August 15, 2018

ባሕር ዳር፡ነሀሴ 09/2010 ዓ.ም (አብመድ)የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች መቀመጫውን ኤርትራ ካደረገው የአማራ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ንቅናቄ (አዲኃን) ጋር የጀመሩትን የሰላም ድርድር ለማስቀጠል የሚያስችል ውይይት ለማድረግ ዛሬ አስመራ ገብተዋል፡፡

የንቅናቄው አመራሮች በአስመራ ዓለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡

በአገሪቱ የተፈጠረውን የለውጥ እንቅስቃሴ እና የሰላም ጥሪ በመቀበል አዲኃን ከትጥቅ ትግል ወጥቶ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ለማድረግ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱ ይታወቃል።

በኢትዮጵያ ቆይታውም ከብአዴን ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮነን እና ከምክትል ሊቀመንበሩ ከአቶ ገዱ አንዳርጋቸው ጋር በአዲስ አበባ እና በባሕርዳር ተወያይተዋል።

የአዲኃን የውጭ ጉዳይ ሰብሳቢ አቶ ታዘዘው አሰፋ ለአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት እንደተናገሩት መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት በውጭ አገር የትጥቅ ትግልን አማራጭ አድርገው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ ሰላማዊ ትግል እንዲገቡ ማድረጉ በጥሩ ጎን የተጀመረ ለውጥ ነው ብለዋል፡፡

የአማራ ህዝብ እየደረሰበት ያለውን ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖዎች ለማስወገድ ከክልሉ መንግስት ጋር ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ለማድረግ ውሳኔ ላይ እንደደረሱ አቶ ታዘዘው ተናግረዋል፡፡

የክልሉ መንግስት ተወካዮችን ልኮ ተጨማሪ ውይይቶችን እንድናደርግ መወሰኑም የቀጣይ የትግል አቅጣጫችን ሰላማዊ ሆኖ ለክልሉ ህዝብ ተጠቃሚነት የበኩላችን እንድናደርግ አቅም የሚፈጥር ነው ብለዋል።

የአማራ ክልል መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅ.ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ንጉሱ ጥላሁን በበኩላቸው አዲኃን ወደ አገሩ በመመለስ ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ እንዲያደርግ መንግስት ፅኑ ፍላጎት አለው፤ የአሁኑ የአስመራ ጉዞም ይህን ዓላማ ለማስቀጠል ያሰበ ነው ብለዋል።

የድርጅቱ ሊቀመንበር እና ወታደራዊ አመራሮች በተገኙበት ለውጡን ስለመደገፍ እና ወደ አገር ቤት በሚመለሱበት ጉዳይ ነገ ሁለተኛው ዙር ምክክር እንደሚደረግም ተናግረዋል፡፡

አዲኃን ባለፉት ስምንት ዓመታት መቀመጫውን ኤርትራ አድርጎ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ስርዓት በመቃወም የትጥቅ ትግል ሲያደርግ የነበረ የፖለቲካ ፓርቲ ነው።
ነገ ውይይቱ በአስመራ ይካሂዳል፡፡
ዘጋቢ፡- ስማቸው እሸቴ እና አብርሃም አዳሙ

አዘጋጅ፡-ግርማ ተጫነ