
አልቃይዳና አልሸባብን ጨምሮ በ2003 ዓ.ም ኦነግን፣ ኦብነግንና ግንቦት 7ን አሸባሪ ድርጅቶች ብሎ የፈረጀዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ በዚህ ዓመት ሦስቱን ከመዝገቡ ላይ ሰርዟል።
በተለያዩ አገራት ሆነው የትጥቅ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩት ኃይሎች ትጥቃቸውን ፈተዉ ወደ አገር ቤት እንዲገቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ያቀረቡትን ጥሪ ተከትሎ፤ የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) ነሐሴ 6/2010 ዓ.ም ልኡኩን ወደ አዲስ አበባ ልኳል።
የኢትዮጵያ አዲሱን የፖለቲካ ሁኔታና ወደፊት የሚፈጠረውን ጉዳይ በመወያየት ለሕህዝብ ሰላምና መረጋጋት የበኩላችንን ለማበርከት ወስነናል የሚለው ኦብነግ፤ የተናጥል የተኩስ አቁም ውሳኔ ላይ በመድረስ ወደ አገር ቤት መግባቱን ይገልጻል።
• አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀው ኦብነግ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር እየተደራደረ ነው
የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አዉጪ ግንባር ሥራ አስፈጻሚ አባልና የኮሚዩኒኬሽን ሃላፊ አቶ ሀሰን አብዱላሂ ለቢቢሲ እንደተናገሩት “ጊዜው የጠመንጃ አይደለም።”
“በሕዝባችን ላይ ይደርስ የነበረው በደልና ጭቆና አሰቃቂ ነበር። እኛም ሕዝባችን ፍትህና እኩልነት እንዲያገኝ ነበር ጠመንጃ ያነሳነዉ። አሁን ደግሞ ጊዜው አይደለም። ሁሉም ነገር በሰላማዊ ድርድር መፍትሄ ይገኝበታል ብለን እናምናለን” ይላሉ።
የኦብነግ ፍላጎት
የሶማሌ ክልል ሕዝብ ከኢትዮጵያ ሕዝብም ሆነ ከቀጠናው አገራት ሕዝቦች ጋር የሚያስተሳስረው ማህበረናዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር ሰፊ እንደሆነ የሚያነሱት አቶ ሀሰን አብዱላሂ “የያዝናቸውን እቅዶች ሁኔታዎችን አይተን የምንተገብራቸው ሲሆን፤ ለወደፊቱ በጠረጴዛ ዙርያ በሰላማዊ መንግድ ችግሮች ይፈታሉ ብለን እናምናለን” ይላሉ።
በግንባሩ ቃል አቀባይ አቶ አዳኒ አብዱልቃድር ጌርሞጌ የተመራው እና ሦስት አባላት ያው የድርጅቱ ልኡክ አዲስ አበባ ሲገባ፤ በቀጠናው ምንም አይነት የተኩስ ድምጽ እንዳይሰማና ክልሉን ለማረጋጋት እንደሆነ ገልጸዋል።
የዋርዴር ኒውስ ዶት ኮም መስራች፣ ጸሃፊና የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ቋሚ ተንታኝ ፈይሰል ሮቤል የኦብነግ ተኩስ የማቆም ውሳኔ መስዋዕትነት ሲከፍል ለነበረው የሶማሌ ክልል ሕዝብ እረፍት የሚሰጥና ሕዝብ ሲጠብቀው የነበረ ጉዳይ ነው ይላል።
ይህ በቀጣይነት ለሚደረጉ የውይይትና አብሮ የመስራት እንቅስቃሴዎች ትልቅ ሚና ቢኖረውም ቀላል ይሆናል ብሎ እንደማያስብ ስጋቱን ፈይሰል ይገልጻል።
“በኢትዮጵያ መንግሥትና ኦብነግ መካከል የሚደረጉ ውይይቶች በፈተና የተሞሉ ናቸው። በመጪው የክልሉ እጣ ላይ የሚያካሂዱት ውይይቶች እንዴት ይሆናሉ? በተለይ ደግሞ የራስ እድል በራስ የመወሰን መብትን በተመለከተ ጥያቄዎች ሊኖሩ ይችላሉ” ይላል ፈይሰል።
ከዚህ ባሻገር ደግሞ “ማዕከላዊው መንግሥት ክልሉ ውስጥ የሚኖረው ሚና ምን፣ በክልሉ ያለው የነዳጅ ሃብት፣ የሚሉና ሌሎች ጉዳዮች ትኩረት የሚሹ ናቸው” ሲል ያስቀምጣል።
ኦብነግ በሶማሌ ክልል ሕዝብ ውስጥ ትልቅ መሰረትና ተቀባይነት አለው የሚለው ተንታኙ፤ ህጋዊ ፓርቲ ሆኖ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል መምጣቱን ሕዝቡ በደስታ እንደሚቀበለው ገልጿል።
የኦብነግ ኮሚዩኒኬሽን ሃላፊ አቶ ሀሰን አብዱላሂ እንደሚሉትም “ድርጅቱ ፍትህና እኩልነት የሰፈነባት አገር በመገንባት ሕዝቡ የወደፊት ዕጣ ፈንታውን እራሱ እንዲወስን ማድረግ ነው። ሆኖም ግን ሕዝቡ ፍትህ፣ ዲሞክራሲና ነፃነትን ካገኘ ኢትዮጵያዊነቱን ሊመርጥ ይችላል” ይላሉ።

በሶማሌ ክልል ስላለው ለውጥ
በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ውስጥ የሚፈጠረው ሰላምና መረጋጋት እንደ አገር ካለው ጥቅም ባለፈ ለቀጠናው መሰረታዊ መፍትሄን በማምጣት የአፍሪካ ቀንድ አገራትም እንዲቀራረቡና እንዲረጋጉ እንደሚያደርግ ሁለቱም ይስማማሉ።
ከሳምንት በፊት በሶማሌ ክልል በተከሰተው ሁከት ህይወት ጠፍቷል፣ ንብረት ወድሟል፣ ሰዎች ተፈናቅለዋል። ይሄንን ተከትሎ የክልሉ ፕሬዚደንት የነበሩት አቶ አብዲ ሞሃመድ ኡመር ስልጣናቸው እንዲያስረክቡ ተደርጓል።
“ሰላማዊ ነው” ከተባለው የስልጣን ሽግግር በኋላ አቶ አሕመድ አብዲ መሀመድ የክልሉ ፕሬዝደንት ሲሆኑ፤ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሃላፊ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሸዴ የክልሉ ፓርቲ ሊቀ-መንበር በመሆን ተሹመዋል።
ይህ በብጥብጥ የታመሰውን ክልል በማረጋጋት የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ቢረዳም “የፌደራል መንግሥት ሰፊ እጅ ያለበት በመሆኑ ክልሉ ያረጋጋል አልልም” ይላል ፈይሰል።
“በአብዲ መሀመድ ሲመራ የነበረው ጨካኝ አስተዳደር ቢነሳም ለውጡ ክርክር እያስነሳ ነው። በአመራር ለውጡ ላይ የፌደራል መንግሥት እጅ አለ የሚሉ ስላሉ፤ ይህ ደግሞ የራሱ ችግር ይዞ ሊመጣ ይችላል።”
ሕዝብ ይህ አካሄድ ላለፉት 27 ዓመታት መንግሥት ሲተገብረው የነበረው ነው በሚል የሚፈጠረው ስጋት አንደኛው ሲሆን፤ ክልሉ ውስጥ ያለው አለመረጋጋት ሌሎች ችግሮችን በመፍጠር ሌላ አደጋን እንዳያስከትል የሚል ስጋትም እንዳለ ይናገራል።
“አዲሱ አመራርም ካለው ችግር ለመውጣት ለሕዝቡ አዲስ ቀን መሆኑ፣ ነገሮች በፌደራል መንግሥት የሚወሰኑ አለመሆናቸውንና አስተዳደሩ ከሕዝቡ የወጣ ነው የሚል አስተሳሰብ መፍጠር አለበት።”
ቀጣይ የአገሪቷ ስጋቶች
አሁን እየታዩ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገቡትን ቃል ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸውና ጊዜ ሳይወስዱ የመፍትሄ እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው ሁለቱም ይመክራሉ።
“በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ እየታየ ያለዉ ችግር መፍትሄ ካልተበጀለት አገሪቷን ወደ መጥፎ ሁኔታ ሊመራት ስለሚችል በሰከነ መንፈስ ሊፈታ ይገባል” ይላኩ የኦብነግ ኮሚዩኒኬሽን ሃላፊ አቶ ሀሰን አብዱላሂ።
በቀጣይ ለአገሪቷ ትልቅ ፈተና ሊሆን የሚችለው፡ አሁን እየቀጠሉ ያሉ ግጭቶች ናቸው የሚለው ፈይሰል ሮቤልም በበኩሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ ስፍራዎች ላይ እየታዩ ባሉት ግጭቶች ዙሪያ ቀዝቀዝ ማለታቸው ተገቢ አይደለም ይላል።
“ቀጠናውን ለማረጋጋት ሲታሰብ አገሪቷ ውስጥ ያሉ ግጭቶችና አለመግባባቶች ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለእነዚህ ችግሮች መፍትሄ ለማበጀት አለመፍጠናቸው መልካም አይደለም። ውይይቶችን ለመጀመርም ዘግይተዋል” ባይ ነው።
ስለሆነም እነዚህን ግጭቶች የሚከታተልና የሚፈታ አደረጃጀት በመፈጠር ዘላቂ መፍትሄ ወደ ሚሰጥ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መግባት ወቅቱ የሚጠይቀው እርምጃ መሆኑን ጠቁመዋል።