ዶ/ር ዐቢይ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ ጀምሮ በግለሰብ ሆነ በመንግስት ደረጃ ልዩ ልዩ አመለካከቶችን ሲንጸባረቁ ማየት የዘወትር ተግባር ሆኗል። ጥናታዊ ባልሆነ መልኩ በግርድፉ ሲታይ ዶ/ሩ ከሚናገሯቸውና ከሚያከናውኗቸው ሥራዎች አንጻር ኢትዮጵያውያንን በአመለካከታቸው በአራት ምድብ ማስቀመጥ ይቻላል።

የመጀመሪያዎቹ  ምድብ  ለውጡን በፍጹም ልባቸውና በፍጹም ነፍሳቸው የሚቀበሉና የሚተገብሩ ሁለተኛው ምድብ ከአሁን በኋላ አስተማማኝና ዘላቂ ለውጥ የሚመጣው በጦር ሳይሆን በሰላማዊ መንገድ የሚሉ ሲሆኑ ሦስተኛው ምድብ ደግሞ የተጀመረው ለውጥ ጥልቀት የሌለውና አስተማማኝ እንዳልሆነ የሚሞግቱ ናቸው፡፡ አራተኛው አይነት አመለካከት ያላቸው ምድቦች ደግሞ ከላይ ከተዘረዘሩት ሦስቱ አመለካከቶች ውጭ በሆነ መንገድ  ለውጡን በአይነትና በጥራት ለመቀበልም ሆነ ለመገምገም የተቸገሩና ለውጡን ከማድነቅም ከማውገዝም በመቆጠብ በተጠናወታቸው ተያዥ የሚነጉዱ ግለሰቦችንና መንግስት ተቋማትን እየታዘብን ነው፡፡ እኔ የዚች ምስኪን አገርና ትውልድ ወዴት እያመራ እንዳለ ሊገባኝ አልቻለም፡፡ ለውጥ የማይቀይረን፣ መደመርን በአፍ እንጂ በተግባር የማናሳይ፣ ከትናንት ዛሬ የማንማር መሆናችንን ሳስብና የትዝብቴ ማጠንጠኛ የሆነው የአማራ ክልል ከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ቢሮ ነው፡፡

ዶ/ሩ የጠቅላይ ሚኒስቴርነት ሥልጣን ከተጎናጸፉ ጀምሮ በአማራ ክልል በሕዝቡ ዘንድ ካልሆነ በቀር አስካሁን ድረስ የመንግስት ተቋምና ከክልል እስከ ወረዳ በሥልጣን ላይ አመራሮች ላይ የለውጥ አብዮት ሳይካሄድ የዕውር ድንብር ጉዞ ላይ እንዳሉ ማሳያ ከላይ በትዝብቴ ያነሳሁት ተቋም ነው፡፡

ይኸው ተቋም በሕግ የተሰጠውን ሥልጣንና ተግባር ወደ ጎን በመተው ከሰው ሀይል አደረጃጀት፣ ከመልካም አስተዳደርና ከአገልግሎት አሰጣጥ ተልዕኮውን በብቃት ባለመወጣቱ ዛሬም ድረስ የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ጥያቄ፣ የስመ ንብረት ዝውውር፣ ሠነድ አልባ ይዞታ ይጽደቅልኝ ጉዳይ፣ የልማት ተነሽዎች የካሣ ክፍያ ተመጣጣኝ አለመሆን፣ የመሠረተ ልማት ጥያቄና በየከተሞቹ የሚገነቡ ግንባታዎች የሕንጻ ሕጉን ባለመከተላቸው የሕዝብ ጤንነትና ደህንነት ስጋት ላይ እንደሆነ በየከተሞች የሚሰሙ እሮሮች ናቸው፡፡

ተቋሙ በርካታ ሕግ፣ ደንብና መመሪያ ቢያወጣ ለበርካታ ዓመታት በሕዝቡ የሚነሱ ቅሬታዎችን ተቀብሎ ሳይመልስና በይደር በማቆየቱ ሳያንስ ከኢፌዴሪ ከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በተዋረድ ካሉ የ10 ዞኖችና የ42 የከተሞች አመራሮች በፖሊሲዎችና በስትራቴጂዎች እንዲሁም በህግ ማዕቀፎች ዙሪያ ከነሃሴ 1 – 15 ቀን 2010 ዓ.ም በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ዘንዘልማ ካምፓስ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እየሰጠ መገኘቱ እጅግ አስገርሞኛል፡፡

የግርምቴ መነሻ ሌላም አይደለም፡፡ በአማራ ክልል በቅርቡ ከላይ እስከ ታች የአመራር ለውጥ እንደሚደረግ እየሰማን ባለንበት ወቅት ቢሮው ለነባር አመራሮች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መስጠቱ ለምን ይሆን? ብየ ራሴን ስጠይቅ የመሸኛ ሥልጠና ሳይሆን አይቀርም ብየ ገመትኩ፡፡ መገመት የግል ልኬታ ነው፡፡ Çነጭ ጤፍ የቄስ መጫወቻÈ እንዲሉ የአገር ሀብትን ላለስፈላጊ አመራር አላስፈላጊ ወጪ መደረጉን ሳስብ ስልጠናው እንዲዘጋጅ የፈቀዱት የቢሮው አመራሮች አንለወጥም እንቆያለን ብለው አስበው የፈጸሙት ከሆነ በጤንነታቸውም ሆነ በአስተሳሰባቸው በኩል እክል እንዳለባቸው ገመትኩ፡፡ በ21ኛው ክፍለ ዘመን እጅግ ኋላቀር በሆነ ፖሊቲካ አገርን ለመምራት መሞከር በዘመኑ ያለመኖርን ያህል ይቆጠራል፡፡

እንዳለመታደል ሆኖ ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ ተቋሙን እየመሩት ያሉት የህወአት ተላላኪና በፖሊቲካ አመራራቸው ብቃት የሌላቸው ትናንሽ አምባገነኖች ናቸው፡፡ ዛሬም የሚስተዋለው ይኸው ነው፡፡ ከወራት በፊት በወያኔዋ ገነት ገ/እግዚአብሔር ምትክ የተተካውና በየተቋሙ እንደ ወንደላጤ ዶርም ሲቀያይር የነበረው ፈንታ ደጀን የተባለው ግለሰብም ከስምንት ዓመት በፊት የነበረበትን የድርጅት ሥልጣን በመጠቀም ከሊቦ ከምከም ወረዳ እስከ ባህዳር ከተማ አስተዳደር የራሱን የዕዝ ሰንሰለት በመዘርጋት ቡድኑን ሲያደራጅና ሲመድብ እንደነበረ የምናስታውሰው ጉዳይ ነው፡፡ ዛሬ ደግሞ ከደቡብ ጎንደር አስተዳዳሪነት ተነስቶ ይህንኑ ተቋም እንዲመራ ስልጣን በያዘበት ወቅት በዚህ በእንደመር የለውጥ ጊዜ ነባር የከተማ አመራሮችን ለማሰልጠን መዘጋጀቱ ለአቀባበል አልያም ለሰንብት ካልሆነ በቀር እንኳን የዞንና የከተማ አመራር ይቅርና እርሱና ግብረአበሮቹ እንደማይቀጥሉ ዕሙን ነው፡፡ ይልቅ ተቋሙን በለውጥ ጎዳና መደመሩ ሳይሻል አይቀርም፡፡