=====================
ባለፉት ሁለት እና ሦስት አመታት ተኪ የሌለውን ህይወታችሁን ጭምር ከፍላችሁ እነሆ ዛሬ የነፃነት፣ የፍትህ እና የእኩልነት ድባብ እንድንጎናፀፍ አስችላችሁናል ፡  ፡  የአንድነት፣ የመከባበር  እና የፍቅር እንዲሁም የይቅር ባይነት መንፈስ እና ተስፋ እንዲለመልም አስችላችኇል::
ትግላችሁ ጥላቻ፣ ቂም በቀልና ጭቆና ቦታቸውን ለፍቅር፣ ለይቅርባይነትና ለነፃነት እንዲለቁ እና ማንም ባልገመተው ፍጥነት በለውጥ ተስፋ እንድንሞላ አድርጎናል::
አሁን የምንገኝበት ወቅት ለውጡ ከተስፋ ተራምዶ የኇላ ማርሽ በማያስገባበት ደረጃ ላይ አልደረሰም:: ይልቁንም አልፎ አልፎ የምናስተውላቸው ድርጊቶች የተስፋችንን ጭላንጭል የማጨለም፤  እርምጃችንን የመግታት እና ወደ ኇላ የመጎተት አደጋ እየደቀኑ ናቸው::
በአንዳንድ የክልላችን አካባቢዎች በከፋው የግጭት፣ ሁከት እና ብጥብጥ ጊዜ እንኳን ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የራሳችንን ንብረት የማውደም፣ በርካታ ተሽከርካሪዎችን የማቃጠል እርምጃዎች ተውስደዋል::
እንዲህ አሁን እንደጀመርነው አይነት ማህበረሰባዊ ለውጥ በራሱ የህዝብን መነሳሳት እና ፈጣን እርምጃን ይዞ የሚመጣ፤  ከወትሮው የተለየ ስነልቡና እና እንቅስቃሴ ይዞ የሚመጣ ሂደት በመሆኑ መስከንን፣ ብልህነትን፣ አስተዋይነትን እና እርጋታን ካላከልንበት ለውጡም ላይሳካ፤  የለውጥ ሀይሎችንም ለፀረ-ለውጥ ሀይሎች ሰይፍ ሊዳርግ ይችላልና ታላቅ ጥንቃቄ ያስፈልገናል::
በክላልችን ባለፉት ሁለት እና ሶስት ወራት ብቻ የለውጡን ወቅት የማይመጥኑ፤ ውዱን የሰው ህይወት ያጠፉ፣  አካል ያጎደሉ እና ንብረት ያወደሙ አሳዛኝ እና አሳፋሪ ክስተቶች ተከስተዋል፤  የንግድ ስርዓቱን የሚያስተጏጉሉ እና የአርሶ አደሩ ምርት ጭምር ወደ ፈለገበት ቦታ እንዳይጏጏዝ የሚያደርጉ እንቅፋቶች ተስተውለዋል ፡  ፡
ለውጡን ለመቀልበስ አቅደው እና አልመው በመንቀሳቀስ ላይ ያሉ ወገኖች የተጠናከረ የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ ጀምረዋል ፡  ፡ እኛም እነሱ ባጠመዱት ወጥመድ እየገባን እጃችን የገባውን የለውጥ ተስፋ በማጨለም እየተባበርናቸው እንገኛለን ፡  ፡
ሄደን ሄደን ትናንት ሻሸመኔ ላይ ያየነው የጭካኔ የመጨረሻው ጫፍ ላይ ደርሰናል ፡  ፡ በክልላችንም አሁን የሚታዩት ምልክቶች ይህንን ዓይነት ክስተት  ይዘው ላለመምጣታቸው ምንም ዋስትና የለም ፡  ፡
ስለሆነም  መደማመጥ፣ መስከን፣  ማስተዋል እና
መረጋጋት እና ለህግ የበላይነት መገዛት ወቅቱ የሚፈልጋቸው ጉዳዮች ሲሆኑ ስሜታዊነት፣  አሉባልታና ግርግር ልንርቃቸው የሚገባ የለውጡ እንቅፋቶች ስለሆኑ ጥንቃቄ ያስፈልገናል ፡  ፡ ወጣቶቻችን ይህንን በመገንዘብም የህግ የበላይነት እንዳይጣስ ግንባር ቀደም ሚና እንድትጫወቱ፣ የፖሊስን ስራ ለፖሊስ በመተው የአጋርነት ሚናችሁን መወጣት ይገባችኇል እንላለን ፡  ፡