15 August 2018

ዳዊት እንደሻው

​​​​​የኦነግና የኦብነግ ልዑካን አዲስ አበባ ገብተዋል

በመንግሥት በተደረገላቸው ግብዣ የአፋር ነፃ አውጭ ግንባር መሥራች የሆኑት ሡልጣን ሐንፍሬ ዓሊሚራህና የአፋር ሕዝብ ፓርቲ አመራሮች አዲስ አበባ ገቡ፡፡

ሡልጣን ዓሊሚራህ በሽግግር መንግሥት ጊዜ የክልሉ አስተዳዳሪ እንደነበሩ ይታወሳል፡፡ ሡልጣኑ ማክሰኞ ነሐሴ 8 ቀን 2010 .. አዲስ አበባ ሲገቡ የክልሉ አመራሮች አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡

የአፋር ሕዝብ ፓርቲ አመራሮች በግዮን ሆቴል በሰጡት መግለጫ፣ ወደ ክልሉ ሄደው የአፋር ሕዝብን በማነቃቃት ለለውጥ እንደሚሠሩ ገልጸዋል፡፡

የፓርቲው ሊቀመንበር ኮንቴ ሙሳ (/) ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በዋናነት የኢትዮጵያ መንግሥትን በመወከል በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወርቅነህ ገበየሁ (/) በተደረገላቸው ግብዣ በአገር ውስጥ ለመንቀሳቀስ ተመልሰዋል፡፡

በክልሉ በአፋርኛ ‹‹ዱቢህና›› የተባለ በህቡዕ የተደራጀ የወጣት ክንፍ፣ ፓርቲያቸው የያዘውን ዓላማ እንደሚደግፍ ሊቀመንበሩ ገልጸዋል፡፡

‹‹ይህ የወጣት ክንፍ በኦሮሚያ ክልል እንዳለው ዓይነት የቄሮ አደረጃጀት ነው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

በቀጣይ ፓርቲያቸው በምርጫ ቦርድ ሕጋዊ ሆኖ ተመዝግቦ እንደሚንቀሳቀስ፣ ከሡልጣን ዓሊሚራህና ክልሉን ከሚያስተዳድረው የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አብዴፓ) ጋር አብረው ለመሥራት ዝግጁ እንደሆኑም አስታውቀዋል፡፡

‹‹አብዴፓ አሁን ከተፈጠረው የለውጥ መንፈስ ጋር መራመድ የሚችል ከሆነ አብረው ለመሥራት ዝግጁ እንደሆኑ፣ ነገር ግን በፓርቲ ደረጃ ፈቃደኝነቱ ከሌለ በፓርቲው ውስጥ ካሉ ለውጥ ፈላጊ የአብዴፓ አባላት ጋር አብረን እንሠራለን፤›› ሲሉ ኮንቴ (/) ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ከእሳቸው ጋር አብረው ወደ አገር ቤት የተመለሱት የአፋር ሰብዓዊ መብት ድርጅት ኃላፊ አቶ ግአስ አህመድ ሲሆኑ፣ ድርጅታቸው እ... 2006 ጀምሮ በአውሮፓ ተመሥርቶ ሲንቀሳቀስ መቆየቱን አስረድተዋል፡፡

ድርጅታቸው በአፋር ክልል የተፈጸሙ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ምርምርና ጥናት እንደሚያደርግ በመግለጫው ወቅት ተናግረዋል፡፡

‹‹በተለይም በሀብት ክፍፍል፣ ከጎረቤት ክልሎች ጋር በሚከሰቱ ግጭቶች፣  እንዲሁም ከመፈናቀል ጋር በተያያዘ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ጥናት እናደርጋለን፤›› ሲሉ አቶ ግአስ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በሌላ ዜና የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ግንባር ልዑካን ማክሰኞ ነሐሴ 8 ቀን 2010 .. አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡ የኦነግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የድርጅቱ ቃል አቀባይ አቶ ቶሌራ አደባ የተመራው ልዑክ፣ በቅርቡ በአስመራ በተደረሰው ስምምነት መሠረት ነው አዲስ አበባ የመጣው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በተመሳሳይ ዜና የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) አመራሮችም ወደ አገር ውስጥ መግባታቸው ተገልጿል፡፡ ግንባሩም ከመንግሥት ጋር ለመነጋገር ፈቃደኛ እንደሆነ ገልጾ፣  የተናጠል ተኩስ ማቆሙን ባወጣው መግለጫ ይፋ አድርጓል፡፡

በሶማሌ ክልል በትጥቅ ትግል አውጆ የቆየው ኦብነግ፣ በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ለመሳተፍ ፍላጎት እንዳለው ማስታወቁ ይታወሳል፡

ሪፖርተር