15 August 2018
የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች ጥቃቶችን አወገዙ
በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሐረርጌ ዞን በማዩ ሙሉኬ ወረዳ የሶማሌ ልዩ የፖሊስ ኃይል በትንሹ 40 ያህል የኦሮሞ ተወላጆችን መግደሉ ተገለጸ፡፡ ከ40 በላይ የሚሆኑም ሰዎች ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ተጠቁሟል፡፡
የኦሮሚያ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) በወረዳው በሶማሌ ልዩ ፖሊስ በተፈጸመ ጥቃት 40 ሰዎች መገደላቸውን ገልጸው፣ ድርጊቱ የተፈጸመው በቅርቡ ከሥልጣናቸው በፌዴራል መንግሥት እንደተወገዱ በሚናገሩ ሰዎች ትዕዛዝ ነው ብለዋል፡፡
በሶማሌ ልዩ ኃይል አባላት የሁለቱን ክልሎች አዋሳኝ በመጣስና ከበድ ባሉ መሣሪያዎች በመታገዝ ጥቃቱን መፈጸማቸውን አስታውቀዋል፡፡
በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ሐምሌ 28 እና 29 ቀን 2010 ዓ.ም. በተፈጸመው ግድያ፣ ዘረፋ፣ የአብያተ ክርስቲያናት ቃጠሎና ከቀዬ መፈናቀል ምክንያት፣ የአገር መከላከያ ሠራዊት ወደ ክልሉ በመግባቱ የሶማሌ ልዩ ፖሊስ ኃይል ማፈንገጡ ሲነገር እንደነበር ይታወሳል፡፡
በመሆኑም የመከላከያ ሠራዊቱ ጅግጅጋና ሌሎች ከተሞች መግባቱንና ቀድሞ የነበሩ የክልሉ አመራሮች ከሥልጣን በመውረዳቸው ቅር የተሰኘው ልዩ የፖሊስ ኃይል፣ ወደ ኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ማዩ ሙሉኬ ሄዶ ጥቃት ማድረሱን የተጎጂ ቤተሰቦች ገልጸዋል፡፡
ነሐሴ 5 እና 6 ቀን 2010 ዓ.ም. ቤት ለቤት በመግባት በሕፃናት፣ በአዛውንቶች፣ በወንዶችና በሴቶች ላይ ጥቃቱን መፈጸሙን ተጎጂዎች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ልዩ የፖሊስ ኃይሉ ድርጊቱን እንዲፈጽም ያደረጉት ከሥልጣን እንዲወርዱ የተደረጉ አመራሮች መሆናቸውን፣ በተፈጠረው አደጋም 40 ያህል ግለሰቦች ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገልጿል፡፡ መንግሥት ልዩ ክትትልና ጥበቃ ካላደረገላቸው በስተቀር አሁንም ሥጋት ውስጥ መሆናቸውን ነዋሪዎቹ ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል በኦሮሚያ ክልል ሻሸመኔ ከተማ እሑድ ነሐሴ 6 ቀን 2010 ዓ.ም. በአንድ ግለሰብ ላይ አሰቃቂ ግድያ መፈጸሙ ይታወሳል፡፡
ግለሰቡን ለመገደል የበቃው ‹‹ቦምብ ይዟል›› የሚል ያልተጣራ መረጃ በመስማቱ ቢሆንም፣ ሟች ግን ምንም ነገር እንዳልያዘ ፖሊስ አስታውቋል፡፡ የተለያዩ አስተያየት ሰጪዎች እንደሚናገሩት፣ ግለሰቡ ምንም ይሁን ምንም የአካባቢው ፖሊሶች ወይም ፀጥታ አስከባሪዎች ሊደርሱለት ይገባ ነበር፡፡ ቦምብ ይዞ ቢገኝ እንኳን ለሕግ አካላት አሳልፎ መስጠት እንጂ፣ የደቦ ፍርድ ተገቢ እንዳልሆነና መወገዝ ያለበት መሆኑን በርካቶች እየገለጹ ነው፡፡ መንግሥት የድርጊቱን ፈጻሚዎች በቁጥጥር ሥር አውሎ፣ ሳይውል ሳያድር ዕርምጃ ወስዶ ለኅብረተሰቡ መግለጽ እንዳለበትም እያሳሰቡ ነው፡፡ ድርጊቱ በአስቸኳይ አስተማሪ ዕርምጃ ካልተወሰደበት ጅማሮው አደገኛ መሆኑን፣ እርስ በርስ የሚያጋጭና ውጤቱም የከፋ ሆኖ እንደሚቀጥል ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
ድርጊቱን በሚመለከት በቀጥታ ተገድሎ ስለተሰቀለው ግለሰብ ባይሆንም በዕለቱ ስለተፈጸመው ድርጊት የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ዓለማየሁ እጅጉ በሰጡት ማብራሪያ፣ በዕለቱ ለኦኤምኤን ዋና ዳይሬክተር ለአቶ ጃዋር መሐመድ አቀባበል ለማድረግ በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎች በመውጣታቸው፣ በተፈጠረው መገፋፋትና መረጋገጥ ሦስት ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል፡፡ በንብረት ላይም ጉዳት ደርሷል፡፡ ቦምብ ጭኗል በሚል የተሳሳተ መረጃም አንድ የከተማው የፀጥታና አስተዳደር ቢሮ ተሽከርካሪ መቃጠሉን ገልጸዋል፡፡ ፖሊስ ባደረገው ማጣራት ግን ቦምብ ስለመኖሩ የተገኘ ፍንጭ እንደሌለ አስረድተዋል፡፡
የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) ለተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን እንደተናገሩት፣ ከግለሰቡ ግድያ ጋር በተገናኘ የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው ነው፡፡
በሌላ በኩል በተለያዩ ሥፍራዎች ካለፉት ሦስት ወራት ወዲህ እየታየ ያለውን ሰላምና ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ የሚያደፈርሱ ችግሮች በሶማሌና በአንዳንድ የኦሮሚያ አካባቢዎች እየተከሰቱ በመሆናቸው፣ መንግሥት በአስቸኳይ ማስቆም እንዳለበት ሰባት የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች አሳሰቡ፡፡
በተለይ በሶማሌ ክልል ሐምሌ 28 እና 29 ቀን 2010 ዓ.ም. የተፈጸመውንና በማንኛውም ቤተ እምነት ተቀባይነት የሌለውን የግድያ፣ የማቃጠል፣ በአካል ላይ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት ማድረስ፣ ዘረፋና ሌሎች ድርጊቶች መፈጸም፣ ኢትዮጵያዊነትን ካለመግለጹም በተጨማሪ ፍፁም አፀያፊና አሳፋሪ በመሆናቸው የተቋማቱ መሪዎች አውግዘዋል፡፡
የሃይማኖት ተቋማቱ የበላይ ጠባቂዎች በሰጡት መግለጫ እንዳሳወቁት፣ በሶማሌ ክልል በሚኖሩ የሌላ አካባቢ ተወላጆች ላይ የተፈጸመው ድርጊት አስነዋሪና ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሊያወግዙት የሚገባ ነው፡፡ ‹‹ሳይቃጠል በቅጠል›› እንዲሉ መንግሥት ሳይውል ሳያድር፣ በድርጊቱ ፈጻሚዎች ላይ የማያዳግምና አስተማሪ ዕርምጃ መውሰድ አለበት ብለዋል፡፡
ለዘመናት ተከባብሮና ተፈቃቅሮ በኖረው ሕዝብ መካከል ጣልቃ በመግባት፣ ‹‹በሃይማኖት ምክንያት የተነሳ ግጭት መብረጃ የለውም›› የሚል የተሳሳተና ሰይጣናዊ እሳቤ ይዞ፣ የሃይማኖት ተቋማትን ማቃጠል የተሳሳተ ግንዛቤና የኢትዮጵያውያን ተግባር ባለመሆኑ ሁሉም ማኅበረሰብ ሊያወግዘው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
መንግሥት የሕዝቡን ሰላም ለማስከበር፣ አንድነቱን ለማጠናከርና ልማቱን ለማፋጠን ጠንካራ ዕርምጃ መውሰድ እንዳለበትም አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
ከሶማሌ ክልል ለተፈናቀሉና ቤት ንብረታቸው ለተቃጠለባቸው ወገኖች የሃይማኖት ጉባዔው መርዳት ስለሚፈልግ፣ መንግሥት ተፈናቃዮቹን ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡ በሃይማኖት ሰበብ ግጭት ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ ማናቸውም አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ፣ ወጣቶችም ከስሜታዊነት ወጥተው ቆም ብለው እንዲያስቡ የተቋማቱ መሪዎች ጠይቀዋል፡፡
በሶማሌ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች አሁንም እንቅስቃሴዎች እንዳሉ የጠቆሙት የሃይማኖት መሪዎች፣ መንግሥት የተጠናከረ ጥበቃ ከማድረግ በተጨማሪ በልዩ ክትትል ችግሩ ከቁጥጥር ውጪ ሳይሆን ሊቆጣጠር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡