August 9, 2018
(ቀሲስ ኤፍሬም እሸቴ)
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከአገራችን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ግማሹን በተከታይነት የያዘች ቤተ ክርስቲያን ናት። በኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ምሥረታ ላይ የአንበሳውን ድርሻ የያዘች እንደመሆኗ ኢትዮጵያ ብሎ የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ጠቅሶ አገሪቱን መዘንጋት አይቻልም። ቤተ ክርስቲያኒቱ በአገሪቱ ውስጥ ያላት ይህንን ያህል የዘለቀና ዕድሜ የጠገበ ታሪካዊ አሻራ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ያላት ሁሉን አቀፍ ድርሻ ግን ለዕድሜዋና ለታሪኳ የሚመጥን አይደለም። እንደ አናሣ የእምነት ዘርፍ እና አናሳ የማኅበራዊ ተቋም ከምትታይበት ደረጃ ላይ የደረሰች ይመስላል። በርግጥ ይህንን የማይቀበሉ ብዙ አማኞች እና መሪዎች ስላሉዋት ሐሳቡን በልዩነት ማለፉ የሚጠበቅ ነው።
ቤተ ክርስቲያኒቱ በአገሪቱ ላይ ያላት ሁሉን አቀፍ ተጽዕኖ ዕለት ተዕለት መቀነሱ እንደተጠበቀ ሆኖ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ እየገጠሟት ያሉት ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች የሚታይና የሚዳሰስ ንብረቷንና ሀብቷን በማጥፋት ሰፊ ሚና እየተጫወቱ ነው። የተፈጥሮ ደኖቿና አፀዶቿ በእሳት ይጋያሉ። ቅርሶቿና አብያተ ክርስቲያኗም በእሳት፣ በስርቆት እና በተፈጥሮ የአየር ለውጥ ምክንያት ይበላሻሉ። ምእመናኖቿ በተለያዩ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ተጽዕኖዎች ምክንያት ሕይወታቸውን ያጣሉ፣ ከሚኖሩበት ይፈናቀላሉ፣ ይህንን መቋቋም ሲሳናቸው እምነታቸውን ይለውጣሉ። ለጋ ወጣቶቿ ገና ከልጅነት በሚሰሙት አሉታዊ ፖለቲካዊ እና እምነት ነክ ትንኮሳዎች ምክንያት በሃይማኖታቸው ተሸማቀው እንዲያድጉ ይገደዳሉ። በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች ክልሎችን የሚመሩ መንግሥታዊ ፓርቲዎች ኦርቶዶክስ መሆንን ለክልላቸው የጠላት እምነት እንደመከተል ስለሚቆጥሩ በመንግሥታዊ ቢሮክራሲ ውስጥ ያሉ ኦርቶዶክሶች ወይ እምነታቸውን በማመቻመች ወይም በመቀየር ይኖራሉ አልያም ሥራውን በመተው ወደሌላ ኑሮ ይገባሉ።
ይህ ሁሉ ሁኔታ ባለበት ሁኔታ ችግሮች ከዕለት ወደ ዕለት እየጠነከሩ መምጣታቸውን የሚመለከተው የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር እና ሌላው አማኝ ለችግሮቹ ተመጣጣኝ የሆነ መፍትሔ ለመፈለግ ያለው ዝግጅት እጅግ በጣም አነሥተኛ ብቻ ሳይሆን የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም። ሌላውን ሁሉ ችግር ብንተወው እንኳን ባለፉት ስድስት እና ሰባት ዓመታት ብቻ በመላው አገሪቱ በተከሰቱ የተለያዩ የእሳት አደጋዎች ብዙ የቤተ ክርስቲያኒቱ ደኖች ሲወድሙ በባዶ እጁ እሳት ለማጥፋት የሚታገለው ምዕመን አሁንም ከስድሰት እና ከሰባት ዓመታት በኋላም እሳት ሲመጣ ሊቋቋምበት የሚችልበት ምንም ዓይነት ዝግጅት የለውም። በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በአጽራረ ቤተ ክርስቲያን የሚፈናቀሉና የሚገደሉ ምዕመናን ቁጥር እየጨመረ መሆኑ እየታየ ለዕለት ርዳታ እንኳን የሚሆን ድጋፍ ሊያደርግ የሚችል ምንም ዓይነት ድርጅት ሳይቋቋም ቆይቷል። ከጅማ በሻሻ አቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስ የ1999 ዓ.ም ጭፍጨፋ ጀምሮ ሰሞኑን በሶማሌ ክልል እስከደረሰው ግድያና የአብያተ ክርስቲያናት ውድመት ድረስ ኦርቶዶክሱ ሕዝብ ለሚደርስበት በደል ፈጥኖ የሚደርስ ምንም ዓይነት ተቋም አልገነባንም። ችግር በተፈጠረ ቁጥር እንደ አዲስ ጉድ ጉድ ስንል፣ እንባችንን ስናፈስስ፣ የሳንቲም ድቃቂ ስንለምን፣ የሰበሰብነውን ገንዘብና ጨርቅ እንኳን በአግባቡ ሊያደርስልን የሚችል ድርጅት ስለሌለን ለተቸገረው ወገናችን መድረስ እየተሣነን ድኩማን ሆነን ቀርተናል።
በዚህ በኩል ሌላውን ሁሉ የቤተ ክርስቲያኒቱን አቅም እንተወውና በየከተማውና ገጠሩ እንዲሁም በውጪው ዓለም ያሉትን የወጣት ማኅበራት እና የሰንበት ት/ቤቶች ብቻ ለማሳያነት እንጥቀስ። እነዚህ የወጣት ማኅበራትና ሰ/ት/ቤቶች ወጣቶችን በየዕድሜያቸው ይዘው ነገረ ሃይማኖትን፣ መዝሙርና ሌሎች ትምህርቶችን የሚያስጨበጡ ናቸው። በአዲስ አበባ በሁሉም አጥቢያዎች ሰንበት ት/ቤቶች አሉ። በውጪውም ዓለምም እንዲሁ። በቁጥር ደረጃ ብንመለከታቸው ከማንኛውም ዓለማዊ ግብረ ሰናይ ድርጅት ያልተናነሰ የሰው ኃይል ያላቸው ተቋማት ናቸው። በነጻ ፈቃድና በመንፈሳዊ ተነሳሽነት ብዙ ማኅበራዊ አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉ ተቋማት ናቸው። እንደ ጅግጅጋው አደጋ ያሉ ሰብዓዊ ቀውሶች ሲፈጠሩ በቶሎ ሊደርሱ የሚችሉ ትኩስ ኃይል ያላቸው ናቸው። ነገር ግን ከጥቂት መንፈሳዊ ዕውቀት እና መዝሙራት ውጪ በሌላ አገራዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶች ላይ እንዲሳተፉ የሚያደርግ ዝግጅትና ዕውቀት ስላልገበዩ የሚወዷት ቤተ ክርስቲያናቸው ላይ አደጋ ሲመጣ የመዝሙር ልብሳቸውን እንደለበሱ ከማልቀስ ውጪ ምንም አቅም የሌላቸው እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። ከዛ ገፋ ሲልም ዝቋላ ደን ላይ እሳት አደጋ ሲከሰት እንዳደረጉት በባዶ እጃቸው እሳት ለማጥፋት እንዲሄዱ ሆነዋል።
ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችላት ሙሉ አቅምና ኃይል እያላት ይህንን ማድረግ አለመቻሏ ያደረሰባትን አደጋ በመመልከት፡-
1ኛ. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አደጋ መከላከል እና ፈጥኖ ደራሽን ሥራ የሚሠራ ትልቅ ተቋም በአገር አቀፍ ደረጃ እና በአህጉረ ስብከት ደረጃ ቢመሠረት፣
2ኛ. የቤተ ክርስቲያኒቱ ወጣቶች ለጥምቀትና ለደመራ በጋራ በዓል ማክበራቸው እንዳለ ሆኖ ለዚህ ዓይነቱ የአደጋ ጊዜ ለሌላው ወገናቸው ፈጥኖ መድረስ የሚያስችላቸውን ዝግጅት የሚያደርጉበት ሁነኛ አካል ቢያዋቅሩና ቢመሠርቱ፤
3ኛ. ሌላው ሕዝበ ክርስቲያን የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተዳደር ይሁንታ እና ቢሮክራሲያዊ ፈቃድ ሳይጠብቅ በክርስቲያንነቱ ከራሱና ከበጎ ፈቃድ በሚያገኘው ገንዘብ ሊያንቀሳቅሰው የሚችለው የአደጋ መከላከልና መቋቋም ድርጅት ቢመሠርት፤ (ምሳሌ፡- ቀይ መስቀልን እና ቀይ ጨረቃን የመሰለ ድርጅት)
4ኛ. በተለያዩ ቦታዎች አብያተ ክርስቲያናት ሲፈርሱና ሲቃጠሉ አዲስ ለመገንባት እጅግ ብዙ የሰው ኃይልና ገንዘብ ይጠይቃል። ነገር ግን ሙያውና ዕውቀቱ ያላቸው ክርስቲያኖች በአንድ ሳምንት ሥራ ለአገልግሎት ሊበቃ የሚችል የቤተ ክርስቲያን አሠራር ለመንደፍ ይከብዳቸዋልን? በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሊይዙ የሚችሉ ድንኳኖች መዘርጋት በሚቻልበት በዚህ ዘመን ቶሎ-ቶሎ የሚደርስ ቤተ ክርስቲያን የሚሠራበትን ጥበብ እንዴት ያጡታል? አሁንም መፍትሔው ከእነርሱም ይፈለጋል። ጅግጅጋና መላው የሶማሌ ክልል ለእነርሱ የቀረበ የቤት ሥራ ነው።
ማጠቃለያ፡-
አገራችን ብዙ ሺህ ዜጎች በተለያዩ ምክንያቶች የተፈናቀሉባት አገር ናት። ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ ኦሮሞዎች፣ ከኦሮሞ ክልል የተፈናቀሉ ሶማሌዎች፣ ከኦሮሞና ሌሎች ክልሎች የተፈናቀሉ አማራዎች፣ ከኦሮሞ ክልል የተፈናቀሉ ጌዴዖዎች ወዘተ ሥፍር ቁጥር የሌለው ሕዝብ የተፈናቀለባት አገር ናት። ለዚህ ሁሉ ሕዝብ በፍጥነት መድረስ ያለባት ቤተ ክርስቲያናችን ግን «ቄሱም ዝም መጽሐፉም ዝም» ሆናለች። የዚህ ሁሉ ዕዳ በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ላይ ብቻ ሳይሆን «ተርቤ አብልታችሁኛል? ተጠምቼ አጠጥታቸረሁኛል? ታርዤ አልብሳችሁኛል? ታስሬ ተይቃችሁኛል? …..» የሚለውን አምላካዊ ጥያቄ በምናውቅ ክርስቲያኖችም ላይ የወደቀ ዕዳ ነው። በያዕቆብ መልእክት 4፥17 ላይ «እንግዲህ በጎ ለማድረግ አውቆ ለማይሠራው ኃጢአት ነው።» የተባለውን ቃል እናውቀዋለን። ስለዚህ ለጅግጅጋ ማልቀስ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ጅግጅጋዎች ሲመጡ እንዴት እንደምንቋቋም ጭምር ነው ማሰብና መዘጋጀት ያለብን።