በአጭሩ ሁሉም የማህበረሰባችን ክፍል ይህን ጉዳይ በአጽኖት ሊያስተውለው ይገባል፡፡ በትላንትናው እለት በሻሻመኔ ሆነ የተባለው ድርጊት ለምንና እንዴት እንደሆነ ወደልባችን ተመልሰን በደንብ እናስተውል፡፡ ሁለተኛም እንዳይመጣብን ለሁላችንም ትምህርት እንዲሆነን ያስፈልጋል፡፡ ጉዳዩ የኦሮሞ የአማራ የእከሌ ሕዝብ ምናምን የሚባል አደለም፡፡ ዛሬ ሻሸመኔ ነው የተከሰተው ነገ ባሕርዳር ሊከሰት እንደሚችል አስበን እልባት የሚሆኑነንን አካሄዶችን ብናሰብ ጥሩ ነው፡፡
ከየፌስቡኩ እንደ ተረዳሁት የሻሻመኔውን አሰቃቂ ድርጊት ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር በማገናኘት ድርጊቱ የሕዝብ ባሕሪን እንደሚወክል አድርገው ብዙዎች አይተውታል፡፡ በጣም ያሳዝናል፡፡ ሁላችንም ደግሜ እላለሁ የኦሮሞን ሕዝብ ተረዱት ብዙ ችግር አለበት፡፡ ነገሮች ከመጀመሪያውም ጀምረው ይሄን ሕዝብ በሌሎች እንዲጠላ ማድረግ ልዩ ስልት ተደርገው የተወጠኑ ናቸው፡፡ አስተውሉ ከጥቂት ወራት በፊት የኦነግን ባንዲራና የተለያዩ ፅሑፎችን በቡኖ በደሌ ሲያሰራጭ የተገኘውን ሰው ማንነት አስቡ፡፡ ግለሰቡ ከእነ ጭርሱም ኦሮሞ አልነበረም፡፡ ያ ቀለል ያለ ክስተት በደንብ አስተውለን ተጠቅመንበት ቢሆን ኖሮ የዛሬውን የሻሻመኔውን አደጋ ቢያንስ መቀነስ እንችል ነበር፡፡ ከዚህም ቢያንስ ድርጊቱ እንኳን ቢከሰት የሕዝብን ምስል ከማጠልሸት ያድነን ነበር፡፡ ዛሬ ላይ ምንም ማለት አልችልም፡፡ አንድ ነገር ግን እረዳለሁ የኦሮሞ ሕዝብ መጠቀሚያ እንደሆነ ብዙዎቻችን እያስተዋልን አደለም፡፡ በዚህ ማህበረሰብ እየተደረጉ ያሉ ድርጊቶች በእርግጥም በዋናነት ኦሮሞ ነን በሚሉ ምሁርና ሰለጠንን በሚሉ የጥላቻና የዘረኝነት ፖለቲካን ከለላ አድርገው እንደሆነ እናስተውላለን፡፡ ሌሎች ይህን አጋጣሚ ተገን አድርገው ይህ በየማህበራዊ ሚዲያውና ሌሎች የዜና ማሰራጫ ሚዲያዎች ሳይቀር የሚሰራጨውን የጥላቻና ፖለቲካ በተግባር ለማሳየትና ሕዝብን በሕዝብነት ለማስጠቆር በስፋት ሲጠቀሙበት ኖረዋል አሁንም እየተጠቀሙበት እንደሆነ በደንብ እናስተውል፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ መከራ ብዙ ነው፡፡ እኳን ሌሎች የዚሁ ማህበረሰብ አካል ነን የሚሉ ተማርን ብለው የሚያስቡ ሊረዱለት አልቻሉም፡፡ ኦሮሞነትን እህልና ውህ ነው ብለው ሌት ከቀን ይጭኑበታል፡፡ ግን ከመሠረታዊ ማንነቱ አውጥተው ለማንም መጠቀሚያ አድርገውታል፡፡ ነጻ ነኝ የሚለው ምሁር ሳይቀር ኦሮሞን ከሌላው ለየት አድርጎ ሥሙን ከእልጠራ በኢትዮጵያዊነት ከጠቀለለው የሚያንስ ይመስለዋል፡፡ ይሄ የኦሮሞ ምሁራን ነን የሚሉ አብዛኞቹ ውስጣቸው የተዋሀደ ይመስለል፡፡ አሁን ሕዝቡን ግራ አጋብተውታል፡፡ ይሄው ኢትዮጵያዊ ሁሉ አነሰም በዛም በተገኘው የሰላም ተስፋ እየተደሰተ ባለበት ሁኔታ ኦሮሞ አሁንም ባይተዋር ሆኗል፡፡ ከዚህ በላይም ይሄው እንዲህ ያሉ ድርጊቶች መጠቀሚያ ሆኖ ይበልጠውንም በሌሎች በልዩ ጥላቻ እንዲታይ እየተደረገ ነው፡፡
በአጭሩ መፍትሄ የሚመስለኝ ሕዝቡ ኦሮሞ ኦሮሞ የሚሉትን በቃን ከእናንተ ጋር ማለት መቻል አለበት፡፡ መሠረታዊ ችግሩ ከጀምሩ ከኢትዮጵያዊነቱ ሲያወጡት ነበር፡፡ በቃን ብሎ ሊል ይገባል፡፡ ይህ የምለው የማይገባችሁ ከሆነ አሁንም ብዙ መከራ አለ፡፡ ጠላቶች እየተጠቀሙ ያሉት ይህን እድል ነው፡፡ ይህ ለኦሮሞ ብቻ አልልም፡፡ አሁን አሁን እየተስፋፋ የመጣው አማራነትም ሌላው አደጋ እንደሆነ አስተውሉ፡፡ ከኢትዮጵያ ማንነት መውጣት ብቻ ሳይሆን የአክራሪነትና ሌላውን የመጥላት ስሜት በራስ ብቻ የተገደበ ሳይሆን ለሌሎች የጥፋትና የሴራ መልዕክተኞች ጥሩ መሸሸጊያ እንደሆነ አስተውሉ፡፡ ዛሬ ኦሮሞ ተለይቶ የኦነግ ባንዲራና ከሌሎች ኢትዮጵያውያን በተለየ የሚየስደስተው ኦሮሞነትን ብቻ መሠረት ያደረገ ፖለቲካ እንደሆነ በትልቅ ምስል ለማሳየት ሁሉንም ተቆጣጥረው የሚመሩት እነማን ናቸው? በእርግጠኝነት አምቦ ላይና በሚሊኒያም አዳራሽ አንድም የኢትዮጵያ ባንዲራ ያልያዘ አለመገኘቱ የማይፈልግ ቀርቶ አደለም፡፡ ግን የኦሮሞ የተባለ ቦታ የኢትዮጵያ የተባለን ነገር ይዞ መገኘት አንደ ነውር እንዲታይ ትልቅ ምስል ስለተሳለ ሕዝቡ ስለሚሸማቀቅ ነው፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ከእነዚህ ለዘመናት በራሳቸው አጥር ያጠሩትና እንደልቡ እንዳይሆን ያደረጉትን ከላዩ ላይ ሊያራግፍና ምንም አይነት ክፍተት በአለመስጠት የራሱን መስል ከሌሎች ጋር ማዋሀድ አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ እነ ለማ ጥሩ እድል ፈጥረውለታል፡፡ እባብ ሞኝን ሁለቴ ነደፈው ይባላል፡፡ ግን እስከመቼ እንነደፋለን? የምለው ከገባችሁ ማለቴ ነው፡፡
ሌሎች ዛሬ በሻሸመኔ ስለሆነ በኦሮሞ ላይ ልዩ ምስል ከመቅረጽ ነግ በእኔ በሉ፡፡ የትንንሽ አስተሳሰቦች ባሪያ ስንሆን ማንም እንዲህ ይጠቀምብናል፡፡ ነገ ባህርዳርና ጎንደር ሊሆን እንደሚችል አስቡ፡፡ ምን አልባትም ተመሳሳይ ምስል ለመስጠት አሁንም ምን እንደታሰበ አናውቅም፡፡ እንደ እውነታው ይህ አይነት ድርጊት በሌሎችም አካባቢዎች ተፈጽሟል፡፡ በአዋሳ፣ በሶዶ፣ በመሳሰሉትም ታይተዋል፡፡ ግን የሻሻመኔውን ያህል አልተዛመቱም፡፡ ለኦሮሞ ሲሆን እንዲከርበት ያደረጉት አሁንም ቀድሞ ከጽንፈኞቹ ያጠራቀምናቸው የጥላቻና ዘረኛ ፖለቲካ ወሬዎች እንደሆኑ እናስተውል፡፡ አሁን ሕዝቡን ሕዝቡን ማገዝ እንጂ ጥፋተኛ ማድረግ በጣም አደገኛ ነው፡፡ ሲጀምር ሕዝብ አንደ ሕዝብ ጥፋተኛ አይሆንም፡፡ አሁንም ደግሜ እላለሁ ኦሮሞ መጠቀሚያ ነው ከሁሉም ሕዝብ በላይ! ይሄ ክስተት የመጨረሻ መማሪያ ሆኖን ይለፍ፡፡ ለኦሮሞ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ማህበረሰብ፡፡ አንድም ቡድን ይሁን ግለሰብ አንድን ሕዝብ ለይቶ የአንተ ወኪል ነኝ ቢል ሕዝቡ አታስፈልገኝም ሊለው ይገባል፡፡ ሕዝብ በመንግስትና በምርጫ ወቅት በሚመርጣቸው መሪዎች እንጂ ማንም እየተብለጠለጠ ሊጠቀምበት አይገባም፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ በተለይ ዛሬ ኦሮሞነቱን እያገዘፉ ልክ ከሌላው የተለየ እንደሆነ የሚነግሩትን ዞር በሉልኝ ለዘመናት በስሜ ነግዳችኋል ሊል ይገባል፡፡ በአማራ ሕዝብ ከጥቂት ጊዜ በኋላ እየተስፋፋ የመጣው ተመሳሳይ ሕዝብን በአማራነት የተለየ የሚያስመስል ፖለቲካ ሌላው አደጋ እንደሆነ ይታሰብበት፡፡ መንግስት እንደመንግስት ከዛሬ ጀምሮ ማንነትን መሠረት ያደረገ ፖለቲካን በይፋ ለመዋጋት መነሳት አለበት፡፡ ኦፒዲኦ ሥም ቀየርኩ ብሎ አሁንም ፒዲኦ ቢል ምንም ትርጉም የለውም፡፡ እንደእውነቱ የኦፒዲኦ በሉት ፒዲኦ አባል የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስቴር ሊሆን አይችልም፡፡ በግልጽ የኦሮሞ ወኪል ነኝ የሚል ግለሰብ ሆነ ቡድን እንዴት ኢትዮጵያን ይወክላል? አብይና ለማ ኢትዮጵያዊ አስተሳሰብ ስላላቸው አሁን የተገኘው ለውጥ ታየ እንጂ በእርግጥም የብዙዎች አስተሳሰብ በዛው በፓርቲያቸው አጥር ልክ ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሁንም የወደቅንበትን የዘር ፖለቲካ ሙጥኝ ብለው የትም አንደርስም፡፡ ሌላው ብዙ ሰነዶች ሕገ መንግስት ተብዬው የክልሎቹን ጨምሮ ብዙ ወንጀል ለመፈጸም በሕግ ያኖሩ ናቸውና፡፡ በአስቸኳይ እነዚህ ሰነዶች እርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል፡፡ መንግስት ከዚህ በኋላ የዜጎችን መብት አፍኖ የቡድ በሚል ቅብ ማንነታችንንም ያጠፋውን አደገኛውን አሰራር ከሥሩ ማጽዳትና የዜጎችን መብት ወደማረጋገጥ መስራት አለበት! በብሔር ውስጥ እየተደበቁ ሕዝብንና አገርን እየገደሉ ብዙ አመት የኖሩ ስለተንጫጩ የሕዝብ የዜግነት መብቶች አሁንም ሁለተኛ ጉዳይ ሊሆኑ አይገባም!
ሁላችንም እናስተውል፣ ኦሮሞ፣ አማራ፣ …. ወዘተ እያልን አራጋቢ ከምንሆን ትኩረት ሰጥተን ሴረኞችን እንዋጋ፡፡ የሻሸመኔው ክስተት ለሁላችንም የመጨረሻ መማሪያ ይሁን፡፡ የሻሸመኔን ሕዝብ ከተፈጠረበት ድንጋጤ በተጨማሪ ሌላ ሞራል የሚነካ ነገር በመናገር ተጨማሪ ሀዘን አንሁንበት፡፡ እንደውም ለሕዝቡ እንዲረጋጋና ጠላቶቹን ነቅሶ እንዲያወጣ ድጋፍ እናድርግ፡፡ መንግስትም ይሄንኑ ቢያደርግ፡፡ በውስጣችን ጠላት እንዳለ አውቀን በንቃት እራሳችንንም፣ ሌሎችንም፣ አገርንም እንጠብቅ!
ልዑል እግዚአብሔር ማስተዋሉን ይስጠን! አሜን
ሰርፀ ደስታ