ፀጋዝአብ ለምለም ተስፋይ

የኢኮኖሚክስ መምህርና ጸሓፊ

(ሸክም የበዛበት ትውልድ፡ 2009 እና የምሥራቃዊት ኮከብ፡ 2010 መጻሕፍት አዘጋጅ)

የሰው ልጅ ኹለንተናዊ ልዩነት በኹለንተናዊ ዘርፎች ውስጥ የነበረው፣ ያለውና የሚኖረው ቢኾንም በአንጻሩ በኹለንተናዊ መንገድ አንድ የኾነበትም የተፈጥሮ ሂደት ባለቤት ነው፡፡ ምንም ይኹን ምን – ከየትኛውም አካባቢ ያለ – በብዙ ነገሮች ከብዙዎች የተለየ ቢኾን – በልዩነቱ ወስጥ ፈጽመው የማይታረቁና በተቃርኖ የሚኖሩ ነገሮች ቢኖሩት እንኳ የሰው ልጅ ይጸነሳል፡፡ ያድጋል፡፡ ደግሞም ይሞታል፡፡

ከዚህ የማይቋረጥ ሂደት ውስጥ ባህሪያዊና ጠባያዊ ማንነቱን መሠረት አድርገን ስንመለከት ሂደቶቹ በሰባት ይከፈላሉ፡፡ እነዚህም፡- አንድ ሰው ይጸነሳል፡፡ ይወለዳል፡፡ የመወለዱ ዕድገት ህጻን የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ የህጻንነቱ ዕድገት – ታዳጊ፤ የታዳጊነቱ ዕድገት – ወጣት፤ የወጣትነቱ ዕድገት – ጎልማሳ፤ የጎልማሳነቱ ዕድገት – አረጋዊ በመሰኘት – የአረጋዊነቱ ዕድገት መጨረሻ ሞት /እረፍት/ ተብሎ ይጠራል፡፡

የመፈጠር መታወቂያ – ጽንሰት፡ ህጻንነት ደግሞ የሱ የዕድገት ደረጃ መጨረሻ መወለድ ተቀባይ የሰው ልጅ ደረጃ ነው፡፡ የህጻንነት ባህሪያዊና ጠባያዊ መገለጫዎች በሙሉ ህጻንያዊነት ተብሎ ይጠራል፡፡ ህጻንያዊነት የህጻንነት መለያ፣ መታወቂያ፣ መታያ፣ መንጸባረቂያና መታወሻ ተፈጥሯዊ በሰው ሰራሽ የአኗኗር ዘይቤ የሚደገፍ የዕድገት ሂደት ደረጃ ነው፡፡

ህጻን ልጅ ባለቤት ቢኖረው መልካም ነው፡፡ በተለያዩ አስገዳጅ ምክንያቶች ባይኖረው እንኳ ለጤናማና ለተስተካከለ ዕድገት ሞግዚት ያሻዋል፡፡

ህጻንነት የሚያደርጉትን በውል ይሄ ነው ተብሎ ድምዳሜ የማይሰጥበት – ሞግዚት የሚያሻበት፤ ደመ ነፍሳዊ ጉዞና በስሜት መጓዝ በእጅጉ የሚጎላበት፤ ትርጉም ያለው ሀሳብ፣ ዕሳቤና ርዕዮት ፈጽመው የማይታሰቡበትና ወደሱ ለመቅረብ ረዥም ርቀትና ትጋት የሚያሻው መኾኑ ይታወቃል፡፡

የኛም የሀገራችን የሥልጣን ፖለቲካ እንዲሁ ከሴራ ወደ ሀሳባዊነት፤ ከተዋናይነትና ከአስመሳይነት ወደ ደራሲያዊነትና ግልጽነት፤ ከስሜትና ከፍረጃ ወደ ሥልጡንና የውይይት ባህል ያላደገ፤ በጥቅሉ የህጻንያዊነት ባህሪያትና ጠባያትን በእጅጉ ልዕልና የሰጠና ያነገሠ ስለመኾኑ ያለፈው ታሪካችንም ኾነ የዛሬው አኗኗራችን ዐቢይ ምስክር ነው፡፡

ህጻን በህጻንያዊነቱ የዕድገት ደረጃ የተነሣ በትንሽ ነገር ይከፋል፡፡ በትንሽ ነገር ደግሞ ይደሰታል፡፡ ስሜቱ እጅግ ተለዋዋጭ ነው፡፡ ተደሰተ ብላችሁ እፎይ ከማለታችሁ ዞር ስትሉ ያለቅሳል፡፡ ደግሞ አለቀሰ ስትሎ ይደሰታል፡፡ አነባ ብላችሁ ስትጨነቁ ሲፍለቀለቅ ታገኙታላችሁ፡፡ በርግጥ ህጻን ልጅ ሲወለድ በእጅጉ እያለቀሰ ይችን ዓለም ይቀላቀላል፡፡ የኛም የሥልጣን ፖለቲካ እንዲሁ ነው፡፡

ለውጦቻችን ኹሉ በነውጥና ነውጥን ተከትለው የመጡ በመኾናቸው የብዙዎችን ማንባትና ብዙዎችን ማስነባትን ልማዱ አድርጓል፡፡ ኹለንተናዊ መስዋዕትነትን በህይወት፣ በአካል፣ በጉልበት፣ በእውቀትና በስሜት አስከፍሏል፡፡ ስሜታችን እጅግ ተለዋዋጭ ነው፡፡ ወሬንና ወረኛዊነትን መነሻውና መዳረሻው ያደረገው የሥልጣን ፖለቲካችን በምንሰማው ትንሽ ነገር ወዲያው ይለዋወጣል፡፡ በምናያት ትንሽ ነገር ከፍና ዝቅ ይላል፡፡ ተደረገና ሊደረግ ነው በሚባል ነገር ልባችን ይቆማል፡፡ ጸጉራችን ይቆማል፡፡ አንደበታችን በአደባባይ እስኪሰማ እንጮሃለን አልያም የት ገቡ እስክንባል ድምጻችንን እናጠፋለን፡፡

ህጻናት ሊኾን የማይችል ነገር ይጠይቃሉ፡፡ ሊኾን የሚችል – ነገር ግን ጊዜ የሚወስድን ነገር አኹኑኑ ካልኾነልኝ ይላሉ፡፡ ህጻናት በጣም የሚወዱት – የሚፈልጉትን የሚያደርግላቸውን የሚያሟላላቸውን – ባያደርግ እንኳ እሺ እሺ የሚላቸውን አብዝተው ይቀርባሉ (የሚጎዳቸው እንኳ ቢኾን)፤ ህጻናት በጣም ትኩረት ይሻሉ፤ መደነቅና መታወስን ከኹሉ በላይ አብልጠው ያፈቅራሉ፡፡ ነገሮችን ቶሎ ይረሳሉ በአንጻሩ ቂመኛነትንም ቀስ በቀስ ይለማመዳሉ፡፡ ከወደዱም እስከ ጥግ ድረስ ነው፡፡

የኛም ሀገር የሥልጣን ፖለቲካ እዩኘ እዩኝ፣ አድንቁኝ አድንቁኝ፣ ስሙኝ ብቻ፣ ተከተሉኝ ብቻ፣ እኔ ያልኩት ብቻ፣ ሊኾን የማይችሉ ነገሮች ይደረጋል ተብሎ ቃል ሲገባ እናያለን፡፡ እንሰማለን፡፡ ብዙ ጊዜ የሚወስዱ ነገሮች በአጭር ጊዜ እንደሚሰሩ ሲለፈለፍ እንሰማለን፡፡ ፈጽመው ሊኾኑ የማይችሉ ነገሮች እንደኾኑና ሊኾኑ እንደሚችሉ ተደርገው ይቀርባሉ፡፡

ወላጆች ህጻናት የሚፈልጉትን በማድረግ ወደ ሚፈልጉት መንገድ እንደሚመሩት ኹሉ የሥልጣን ፖለቲካችን ምን መኾን አለበት? ምንስ ያስፈልጋል? ብሎ በምክንያት፣ በዕሳቤና በርዕዮት ላይ መሠረትን፣ መነሻና መዳረሻን ከመጣል ይልቅ ሰው ምን ይፈልጋል? ምን ብል አስደስተዋለሁ? ምን ብልስ አስከፋዋለሁ? በሚል ጥያቄና መልስ ላይ መነሻውና መዳረሻውን በማድረግ ይንቀሳቀሳል፡፡

ህጻናት እጅግ ጥቃቅንና አነስተኛ ጉዳዮች ትኩረታቸውን እንደሚስበው ኹሉ የሥልጣን ፖለቲካችን በእጅጉ በጥቃቅንና አነስተኛ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር፣ በርሱም የተሞላና የተጥለቀለቀ ነው፡፡ ለምን? እንዴት? ስለምን? ፋይዳውስ ምንድነው? በሚሉ ትርጉም ያላቸው ጥያቄዎች በአስተውሎት ቢፈተሸ ጓዳው በእጅጉ ባዶያዊነት ይጎላበታል፡፡

ህጻንያዊነት ከዕውቀት ይልቅ ስሜታዊነት፤ ራስን ከመግዛት – በራስ ከመመራት ይልቅ በኹኔታዎች የሚመራና በሞግዚት እንደሚደገፍ – ወደ ኃላና የዛሬን እንጂ ነገን ማዕከል አድርጎ እንደማይንቀሳቀስ ኹሉ የሥልጣን ፖለቲካችን በታሪክ ትርክቶች ቅኝ የተገዛ፤ ትላንትን ለዛሬ መኖሪያነት ማስከበሪያ መሣሪያ የሚያደርግ ኹኔታዎችን ትርጉም ባለው መንገድ ከመምራት ይልቅ በኹኔታዎች የሚመራ ነው፡፡

ህጻንያዊነት የሚያስጨንቅና ትላልቅ ነገሮችን በተፈጥሯዊ የዕድገት ደረጃው የተነሣ መሸከም አይችልም፡፡ የኛ የሥልጣን ፖለቲካ እንዲሁ እጅግ ከባድ የኾኑ ጥያቄዎችን መጠየቅን፣ ልዩነትን፣ አርቆ ማሰብን፣ ችግሮችን አቅልሎ ማየት እንጂ ውስብስብነቶችንና አድማሳዊ ስፋቱን ከግንዛቤ ውስጥ የከተተ ማሰላሰልና ጥልቅ ጥናትን ይፈልጋል ሲባል ማናነቅና ማጣጣል ግብረ መልሱ ይኾናል፡፡

ወላጆች ህጻናቶቻቸው ቢያጠፉ እንኳ እንደሚሸፍኑላቸውና ጠበቃ ኾነው እንደሚቆሙላቸው ኹሉ ህጻናትም በወላጆቻቸው ይመካሉ፡፡ የኛም ሀገር የሥልጣን ፖለቲካ ለደገፉት፣ ለወደዱትና ለተከተሉት ቢያጠፋ እንኳ ማጥፋቱ የአደባባይ ምሥጢር ቢኾን እንኳ በዛም በዚ ተብሎ የማይገናኝ ነገር አገናኝቶ ለመከላከል መሞከር፤ የራሴ የሚሉትን ሰው አሳልፎ ያለ መስጠት መርህ መከተል፤ በደገፉትና በተከተሉት መመካት – በሚወዱት መኩራትና “እኛ እኮ እንዲህ ነን!”፤ “የኛ ሰው እኮ ነው!”፤ “የነ እንትና – እንትን ነን!” እያሉ ራስን መካብ – በመካብ ውስጥ መሰሌ የሚሉትን መቆለል ሌላውን በተገኘው መንገድ ኹሉ ማቅለል፣ የሌላውን ሥራ ማቃለል፣ አቃቂር ማውጣትና ትኩረት መንፈግ የተለመደ ተግባር ነው፡፡

ህጻንያዊነት ሁለገብነትን የሚያስሞክርና የሚሞክር እንደመኾኑ መጠን የሥልጣን ፖለቲካችን ሁለገቦች – በሁሉ ጉዳይ ካልገባን፣ ካላቦካን፣ ካልጋገርን፣ ካላቀረብን፣ ካላደልንና ካልተመገብን የሚሉ አካላት በግለሰብ፣ በቡድንና በተቋም ደረጃ ይበዙበታል፡፡ በኹሉ ጉዳይ ላይ ያለ ዕውቀታቸው በድፍረት ስለኹሉ ጉዳይ ካልጻፍን፣ ካልተነተን፣ እኛ ያልነው ካልኾነ፣ ካልተናገርን፣ ካልተገኘንና ካልወሰንን የሚሉ አደባባይን አብዝተው የሚወዱ ሰዎች በእጅጉ ይበዙበታል፡፡

የህጻናት ጥል የህጻንያዊነት አንዱ መለያ ነው፡፡ ህጻናት በጣም ትንሽ ነገር ታጣላቸዋለች፣ በመሐከላቸውም ኩርፊያ፣ መሰዳደብ፣ መነጣጠልና መለያየትን እንደምታመጣባቸው ኹሉ የሥልጣን ፖለቲካችን በትናንሽ ልዩነቶች ፓርቲዎች እንደበሶ ሲበጠበጡ፣ ሲከፋፈሉ፣ ሲለያዩ፣ ስም ሲጠፋፉ፣ በዕድሜ እንኳ አረጋውያንና ጎልማሶች ቢኾኑ ሲኮራረፉ – ሰላምታ የማይሰጣጡ፣ የሚሰዳደቡና የተነጣጠሉ ኾነው ማየት የተለመደ ነው፡፡ በአንድ ወቅት እንደነሱ ወዳጅነት የትም አይገኝም የተባለላቸው – በጠላትነት የሚተያዩ ኾነው ተመልክተናል፡፡ አንድ ነን ያሉን ተለያይተው – አንለያይም ያሉን ከመለያየት አልፈው በጠላትነት ሲተያዩ እንደነበር የነበረ ሃቅና ያለ ነባራዊ ኹኔታ ነው፡፡ ታዲያ ከዚህ በላይ ህጻንያዊነት ከወዴት ይገኛል?

አንዳንዶች ደግሞ የህጻንያዊነታችን ማንነታችን እጅግ ጥልቅ በመኾኑ የተነሣ ፉከራችን፣ ማንአለብኝነታችን፣ እልሃችን፣ ፍረጃችን፣ ፉከራችን፣ ፈራጅነታችን፣ ስሜታዊነታችን ጉድ የሚያሰኝ ነው፡፡ በአንጻሩ የአረጋዊነትና የጎልማሳዊነት ተግባርና ውጤት እንዲኖር በእጅጉ እንደሰኩራለን!!! ይህ ካልኾነ ሞተን እንገኛለንና እንገላን እንላለን!!!

የህጻናት ህልምና ቅዠት ድንበር የለውምና የህጻንያዊነትም አንዱ አካልና መለያም እርሱ ነውና አይፈረድብንም፡፡ ከ200 ዓመታት በላይ ተቋማዊነት የገነቡ ሀገራት የፖለቲካ ኹኔታ በሀገራችን እንዲኖር መወትወታችን፤ ምክንያታዊና ጠያቂያዊነትን ባህል ሳናደርግ የሱን ውጤት መጠበቃችን፤ አስመሳይነትና መሰሪነትን ባህል ባደረግንበት ሴረኛነትን የጀግንነት መተርጎሚያ ብለን ባስቀመጥንበት ኹኔታ፤ ምቹ ኹለንተናዊ ኹኔታዎች ሳይኖሩን የምቹ ኹኔታ ምርት ከሌለ ብለን መሟገታችን፤ ግትሮችና ትዕቢተኞች ኾነን ሳለ ቅንነትና ሀሳባዊነትን ማንነት መመኘታችን፤ ወረኞች – “ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው” ብለን የምንኮራ ኾነን ሳለን የዕሳቢያዊነትን ዘር መሻታችን፤ ጠላትነትን የኑሮና የአኗኗር መሰረት አድርገን የምንኖር ሳለን – ከፋፋዮችና የመንፈስ አንድነት የሌለን ኾነን በህብረት፣ በአንድነትና በመንፈስ መግባባት የሚገኝን ፍሬን ሳንዘራ፣ ሳንተክል፣ ሳንከባከብና ጊዜውን ሳንጠብቅ ፍሬውን ለመብላት መስገብገባችን – – – ያው ህጻን ስለኾንና ስለኾኑ ነውና አትፍረዱብን! አትፍረዱባቸው!!!

ቢያንስ በዓለም ታሪክ እንደነበረንና እንዳለን ቦታ፤ እንደብዛታችን ከምዕተ ዓመታት በፊት ከህጻንያዊነት ወደ ታዳጊያዊነት፤ ከታዳጊያዊነት ወደ ወጣትነት፤ ከወጣትነት ወደ ጎልማሳዊነት መሸጋገር ይኖርብን ነበር፡፡ እጅግ በጣም ኃላ ቀረን እንኳ ቢባል በቀጥተኛ ቅኝ ያልተገዛን ነንና ቢያንስ ቢያንስ የሥልጣን ፖለቲካ ባህላችን ፈቅ ብሎ ከህጻንያዊነት ወደ ታዳጊያዊነት ከፍ ማለት ነበረበት ነገር ግን የህጻንያዊነት ባህሪያትና ጠባያት በእጅጉ ሠልጥኖብናል፡፡ ሞልቶናል፡፡ አጥለቅልቆናል፡፡ ግን ለምን? ብዙ እልፍ አላፍ የውስጥና የውጭ ምክንያቶች ይኖራሉ፡፡

ስለኾነም በሀገራችን እውነተኛ፣ ዘላቂና አስተማማኝ መሠረታዊ ለውጥ በኹለንተናዊ ዘርፍ ለኹለንተናዊ ተጠቃሚነት በኹለንተናዊ መንገድ ይመጣ ዘንድ ከህጻንያዊነት ወደ ታዳጊያዊነት፤ ከታዳጊያዊነት ወደ ወጣትያዊነት በፍጥነት መሻገር ይኖርብናል፡፡ ብዙዎቻችን ህጻንያዊነት ሠልጥኖብናል፡፡ የህጻንነት ባህሪያትና ጠባያት በእጅጉ በእምነታችን (በአስተሳሰብና አመለካከታችን)፣ በእውቀታችን (በስልትና ስትራቴጂያችን) እና በተግባር (በድርጊታችን) ሠልጥኗል፡፡ እንዲሁም በአኗኗራችን ይታያልና ይህ መቀየርና መለወጥ አለበት፡፡

የህጻንያዊነት ባህሪያትና ጠባያቶቻችን በታዳጊያዊና በወጣትያዊነት ባህሪያትና ጠባያት መተካትና መለወጥ ይኖርባቸዋል፡፡ አለበለዚያ መሠረታዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ይመጣል ብሎ መደስኮር የአክሱም ሃውልት ከዘመን ብዛት ትግርኛ ይናገራል ብሎ መጠበቅ ይኾናል፡፡ ፈጣሪ ሀገራችን ነጻ ፍቃድን የኹሉ ነገር ማዕከል ወደ ሚያደርግ የዕሳቤ ሂደት ትገባ ዘንድ ይርዳን!

ቸር እንሰንብት!