• ቅዱስነታቸው፣ ከአሜሪካ የመልስ ጉዞ ወቅት፥“ትጠይቀኛለኽ ወይ? ሥራ ይበዛብሃል፤ ማን ይጠይቀኛል አኹን? እንዴት ትጠይቀኛለህ?” ሲሉ ጠ/ሚኒስትሩን ጠይቀዋቸው ነበር፤
  • ቅዱስነታቸው፥ ከመናገር አብዝተው ሲታቀቡ ቢስተዋልም ይነጋገራሉ፤ ከቅርብ ልዩ አገልጋይ(ረዳት) ጀምሮ በግል ሐኪምና ነርስ ክትትል ይደረግላቸዋል፤
  • እንደሚጠይቋቸው ቃል የገቡላቸው ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ዛሬ ከቀትር በኋላ በመንበረ ፓትርያርኩ ማረፊያቸው ተገኝተው አይተዋቸዋል
  • ቤተ ክርስቲያን፥ ለአገር የመጸለይና የማስታረቅ ሓላፊነቷን እንድትወጣ፤ በሰላም፣ በልማትና በማኅበራዊ ጉዳይ መንግሥትንና ሕዝብን እንድታግዝ አደራ አሉ፤

†††

  • ዶ/ር ዐቢይ፥ የኢትዮ ሶማሌ ክልልን ጸጥታ ጉዳይ ሲከታተሉ መሰንበታቸውን ጠቅሰው፣ በመግደል ጸጸት እንጅ ማሸነፍ እንደሌለ ተናግረዋል፤
  • የተገንጣዮችን ሐሳብና አሠቃቂ ድርጊት ሲቃወሙም፣ “ኢትዮጵያ በዋዛ ፈዛዛ አትበተንም፤ ሰው ኾኖ የማይሞት የለም፤ ባልተገባ ጊዜ መግደል ደግሞ ውድቀት ነው፤” ብለዋል፤
  • አብረዋቸው ቅዱስነታቸውን የጠየቁት የክልል ትግራይ ም/ል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል፣ ሲኖዶሳዊ ዕርቀ ሰላሙ፣ለኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነትና መተባበር አብነታዊ እንደኾነ ገልጸዋል፤
  • በጥየቃቸው ደስታቸውን የገለጹት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ትኩረቱ፥ ለቤተ ክርስቲያን ታሪካዊነት፣ ሥራና ዕድገት ቀጣይነት ጥሩ ዕድል እንደኾነ ጠቅሰው አመስግነዋል፤

†††

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ፣ ስለ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ መርቆሬዎስ ጥየቃቸው፤

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን ጎበኙ

ለውይይት አልመጣኹም፤ አለባበሴን እንደምታዩት ቤተሰብ ጥየቃ ነው የመጣኹት፤ ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን ከአሜሪካ ስንመጣ መልሼ እንድጠይቃቸው ቃል አስገብተውኝ ነበር፡፡ ቃል ብርቱ ነው፤ መጠበቅም አለበት፤ እኔ ባለፈው ሳምንት ከመጣን ጊዜ ጀምሮ በምሥራቁ የኢትዮጵያ ክፍል በነበረን ኹኔታ ያን ለማረጋጋት፣ የሰው ሕይወት ከጠፋው በላይ እንዳይጠፋ፣ አሁን በችግር ላይ ያሉ ሰዎች መታገዝ እንዲችሉ፣ አካባቢው እንዲረጋጋ፣ ብዙ ጊዜዬን እዚያ ላይ ስላጠፋሁና ላገኛቸው ስላልቻልኹ፣ ዛሬ ፋታ ሳገኝ እርሳቸውን ለማየት፣ ለአገር እንዲጸልዩ ለመጠየቅ፤ ሌሎችም ጳጳሳት በቀደም የተጀመረው የዕርቀ ሰላም ማብሠሪያ ጉባኤ በአዲስ አበባ እንዳይታጠር፤ በየክልሉ፣ በየከተማው መሰል ፕሮግራም ተደርጎ ሕዝብንና ሕዝብን ማስታረቅ፣ ለአገር መጸለይ፣ ቤተ ክርስቲያኗ በአላት አቅም፥ በሰላም፣ በልማትና በማኅበራዊ ጉዳይም መንግሥትንና ሕዝብን እንድታግዝ አደራ ለማለት ነው፡፡

38904827_10214678062197625_4565368936488501248_n

ቡና ጋብዘውኝ ተቀባብለን እንደ ቤተሰብ ተጨዋውተናል፡፡ በጣም በጥሩ ጤንነት ላይ ይገኛሉ፡፡ እርሱን ለማረጋገጥ ነው የመጣኹት፤ ቃል ስለገባኹ ቃሌን ለመጠበቅ ማለት ነው፡፡

የኢትዮ ሶማሌ ክልልን የወቅቱ የጸጥታ ኹኔታን በሚመለከት፤

በጣም ጥሩ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ለጠብ፣ ለግጭት፣ ለመለያየት፣ ለማጥፋት ብዙ ምክንያት አያስፈልግም፡፡ በትንሽ ምክንያት ወደ ችግር እንገባለን፡፡ ብዙ ሰው፣ ጠይቆ፣ አውቆ፣ ተረድቶ፣ አመዛዝኖ አይደለም የሚወስነው፡፡ ሲሰማ ይወስናል፡፡ ይኼ የኢትዮጵያውያን ባህል ነው እስንቀየር ድረስ፡፡ በዚህም ምክንያት እዚያ አካባቢ አንዳንድ ችግሮች ገጥመው ነበር፡፡ ችግሩ እንዳይስፋፋ፣ አገርን ወደ ቀውስ እንዳያስገባ ሰፊ የምክክር ጊዜ ነበረን፡፡ በጣም አድካሚ ጊዜ ነው የነበረው፤ አኹን መሥመር እየያዘ ነው፤ ክልሉን ከሚመራው ድርጅት ጋራ ሰፊ ውይይት እያደረግን ነው፡፡ መሥመር ይይዛል፡፡

ከዚህ ጋራ ተያይዞ፣ በርካታ ሰዎች የመገንጠል ጉዳይ ያነሣሉ፡፡ ለኢትዮጵያውያን ማረጋገጥ የምፈልገው፣ የኢትዮጵያ አንድ አካል የአንድ ዛፍ አንድ ቅጠል አይደለም፡፡ እንደው ዝም ብሎ የሚረግፍ አገር አይደለም፡፡ እኛ ስለፈለግን የምንጠብቀው፣ ስላልፈለግን የሚፈርስ አገር አይደለም፡፡ ሕዝቡ፣ አንዱ በአንዱ ውስጥ ያለ፣ ማኅበራዊ ትስስር ያለው፣ በዋዛ ፈዛዛ የሚበተን አገር አድርጎ ማሰብ ስሕተት ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን፣ ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ፤ እንዳልነው፣ ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያ ሳይኾኑ እንዲሁ በዋዛ እንበተናለን ብሎ መጠበቅ ከንቱ ሕልም ነው የሚኾነው፡፡

አገራችንን መጠበቅ፣ ማስፋት ማሳደግ የኹሉም ዜጋ ሓላፊነት ነው፡፡ ይህ እንዲኾን ደግሞ፣ ጥላቻንና ክፉ ነገርን ከሚዘሩ ሰዎች መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ ብዙ ጊዜ ሰዎች ክፉ ሐሳብ ያሠራጫሉ፡፡ ያን ካልገዛነው እዚያው ይቀራል፡፡ ያን ሐሳብ ተሸክመን ካስፋፋነው ደግሞ በርካቶች ይጎዱበታል፡፡ በመግደል ማሸነፍ እንደሌለ የሱማሌው ጉዳይ ያመለክታል፡፡ ዐሥር ሰው፣ ኻያ ሰው ብትገድልና ብትቀጥል፣ ጸጸት ይዘህ ትቀጥላለህ እንጅ አታሸነፍም፡፡ ሰው ኾኖ የማይሞት የለም፡፡ ባልተገባ ጊዜ መግደል ደግሞ ውድቀት ነው፡፡ ያ እንዳይኾን ኢትዮጵያውያን በረጋ መንፈስ፣ አንዳንድ መረጃ ሲመጣም ጊዜ ወስዶ ማሰላሰል፣ ማሰብ፣ ከየት መጣ ብሎ ማጣራት ያስፈልጋል፡፡ ወደ ግጭት አለመፍጠን፤ ወደ ዕርቅ፣ ወደ ሰላም፣ ወደ ልማት ሲኾን ደግሞ ብዙ አለማሰብ፣ መግባት፤ ከልማት ውጭ የኾነ ሐሳብ ሲመጣ ደግሞ ቆም ብሎ ማየት ያስፈልጋልና ይኼን በዚሁ አጋጣሚ አደራ ለማለት እፈልጋለሁ፡፡ አመሰግናለሁ፡፡


‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፤

FB_IMG_1533058052690

በጣም ደስተኛ ነኝ፤ ቤተ ክርስቲያንም ተደስታለች፤ ተለያይታ የነበረች፣ ለኹለት ተከፍላ የነበረች ቤተ ክርስቲያን ወደ አንድነት በመመለሷ፤ ቅዱስ ፓትርያርኩ ወንድማችንም፣ ወደ ሀገራቸው በመመለሳቸው፣ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩም፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ ጉዳይ የሀገር ጉዳይ መኾኑን አስበውበት አንድ እንድትኾን በማድረጋቸው በጣም ደስ ብሎናል፡፡ ዛሬም ደግሞ፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን ለመጠየቅ እዚህ ድረስ መጥተው ብዙ ቆይታ አድርገናል፡፡ ይኼ ኹሉ በጣም ደስ የሚያሰኝ ነው፡፡

መቸም፣ ኹሉ እንደሚያውቀው ቤተ ክርስቲያናችን፣ ታሪካዊት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ይህ ኹሉ ታሪካዊነቷ፣ ሥራዋና ዕድገቷ እንዲቀጥል ግድ ስለሚለን ነው፡፡ ለቤተ ክርስቲያናችንም ኾነ ለአገራችን ጥሩ ዕድል እያየን ነው ያለነው፡፡ ቅዱስ ፓትርያርኩ ተመልሰው በመምጣታቸው ኹሉም ደስ ብሎታል፤ ሀገሩ ኹሉ ተደስቷል፡፡ አኹን ደግሞ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይኸው ሊጠይቋቸው መጥተው እዚህ ይገኛሉ፡፡ ይህ ኹሉ ትልቅ ደስታ ነው፤ እናመሰግናለን፡፡


‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡

የክልል ትግራይ ምክትል ርእሰ መስተዳድር ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል፤

 

ዶክተር ደብረ ጽዮን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን ጎበኙ

በአቡኑ መመለስ ኹላችንም ደስተኞች ነን፡፡ በአሜሪካ ሌላ ፓትርያርከ፣ በአገራችንም ሌላ ፓትርያርክ እየተባለ ለረጅም ጊዜ እንደቆየ ኹላችንም የምናውቀው ነው፡፡ ይኼ የነበረው መራራቅ፣ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን አሜሪካ ሔደው፣ ቤተ ክርስቲያናችንም በራሷ ጥረት ስታደርግ እንደነበር እናውቃለን፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ አሜሪካ ከሔዱ በኋላ መቋጫ ያገኘበት ነው፡፡ ቅዱስ ፓትርያርኩን አብረው ይዘው በመምጣታቸው በጣም ትልቅ ደስታ ነው የተሰማን፡፡ እኔ በአጋጣሚ መንገድ ላይ አልተሳተፍኩም፡፡ ነገር ግን ዛሬ እጎበኛቸዋለኹ ሲሉ በሌላ ሥራ አብረን ነበርንና፣ እኔም ስላልጠየቅኋቸው ከእርስዎ ጋራ መሔዱ በጣም ጠቃሚ ነው በሚል ነው የመጣኹትና በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ ቅዱስነታቸውንም አግኝቻቸዋለኹ፡፡

ኹለቱንም ፓትርያርኮች በጋራ ስላገኘናቸው፣ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ብቻ ሳይኾን ለአገራችን ሕዝቦችም ትልቅ አብነት ነው የሚያሳየን፡፡ ይኼ መራራቁ በጣም ጎጅ እንደነበረ፣ ከቤተ ክርስቲያንም አልፎ ሕዝቡ ላይ የነበረው ስሜት እንዲራራቅ አድርጎ ስለነበረ፣ አኹን አማኙ ብቻ ሳይኾን የኢትዮጵያ ሕዝብም አንድ እንዲኾን፣ ተባብሮ አገሩን ለማልማት፣ ተባብሮ የአገሩን ሰላም ለማስጠበቅ የራሳቸውን ሚና እንደሚጫወቱ ስለምናምን በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ በጥሩ ኹኔታም ነው ያገኘናቸው፤ በዚህ ዕድልም ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋራ ተያይዘን ስለመጣን በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ አመሰግናለኹ፡፡


ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ሰላም አስተማማኝ እየሆነ ነው ሲሉ ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ሰላም አስተማማኝ እየሆነ ነው ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ

 

የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ሰላምን አስተማማኝ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለፁ፡፡

ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል አመራሮችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሰላሙን ዘላቂና አስተማማኝ ለማድረግ ሰፊ ምክክር ማድረጋቸውንና ከመግባባት ላይ መደረሱንም ተናግረዋል፡፡

እስካሁንም የክልሉ ሰላም ወደ ቀድሞው ይዞታ መመለሱን ተናግረዋል፡፡

የሰው ህይወትና ንብረት መጥፋቱ አሳዛኝ ድርጊት መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

የሶማሌ ክልል የመገንጠል ጥያቄ አንስቷል ተብለው ለቀረበላው ጥያቄ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ዝም ብሎ እንደ ዛፍ ፍሬ የሚገነጠል አይደለም፣ ግለሰቦች የፈጠሩትን ችግር መስመር ለማስያዝ እየተሰራ መሆኑን ለመገናኛ ብዙኃን ዛሬ ተናግረዋል፡፡

ebc