የፌደራል መንግሥት የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስን ትጥቅ ለማስፈታት ዕቅድ እንደሌለው በሃገር መከላከያ የኢንዶክትሬኔሽንና ሕዝብ ግንኙነት ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ሜጀር ጀነራል ሞሃመድ ተሰማ ለቢቢሲ ገለጹ።

ሜጀር ጀነራል ሞሃመድ የፌደራል የፀጥታ ኃይል የሶማሌ ክልልን የፀጥታ ኃይል ትጥቅ የማስፈታት ዓላማ ይዞ አልተንቀሳቀሰም። ልዩ ኃይሉ ቀድሞም እንዲሰለጠን እና እንዲታጠቅ ያደረገው የፌደራሉ መንግሥት ነውብለዋል።

ጨምረውም ልዩ ኃይሉ ሰልጥኖና ታጥቆ ከክልሉ መንግሥት ጋር ብዙ ሥራ መስራቱንና አሁንም እየሰራ መሆኑን ተናግረው፤ በአሁኑ ወቅትም ልዩ ኃይሉ ፀጥታ የማስፈኑ ሥራ አካል ሆኖ እንዲሰራ የማድግ ተግባር እየተከናወነ እንጂ ትጥቅ የማስፈታት ዓላማም ሆነ ዕቅድ የለምብለዋል።

• መቋጫ ያልተገኘለት የኦሮሚያ ሶማሌ ጉዳይ

• በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች ድንበር ግጭት የገዳ ስርዓት መፍትሔ ለምን አላመጣም?

• አቶ አብዲ ስለተናገሩት ጉዳይ እንደማያውቅ ኢህአዴግ ገለፀ

• ባለፉት ሦስት ቀናት በምሥራቅ ሐረርጌ በተፈፀመ ጥቃት 22 ሰዎች ተገደሉ

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እና ተቺዎች የክልሉ ልዩ ፖሊስ አመሰራረት ምንም አይነት የህግ መሰረት የለውም ቢሉም፤ ሜጀር ጀነራል ሞሃመድ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉት ሁሉም ክልሎች ውስጥ የልዩ ኃይል አደረጃጀት እንዳለ አመልክተዋል።

መደበኛ ፖሊስ፣ ልዩ ኃይል እና ሚሊሻዎች አሉ። የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልልም እንደማንኛውም ክልል የልዩ ኃይል ፖሊሶችን አሰልጥኖ በማሰማራት ከፌደራል ኃይል ጋር የፀጥታ ማስከበር ሥራዎችን ሲሰራ ቆይቷል። በዚህም በአካባቢው የተሻለ መረጋጋት ተፍጥሯል። ከሕጋዊ ዕውቅና ውጪ የተቋቋመ አልነበረምብለዋል።

ልዩ ፖሊስ የታጠቀው መሳሪያ የሌሎች ክልል ፖሊሶች ከሚታጠቁ መሳሪያ አንጻር ከባድ እና የዘመነ ነው እየተባለ ለሚነሳው ቅሬታም ሜጀር ጀነራል ሞሃመድ በሶማሌ ክልል የፀጥታ ችግር እንደነበረና ይህን ችግር ለመቅረፍ ከፌደራል የፀጥታ ኃይል ጋር ልዩ ኃይሉን የማጠናከር እና የማዘጋጀት ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል።

• ጫካ ውስጥ አስቀምጠው ለተከታታይ ቀናት ደፍረውኛል

• መንግሥት ልዩ ፖሊስን እንዲበትን አምነስቲ ጠየቀ

• ሰመጉ በኦሮሚያና የሶማሌ ክልሎች የፀጥታ አካላት የመብት ጥሰቶችን መፈፀማቸውን በሪፖርቱ ገለፀ

በዚህም የፀጥታ ችግሩንም ለመቅረፍ ተችሏል። አሁን ምንድነው መስተካከል ያለበት በሚለው ላይ መንግሥት በሚሰጠው አቅጣጫ መሰረት የሚከናወን ይሆናል። በወቅቱ ግን አስፈላጊ ነገር ስለሆነ የተደረገ ነገር ነውብለዋል።

የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል በተደጋጋሚ በክልሉ ውስጥ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እንደሚፈጽም ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋቾች እንዲሁም በሶማሌ እና ኦሮሚያ ክልል ድንበር አቅራቢያ የተፈናቀሉ ዜጎች በተደጋጋሚ ገልጸዋል።

ሜጀር ጀነራል ሞሃመድ የሶማሌ ልዩ ኃይል አባላት ብዛት እና አደረጃጀት ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።