በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)

የአቶ አጥናፉ ጥገት ላሜ ቦራና አሞሌ ጨው፤ የአማራ ሆደ ባሻና የኢትዮጵያ አንድነት ተመሳሳይ እየሆኑ መጡ፡፡ የአቶ አጥናፉ ላሜ ቦራ ጨው ካላላሷት እንኳን ለመታለብ እግሯን ልትከፍት እንደ አመጠኛ በቅሎ እረግጣቸው ትሄድ ነበር፡፡ አቶ አጥናፉም ይኸንን ቅብጥብጥ አመሏን ስለሚያውቁ ከአባ ሙዴሲር ሱቅ በደረቴ ባለዝናሩን አሞሌ ጨው ይገዙና እንደ ሸንኮራ ላራት ከፍለው አንዱን አንኳር ሲያልቡ ጥጃውን ለሚይይዝላቸው ልጃቸው “አልሳት!” ይሉና ይሰጣሉ፡፡ ልጃቸውም በአንድ እጁ ጥጃውን በሌላው እጁ አንኳሩን ይዞ ሲያልሳት ኬክ ሲያቀርቡለት ፍንድቅድቅ እንደሚለው ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ላሜ ቦራም በምትልሰው ጨው ፍንድቅድቅ ትልና እግሮቿን አንፈራጣ አራቱንም ጡቶቿን የተነፋ ጓንት አስመስላ ለአቶ አጥናፉ ጣቶች ታስረክባለች፡፡ አቶ አጥናፉም ለጥጃዋ ጠብታ ሳያስቀሩ ላሜ ቦራን እንደ እንሰት ልገው ያልቡና ወተቱንም ጨውንም መንጪቀው እቤታቸው ይገባሉ፡፡

ሆደ ባሻ አማራም የአቶ አጥናፉን ላሜ ቦራ እየመሰለ ነው፡፡ አማራ ከሩብ ክፍለ-ዘመን በላይ በተናጥል የታለበው ጨጓራውን ስለላጠው  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደ አያቶቹ አጉረምርሞና እንደ ከንች ከትሞ ወግድ ማለት ጀምሯል፡፡ በዚህ የአማራ ማጉረምረምና መከተም የተቅበዘበዙ አላቢዎችም እንደ አቶ አጥናፉ ከኢትዮጵያ የተሰራ ጨው መጠቀም ጀምረዋል፡፡ ከአቶ ሙዴስር ሱቅ እንደ ተገዛው ጨው ኢትዮጵያን አንገቷን ሰብረው ለወለደቻቸው ኤርትራ፤ ፍሪንባዋን አውጥተው ላሳደጋቸው ሱዳን እንዳስረከቡ ይታወቃል፡፡ ተሸራርፋ የቀረችውን ኢትዮጵያ ደግሞ አሞሌ ጨው ሰርተው ሆደ ባሻ አማራን እያላሱ ማለቡን ቀጥለዋል፡፡ የአማራን ማጉረምረም፣ መከተምና ወግድ ባይነት አስቁሞ ለሌላ እሩብ ክፍለ-ዘመን ለማለብ “ኢትዮጵያ!” እያሉ እሚለፈልፉ ጥጃ ያዥ እረኞች እንደ ልዋጭ ነጋዴ በውስጥም በውጪም አሰማርተዋል፡፡ የልዋጭ ነጋዴ በአማራ የፈጠመውን ግፍ ሆደ ባሻው ቢረሳው ልባሙ አማራ ያስታውሳል፡፡

ሆደ ባሻ አማሮች አላቢዎቻቸው የለበጣ መናገር የጀመሯትን ኢትዮጵያ እንደ ላሜ ቦራ እየላሱ ሌላ ሩብ ክፍለ- ዘመን ለመታለብ የተዘጋጁ ይመስላል፡፡ ሆደ ባሻ አማሮች እስካሁን ያለው አገዝዝ በአማራ ጥላቻ ዙሪያ የተዋቀረ መሆኑን የሚልሱት አሞሌ ያስረሳቸው ይመስላል፡፡ ለገሰ ዜናዊ ኢትዮጵያን ሲጠራ ሥሩ የኮርቤሳ ቀንድ ይመስልና ትናጋውም ትኩስ ድንች እንደጎረሰ ይወለካከፍ የነበረው ኢትዮጵያን ሲያስታውስ ኢትዮጵያን የገነባው አማራ ስለሚታየው ለመሆኑ የደደቢቱ ማንፌስቶና በአማራ ላይ የሰራው ግፍ ምስክር መሆኑን የሳቱ ይመስላል፡፡

ሆደ ባሻ አማራ ሆይ! ከደደቢቱ ማንፌስቶ አማራ እንጅ ኢትዮጵያ ጨቋኝ የሚል አንብበሃል? ከደደቢቱ ማንፌስቶ አማራ እንጅ ኢትዮጵያ ጠላት የሚል ተጽፎ አይተሃል? የደደቢት ተማሪዎች አማራ እንጅ ኢትዮጵያ ጠላታቸው እንደሆነች ተማርን ሲሉ ሰምተሃል? ለገሰ ዜናዊ በሱዳን ካሚዎን ቤተመንግስት ገብቶ እንደ አምባሻ በጠፈጠፈው “የሽግግር መንግስት” የደደቢቱን ማንፌስቶ ያልተቀበለ፤ አማራን ጨቋኝ፣ ነፍጠኛና ትምክተኛ ብሎ ያላወገዘ አሳትፎ ነበር? በአማራ ጨቋኝነት ያላመነ፣ አምኖም ያልተጠመቀ፤ ተጠምቆም ሌላ ያላጠመቀ ስልጣን ሰጥቶ ያውቃል? ስለዚህ ለገሰ እንደ ዱላ እየዠነጠፈና እየመለመለ ከአገዛዙ ቀለበት የዶላቸው ተከታዮቹ ችግር ከአማራ ወይስ እነሱም ከሚጋሯት ኢትዮጵያ ይመስልሃል?

ሆደ ባሻ አማራ! እባክህ የእሳት ልጅ አመድ፤ የቆቅ ልጅ ድንቢጥ እየሆንክ ኩሩን አማራ አታሸማቅ፡፡ ለሃምሳ ዓመታት የካዱህን፣ የዋሹህን፣ የዘረፉህን፣ ያሰቃዩህንና የገደሉህን ወግድ የምትልበት አሞት ከሌለህ፣ ቢያንስ የምትጠራጠር ልብ ትኑርህ፡፡ ለኢትዮጵያ አንድነት ይሰሩ የነበሩ ድርጅቶችንና ግለሰቦችን በወታደርነት፣ በጀሮ ጠቢነትና በስልክ ጠላፊነት ተሰማርተው ሲያጠፉ የኖሩ የቀበሮ ባህታውያን ኢትዮጵያ የሚል አንካር ጨው እያላሱ እንደ ላሜ ቦራ አይለቡህ፡፡

ሆደ ባሻ አማራ! በሚላወሰው አንጀትህ ሳይሆን በአይምሮህ አስብ! የአየር ንብረት ተንባይ የወደፊቱን የሚተነብየው ያለፉትን አመታት አየር ንብረት መርምሮ ነው፡፡ ተመራማሪም መላ የሚመታው አንጀቱን ጠይቆ ሳይሆን አይምሮውን ከዚህ በፊት ምን ሆነ ሲል ጠይቆ ነው፡፡ በእህል መፍጫ አንጀት አስቦ ትክክል ከመሆን በሐሳብ አበጣሪው አይምሮ ቀምሮ መሳሳት የተሻለ ነው፡፡

ሆደ ባሻ አማራ ሆይ! “ሳያዩ ያመኑ ብፁዓን ናቸው” የተጣፈው ለመለኮት እንጅ እንደ ይሁዳ ለካዱህ፣ እንደ እባብ ለነደፉህ፣ እንደ በርባን ለዘረፉህ፣ እንደ ፈሪሳውያን ላስገረፉህና ላሰቀሉህ የሳጥናኤል ተከታዮች አይምሰልህ፡፡ እባክህ ለሌላ እሩብ ክፍለ-ዘመን ልገው ለማለብ እንደ አቶ አጥናፉ ላሜ ቦራ በጨው አያታሉህ!

ሆደ ባሻ አማራ እባክህ ልብ በልማ! ጦቢያ በቋንቋ ቢለዋ የታረደችውና የወደብ እስትንፋሷ የተዘጋው አማራን ለመጉዳት ነው፡፡ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ቅርሷን የሚያዘርፉና ነፍሰ-ገድዮችን የሚደግፉ “ፓትሪያሪኮች” የተሾሙባት አማራን ለማዳከም ነው፡፡ የመሐሉ፣ የዳሩና የደቡቡ ሕዝብ በጎሳው እንዲደራጅ የተደረገው አማራን በደምና በአጥንቱ ሲጠብቃት በኖራት አገሩ ስደተኛ ለማድረግ ነው፡፡ ይህ በጎሳ የመደራጀት ሸር እንደ ሸረሪት ድር የተደራው አማራን የሚያስጠላ ጀርም ባሰራጩ የውስጥና የውጪ መናጢዎች ነው፡፡ እነዚህ መናጢዎች አማራን እሚጎዳ ከመሰላቸው የሸር ድር ከማድራት አልፈው በራሳቸው አይንም በርበሬ እስከ መነስነስ የሚደርሱ አማራ ጠሎች ለመሆናቸው ለግማሽ ክፍለ-ዘመን በአማራ የፈጸሙት ግፍ አስረጅ ነው፡፡

እነዚህን አማራን ለመጎዳት በአይናቸውን በርበሬ እስከ መነስነስ የሚደርሱትን መናጢዎች የለከፈው አማራን የሚያስጠላ ጀርም መቼ እንደተፈጠረ ባይታወቅም ይህ ጀርም የተባዛው ደደቢት በርሃ መሆኑን ከደደቢት የወጣው መዝገብና መዝገቡ ሲጠረዝ አባሪ የነበሩ ሰዎች እንደዚሁም አማራን በጠላትነት የተማሩት የደደቢት ተማሪዎች የመሰከሩበት ጠቅላላ እውቀት ነው፡፡ ከወጣው መዝገብና ከመሰከሩት ሰዎች በላይም ለአርባ ሁለት ዓመታት በመላ አገሪቱ የፈሰሰው የአማራ ደምና የተነጠቀው እርስት ምስክር ነው፡፡ እግዚአብሔር አይበለውና በዚህ ፍጥነት አማራ እንደ ደን መጨፍጨፉና ከእርስቱ እንደ ሽንኩርት መነቀሉ ከቀጠለ ዜናው ካማራና ደን አስር በመቶ ቀነሰ ወደ አማራና ደን ሶስት በመቶ ቀረ እሚሸጋገር ነው፡፡

ደኖች ተጨፍጭፈው በበርሃ እርስታቸውን የተነጠቁት ራሳቸውን መከላከል ስላልሞከሩ ነው፡፡ የመጨፍጨፍ አደጋ እንደሚገጥማቸው ተገንዝበው መከላከያ ዘዴ ቢፈጥሩ አለዚያም ገና አንዱ ዛፍ ሲቆረጥ ለመከላከል ቢሞክሩ ደኖች እርስታቸውን በበረሃ አይነጥቁም ነበር፡፡ ደኖች እንደ ጠጀ ሳር የሚጥም ሽታ ማመንጨቱን ትተው አፍንጫን ሰንፍጦ ሳንባን ውሃ እሚሞላ መርዝ ቢፈጥሩ እንኳን ጨፍጭፎ እርስታቸውን ለበርሃ የሚያስረክበው ሰው እንደ ዋሽንት አፉጫጭታ መንፈሳቸውን የምታድሰው ወፍም ድርሽ አትልባቸውም ነበር፡፡

አማራም እንደ ደኖች እየተጨፈጨፈ እርስቱን የተቀማው በውስጥ ጀርሞች እንደሚወረር አስቀድሞ ስላልተገነዘበ ነው፡፡ አማራ እንደ ደኖች እየጠፋ ያለው አገር፣ አንድነት፣ ወንድምማችነት፣ ፍቅርና ይሉኝታ የሚባሉ እንደ ጠጀ ሳር የሚሸቱ ማዛዎች እያመነጨ ራሱን ከአገር ውስጥ ጀርሞች የሚከላከልበት ኮምጣጤ ማመንጨት ስላልጀመረ ነው፡፡ አማራ ኮምጣጤውን አመንጪቶ መከላከል ሲጀምር እንኳን ራሱን ሌሎችንም ከመጥፋት እንደሚያድን ኮምጣጤውን የቀመሱት አውሮጳውያንም የሚመስክሩት ነው፡፡

ይህ ያልተተነበየና ያልተጠበቀ የአማራ ዘፅአት ዘመን ነው፡፡ ይህ ዘመን አማራ በመላ አገሪቱ ስደተኛ ከመሆን ለመዳን ጥበቡን፣ ጉልበቱንና ሐብቱን እንዲያቀናጅ የሚጠይቅ ዘመን ነው፡፡ ይህ ወቅት አማራ ሊያጠፋው የወረረውን ጀርም ለመቆጣጠር መከላከያውን እንዲያጠናክር የሚያስገድድ ወቅት ነው፡፡

አማራ የወረረውን ጀርም መቆጣጠር እሚችለው ሳይንስ ያበረከታቸውን ሶስቱን የበሽታ መከላከያ እርከኖች ከተጠቀመ ነው፡፡ እነዚህ መከላከያ እርከኖች ፍሬያማ የሚህኑትም በዚህ ጀርም ተጠቂው ሕዝብ እንደ አድዋውና አምስቱ ዘመን ተጋድሎ እንደ ተርብ ሲረባረብ ነው፡፡

እነዚህ የተጠቂ ሕዝብ ርብርብ የሚያስፈልጋቸው መከላከያ እርከኖች የመጀመርያ፣ ሁለተኛና ሶስተኛ ዕርከን መከላከያዎች ናቸው፡፡ የመከላከያ ዘዴዎች የዕርከናቸው ቁጥር ሲጨምር የውጤታቸው መጠን ግን እየቀነሰ እሚሄድ ነው፡፡

የመጀመርያ ዕርከን መከላከያ ዘዴ ጀርሙና ተጠቂው ከመገናኘታቸው በፊት የሚደረግ መከላከያ ነው፡፡ ለምሳሌ የፈንጣጣ የመጀመርያ ዕርከን መከላከያ የፈንጣጣው ጀርም ከተጠቂው አካል ሳይደርስ የሚሰጥ ክትባት ነው፡፡ ፈንጣጣ ክትባት የተከተበ በፈንጣጣ የመጠቃቱ ዕድል የመነመነ ነው፡፡ ፈንጣጣ ሶማሊያ ተማርኮ ላቦራቶሪ ግዞት የወረደው ሕዝብ በተከታቢነት፣ ባስከታቢነትና በከታቢነት እንደ ተርብ ስለተረባረበ ነው፡፡

ሁለተኛው ዕርከን መከላከያ ጀርሙና ተጠቂው ከተገናኙ ወይም ጀርሙ ተጠቂውን መጉዳት ከጀመረ በኋላ የሚደረግ መከላከያ ነው፡፡ የዚህ መከላከያ አገልግሎት ጀርሙ ተጠቂውን ጎድቶ የአካላዊ ወይም የመንፈስ ስንክልና እንዳያደርስ በመድሐኒት መከላከል ነው፡፡ ለምሳሌ የፈንጣጣ ጀርም የመጀመርያውን መከላከያ (ክትባት) ባላገኘ ተጠቂ የሚያመጣውን የቆዳ መበላሸትና የአይን መጥፋት እንደዚሁም የመሞት አደጋ ለመቀነስ የሚደረግ መከላከያ ነው፡፡

ሶስተኛው የመከላከያ እርከን እንደዚሁ የመጀመርያውና የሁለተኛው ዕርከን መከላከያዎች ሳይተገበሩ ወይም ሳይሰሩ ቀርተው ተጠቂው የማይሽር የአእምሮ ወይም የአካል ጉድለት ሲደርስበት ተጠቂውን ከሞት ለመከላከል የሚደረግ መከላከያ ነው፡፡ ለምሳሌ በፈንጣጣ የታወረ ገደል እንዳይገባ መሪ ማዘጋጀት ሶስተኛ ዕርከን መከላከያ ነው፡፡

ታሪክ እንደሚያስረዳው አማራ የውጪ ጀርሞችን ሲመክት ሶስቱንም የመከላከያ ዘዴዎች ከሞላ ጎደል ተጠቅሟል፡፡ ዜጎቹን በወኔ፣ በጀግንነትና በታማኝነት የሚያንፅ የዘፈን፣ የቀረርቶ፣ የፉከራ፣ የሰምና ወርቅ፣ የቅኔና የሃይማኖት ክትባት በመክተብ ባንዳ ከመሆን የሚድንበትንና ከተንኳሽ ጀርም የሚከላከልበትን የመጀመርያውን ዕርከን መከላከያ ከሥራ አውሏል፡፡ የውጪ ጠላት ሲወረውም ጠላቱን በሚገባው ቋንቋ የሚያነጋግር መድሐኒት ሰጥቶ ቅኝ ግዛት የሚባል የመንፈስ ሽባ የሚያደርግ ደዌ ድራሹን ለማጥፋት ሁለተኛው ዕርከን መከላከያ ተጠቅሟል፡፡ የሚገባቸውን ያህል ባይሆንም ጠላትን በሚገባው ቋንቋ ሲያነጋግሩ የአካልና የመንፈስ ጉዳት የደረሰባቸውንም እያከበረ ሶስተኛውን የመከላከያ ዕርከን ለመፈፀም ሞክሯል፡፡

የዉጪ ጀርሞችን በሚያስደንቅ ሁኔታ የተከላከለው አማራ የውስጥ ጀርሞች ሲወሩት ግን ከመጀመሪያው ዕርከን መከላከያ ተቸክሎ ቀርቷል፡፡ ጀርሞች በወገቡ ተጠምጥመው እንደ መጋዝ እየገዘገዙትም ኢትዮጵያ፣ አንድነት፣ ወንድማማችነት፣ ተዋልደን ተካብደን የሚሉ የበሽታውን ደረጃ ያልጠበቁ የመጀመሪያ ዕርከን መከላከያ ክትባቶች መጋዙን እንደሚያዶለዱሙ በማመን የፈዘዘ አማራ በየቦታው ይገኛል፡፡ በዘር ተደራጅተው አፈሙዝ የደቀኑበትን ጀርሞች ይህ ክትባት ምላጭ ከመሳብ ያድናቸዋል እያለ እሚንዘላዘል አማራም ሞልቷል፡፡ ይህ እንደ ኤች አይ ቪ ቫይረስ መልኩን የሚቀያይር ጀርም ክትባት እንደማይቆጣጠረው ያልተረዳ አማራ በገጠር በከተማው ተትረፍርፏል፡፡ ይኸን የማይሰራ ክትባት ተማምኖ የተጎለተውን አማራ ባህሪ የተረዳው ጀርምም ለአማራ ጨቋኝ፣ ነፍጠኛ፣ ትምክህተኛና የድሮ ሥርዓት ናፋቂ የሚሉ ኮዶች ሽፈራው ሽጉጤን በመሳሰሉ ቫይረሶች ዲ ኤን ኤ እያራባ አማራን ሲያስጨረግድ ኖሯል፡፡

በእነ ሺፈራው ሽጉጤ ዲ ኤን ኤ እየተዘዋወረ አማራን በሚያስጨርሰው ጀርም ተለዋዋጪ ባህሪ ምክንያት አማራ የሚጠቀምበት የመጀመርያ ዕርከን መከላከያ ዘዴ ከሸፈ፡፡ በመክሸፉም አማራ በዚህ ጀርም በተለከፉ አውሬዎች ደሙ እንደ ጅረት ፈሰሰ፤ ታሰረ፣ በኮረንቲ ተጠበሰ፣ ታመመ፣ ተራበ፣ ተሰደደ፡፡ ለአርባ ሁለት አመታት ባዶ ስድስት ፍዳቸውን አይተው ከሞቱት የወልቃይታና የራያ ወገኖች ቀጥሎ አማሮች በበደኖ ከነነፍሳቸው ገደል ተወረወሩ፤ አርባ ጉጉ አንገታቸውን ተቀነጠሱ፤ በጉራ ፈርዳና ኢሉባቦር በገጀራ ተሰው፤ ከመሰዋት የተረፉትም መንገድ አዳሪ ሆኑ፡፡ አገር ምስራች አማሮች ከእውነተኛ ትምህርት፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ስልጣን ተገለሉ፡፡ በከርቸሌም ከሌላው በከፋ ሁኔታ እንደ ድንች ተጠበሱ፤ እንደ ንፍሮ ተቀቀሉ፤ እንደ ቋንጣም ተሰቀሉ፡፡ መነኩሴው ሳይቀር ራቁታቸውን ግድግዳ እየገፉ በሴት ተገረፉ፡፡

የመጀመርያው ዕርከን መከላከያ ከሽፎ ጀርሙ አምስት ሚሊዮን አማሮችን በተለያየ መንገድ እንደ ፈጀ የተገዘቡ ወጣቶችና ጎልማሶች ሁለተኛውን መከላከያ እርከን ጀመሩ፡፡ ለዚህ ሁለተኛ እርከን መከላከያም ” ተጋደል”፣ “ተደራጅ”፣ “መክት” የመሳሰሉ ስሞችን አወጡ፡፡ ይህ ሁለተኛ ዕርከን መከላከያ ግን የአማራ ደም ጎርፍ ከተቸከሉበት የመጀመርያ ዕርከን መከላከያ ለአምሳ ዓመታት ሊያነቃንቃቸው ባልቻለው ችካሎች ተቀባይነት አጣ፡፡ ከመጀመርያው ዕርከን የተቸከሉት ችካሎች ሁለተኛውን ዕርከን  ለመውጣት ለሚፍጨረጨሩት ተሻጋሪዎች አሚካላ ሆኑና አረፉ፡፡

በአሚካላዎቹና በተሻጋሪዎቹ መካከል የተፈጠረውን ውጥረት እንደ ጥሩ አጋጣሚ ተጠቅመው ጀርሞች አሁንም አምባ ጊዮርጊስ የህፃናትን ጭንቅላት በረቀሱ፤ ጎንደርና ደብረታቦርም ስንት ዜጎችን ገደሉ፡፡ ከገዥዎች ጽ/ቤት ጣራ ከትመው በባህርዳር ወጣትና ጎልማሳውን በስናይፐር አረገፉ፡፡ ዳንግላ፣ ቡሬ፣ ደብረ ማርቆስና ማጀቴም የስንቱን ደም አፈሰሱ፡፡ ወልድያ ስንቱን ህፃናት፣ ጎልማሳና አዛውንት ከታቦቱ ጀርባ እንደ አበባ አረገፉ፡፡ በብዙ ሺህ እሚቆጠር ወጣትም ወህኒ አስተኝተው እንደ ጪቃ ረገጡ፤ እንደ ጣውላም በምስማር ወጉ፤ እንደ ስንጥር በፔንሳ ጥፍር አወለቁ፤ እንደ ክርስቶስም ከግንድ አጣብቀው ገረፉ፤ እንደ ስብም በኮረንቲ ጠበሱ፤ እንደሰንጋም ሰለቡ፡፡ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች አማራውን እንደ ድኩላ ማባረሩንና ማረዱን ቀጠሉ፤ ከእልቂት የተረፉትም እንደ ሚዳቋ በስጋት እንዲኖሩ አስገደዱ፡፡

ይህ ናዚ በአይሁዳውያን ከፈጠመባቸው የከፋ ግፍ ወደ ሁለተኛው መከላከያ እርከን ለመሻገር የሚፈልጉትን ተሻጋሪዎች ከመጀመሪያው እርከን ከተቸከሉት አሚካላዎች አጋጫቸው፡፡ በተሻጋሪዎች ቁርጠኝነትና በአማራ ጀብዱ የሰጋው ጀርምም እንደተለመደው ባህሪውን ቀይሮ ኢትዮጵያ፣ አገር፣ አንድነት፣ ጉርብትና የሚሉትን የመጀመሪያ ዕርከን መከላከያ መዝሙሮች የለበጣ እየዘመረ አሁንም አሚካላዎች ተቸክለው እንዲቀሩ ከንቱ ተስፋን አስረግዞ አንዘላዘላቸው፡፡ የጀርሞችን ከንቱ የተስፋ ዲቃላ ያረገዙ ችካሎችም ተሻጋሪዎችን እያደናቀፉ መጣሉን ቀጠሉ፡፡ አሚካላዎችን ግማሽ ክፍለ ዘመን ያንዘላዘሉት ጀርሞች ግን የዘር ድርጅራቸውን ይበልጥ አጠናክረው በወልቃይት፣ በራያ በመተክል፣ በሸዋ፣ በሀረርጌ ፣ በከፋና ሌሎችም ሥፍራዎች አማራን ማሳደዱንና ማሰቃየቱን ቀጠሉ፡፡

አሚካላ ሆይ! ለሃምሳ ዓመታት የተንዘላዘሉት በሽታን ለመከላከል ወይም ለመቆጣጠር በሽታው የደረሰበትን ደረጃ እሚመጥን የመከላከያ ወይም የመቆጣጠሪያ ዘዴ አስፈላጊ መሆኑን ባለመረዳትዎ መሆኑን ያውቃሉ? ለአርባ ሁለት ዓመታት አማራን ያስጨረሱት የመጀመርያ ደረጃ መከላከያ ዘዴን ብቻ በመጠቀምዎ መሆኑን አጢነዋል? ጀርሙ ተሰራጪቶ ሕዝብዎን እየገደለውና አካል ጎደሎ እያደረገው የክትባት ሲሪንጅ ብቻ ጨብጦ መንከርፈፍን ምን ይሉታል?

አሚካላ ሆይ! ደደቢት በርሃ አማራውን የሚፈጅ ጀርም ያባዙትንና በዚህ ጀርም የነፈረቁትን እንደ ሽፈራው ሽጉጤ ያሉ አረመኔዎችን አንድነት፣ ወንድማማችነት፣ ጋብቻ፣ ፍቅርና ይሉኝታ የሚባሉ የመጀመርያ ዕርከን መከላከያዎች እንዴት ሊፈውሱ ይችላሉ? ወንድማማችነት፣ ተዋልደን፣ ተካብደን የሚሉት የመጀመርያ ዕርከን መከላከያ ብቻውን ላለመስራቱ ግማሽ ክፍለ-ዘመን ራስዎ ካደረጉት ሙከራ የተሻለ ምን መረጃ ይፈልጋሉ? ሃምሳ ዓመታት ተጉዘውበት ገደል በከተተዎት መንገድ ለምን እንደገና ጉዞ ይጀምራሉ? ገደል በሚከተው መንገድ ደጋግሞ የሚጓዝ እንኳን አይምሮ ያለው ሰው ሙጃ ያዬ በሬስ የት አገር ነው ያዩ?

አማራ ሆይ! በቅድመ ዓያቶችህ ሥጋ አፈርነትና በደማቸው ውሀነት የተሰራችውን ጀበናህን ከእነ ውበቷ ለማኖር እንደ ደን እየጨፈጨፉህና እንደ ዝልዝል እየጠበሱህም ከኢዮብ የበለጠ ታግሰሃል፡፡ እንደ ሰንጋ እየሰለቡህም፣ እንደ መሲና እያመከኑህም፣ እንደ ንብ ከቀፎህ እያሰደዱህም አንድነትን፣ ወንድማማችነትንና ፍቅርን እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት ሰብከሃል፡፡ አንድነትንና ፍቅርን ብትሰብክም እነሱ ግን በየቦታው እንደ ሽንኩርት እየነቀሉ ይጥሉሃል? እንግዲህ ምን ይሻልሃል?

አማራ ሆይ! ለመሆኑ የመጀመርያ ዕርከን መከላከያህ አለመስራቱን በየቀኑ ከሚታረዱትና ከሚሰለቡት ልጆችህ በላይ ማን እንዲያሳምንህ ሽተሃል? ለግማሽ ክፍለ-ዘመን የተቸከልክበት እርከን መናዱን በሥምህ እንደ ታረደ በግ ተጋድመው ዓይናቸው ከወጣውና ተንጠልጥለው ጥፍራቸው በጉጠት ከተነቀሉት ልጆችህ ወዲያ ማን እንዲነግርህ ፈልገሃል? ለአምሳ ዓመታት የተከተልከው መንገድ እንጦሮጦስ እንደከተተህ በአጥንቱ ባቆማት አገሩ ስድተኛ ከሆነው፣ ከምጣኔ ሐብትና ከትምህርት ተገሎ በችጋርና በበሽታ ከሚረግፈው ወገንህ በላይ ምን ማስረጃ እንዲቀርብልህ ጠብቀሃል?

አማራ ሆይ “ደካማን ሳይ ታገለው ታገለው ይለኛል” የሚለውን ብሂልህን ዳግም ማሰላሰል ይጠበቅብሃል፡፡ ስንቱን ኃያል መንግስት ያንበረከክ ጀግና ቻለው ሆዴ ብትል ደካማ መስልህ ታይተኸው ወፍ አሞራው ደፍሮሃል! እየጫረ ዓይንህ ዘንቁሯል፤ ደምህን አፍሷል፡፡ የሚዘንቁርህን አሞራ ለመከላከል እንደምታውቅበት ወንጪፍህን ታነሳ ዘንድ የዳዊትና ያንተ አምላክ እግዚአብሔርም ፈቅዷል፡፡

አማራ ሆይ! ራሱን ለመከላከል ያልጣረን ዝቅዝቅ የምታየው ምድርም ሆነ አንጋጠህ የምትመለከተው ሰማይ ስለማይረዳ እንደ ባህልህና እንደ ወትሮህ አንገትህን እንደ ካስማ ቀስረህና ትከሻህን እንደ ሻኛ አጎማለህ ራስህን ተከላከል፡፡

አማራ ሆይ! ራስህን ስትከላከል “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” የሚለውን ብሂልህንም ከግብር አውል፡፡ ከክብርህ ማማ እንድትቆናጠጥ እንደ ገመድ መጓተቱን ትተህ እንደ ማግኔት ተሳሳብ፡፡ እንደ ወፍጮ መፋጨቱን አቁመህ እንደ ሙዳይና ክዳኗ ተሳሳም፡፡ እንደ ውልክፋ መወላከፉን ትተህ እንደ ባላ ተደጋገፍ፡፡ እንደ ባንዳ መሽሎክለኩን አስወግደህ እንደ አርበኛ ክተት፡፡ ከተህም እንደ ወይፈን መክት፡፡ ስትመክትም ከአንዱ መከላከያ እርከን ወደ ሌላው እንደ እምቦሳ ዝለል፡፡ እንደ አሚካላ ከአንድ እርከን ተቸክለህ ተሻጋሪዎችን እንደ እንቅፋት እያደናቀፍክ አትጣል፡፡

አማራ ሆይ! ዓለም በአሪዎሶች እንጅ በቅዱሳን ተመርታ አታውቅም ወደፊትም በቅዱሳን አትመራም፡፡ ስለዚህ ከአሪዎሶች ጭካኔ ለመዳን ሶስቱን የመከላከያ እርከኖች አጢነህ በአግባቡ ተጠቀም፡፡ በዘሩ ሰንሰለት ሰርቶ እየገደለህና አካለ-ስንኩል እያደረገህ ያለን ጀርም “አብረን ኖረን፣ ተጋብተን፣ ተዋልደን” በሚል የሚሾ ክትባት አትገላገለውም፡፡ በልመና ክብርም አይገኝም፡፡ በልመና ከተገኘም እርጥባን እንጅ ክብር አይባልም፡፡ ክብርህ በራስህ እጅ ናት፡፡ ከጠነከርክ ክብርህን ከፍ ታደርጋታለህ፤ ከዛልክም ትጥላታለህ፡፡ ክብርህን ማንም አይሰጥህም፡፡ ክብርህን የምታገኛት ራስህ ነህ፡፡  ክብርህን ራስህ አንሳት፤ ክብርህን ራስህ ጠብቃት፡፡ ዳግመኛም ከእጅህ እንዳትሾልክ ጥበብና ጉልበት ፈጥረህ በምርምር አዳብርላት፡፡

አማራ ሆይ! የመከላከያ ኃይሉ የደከመ ገላ እንኳን በአውሬው በለማዳው ጀርምም ይጠቃልና የአማራ ልጅ ጀርሞችን ለመቆጣጠር መከላከያህን አጠንክር፡፡ ባልጠበከው መንገድ ጊዜ ሸርተት አርጎህ አማራን በሚያስጠላ ጀርም እንደ ቡግንጅ የነፈረቁ ድውያኖች ጥፍርህን እንደ ምስማር በጉጠት ሲነቅሉትና ዓይህን ቆፍረው እንደ ድንች ሲያወጡት የተመለከተው አምላክ ይርዳህ!

አባሪ፡

የአግባው ሰጠኝ ሰቆቃ

https://ethsat.com/2018/05/esat-hr-interview-with-ago-agbaw-tegegn-25-may-2018/

የአባ ጡመልሳን ዘሚካኤል መከራ https://ethsat.com/2018/05/esat-menalesh-meti-with-qomos-aba-tumelessan-zemichael-and-artist-senaiet-berhanu/

የተስፋዬ ታሪኩ ሰቆቃ

https://ethsat.com/2017/07/esat-hr-interview-ato-tesfaye-tariku-30-july-2017/

የአንዷለም አያሌው ሰቆቃ

https://ethsat.com/2018/05/esat-tikuret-reyot-with-andualem-ayalew-sat-26-may-20-2018/

የእነ ማስረሻ ሰጠኝ ሰቆቃ

https://www.youtube.com/watch?v=U2nB1mMeqx4

https://www.youtube.com/watch?v=Vo67GXNWBbI

http://musicbaby.xyz/video-online-masresha-setie.h6BnaHiJf4hzk3o.html

https://www.youtube.com/watch?v=lbHF_u3CudM

የእነ ጌታ አስራደ ሰቆቃ

https://ethioexplorer.com/graphic-recently-freed-prisoners-of-conscience-from-amhara-region-narrate-despicable-torture-committed-under-the-tplf-dominated-regime/

http://debirhan.com/2018/07/graphic-recently-freed-prisoners-conscience-amhara-region-narrate-despicable-torture-committed-tplf-dominated-regime/

 

ግንቦት ሁለት ሺ አስር ዓ.ም.