ዴሞክራሲ ብቻ!
***
ብርሃኑ አበጋዝ (ዶ/ር)
***
በኢትዮጵያችን ዴሞክራሲን የግድ የሚያደርገውም የዴሞክራሲ (የዴሞክራሲ ሽግግር) አንቅፋቱም ዘውጌ ብሔርተኝነት ነው፡፡ ሆኖም የኢትዮጵያ መድኀን ዴሞክራሲ ነውና መንገዱ አስቸጋሪም ቢሆን በዚኸው አቅጣጫ ከመግፋት ውጪ ሌላ አማራጭ የለም፡፡
ሁሉም እንደሚያውቀው በአገራችን ላለፉት ከአርባ በላይ ዓመታት ሲቀነቀን የኖረው የዘውግ ፖለቲካ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ ማዕከላዊ ቦታ ከመያዙም በላይ፣ ሌላ የፖለቲካ ትርክት የጠፋ ይመስል ሁሉም ነገር ዘውግ ተኮር ሊሆን በቅቷል፡፡ ዘውገኝነት በፖለቲካው አካባቢ ሳይወሰን የግል ዘርፉንም በክሎታል፡፡ የሠራተኛ ቅጥሩ፣ የሸር ካምፓኒ ምሥረታው፣ የኢንቨስትመንት ቦታ መረጣው ወዘተ. ሁሉ ዘውግ ተኮር ሆኗል፡፡
ይህን ነባራዊ ሐቅ ሊያስተናግድና በሒደት መልክ እንዲይዝ ሊያደርግ የሚችለው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ብቻ ነው፡፡ የኢዴሞክራሲ አማራጭ (አማራጭ ከተባለ) ወደ ምስቀልቅል ብቻ ነው ሊወስደን የሚችለው፡፡ ከዚህ በኋላ በልማታዊ መንግሥት ወይም በሌላ ‹ኢ-ሊብራል› አማራጭ እያሳበቡ የኢኮኖሚ ልማት እስኪረጋገጥ ድረስ በኢዴሞክራሲያዊ መንገድ ማዝገም ይቻላል ማለት ፈጽሞ ጊዜው አልፎበታል፡፡ “መደመር” የሚለው የነ ዶ/ር ዐቢይ መርህ ከዚህ የተለየ ስለመሆን አለመሆኑ ወደፊት የሚታይ ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያዊያን እየወደቅንም እየተነሳንም፣ እያጠፋንም እያለማንም ቢሆን ዴሞክራሲን ብቻ ነው መለማመድ ያለብን፡፡
ወጣቱ፣ ዘውጌ ብሔርተኝነትና ዴሞክራሲ
***
በግልጽ እንደሚታየው የለውጡ እንቅስቃሴ ሞተሩ ወጣቱ ነው፡፡ ይኽ በገጠርም በከተማም የሚኖር ወጣት የኅብረተሰብ ክፍል ደግሞ 70 ከመቶ የኅብረተሰብ ክፍል ድርሻ አለው፡፡ ወጣቱ ነገሮች ቢመቻቹለት በአጭር ጊዜ ወደ መካከለኛ መደብ ሊደርስ የሚችል ኀይል ነው፡፡ ነገሮች ቢመቻቹለት፣ ትክክለኛ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ቢቀየስለት፣ ትክክለኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ቢዘረጋለት በአጭር ጊዜ ውስጥ መካከለኛ ገቢ ሊኖረው የሚችል፣ የዴሞክራሲም ጠበቃ የሚሆን የኅብረተሰብ ነው፡፡ የሚጠይቀውም ትክክለኛ ጥያቄ ነው፡፡ በገጠር ያለው አብዛኛው መሬት ይፈልጋል፡፡ በከተማ የሚኖረው ሥራ ይፈልጋል፤ የራሱን ሥራ ፈጥሮ ለመሥራትም መነሻ ካፒታልና የክህሎት ድጋፍ ያስፈልገዋል፡፡
ችግሩ፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ብዙ ሲወራለት ቢከርምም በሚሊዮን የሚቆጠረውን ሥራ አጥ ወጣት የሚሸከም (‹አብዞርብ› የሚያደርግ) አቅም የለውም፡፡ ወጣቱ የለውጡ ሞተር እኔ ነኝ ብሎ አምኗል፤ ነውም፡፡ ስለሆነም ከዚህ ለውጥ የሚጠብቀው በጣም በርካታ ነገር አለ፡፡ የሥራ ዕድል እንደሚመቻችለት ያምናል፤ የራሱን ሥራ ፈጥሮ መሥራት የሚፈልገውም የካፒታልና ልዩ ልዩ ግብዓት በአገዛዙ በኩል እንደሚያገኝ ከፍ ያለ ተስፋ ሰንቋል፡፡ ሰብአዊ መብቱና ክብሩ እንዲጠበቅለትም ይፈልጋል፡፡ ትልቁ መከራ፣ አገዛዙ የወጣቱን ጥያቄ ሊያሟላ በሚችልበት ቁመና ላይ አለመገኘቱ ነው፡፡ በአንድ በኩል፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አሁን ባለው ይዞታው ወጣቶቻችን የሚገምቱትንና የሚጠብቁትን ነገር ሊያቀርብላቸው እንደማይችል በጣም ግልጽ ነው፡፡ እየተንገዳገደ ያለ ኢኮኖሚ ነውና፡፡ በኹለተኛ ደረጃ፣ የሰብአዊ መብትና ዴሞክራሲንም በሚመለከት ብዙ ያልለየላቸው ነገሮች እየታዩ ስለሆነ የወጣቱ ፍላጎት በቀላሉ የሚሟላ አይመስልም፡፡ የዶ/ር ዐቢይ አገዛዝ በይቅርታ ስም አሁንም ሕዝብ ያማረሩና የሕዝብና የአገር ሀብት የዘረፉ ግፈኞችን አቅፎና ደግፎ እንደያዘ ነው፡፡ እነዚህ በአገርና ሕዝብ ሀብት ላይ መጠነ-ሰፊ ዘረፋ የፈጸሙና ሕዝብ ያስለቀሱ ሰዎች እያሉ ደግሞ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ይገነባል ማለት ዘበት ነው፡፡ በዚህ ሁሉ መሃል ደግሞ ከፍ ሲል የተጠቀሰው ሌቦችም ቢሆኑ የእኔ ወገን እስከሆኑ ድረስ አትንኳቸው የሚል ጽንፍ የወጣ ዘውጌ ብሔርተኝነት አለ፡፡
የአገራችን ህልውና ተጠብቆ እንዲቀጥል፣ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን እና ዴሞክራሲና ልማት እንዲረጋገጥ ከአገዛዙም ከእኛ ከዜጎችም ብዙ ነገር ይጠበቃል፡፡ ዶ/ር ዐቢይ የሚመሩት አገዛዝ ወገቡን አስሮ በኢኮኖሚው መስክ ያሉትን ማነቆዎች በማስወገድ ኢኮኖሚው እንዲያድግና ወጣቱን የሚሸከም እንዲሆን ሌት ተቀን መሥራት መቻል አለበት፡፡ ይህ በሚሊዮን የሚቆጠር ሥራ አጥ ወጣት ሥራ እስካላገኘ ድረስ የአገራችን ሰላምና መረጋጋት አደጋ ላይ እንደሆነ ይቀጥላል፡፡ በየአካባቢው በቀላሉ ወደ አመጽ የሚያመራውና ሰብአዊ ፍጡርን ዘቅዝቆ እስከመስቀል የደረሰው ሥራ አጥ ወጣት ነገ ምን ሊያደርግ እንደሚችል መገመት አይከብድም፡፡
ኢኮኖሚውን ከማሳደግ ጎን ለጎን አገዛዙ ዓይነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነብበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠርና ራሱ ገዥው ግንባርም ለዴሞክራሲ የሚገዛ መሆን ይኖርበታል፡፡ አገዛዙ ብቻ ሳይሆን ሁሉም የአገራችን የፖለቲካ ኀይሎች ለኢትዮጵያ ህልውና መጠበቅ ከዴሞክራሲ ውጪ አማራጭ የለም በሚለው መሠረታዊ አጀንዳ ላይ መግባባት መቻል አለባቸው፡፡ ከዚህ በኋላ አንድ ቡድን በየትኛውም ስም ተቀባብቶ በብቸኝነት ኢትዮጵያን መምራት እንደማይችል፣ የተራ ጥያቄም ከዴሞክራሲ ጋር የተጣላና አገራችን ወደመቀመቅ የሚወስድ አደገኛ አካሄድ መሆኑን በሚገባ መቀበል ያስፈልጋል፡፡
እኛም ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ሁሉንም ነገር ከአገዛዙ ሳንጠብቅ የሰላም ዘብ እና የዴሞክራሲ አርበኞች መሆን ይኖርብናል፡፡ ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያ ህልውና ሊጠበቅ የሚችለው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሲገነባ ብቻ መሆኑን ከልብ መቀበል፣ በሕዝብ መሀከል ጥላቻና ግጭት በሚፈጥሩ ቅስቀሳቀዎችና ድርጊቶች አለመሳተፍ እና የመፍትሔው አካል መሆን ይኖርብናል፡፡ በተለይ የግሉ ዘርፍ ደግሞ ትልቅ ኀላፊነት አለበት፡፡ ወጣቱ ወደ አመጽ መንገድ ሲሄድ በየጊዜው ተጎጅ የሚሆነው፣ ንብረቱ የሚጋየውና የሚዘረፈው የእሱ ነውና፡፡ የግሉ ዘርፍ ሊኖርና ሊያድግ የሚችለው ሰላምና መረጋጋት ሲሰፍን እና ዴሞክራሲ ሲኖር ነው፡፡ ስለሆነም በግሉ ዘርፍ የተሰማሩ ኢትዮጵያዊያን ኢኮኖሚው ስለሚያድግበት እና ሥራ አጥነት ስለሚቀንስበት ሁኔታ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡