እንደዚያም ሆኖ አባላቶቹ፣ አመራሮቹ እየታሰሩበትም አንድነት በመላው አገሪቷ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ሲያዸርግ ነበር። የሚሊዮኖች ድምጽ እንቅስቃሴን ፣ ሁሉ ነገር በተዘጋበት ወቅት ሕዝብን ሲያነቃንቅ እንደነበረ የሚታወስ ነው።

አንድነት ፍኖተ ነጻነት የተሰኘውን ጋዜጣው እንዳይታተም ወያኔ ከለከለከ። ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት አላትምም አለ። የግል ማተሚያ ቤቶችም ከደህንነት መስሪያ ቤት ማጠንቀቂያ ደርሷቸው አናትምም አሉ። ሆኖም አንድነቶች ተስፋ አልቆረጡም። በር ሲዘጋ ሌላ ማስከፈት ግድ ስለሆነ ከአባላትና ከደጋፊዎች ገንዘብ አሰባስበው የራሳቸው ማተሚያ ገዙ። ወያኔዎች መብራት ሃይልን ተጠቅመው ኤሌትሪክ ማስቆረጥ ጀመሩ። አንድነቶች አሁን የራሳቸው ጀነሬተር ገዙ። የበፊቱ ፍኖተ ነጻነት ብቻ ሳይሆን ሌላ ሁለተኛ የሚሊዮኖች ድምጽ ጋዜጣ በማተም ሕዝቡን መቀስቀስ ጀመሩ።

ከአዲስ አበባ ውጭ ወደ ሰላሳ አራት ጽ/ቤቶችን ከፍተው ለ 2007 ምርጫ መዘጋጀት ጀመረ። ከ 547 የፓርላማ መቀመጫ ወደ 508 መቀመጫዎች ተወዳዳሪ ለማሰለፍ ተዘጋጁ። አማራጭ ሐሳቦችን በማቅረብ ዳንዲ የሚባል መጽሔት ለማሳተም፣ አማራጮቹን በስብሰባዎች ለሕዝብ ለማቅረብ በዝግጅት ላይ እያሉ፣ ከፍተኛ የሕዝብ ድጋፍ እንዳለው ስላወቁ፣ ህወሃቶች አንድነት እንዲዘጋ ወሰኑ። በወቅቱ አንድነት ሲዘጋ ፣ የአምስት ደርጅቶች ስብስብ የሆነው መድረክ 270 መቀመጫ ብቻ ነበር ያሰለፈው። ሰማያዊ 139 መኢአድ 120 አካባቢ መቀመጫዎች።

አንድነቶች ፓርቲያቸው በጉልበት ቢዘጋም ትግሉን አላቆሙም። የተወሰኑቱ ወደ ኤርትራ ሄዱ፣ የተወሰኑት ሰማያዊ ፓርቲ ገቡ። ጥቂቶች ወደ ኦሮሞና አማራ ድርጅቶች ሄዱ። የተወሰኑትም በግላቸው መጻፍና መጦመር ጀመሩ።

አንድነት ትልቅ ፓርቲ ነበር። አባላቶቹና ደጋፊዎቹ ብዙ ዋጋ ከፍለዋል። የአንድነት ፓርቲ ሲያደረገው የነበረ የሰላማዊ ትግል አሸነንፎ ፣ የትጥቅ ትግል የሚሉትም በቦሌ እየገቢ ነው በሰላም ለመታጋል።

ትልቁና አስደሳቹ ነገር ደግሞ ሲታገሉ፣ ሲደክሙ፣ ሲሰሩ የነበሩ ፣ የወያኔ ዱላ አርፎባቸው ተበታትነው የነበሩ እየተሰባሰቡ ነው። አዳዲስ፣ ብቃት ያላቸውን ኩሩ ኢትዮጵያዉያንን እያሰባሰቡ ነው። በትግል የተፈተኑ፣ ኢንቴግሪቲ ያላቸው እንደ አንዱውዋለም አራጌ ያሉ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ፣ አገራችንን በፍቅር፣ በአንድነት፣ በመቻቻል ላይ ያተኮረ የሰለጠነ አማራጭ ይዘው በቅርብ ይመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።