አቶ ኪያ ፀጋዬ እና አቶ ውብሸት ሙላት
አጭር የምስል መግለጫ አቶ ኪያ ፀጋዬ እና አቶ ውብሸት ሙላት

ከሃያ ሦስት ዓመታት በፊት የአህገሪቱ ላዕላይ ህግ ሆኖ የፀደቀው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንግሥት አዋጅ በውስጡ 106 አናቅፅትን ይዟል።

ከመነሻውን አንስቶ በሕገ-መንግሥቱ ዙሪያ ተመሳሳይ ህዝባዊ አስተያየት ኖሮ ያውቃል ማለት ቢያዳግትም በ39ኛው አንቀፅ የሰፈሩትን “የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብቶች” ያህል አቋምን የከፋፈለ እና ጭቅጭቅ ያስነሳ የሕገ-መንግሥቱ አካል መኖሩ ያጠራጥራል።

ዋነኛው የውዝግብ አስኳል በአንቀፁ ከተካተቱ አምስት መብቶች ቀዳሚ ሆኖ የተቀመጠ ሲሆን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን ገደብ አልባ መብት እንደተጎናፀፉ፤ ይህ መብታቸው ራሳቸውን ከፌዴሬሽኑ ገንጠለው ነፃ አገር እስከማድረግ የሚደርስ መሆኑን ያትታል።

በአንድ በኩል አንቀፁን የአገር የግዛት አንድነት ላይ ፈተናን የሚደቅን፣ ፌዴሬሽኑን ከማፅናት ይልቅ መበታተንን የሚጋብዝ እምቅ አደጋዎችን ያቀፈ ጦሰኛ ሃሳብ የተካተተበት ነው እያሉ የሚነቅፉት አሉ።

እኛ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝቦች. . .?

ጥያቄን ያዘለው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን

በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያን ብዝሃነት በአግባቡ ለማስተናገድ እንዲሁም መከባበር የሰፈነበትን አብሮነት ለማጎልመስ በአገሪቱ ውስጥ ላሉ ብሔሮች እና ሕዝቦች ራሳቸውን እስከመገንጠል የሚደርስ ዋስትና መስጠት ብልህነት ነው ሲሉ አንቀፅ 39ን የሚያወድሱ ሞልተዋል።

በዚሁ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የሚያጠነጥን “አንቀፅ 39” የተሰኘ መፅሐፍን ለህትመት ላበቁት ለሕግ ባለሙያው አቶ ውብሸት ሙላት፤ በአንቀፁ ዙርያ የሚሾረው ንትርክ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ መሻገሩ ምናልባትም ሕዝባዊ ውሳኔን የሚፈልግ የቤት ሥራ መኖሩን ጠቋሚ ነው።

“ሕዝብ እንዲስማማበት ማድረግ የተሻለ አማራጭ ነበር” ይላሉ አቶ ውብሸት ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ። “ሲጀመርም ሕገ-መንግሥቱን ያረቀቁት እና በኋላም ያፀደቁት አካላት መካከል ያን ያህል መከፋፈል ከነበረ ይሻል የነበረው ወደ ሕዝቡ ማምጣት እና እንዲወስንበት ማድረግ ነበር። በመካከሉም ሕገ-መንግሥቱ ከፀደቀ በኋላም ይሄንን ማድረግ ይቻል ነበር።”

ለመገንጠል ምን ያስፈልጋል?

በቅርቡ በሶማሌ ክልል መዲና ጂግጂጋ ግጭት ተቀስቅሶ በርካቶች ከሞቱ በኋላና ለቀውሱ መባባስ አንዱ ምክንያት የክልሉ የቀድሞ ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ መሃመድ ኦማር አንቀፅ 39ን ተጠቅመው ክልሉን ከኢትዮጵያ ለመገንጠል መሞከራቸው ነው ተብሎ ከተዘገበ በኋላ አንቀፁ በሚያጎናፅፋቸው መብቶች ዙርያ መጠነኛ ውይይት በማኅበራዊ ሚዲያ ሲንሸራሸር ተስተውሏል።

በውይይቶቹ መገንጠል ቀላል እና ቅርብ መስሎ መታየቱ ስጋት የፈጠረባቸው ኢትዮጵያዊያን እንዳሉ መገንዘብ ይቻላል።

ሕገ-መንግሥቱ የመገንጠል መብትን ያለምንም ገደብ ያጎናፅፋል የሚሉት አቶ ውብሸት ሒደቱ የሚያልፋቸው ሥነ-ሥርዓቶች መኖራቸውን ግን ጨምረው ይገልፃሉ።

“ሕገ-መንግሥቱ ተተኪ ጠቅላይ ሚኒስትርን በሚመለከት ክፍተት አለበት” ውብሸት ሙላት

የመገንጠል ጥያቄ ተቀባይነት እንዲኖረው በመጀመሪያ በብሔር፣ በብሔረሰቡ ወይንም በሕዝቡ የህግ አውጭ ምክር ቤት ሁለት ሦስተኛ ድጋፍ ማግኘት መቻል አለበት።

የምክር ቤቱ ውሳኔ ከተላለፈ በኋላ ባሉ ሦስት ዓመታት ውስጥ የፌዴራል መንግሥት ሕዝበ-ውሳኔን የማዘጋጀት ኅላፊነት የሚኖርበት ሲሆን፤ በሕዝበ-ውሳኔው ከጠቅላላው ሕዝብ ከግማሽ በላዩ የመገንጠል ሃሳቡን የሚደግፍ ሆኖ ከተገኘ የፌዴራል መንግሥት ስልጣኑን ያስረክባል፣ የሃብት ክፍፍልም ይደረጋል።

የሕግ ባለሙያ እና የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት አቶ ኪያ ፀጋዬ “ሰፊ እና ለትርጉም አሻሚ” ነው የሚሉት አንቀፅ 39 በቁጥር አራት ከዘረዘራቸው አምስት ሒደቶች ባሻገር ውስብስብ የሆነውን የመገንጠል ክንውን የሚያስፈፁሙ ዝርዝር ህግጋት ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ያለመውጣታቸውን ይገልፃሉ።

“በእርግጥ ሕጉ በሚረቀቅበት እና በሚፀድቅበት ጊዜ የአርቃቂ ጉባዔው ይሄንን አንቀፅ በተመለከተ የነበረው ትክክለኛ ዓላማ ምንድን ነው? የሚለውን ለማወቅ በወቅቱ የነበረውን ቃለ-ጉባዔ መመልከት ያሻል” ሲሉ ያብራራሉ አቶ ኪያ “ሆኖም የመገንጠል መብት በወቅቱ የነበረውን የፖለቲካ ግለት ለማብረድ እና ጥርጣሬ ለነበራቸው የተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖች ዋስትና ለመስጠት ታስቦ የተካተተ ይመስለኛል።”

አቶ ኪያ እንደሚሉት በመገንጠል አፈፃፀም ዙርያ ዘርዘር ያሉ ሕግጋት ያልወጣው ዋነኛው አስፈላጊነቱ ፖለቲካ ዋስትና ለመስጠት ስለነበርና ይሄንንም ሕገ-መንግሥቱ ውስጥ አንቀፁን በማካተት ማሳካት በመቻሉ ነው።

FDRE Constitution

የአፈፃፀም ፈተናዎች

የሕግ እና የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ኪያ ሕዝባዊ አመኔታ እና ቅቡልነት ያለው ዲሞክራሲ ማስፈን እስካልተቻለ ድረስ የአንድ ክልል ሕግ አውጪ ምክር ቤት ሕዝቡን በትክክል ይወክላል ማለት ይከብዳል ይላሉ።

“የክልል ፓርላማዎችን ተዓማኒ ባለሆነ ምርጫ ተመሳሳይ የፖለቲካ ወገንተኝነት ባላቸው ሰዎች መሙላት ይቻላል። እነዚህ ሰዎች በትክክል [መገንጠል ይፈልጋል የተባለውን] ብሔር ወይንም ሕዝብ ፍላጎቶች ይወክላሉ ወይ? የሚለው ላይ ጥያቄ ይኖረኛል።”

የሕዝብ ውሳኔውም ቢሆን በአብላጫ ድምፅ ወይንም ሃምሳ በመቶ ሲደመር አንድ መሆኑ መገንጠልን በሚያህል ትልቅ ውሳኔ ላይ ተገቢ እንደማይመስላቸው የሚገልፁት ደግሞ አቶ ውብሸት ናቸው።

“አንድ መገንጠል የፈለገ ብሔር አንድ ሚሊዮን ሕዝብ አለው እንበል። ከእነዚህ መካከል ሃያ በመቶ የሚሆኑት ዕድሜያቸው ባለመድረሱ እና በተለያዩ ምክንያቶች በሕዝበ-ውሳኔው ሳይሳተፉ ቢቀሩ፤ ከተሳተፉት ደግሞ ሃምሳ በመቶ እና አንድ የሚሆኑቱ መገንጠልን ወይንም መቆየትን ቢደግፉ፤ ይህ ውሳኔ ከጠቅላላው ሕዝብ የአርባ በመቶውን ብቻ ነው የሚወክለው ማለት ነው” ይላሉ።

ሕገ-መንግሥቱ ከመፅደቁ በፊት በነበረው የሽግግር ሰነድ (ቻርተር) ላይ የመገንጠል መብትን ከመተገበር የሚያቅቡ ቅድመ ሁኔታዎች እንደነበሩ ያነሳሉ አቶ ውብሸት።

“የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት አንዱ ነው”

እንደዚህ ዓይነት ቅድመ ሁኔታዎች በሕገ-መንግሥቱ ውስጥ ኖረው ቢሆን፤ እንዲሁም ሕዝበ-ውሳኔዎች ለስሜታዊነት ተጋላጭ የመሆን ዕድል እንዳላችው በዓለም ዙርያ በተደጋጋሚ በመታየቱም የማሰላሰያ ጊዜ ቢኖርና ዳግመኛ የሚከናወኑበት አማራጭ ቢኖር እንደሚመርጡም ጨምረው ይገልፃሉ።

አሁን ባለው እውነታ ከመገንጠል ጋር ተያይዘው ከሚመጡ የራስ ምታቶች እንደኛው የንብረት ክፍፍል ነው።

በምትገነጠለው ግዛትና በቀሪው ፌዴሬሽን መካከል የሚኖረውን የንብረት ክፍፍል የሚያብራሩ ሕግጋት ባለመኖራቸው “ሁኔታው የሚከናወነው በዓለም አቀፍ ህግ መሰረት ነው? ግልፅ አይደለም።”

አቶ ኪያ ሕገ-መንግሥቱ የመገንጠልን መብት የሚሰጠው ለብሔሮች፣ ለብሔረሰቦች እና ለሕዝቦች እንጂ ለክልሎች ባለመሆኑ በክልሎቹ የሚኖሩ ሌሎች ብሔሮች በክልል ምክር ቤቶች ውስጥ መቀመጫ ያላቸው ሌሎች ብሔሮች ጉዳይ ሌላ ጥልፍልፍን ይፈጥራል ባይ ናቸው።

የሕግ ባለሙያው አቶ ውብሸት ግን በኢትዮጵያ ክልላዊ አወቃቀር መሰረት ክልሎች የብሔሮች ናቸው ይላሉ። “የአማራ፣ የኦሮሚያ፣ የትግራይ፣ የሶማሌ ወዘተ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ነው የሚባሉት። ክልሎቹ የብሔሮቹ ናቸው ማለት ነው።”

ለመገንጠል የሻተው ብሔር ወይንም ሕዝብ በሕዝበ ውሳኔ አማካይነት ድምፁን ካሰማ በኋላ፤ የሕዝበ-ውሳኔው ውጤት ላይ ቅሬታ ቢኖረው አቤቱታውን የሚያሰማው “ቅሬታ ለፈጠረበት ለፌዴራላዊው መንግሥት የምርጫ ቦርድ ነው። ይሄም ራሱ ሌላ እንቆቅልሽ ነው” ይላሉ አቶ ውብሸት። “ምርጫውንም የሚያከናውነው የኢትዮጵያው ምርጫ ቦርድ ነው።”

የአንቀፅ 39 መፃዒ ቀናት

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ስልጣን ላይ ከወጡበት ጊዜ አንስቶ በርካታ የአንቀፅ 39 ነቃፊዎች፤ በአንቀፁ የተካተተውን የመገንጠል ሃሳብ እንደሚፍቁላቸው ተስፋ የሰነቁ ይመስላል።

በተለያዩ ትዕይንተ-ሕዝቦች ላይ በአንቀፁ ላይ ያነጣጠሩ የትችት መፈክሮች ተስተውለዋል።

ይሁንና አንቀፁን መፋቅም ሆነ ለማስተካከል መሞከር አሁን ካለው የአገሪቱ የፖለቲካ እውነታ አንፃር የመሆን ዕድሉ ዝቅተኛ ነው ይላሉ አቶ ውብሸት።

“ከደርግ ጊዜ አንስቶ ለሕግ ያለን አመኔታ እየወረደ መጥቷል፤ አሁንም በአንቀፅ 39ም ሆነ እንደ ሠንደቅ አላማ ባሉ አጨቃጫቂ ጉዳዮች የሚነሳው ንትርክ የእልህ ጉዳይ የሆነ ይመስለኛል” ይላሉ አቶ ውብሸት።

“በመሆኑም ኅብረተሰቡም ሆነ የፖለቲካ ልኂቃን ሰክን ብለው በዚህ ጉዳይ ላይ ለመወያየት የሚችሉበት ጊዜ ላይ የደረስን አይመለኝም።”