች ከወቅቱ የደኢሕዴን ሊቀመንበርና የፖለቲካ ክፍል ኃላፊ ፖለቲካዊ መመሪያ ተሰጥቷቸው ያለርህራሄ በጭካኔ ምንም ወንጀል ባልሰሩ ሰዎች ላይ አምስት ዓመት ፈርደውባቸው ወላይታ ሶዶ ማረሚያ ቤት በእሥራት ተቀጥተዋል፡፡ እጅግ የሚያሳዝን ነው፡፡ ከሕዝብ አደራ የተሰጠው አመራር በሌላ ወገኑ ላይ እንዲህ ያደርጋል? የሚገርመው ሁለቱም በሥልጣን ላይ አሁን የሉም፡፡ ወደፊት እግዚአብሔርና ጊዜ አንድ ቀን በሕግ ፊት ተጠያቂ ያደርጋቸዋል፡፡
ይህ የሕዝብ በደል ያንገሸገሸው መምህር የኔሰው ገብሬ ወጣቶችን አስተባብረሃል ሕዝብን አነሳስተሃል ተብሎ አላግባብ ታስሮ ተቀጥቷል፡፡ የሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ጥያቄ ፍጹም አንባገነን በሆኑት ጥቂት የዞንና የክልል አመራር መጨፍለቁና የሕዝብ መንገላታት አንገሽግሾት ራሱ ላይ ቤንዚን አርከፍክፎ በእሳት በመቃጠል ዴሞክራሲያዊ ትግሉን የበለጠ አቀጣጥሎት አልፏል፡፡ የተከበሩ አፈ ጉባኤ ይህ የሰሞኑ የወጣቶች እንቅስቃሴና አመጽ የተዳፈነ ብሶት የወለደው ነው፡፡ መፍትሄውም እንደዚሁ ጥናትና ግልጽ የመንግሥት ምላሽ የሚሻ ነው፡፡
ለመግቢያ ያህል ይህን ካልኩ ወደ ሰሞኑን የወጣቶች / ላካይቶዎች አመጽ ላምራ፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ በወላይታና በዳውሮ ዞን አዋሳኝ ሆኖ የሚፈሰው የኦሞ ወንዝ ግልገል ግቤ ቁጥር 3 ግድብ ተሰርቶበታል፡፡ ግድቡ በሀገር ደረጃ ያለውን የኃይል ምንጭ እጥረት ለመቅረፍ ከሚጫወተው ሚና በላይ ለሀገራችን የሚያበርክተው የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ከፍ ያለ ነው፡፡ የተጠራቀመው ውሃ ከ2/3ኛው በላይ የተኛው ወደ ዳውሮ ነው፡፡ በዚህ የተነሳ የለበቂ የንብረት ካሳ የተባረሩትን አርሶ አደሮች በደል ሳይጨምር ሁለት ጉዳቶችን አስከትሏል፡፡
የመጀመሪያው ከዳውሮ ተርጫ ዋካ ወላይታ ሶዶ አዋሳ የሚወስደውን የጠጠር መንገድ ከ50 ኪ.ሜ. በላይ አርዝሞታል፡፡ ሁለተኛው አይተኬውን የዳውሮ ቅርስ የሆነውን የካዎ ሃላላ የድንጋይ ካብ አጥር ላይ የግድቡ ውሃ ተኝቶበታል፡፡ በዚህ የተነሳ ታሪካዊ ቅርሱ ተጎድቷል ከጥቅም ውጭ አድርጎታል፡፡ ወደ አዋሳ የሚወስደውን የመንገድ ርዝማኔ ከግንዛቤ አስገብቻለሁ ያለው የኢሕአዴግ / ወያኔ መንግሥት ዳውሮን ከአዋሳ የሚያገናኝ አዲስ የጠጠር መንገድ እገነባለሁ ብሎ ቃል ይገባል፡፡ የሚገነባውም አዲስ መንገድ ዳውሮ ተርጫ ወልደሃኔ ዱርጊ ዱራሜ አዋሳ እንደሚሆን ለሕዝብ ይፋ ተደርገ፡፡ ይህ ሊሰራ ቃል የተገባው የጠጠር መንገድ ወደ አዋሳ ለመጓዝ በወላይታ ሶዶ በኩል ከሚያልፈው መንገድ ፍጹም አጭር ነው፡፡
ሕዝቡም ተደሰተ እግዚአብሔርንና መንግሥትን አመስግኖ ውጤቱን ይጠብቅ ጀመር፡፡ ካድሬዎቹም መንግሥታችን መንገድ በብዙ ሚሊዮን ብር ሊገነባ ነው የምርጫ ድምጽ ስጡን ንቧን ምረጡልን ብሎ ስበኩ፡፡ ሕዝቡም ካድሬውን መንግሥትን አምኖ አደረገ፡፡ ከዚያ ቢጠበቅ ቢጠበቅ ምንም የመንገዱ ወሬ የለም፡፡ ወረዳ አመራር ቢጠየቅ ዞን ያውቃል ሆነ መልሱ፡፡ ዞን ሲጠየቅ ክልል ያውቃል እኔ አላውቅም ይል ገባ፡፡ ይህ ጉዳይ እያደር ወጣቱን ያስቆጣው ጀመር፡፡
የዳውሮ ወጣቶች ይህ ቃለአባይ የሆነ ውሸተኛ መንግሥት አበሳጫቸውና ምን እናድርግ ብለው መክረው ጥንት አያቶቻችን ከጠላት ራሳቸውን ለመከላከል የዳውሮን ዙርያ መለስ በድንጋይ ካብ አጥረዋል፡፡ ስለዚህ እኛም የእነርሱን የአያቶቻችንን ወኔ አንግበን ይህን መንገድ በዶማ በአካፋና ባለን ኋላቀር መሳሪያ መሥራት አለብን ብለው ይወስናሉ፡፡ ወደ ተግባርም ይገባሉ፡፡ ባለፈው ሐምሌ 28 ቀን 2010 ዓ.ም የመጀመሪያውን የመንገድ ሥራ ዘመቻ እጅግ በሚደንቅ ወኔ ፍቅርና አንድነት አከናወኑ፡፡ ላባቸውን አፈሰሱ፡፡ የሀገር ሽማግሌዎች የሃይማኖት አባቶች የተሳተፉ ሲሆን ሴቶች እናቶቻችን ያላቸውን አዘጋጅተው ስንቅ ቋጥረው ከወጣቶቹ ጎን ተሰልፈዋል፡፡ ቃላት የማይገልጸው ትልቅ ሥራ ተሰራ፡፡
ይህንን የመሰለ የወጣቶች / ላካይቶዎች እልህ የተሞላውን የሥራ ዘመቻ የሕዝብ ተሳትፎ ድካምና ውጤት የደቡብ ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ ተሳለቀበት፡፡ ቀደም ሲል የነበረ መንገድ በሕዝቡ ተሳትፎ ተጠገነ የሚል ውሸት የሆነ ዜና በፌስ ቡክ አካውንቱ አሰራጨ፡፡ ከላይ በመግቢያው ላይ በጠቀስኳቸው መነሻዎች ሆድ ብሶት የነበረውን ወጣት ዜናው የበለጠ አበሳጭቶት አስቆጥቶት ወደ አመጽ መሩት፡፡ መጣቱ የራሱን ንብረት መልሶ አጠቃው፡፡
አመጽ በምንም መስፈርት አይደገፍም፡፡ የሕዝብንም ሆነ የግለሰብን ንብረት ማቃጠል፣ ከየቢሮው መረጃ መቀዳደድና ማውደም ፍጹም ተገቢ አይደለም፡፡ ሕገ ወጥነት ነው፡፡ ስህተት ነው፡፡የመረጃና ማስረጃ ማውደም ተግባር የተከናወነው በወጣቶች / ላካይቶዎች ፍላጎት ብቻ የሆነ ነው ብዬ ለማመን ይቸግረኛል፡፡ ሌላ ብዙ ለማለት መረጃ የለኝም፡፡ ሌላውና ትልቁ ችግር ሕዝብና የፖለቲካ አመራሩ በተለያዩ በርካታ ምክንያቶች ሆድና ጀርባ ሆኗል፡፡ በፍጹም ላይስማሙ ተለየይተዋል፡፡ ይሄ ችግሩን አባብሶታል፡፡
የዳውሮ ካድሬዎና አመራሮች አሁን ሀገራችን ውስጥ ለውጥ ለማምጣት ትግል ጥረት እየተደረገ ስለመሆኑ ማወቃቸው ያጠራጥረኛል፡፡ ምክንያቱም ከወጣቶች ለሚቀርብላቸው ጥያቄ የሚሰጡት ግብረ መልስ ይገርመኛል፡፡ ዶክተር ዐቢይ አህመድ በአጭር ጊዜ ያመጡትን ለውጥ በመደገፍ ሰልፍ ለማድረግ ወጣቶች እንደተቸገሩ አውቃለሁ፡፡ ሰልፍ ማድረግ አትችሉም ብለው ማስታወቂያ በመለጠፍ ወጣቶችን ያስፈራሩ ወረዳዎች አሉ፡፡ ይህ የሚያሳየው በሀገራችን ላይ እየመጣ ያለውን ለውጥ የማይደግፍ ብቻ ሳይሆን ለማደናቀፍ እንዲሁም ወጣቱ ሕዝቡ ጸረ ለውጥ እንዲሆን እየሰሩ ያሉ ይመስለኛልና ይህንን የማስተካከል ሥራ ሊሰራ ይገባል፡፡
የተከበሩ የደኢህዴን ሊቀመንበር አንድ ትክክለኛ መረጃ ልስጦት፡፡ እውነትነቱን አጣርተው አረጋግጠው ለዚህ ሕዝብ እንደሚያዝኑ እርግጠኛ ነኝ፡፡ የዳውሮ ተርጫ ወልደሃኔ ዱርጊ ዱራሜ መንገድ በፌዴራል ደረጃ የቅየሳ ሥራ ተሰርቷል፡፡ የመንገዱ ግንባታ ሥራ እንዲከናወን የጨረታ ማስታወቂያ በ2007 ዓ.ም በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ በይፋ ወጥቷል፡፡ በወቅቱ የነበሩ የትራንስፖርትና መገናኛ ሚኒስትርን ይጠይቁ፡፡ ስማቸውን ላለማንሳት ብዬ ነው፡፡ የአዲሱ የለውጥ ኃይል አጋዥ በመሆናቸው በአቅራቢያዎ አሁንም አሉ፡፡ መስሪያ ቤታቸው ያወጣውን ጨረታ በሌላ ማስታወቂያ ጨረታውን ቶሎ ሰርዝ ተብለው ተገድደው እንዲሰርዙ ተደርጓል፡፡ ለምን ይህ እንደተደረገና ይህን እንዲፈጽሙ ማን እንዳዘዛቸው ይጠይቋቸው፡፡ የመንገድና ትራንስፖርት ሚኒስትሩ ታዘው ነው ሥራው የቆመው፡፡ የወቅቱ የትራንስፖርትና መገናኛ ሚኒስትር ለሕዝብ ይፋ ባያደርጉ እንኳን ለእርስዎና ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ እውነቱን ይናገራሉ ብዬ አምናለሁ፡፡ መንገዱ እንዳይሰራ የተቆለፈው በፌዴራል ደረጃ ነው፡፡ መፍትሔው ቁልፉን ፈትቶ ጨረታው እንደገና እንዲወጣ አድርጎ ሥራውን ማስጀመር ብቻ ነው፡፡ ቢቻል ይህንን ሆን ብሎ የቆለፈውን ግለሰብ ሕዝብን ይቅርታ እንዲጠይቅ ማድረግ ነው፡፡
ችግሩን ለመፍታትና ለሕዝቡ ፍትሃዊ ውሳኔ እሰጣለሁ የሚል አመራር ፌዴራል ደረጃ ያለ ባለሥልጣን ብቻ ነው፡፡ ችግሩ በክልል ደረጃ አይደለም፡፡ እርስዎ ደግሞ እንደ አጋጣሚ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ እንደመሆንዎ መጠን ያልዎትን ሥልጣን ተጠቅመው ሁሉንም ነገር ወደ መንደሬ በሚል ኢትዮጵያዊነት በጎደለው መንደርተኛ አንባገነን የተዘጋውንና የተሰረዘውን መንገድ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ጋር ተወያይተው ከቆመበት ቢያስቀጥሉ ፍትሃዊ የሆነ አመራር / መሪ / ያስብልዎታል፡፡ ችግሩን ደርሰውበት መፍትሔ ይሰጡ ዘንድ የዚህን ደብዳቤ ግልባጭ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አደርጋለሁ፡፡
አንዲት ነገር ላክልና ላብቃ፡፡ፌዴራል ፖሊስ በተደጋጋሚ ዳውሮ ገብቶ ያውቃል፡፡ ጊዜያዊ ማስታገሻ በመሆን አመጹን ይበትናል እንጂ ዘለቄታዊ መፍትሄ አይሰጥም፡፡ በመሆኑም በዚህ የዳውሮ ተርጫ ጉዞዎ ከሕዝቡ በተለይም ከወጣቶች ለሚነሱ ጥያቄዎች ፖለቲካዊ ብቻ ሳይሆን ተጨባጭ ምላሽ የሚሆን ነገር ለማቅረብ ይዘጋጁ፡፡ ፖለቲካዊ የሆነ የውሸት መልስ መድረክን ለመሹለክ ተብሎ የሚሰጥ የፈጠራ ወሬ ሕዝብንና መንግሥትን የለየው በመሆኑ እንደ አንድ የለውጥ ኃይል ይህ ከእርስዎ አይጠበቅም፡፡ በመሆኑም ህዝቡን ያዳምጡት ተጨባጭ ምላሽ ይስጡት፡፡
በመጨረሻም የግል አስተያየቴን ላስቀምጥና ላብቃ፡፡ የዳውሮ ወጣቶች/ ላካይቶዎች ሕግና ሥርዓትን የሚያውቁና የሚያከብሩ ናቸው፡፡ ዳግም እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ እንዳይከሰት የየበኩላቸውን ድርሻና ኃላፊነት እንደሚወጡ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ በእርስዎ በኩል የሚከተሉትን ነጥቦች ቢያዩዋቸው በጎ ነው፡፡
ሕዝብን የበደሉ፣ ሕዝብ የጠላቸውን አመራሮች በሕዝብ ቀጥተኛ ተሳትፎ ከቀበሌ እስከ ዞን አመራር ድረስ ያሉት ካድሬዎች ገምግመው ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ ቢያደርጓቸው? ሕዝብን የበደሉ የመዘበሩ የዘረፉትን ሌቦች ከሕዝብ በሚቀርበው መረጃ ትክክለኛነቱ በኦዲት ተጣርቶ ወደ ሕግ እንዲቀርቡ ቢያደርጉ? አውቀውም ይሁን ሳያውቁ አዲስ እየመጣ ያለውን ለውጥ ወደ ዴሞክራሲ እየሄድን ያለንበትን መንገድ ለመዝጋት፣ ጉቶ ለመሆን፣ ከቻሉም ዴሞክራሲያዊ ትግሉን ለመቀልበስ የሚሰሩ ካድሬዎች አሉና ከመንገድ ላይ ዞር እንዲሉ ማድረግ ቢችሉ? የድጋፍም ሆነ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ የዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብት እንደመሆኑ ማንም ካድሬ መከልከል እንደማይችል በይፋ ካድሬዎችን ቢመክሩ ቢያስተምሩ? በየመዋቅሩ በምትካቸው የሕዝብ ተቀባይነትና አመኔታ ያላቸው፣ የተማሩ፣ ጨዋ የሆኑ፣ ሕዝብን በተለይም ወጣቱን ማዳመጥ የሚችሉ ሰዎች የድርጅትዎ አባል መሆኑ እንደ መሥፈርት ሳይታይ በሕዝብ ቀጥጠኛ ተሳትፎ እንዲተኩና አመራሩን እንዲይዙ ቢያደርጉ? በዞኑ መረጋጋት ከመምጣቱም ባሻገር ቀጣይ ሀገራችንን ፍጹም ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ የሚደረገውን የለውጥ ትግል ያሳድገዋል፡፡ ሕብረተሰቡም መጠነኛ ፋታ ያገኛል እርስዎንም ያመሰግንዎታል ብዬ አምናለሁ፡፡
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
ኢትዮጵያ ሀገራችንን እግዚአብሔር ይባርክ!
ግልባጭ ለኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ
አዲስ አበባ
ለደኢሕዴን / ኢሕአዴግ ምክር ቤት ” የለውጥ ትግሉን ተቀላቀሉት”
ክፍል 2
ዋካ ከስውዲን
”ጮሻይ ይና አቻይ አሼና” ከውስጥ ገፍቶ የመጣን ትውኪያ ጥርስ አያቆመውም በሚል እንድ መልዕክት
አስተላልፌላችሁ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ከአርባ አምስት የደኢሕዴን ተወካይ የሆናችሁ የኢሕአዴግ ምክር ቤት አባላት ወደ 20 የምትሆኑ ጥሪዬን ተቀብላችሁ ዶክተር ዐብይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው እንዲመረጡ ድምጽ በመስጠታችሁ ጥሪዬን ለተቀበላችሁት አመራሮች ምንም አንኳን ማንነታችሁን ባላውቅም ከልቤ
አመሰግናችኋለሁ፡፡ የሰራችሁትን ሥራ ውጤት እያያችሁት ነው፡፡ ሀገር ወደ ለውጥ ጎዳና ገብታለች፡፡ ሁሉም ተባብሮ ለውጡን እውን ለማድረግና ዴሞክራሲያዊት ሀገር እንድትኖረን ለማብቃት የየድርሻውን ማበርከት ይጠበቅበታል፡፡
ደኢህዴን/ ኢሕአዴግ የደቡብ ክልል ገዢ ፓርቲ ነው፡፡ የመንግሥት መዋቅሩንም የተቆጣጠረው ይኸው ፓርቲ ነው፡፡ ደኢሕዴን አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ተፍረክርኳል፡፡ በክልሉ ውስጥ ያሉትን ብሔር ብሔረሰቦችን በፍትሃዊነት በእኩልነት እየመራ ያለ አይመስልም፡፡ ለዚህ ብዙ ማስረጃ ማቅረብ ቢቻልም በሲዳማ ውስጥ በሚኖሩ የወላይታ ተወላጆች በሆኑት ወገኖቻችን ላይ የሲዳማ ወገኖቻችን ያደረሱባቸው እጅግ አሳዛኝ ዱላና
ዝርፊያ እንዲሁም ግድያ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ በክልሉ የሚኖሩ ኦሮሞ ወገኖቻችንን ለረጅም ጊዜ ከኖሩበት ሀብት ንብረት ካፈሩበት ቀዬ ማፈናቀል ሌላው ማሳያ ነው፡፡ በራሱ ክልልም ሆነ ከሌሎች ክልሎች ጋር የተፈጠረን ችግር ደኢህዴን የመፍታት አቅሙ ተሽመድምዷል፡፡
በጥላቻ ተነሳስተው ሕዝብን በማፈናቀልና ወንጀል የሰሩትን ግለሰቦች ለይቶ አጣርቶ ወደ ሕግ አቅርቦ የተበደሉትን ክሶ የተፈናቀሉትን ወደ ቀድሞ ቀያቸው የመመለስ ውሳኔ ከደኢሕዴን የክልል አመራር ይጠበቅ
ነበር፡፡ ግን ምንም የሚታይ የረባ እንቅስቃሴ የለም፡፡ የእርምት እርምጃ በሚፈለገው ደረጃ አለመወሰዱ ውስጥ ለውስጥ የልዩነትን መጋረጃ እያሰፋው ነው፡፡ ይህ ድርጊት መጥፎ አርአርያነት ያለው እንደመሆኑ መጠን በቂ ጥንቃቄ ካልተደረገ ችግሩ ቀስ በቀስ ወደ ሌሎች ዞኖች በስፋት እያደገ እንዳይሄድ ሥጋት አለኝ፡፡ ባለኝ መረጃ
በአንዳንድ ዞኖች ተመሳሳይ ችግሮች ይታዩ ጀምሯል፡፡
የደኢህዴን/ ኢሕአዴግ ክልሉን በብቃት መምራት አለመቻል በክልሉ በግልጽ እየታየ ነው፡፡ የዞንና የወረዳ የአስተዳደር መዋቅሮችን እጅግ እየተዳከሙ ነው፡፡ ከአሁን አሁን የሕዝብ ማዕበል መጥቶ ይውጠኛል እያለ
እያንዳንዱ አመራር ፍርሃት ገብቶታል፡፡ የሕዝቡ የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ እንዲሁም የልማት ጥያቄ
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተ መጥቷል፡፡ በዞኖች በወረዳዎችና በከተማ አስተዳደሮች ውስጥ የሚገኘው የተማረ የሰው ኃይል የሥራ እድል እንዲያገኝ መንግሥት በተገቢው ደረጃ ስላልሰራ ሰርቶ ራሱን ችሎ ሀገር ማገልገል የሚችለው ወጣት የሰው ኃይል የሥራ አጥ ሆኖ ደክሞና ለፍቶ ያስተማረው ቤተሰቡ ጫንቃ ላይ ወድቋል፡፡ ይህ ቀጣይ የሚማረውን ታዳጊ ወጣት የመማር ተነሳሽነትን ያሳጣ ሲሆን ወላጅንም ልጆቹን ተግቶ እንዳያስተምር ሞራሉን እየጎዳው ይገኛል፡፡
ከወጣቶች የሥራ ዕድልና በልቶ የመኖር ጥያቄ ባሻገር ሕዝቡን እጅግ ያማረሩትን አንዳንድ ነገሮችን እንመልከት፡፡ በየወረዳው የመሠረተ ልማት አለመሟላት፤ የመልካም አስተዳደር አለመኖር፤ የሕብረተሰቡ የተጨማሪ ወረዳ ጥያቄ በተገቢው መንገድ ተጠንቶ መፍትሔ እንዲያገኝ አለማድረግ፤ ሕብረተሰቡ ተገድዶ እንዲወስድ የተደረገውን የማዳበሪያ ዕዳ እንዲከፍል እየተገደደና እየደረሰበት ያለው ጫና ፤ ከቀበሌ አስተዳደር ጀምሮ በየደረጃው ባሉት የመንግሥት መዋቅሮች ሁሉ ሕዝቡ የለማንም ጣልቃ ገብነት ያሻውን አመራር በዴሞክራሲያዊ መልኩ መርጦ
አመራር የሚያደርግበት መብት ማጣት፤ በደኢሕዴን ተጽዕኖና ውሳኔ ወደ አመራር የሚመጡ ካድሬዎች የሕዝቡን ችግርና ፍላጎት ተረድተው ተገቢና ወቅታዊ የሆነ ምላሽ ለመስጠት አለመቻል፤ በየደረጃው ያለው አብዛኛው አመራር ከካድሬነት የዘለለ ከሚጠበቅበት የሥራ ድርሻ ጋር የተመጣጠነ እውቀት፣ የሥራ ችሎታና
ልምድ አለመኖር፤ አንዳንድ አመራሮች በሙስና የሕዝብንና የመንግሥትን ካዝና በማራቆት ተገቢ ባልሆነ መልኩ መበልጸግ ወዘተ የመሳሰሉት ችግሮች ተዳምረው ሕብረተሰቡን ያማረሩና ወደ ለውጥ እንቅስቃሴ ወይም ትግል እንዲገባ አስገድደውታል፡፡
ሁሉም ዜጋ ተጠቃሚ ሊሆን የሚችለው በኢትዮጵያችን እየመጣ ያለው የለውጥ እንቅስቃሴ በአግባቡ ከተመራና ወደሚፈለግበት ግብ መድረስ ሲችል ብቻ ነው፡፡ በዶክተር ዐብይ አህመድና በጓዶቻቸው ብርቱ ትግል እየመጣ ያለውን ለውጥ ሊጎዳ ከሚችል ማንኛውም አፍራሽ እንቅስቃሴ የደኢሕዴን ካድሬ ሁሉ ሊታቀብ
ይገባል፡፡ የምንፈልገው ለውጥ እንዳይመጣ የሚሹ አሉ፡፡ ጥቅማችንን ያሳጣናል ሥልጣን ያስለቅቀናል የሚሉ አሉ፡፡ አንዳንድ የደቡብ ዞኖች ወጣቱ ለዶክተር ዐብይ አህመድና አመራራቸው የድጋፍ ሰልፍ እናድርግ ብለው ጠይቀው የተከለከሉና ችግር ቢፈጠር ኃላፊነት ትወስዳላችሁ በሚል ማስፈራሪያ የድጋፍ ሰልፍ የከለከሉ ዞኖች አሉ፡፡ ይህ የሚያሳየው ለውጡ ያልተዋጣቸው አመራሮች እንዳሉ ያመላክታል፡፡
ሕዝቡ በተለይም ወጣቱ በየዞኑና በየወረዳው እያካሄደ ያለው የትግል እንቅስቃሴ በአግባቡ ካልተመራ ወደማይፈለግበት አቅጣጫ ሊያመራ ይችላል፡፡ ሥርዓተ አልበኝነት ተፈጥሮ ነገ ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ሁኔታ እንዳይፈጠር ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል፡፡ በዚህ ረገድ የሕዝብ አመኔታ ያላቸው የሀገር ሽማግሌዎች፤ የየአካባቢው ምሁራን፤ የለውጥ እንቅስቃሴውን የሚመሩ ወጣቶች፤ በየእርከኑ ያላችሁ ካድሬዎች፤ የፖሊስና
የጸጥታ ኃይሎች ብርቱ ሥራ ከፈታችሁ ይጠብቃችኋል፡፡ የእናንተ በጋራ ተባብሮ መሥራት በየአካባቢው ሊከሰት የሚችለውን ተገቢ ያልሆነን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ከማስቻሉም በላይ በሀገሪቱ እየመጣ ያለውን የለውጥ
ትግል ወደ ትክክለኛ ግብ እንዲደርስ ይረዳዋል፡፡
የሀገር ሽማግሌዎች ይህ እየመጣ ያለው ለውጥ እንዲሳካ መጫወት የሚገባችሁ ሚና አለ፡፡ በሁሉም የደቡብ
ክልል የማሕበረሰብ ክፍሎች ባለው ባህል መሠረት የሀገር ሽማግሌዎች ትከበራላችህ፡፡ የምትሉት ይደመጣል፡፡ በጎ ተጽዕኖ ማሳረፍ ትችላላችሁ፡፡ ስለዚህ ይህንን ተሰሚነታችሁን ተጠቅማችሁ በአካባቢያችሁ ለውጡን ሊያደናቅፍ የሚችል እንቅስቃሴ እንዳይኖር ተግታችሁ ተከታተሉ፡፡ ወጣቶች የሚያነሱት ጥያቄ ትክክል ነው፡፡ ሥርዓቱ
የፈጠረው ችግር ነው፡፡ ደክመው ተምረው የሥራ ዕድል በማጣታቸው ተቆጥተው ወደ ለውጥ ትግሉ ገብተዋልና የሚያደርጉት ትግል በቁጣ ወደ ማይፈለግበት መስመር እንዳይሄድ ክትትላችሁ ምክራችሁ ተግሳጻችሁ እጅግ
አስፈላጊ ነው፡፡
የየአካባቢው ምሁራንም የሚጠበቅባችሁ ሥራ አለ፡፡ ዕውቀታችሁንና ልምዳችሁን ተጠቅማችሁ የለውጥ ኃይሉን ተቀላቀሉ እርዱ፡፡ ለውጡ አይቀሬ መሆኑን ታውቃላችሁ፡፡ ከዳር ሁናችሁ አትመልከቱ፡፡ የሚመጣው ለውጥ ጥቅሙ ለሁሉም ዜጋ ነው፡፡ ትግሉ በትትክክለኛ መስመር እንዲሄድ የራሳችሁን ድርሻ ተወጡ፡፡ ወጣቶችን በኃሳብ በምክር በማቴሪያል እርዷቸው፡፡ ለውጡ በአግባቡ ከተመራ የሚኖረውን በጎ ፋይዳና
በአግባቡ ካልተመራ በሀገር ደርጃ የሚያስከትለውን አደጋ እያሳያችሁ ከወጣቱ ጋር ሁናችሁ የምትችሉትን ሁሉ አድርጉ፡፡ የለወጡ ሂደት ያልታየው የተኛ ካድሬ አይታጣምና ቀስቅሳችሁት ምከሩ፡፡ ሕዝቡንም ስለመብትና ግዴታው አስተምሩ፡፡ የለውጥ ኃይሉን የመርዳት ኃላፊነታችሁን ተወጡ፡፡
በየደራጃው ያላችሁ ካድሬዎች በዞናችሁና በወረዳችሁ ሕዝብ የሚያከብራቸው፤ በሥራቸው ተቀባይነትና ተሰሚነት ያላቸውን ባለሙያዎች የተለያየ ምክንያት ፈጥራችሁ ከፖለቲካው መስመር አስወጥታችኋል፡፡
አንዳንዶቹን ከአካባቢው አስኮብልላችኋችዋል፡፡ ከሥራና ከደመወዝ አግዳችሁ አስፈራርታችሁ አርቃችኋቸዋል፡፡ ከእናንተ በእውቀት በሥራ ልምድ በችሎታ የሚበልጥ ሰው ምንም የሕዝብ ፍቅርና ተቀባይነት ቢኖረውም ባላችሁ የሥልጣን ስስት የተነሳ ዘላለም የምትገዙ መስሏችሁአርቃችኋቸዋል፡፡ በተልካሻ ምክንያት በሐሰት ክስና ውንጀላ የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ እናንተን የሚተካ የተማረ ሰው በዙርያችሁ እንዳይኖር ሰርታችኋል፡፡ በቀላሉ የማይተኩ ልምድና እውቀት ያላቸውን ምሁራን ገፍትራችሁ ያለ ዕድሜያቸውና ፍላጎታቸው በጡረታ ሥም አስወግዳችኋቸዋል፡፡ አሁን አሁን ወጣቱ በሚመራው የለውጥ እንቅስቃሴ እየከፈላችሁ ያላችሁት ዋጋ ይህንንም ይጨምራል፡፡ በመሆኑም ቀጣይ ሥልጣናችሁን ለሕዝብ አስረክባችሁ ይቅርታ ለመጠየቅ ወስኑ፡፡
ካድሬዎች ሆይ የለውጡ ሐዋርያ የሆኑትን ወጣቶች እንደ አፍራሽ ኃይል አትመልከቷቸው፡፡ የሚያቀርቡትን የመብት ጥያቄ መፍትሔ መስጠት አለመቻላችሁን ብታውቁትም ቢያንስ ለማዳመጥ ሞክሩ፡፡ በሐሰት
አትወንጅሏቸው፡፡ ሥራ ስላጡ ብቻ የሀገርና የሕዝብ ጠላት አድርጋችሁ የማየት ልምዳችሁን አጥፉት፡፡ ነገ ሀገር ተረካቢዎች እነርሱ ናቸው፡፡
በየወረዳው የምትገኙ ወጣቶች ሆይ! እሮሯችሁን እሰማለሁ፡፡ የምታቀርቡት የመብት ጥያቄ ነው፡፡ ሥራ አጥ ያደረጋችሁ የፖለቲካው አመራር ድክመትና መንግሥት ሲከተለው የነበረ ደጋጋ ፖሊሲ ውጤት ነው፡፡ ይህ የሚለወጠው በጋራና በተቀናጀ ትግል ሙሉ በሙሉ የሥርዓት ለውጥ ሲመጣ ብቻ ነው፡፡ የወያኔ ኢሕአዴግ ሥርዓት በአንዳችም ጥገናዊ ለውጥ ይሻሻላል ተብሎ ጊዜ የሚሰጠው አይደለም፡፡ ስለዚህ ወጣቶች እጅ ለእጅ ተያይዛችሁ ጉዞአችን እስከ ቀራንዮ ነው ብላችሁ የሥርዓት ላውጥ ለማምጣት ትጉ ታገሉ፡፡ ሁሉም ካድሬ የቀን ጅብ አይደለም፡፡ የምታደርጉት እንቅስቃሴ ሁሉ በማስተዋል ይሁን፡፡
ደቡብ ውስጥ ክልል ቢሰጠው የሚጠላ አንድም ብሔር ወይም የዞን መዋቅር የሚገኝ አይመስለኝም፡፡ ነገር ግን በጋራ ሁሉም ተሳስቦ፤ እርስ በርስ መበዳደል ቀርቶ፤ ለሁሉም የሚበጅ ሥርዓት ገንብቶ፤ እኩል ተጠቃሚነትን
እውን በማድረግ፤ በኢትዮጵያዊነት ተቃቅፎ ተደጋግፎ በፍቅር በአንድነት መኖር ይሻላልና ሁላችንም ለአብሮነት ብንሰራ ይበጀናል፡፡ የራስን ብሔር መሸሸጊያ ለማድረግና ወንጀል ሰርቶ ለመደበቅ ተብሎ ክልል ለመሆን የሚደረግ ትግል ወደ ታች የበለጠ ቁልቁል ያሳንሰናል እንጂ ከፍታ አይመስለኝም፡፡
ክልል መጠየቅ መብት መሆኑን አስተውላለሁ፡፡ አሁን ሀገራችን ያለችበትን ተጨባጭ የፖለቲካ ሁኔታ ያላገናዘበ የክልል ይገባናል ጥያቄ ጤንነት ያሳስበኛል፡፡ ወደፊት ጊዜውን ጠብቆ የለውጥ ትግሉ ሲገባደድ ሊነሳና መፍትሔ ሊያገኝ የሚችል ነው፡፡ እኛ ክልል እናግኝ እንጂ ለሌላው አይገደንም ማለት ምን ማለት ነው? በእንዲህ ዓይነት
አካሄድ ነገ ሀገር ይኖረናል ወይ? መንግሥት ደቡብን ወደ ሃምሳ ክልል አድርጎ መሸንሸን ይችላል ወይ? የክልል ጥያቄን በሰፊው አጋግሞ ሕዝብን ቀስቅሶ አነሳስቶ ጥያቄውን የወንጀለኞች የሙሰኞች መከለያ መሽሸጊያ ለማድረግ የታሰበ ይመስላልና የእያንዳንዱ ዞንና ልዩ ወረዳ ሕዝብ ቢያስብበት መልካም ነው፡፡
በየደረጃው ያላችሁ የደኢሕዴን ካድሬዎች አሁን በሞተ ሰዓት የምታደርጉት መተራመስ የሚጠበቅ ቢሆንም ሕዝቡ በትግሉ ያመጣውን ለውጥ ለማስቆም አትችሉምና ለዚያ አትስሩ፡፡ በወላይታና በአንዳንድ ዞኖች ለደኢሕዴን የምታዋጡትን የአባልነት መዋጮ ማቆማችሁ ሌሎችንም ማስቆማችሁ ጥሩ ነው ቀጥሉበት፡፡ ነገር
ግን የየብሔራችሁ ሕዝብ ቀስቅሳችሁ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር የማለያየት የማጣላት ሥራ እየሰራችሁ ያላችሁ አቁሙ፡፡
የሰራችሁትን ወንጀል ለመሸፈን ወይም አላግባብ የመዘበራችሁትን ሀብት ለመታደግ ስትሉ ሕዝብን እንደ መደበቂያ ዋሻ ለመጠቀም ሲባል የሚደረግ ትግልና ጥረት የኋላ ኋላ ውጤቱ እናንተ ራሳችሁን የበለጠ የሚጎዳ ይሆናል፡፡ ስለዚህ የምመክራችሁ እናንተም ከለውጥ ኃይሉ ጋር አንድ በመሆን መቀነስ ሳያገኛችሁ ፈጥናችሁ ተደመሩ፡፡
ሕዝብን በአግባቡ ልትመሩ የሚያስችላችሁ የሀገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ ያገናዘበ ፖሊሲ ሳይኖራችሁ ሕዝቡን ወደ ቁልቁለት መርታችሁታልና በዚህ አድራጎታችሁ ተጸጽታችሁ የለውጥ ትግሉን ተቀላቀሉ፤ እውነተኛ የሕዝብ ተመራጭ ባለመሆናችሁ የተነሳ የሕዝብ እምነት ስለሌላችሁ በፈቃዳችሁ ሥልጣናችሁን ለቅቃችሁ የለውጥ ትግሉን ተቀላቀሉ ፤ መልካም አስተዳደር አገልግሎት ልትሰጡ የሚያበቃ የትምህርት ዝግጅት የሥራ ልምድና
ቅንነት በማጣታችሁ እንድትመሩት እንዳልፈለገ አውቃችኋልና ለሕዝቡ ሥልጣን ማስረከብ ወቅታዊ እርምጃ መሆኑን አምናችሁ አኩራፊነትን ትታችሁ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ከሚመሩት የለውጥ ትግል አካል ሁኑ፡፡
ጥሪ ለደኢህዴን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሙሉ፥
“” ጮሻይ ዪን አቻይ አሼና ” ከውስጥ ገፍቶ የመጣን ትውኪያ ጥርስ አያቆመውም
ዋካ ከስዊድን
በደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ውስጥ ከሚገኙት የምርጫ ወረዳዎች የተውጣጣችሁ የፌዴራል ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የሆናችሁ ወንድምና እህቶች በያላችሁበት የከበረ ሰላምታዬ ይድረሳችሁ!
ይህንን መልዕክት የማስተላልፍላችሁ አንድ የክልሉ ተወላጅ የሆንኩ ኢትዮጵያዊ ወንድም ነኝ፡፡ መልዕክቴ በሌሎች ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች ያልተላለፈና የማታውቁት ያልሰማችሁት አዲስ ነገር አይደለም፡፡ እንደ በጎች በቀኝ እንደ ፍየሎች ደግሞ ከግራ የምንቆምበት ትክክለኛው የሰማያዊው የፍርድ ቀን እንደሚጠብቀን አብዛኛዎቻችን እንደምናምን ሁሉ አሁን በምንሰራውና በምንወስነው የምድራዊው ሥራ ሕዝብ የሚፈርድበት እያንዳንዳችን እንደየሥራችን የምንጠየቅበት እንደበጎነታችን የምንመሰገንበት እንደወንጀላችን ደግሞ ለፍርድ የምንቆምበት አንድ የፍርድ ቀን በቅርብ እፊታችን እንደሚኖር አምናለሁና የሰማችሁትም ስሙት ባትሰሙትም ስሙት ብዬ የጉዳዩን እጅግ አንገብጋቢነት አበክሬ በመግለጽ ከሕዝብና ከእውነት ጎን እንዳትለዩ ለማሳሰብ ነው፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ተጨባጭ ሁኔታዎችን እንደምትገነዘቡ እሙን ነው፡፡ ሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራት / TPLF / የ”ኢሕአዴግ” አባል የሆኑትን አራቱን ብሔራዊ ድርጅቶችን /ህወሃትን ጨምሮ / አጋር ፓርቲዎች እያለ የሚያንቆለጳጵሳቸውንም የብሔር ድርጅቶችን ጠቅልሎ የሚመራው የሚቆጣጠረው አመራሮችን የሚሾመው የሚሽረው የሚቆርጠውም ሆነ የሚፈልጠው ህወሃት መሆኑን እናንተን ለማስረዳት መሞከር ድፍረት ነው፡፡
እንደምታውቁት የደቡብ ክልል አወቃቀር በራሱ የህውሃት የእጅ ሥራ ውጤት ነው፡፡ አንዳች ታሪካዊ መሠረት የሌለው በጉልበትና በማን አለብኝነት የተመሰረተ አስተዳደር ነው፡፡ ከትግራይ ክልል ጋር እንኳን ብናነጻጽር ቢያንስ አራት ክልል ሊሆን የሚችል ሰፊ የህዝብ ቁጥርና የቆዳ ስፋት ያለው በጫና ያለ ሕዝቡ መልካም ፈቃደኝነት የተዋቀረ ክልል ነው፡፡
ከወያኔ ቀደም ሲል በነበረው የሀገር አስተዳደር መዋቅር የትግራይ ክፍለ ሀገር 7 አውራጃ የነበረው አንድ ክልል እንዲሆን ሲከለል ጋሞ ጎፋ ከፋ ከፊል ሸዋና ሲዳሞ አራት ክፍለ ሀገሮች በአንድ ደቡብ ክልል እንዲዋቀሩ የተደረገበትን ግፍ በግልጽ ታውቁታላችሁ፡፡ ሁሉም የተከናወነው በህወሃት ውሳኔ ነበር፡፡ አራትና አምስት የተለያዩ ቋንቋዎችን ቀይጦ ሌላ አዲስ ቋንቋ ለመፍጠር ቤተ ሙከራ የነበረውም የዚህ ሕዝብ ክልል ነበር፡፡ ይህ ድርጊት ትክክል አይደለም በሚል እንዲስተካከል በተለያየ ወቅት ጥያቄ ያነሱና ይህ እንዲስተካከል ጥረት ያደረጉ የክልሉ ምሁራን በሹመት ከተሰጣቸው ቦታ ብቻ ሳይሆን በሜሪታቸው ከሚሰሩት የሙያ ሥራቸው ተወግደዋል፡፡
የደቡብ ክልልን ህወሃት ያዋቀረው የክልሉን ጥሬ ሀብትና ማዕድናትን በመመዝበር የአገዛዝ ዘመኑን ለማርዘምና ለኢኮኖሚ ግብዓት እንዲያመቸው ነው፡፡ የክልሉ አወቃቀርና ያለው ነባራዊ ሁኔታ ለአስተዳደር ለልማትና ዕድገት በፍጹም እንደማይመች ግልጽ ነበር፡፡ ለምሳሌ አንድ አርሶ አደር ለአቤቱታ ከማሻ ተነስቶ እስከ አዋሳ ከ3-4 ቀን ፈጅቶበት ተጉዞ የትራንስፖርት ወጪውን ችሎ ፍትህ ሊያገኝ እንደማይችል እንዲሁም ለልማት አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን ከክልል ዋና ከተማ ወደ ተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች ማድረስ ከፍተኛ ወጪ የሚያስከትል መሆኑ ይፋ ነበር፡፡ አሁንም በተጨባጭ ሕዝቡን የልማት ተቋዳሽ ለማድረግ በፍጹም አልተቻለም፡፡ እጅግ ብዙ ማሳያዎች እንዳሉ ታውቃላችሁ፡፡
ሕዝቡ ልማትን ይሻል፡፡ ሌሎችንም ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎችን ያነሳል፡፡ የሚሰጠው ምላሽ ግን ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ እልዲሉ ነው፡፡ የፖሊሲ ችግር አይደለም የመልካም አስተዳደር ነው እንጂ የሚል ቅጥፈት፤ ማንኛውንም ጥያቄ ጠይቁ ነገር ግን ሕገመንግሥት ይከበር የሚል ማወናበጃ፤ አባይን እየገደብን ነው ህዳሴያችንን እናስቀጥላለን የሚል አሰልቺ ወሬ ወዘተ እየፈበረከ የሕዝቡን ሰላማዊ የፍትህና የልማት ጥያቄ አቅጣጫ በማሳትና በማቆልመም ህወሃት የራሱን የሥልጣን ጊዜ ለማራዘም የሚጠቀምበት እንክብል መሆኑን እያያችሁት ነው፡፡ አሁን ይባስ ብሎ ወደ ለየለት ጣሊያናዊ አገዛዝ ተሸጋግሯል፡፡ ወታደራዊ መንግሥት ሊገዛን ጀምሯል፡፡ ታዲያ ሊፈቀድለት ይገባል? ይኼ ማብቂያው መቼ ነው?
ገዢው ህወሃት ሀገሪቱን ለመቆጣጠርና ሕዝቧን ለመግዛት እየተጠቀመ ያለው ዘዴ ግልጽ ነው፡፡ ሕብረተሰቡን በዘር በቋንቋ በመንደር በማደራጀትና እርስ በርስ አንዱ ብሔር በሌላው ላይ ጥርጣሬ እንዲያድርበትና መግባባት እንዳይኖር አቅዶ በመሥራት ነው፡፡
ጠቅለል አድርገን ስናየው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄ አጭርና ግልጽ ነው፡፡ በሀገሬ የመጻፍ የመናገር የመደራጀት ነጻነት ይኑረኝ ነው፡፡ እኩልነት ፍትህና ዴሞክራሲ ይገባኛል ነው፡፡ ከአያት ቅድመ አያቶቼ በወረስኩት መሬት ላይ ልኑርበት አፈናቅላችሁ ሜዳ ላይ ለአውሬ አትስጡኝ ነው፡፡ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በሀገሩ ተዘዋውሮ ባሻው ቦታ የመኖር ንብረት የማፍራት መብቱ ይከበር ነው፡፡ ያለ አግባብ ሰውን የማሰር የማሰቃየት በሐሰት የመወንጀልና የመፍረድ እንዲሁም የመግደል ሂደት ይገታ ነው፡፡ ዘርን መንደርን ቤተሰብን መሠረት ያደረገ የመጥቀምና የመበደል አካሄድ አይመቸኝም ነው፡፡ ለጉልበተኛ የመገዛትና የባርነት ታሪክ የለኝምና ባሪያ ሆኜ ለማንም አልገዛም ነው፡፡ በሀገሪቱ ሥልጣን የሚያዘው በጉልበት ሳይሆን በሕዝብ ፈቃደኝነትና በእውነተኛ የሕዝብ ምርጫ ይሁን ነው፡፡ የጌታና የሎሌ ሥርዓት ይብቃ ነው፡፡ የሀብት ፍትሐዊ ሥርጭት ይኑረን ነው፡፡ በአጭሩ የጋራችን የሆነች ህዝቧ በእኩልነት የሚኖርባት ኢትዮጵያ የምትባል የጋራ ሀገር ትኑረን ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ሕዝቡ ሆ ብሎ ሥርዓቱን በቃኸን ብሎ በእንቢተኝነት ትግሉ ጠንክሮ እየታገለ እየታሰረ እየተደበደበ እየሞተ ይገኛል፡፡
በግፍ የታሰሩት የተደበደቡት የተገደሉት ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ናቸው፡፡ በደላቸው ሊሰማን ሊያመን ይገባል፡፡ የጉራጌ ዞን በደቡብ ክልል ከሚገኙት ዞኖች አንዱ ነው፡፡ በጉራጌ ዞን ዋና ከተማ በሆነችው ወልቂጤ በውጭ ድጋፍ የሚሰራ ሆስፒታል የመሰረት ድንጋዩ ተተክሎ ግንባታው ሲጠበቅ በጀቱን ወያኔ ውሃ አጠጣው፡፡ በዚህ የተነሳ ሕዝቡ ሆስፒታላችን ይሰራልን የሚል ጥያቄ አቅርበ፡፡ የተሰጠው ምላሽ ግን እጅግ አሳዛኝ ነው፡፡ ለምን ትጠይቀናለህ በሚል ድብደባ እስራትና ግድያ ሆነ፡፡
ወያኔ የአገዛዝ ሥርዓቴ ወደዳችሁም ጠላችሁ ይቀጥላል ብሏል፡፡ በተግባርም በእንቢተኝነት ለሰልፍ የወጣን ሕዝብ በመደብደብ በማሰር በመግደል ሕዝባዊውን እንቅስቃሴ ለማቆም እየሰራ ይገኛል፡፡ በቀጣይ ምንም ዓይነት ሕዝባዊ እንቅስቃሴ በመላው ሀገሪቱ እንዳይከናወን ለማድረግ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጓል፡፡ በዚህ አዋጅ አንድ ዜጋ እንዲጠቀም የተተወለት ነገር ቢኖር የምንተነፍሰው አየር ብቻ ነው፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዓላማ ሕዝቡን በማፈንና ሰቆቃውን በማብዛት ሀገሪቱን ለመዝረፍ እንዲሁም በሕዝብ እንቢተኝነትና አልገዛም ባይነት እየመጣ ያለን የለውጥ እንቅስቃሴ ለማቆም ያስችለው ዘንድ ነው፡፡ ይህ አዋጅ የሚጸድቀው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 2/3ኛ አባላት በድምጽ ስትደግፉት ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌ ከጥቂት ሳምንታት በፊት የአዲስ አበባን ልዩ ጥቅም ለማስከበር ይጠቅማል የሚል ሕግ ለማስጸደቅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረበውን አጀንዳ አስተውሉት፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ የኦሮሚያን ልዩ ጥቅም ማስከበሪያ አዋጅ በሚል ወያኔ ያቀረበውን አጀንዳ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የሆኑት የኦሮሚያ ክልል ጓደኞቻችሁ ወቅታዊ አይደለም የኦሮሞ ሕዝብ ያልመከረበት ነው ከአምስት መቶ ሺህ በላይ ቁጥር ያለው ኦሮሞ የሆነ ሕዝብ በዘሩ ምክንያት ብቻ ከሶማሌ ክልል ከቤትና ከንብረቱ ተፋናቅሎ በድንኳን ውስጥ የተጠለለበትና የእኛን ድጋፍ በሚሻበት ሁኔታ ላይ ነንና ይህን አጀንዳ ልንወያይበት ልናጸድቀውም አይገባም ብለው ውድቅ አድርገውታል፡፡
እነዚህ የኦሮሞ ህዝብን ወክለው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚገኙት አባላት ለሕዝባቸው ለክልላቸው ልማትና ጥቅም መቆማቸውን በተግባር አሳይተዋል፡፡ ወያኔ እንዳሻው ሕዝብን ከሕዝብ ብሄርን ከብሄር ለማጋጨት የሳበውን ጥቁር ካርድ አስጥለውታል፡፡ በዚህ ተግባራቸው ታሪክ ሰርተዋልና ሲዘከሩ ይኖራሉ፡፡
አሁን ተራው የፌዴራል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሙሉ ሆኗል፡፡ እናንተን የሚመለከት ነገር በግልጽ መጥቶባችኋል፡፡ ልትሸሹት አትችሉም፡፡ ነገ አልሰማሁም የምትሉት አይደለም፡፡ ከሌሎች የኦሮሞና የአማራ እንዲሁም የጉራጌ ወንድሞቻችሁ ጎን በመሰለፍ ሕዝብንና ሀገርን የምትታደጉበት ከባድ ኢትዮጵያዊና ሕሊናዊ ውሳኔ እንድታስተላልፉ የሚሻ ጥያቄ ከፊታችሁ ይጠብቃችኋል፡፡
ይኸውም ወያኔን ወግኖ ሕዝብንና ሀገርን አደጋ ውስጥ የመጣል የክህደት ውሳኔ ማስተላለፍ ወይም ሕዝብንና ሀገርን በመታደግ ታሪክ ሰርቶ ኢትዮጵያችን ይህን የተጋረጠባትን የመፈረካከስና ልጆችዋ እርስ በርስ እንዲተላለቁ የተወጠነን ጸያፍ የሆነን የወያኔን እኩይ መንገድ ዘግቶ ወደ ዴሞክራሲ ፍትህና እኩልነት ማሻገር መቻል፡፡ የሚጠብቃችሁ ምርጫ ይህ ነው ፡፡ አንዱን መንገድ መምረጥ የግድ ነው፡፡
አሁን ሀገራችን ያለችበትን ተጨባጭ እውነታ አስሉ፡፡ የወያኔ ግዢዎች የጥፋት ተልዕኮአቸውን ጊዜ ለማርዘም የቻሉትን ከመጣር ባሻገር ሀገርን መቦጥቦጥና መዝረፍ ሕዝብን በአፈሙዝ ረግጦና አፍኖ መግዛት ከማይችሉበት ደረጃ መድረሳቸውን አውቀውታል፡፡ ድጋፍ የሚያደርጉለት ምዕራባውያን ሀገሮች ጀርባ እንደሰጡት ሰሞኑን በአገዛዙ ላይ የሚያሰሙትን ግልጽ ተቃውሞ እያየን ነው፡፡
የፖለቲካ ተቃዋሚም ሆነ ጋዜጠኛ ማንም ግለሰብ በፖለቲካ አመለካከቱ የተነሳ የታሰረ የለም ወንጀለኛና አሸባሪ እንጂ እያለ የሚያላግጠው ቡድን ሳይወድ በግድ በግፍ ያሰራቸውን እንዲፈታ የሚያስገድድ ሀገር አቀፍ የእንቢተኝነት ተቃውሞ ሀሪቱን እየናጣት ይገኛል፡፡ በተግባርም ይማላገጡ ሂደት በቅቶ እስረኞችን መፍታት ጀምረዋል፡፡
በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች በሀገሪቱ የለውጥ መምጣት የግድ አስፈላጊና ወሳኝ እንደሆነ እያስገነዘቡ ያለበት ጊዜ ነው፡፡ የነጻነት ታጋች ከሕዝቡ ጎን በመሰለፍ ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውንና ይህንንም እየተገበሩ እንዳለ እያየን ነው፡፡ የሽግግር መንግሥት በመመስረት ሀገሪቱን ወደ ተሻለ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማምጣት ከፍተኛ ጥረትና ትግል እየተካሄደ ነው፡፡
ከላይ እንዳልኳችሁ ወክለነዋል ብላችሁ ለምታስቡት ሕዝብ የነጻነት የዴምክራሲና የእኩልነት ባለቤትነን የሚያጎናጽፈውን ታላቅ ወሳኝና ታሪካዊ ውሳኔ የምታስተላልፉበት ጊዜ ላይ ደርሳችኋል፡፡ እውነቱን እውነት ነው ብላችሁ ልትወስኑ አሊያም ፈርታችሁ ወይም ሆዳችሁ በልጦባችሁ እድሜ ልካችሁን የምትጸጸቱበት ከለይ ከፈጣሪም የሚያስጠይቃችሁ እንዳይሆን እንድታስተውሉ አሳስባችኋለሁ፡፡ በምድር ወክለነዋል መርጦናል ከምትሉትም ሕዝብ ፊት ቀርባችሁ በሥራችሁ በፀረ ሕዝብ ውሳኔያችሁ ወደ ፍትህ የምትቀርቡበት ቀን ይኖራልና ለውሳኔ ድምጽ እጅ ስታወጡ አስተውሉ፡፡
በታሪክም ፊት የምታፍሩበትን ሁኔታ የሚፈጥር ታላቅና ወሳኝ መድረክ ነውና እውቁ፡፡ ስም ከመቃብር በላይ ይኖራልና ከሕዝባችሁ ጎን በመቆም የትክክለኛ ሕዝባዊ ውሳኔ አካል እንድትሆኑ አሳስባችኋለሁ፡፡ ይህ አጋጣሚ ቀደም ሲል በሰራችሁት የበደል ሥራ ወይም በውሳኔያችሁ ቅር የተሰኘን ዜጋን ክሳችሁ ይቅርታ የምትቀዳጁበት ዳግም ላታገኙት የምትችሉት ትልቅ አጋጣሚም ይሆናል ብዬ አምናለሁ፡፡
ለማጠቃለል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዳያልፍ በማድረግ እንዲሁም ለሀገራዊ መግባባት ሁሉን አቀፍ የሆነ የሽግግር ሂደት እንዲፈጠር የድርሻችሁን ተወጡ፡፡ ” ጮሻይ ዪን አቻይ አሼና ” ከውስጥ ገፍቶ የመጣን ትውኪያ ጥርስ አያቆመውም እንዲሉ የዳውሮ አባቶች የህዝቡ የእንቢተኝነት ትግል ከግቡ ሳይደርስ አይቆምምና ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን ቁሙ፡፡ አበቃሁ፡፡