ከመሐመድ ዓሊ መሐመድ ፌስቡክ ገፅ የተወሰደ
ጽሁፉ ረዘም ቢልም በትዕግስት ብታነብቡት ደስ ይለኛል?
———————————————————————–
የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ለምን የጥቃት ኢላማ ሆነች?
የሙስሊሞች መገፋትና ቅሬታ
***********************,,
“ተዋድዶ ያለበት – ሙስሊም ክርስቲያኑ
ተዘነጋን እንዴ – ኢትዮጵያ መሆኑ”
************************
አልቅሼም አልወጣልኝ፣
============
ዛሬ ምሣ ሠዓት ላይ መገናኛ አካባቢ ከጥብቅና ሥራ ረዳቴ ጋር ቡና እየጠጣን ሳለ ዐይኔ የቋጠረውን እንባ መቋጠር አቅቶኝ ድንገት ዘረገፍኩት፡፡ ጉንጮቼን እያቋረጡና ኮለል እያሉ የሚወርዱ የእንባ ዘለላዎችን በቀላሉ ማቆም አልቻልኩም፡፡ ውስጤ ድረስ ዘልቆ የተሰማኝ ነገር የእንባ ከረጢቶቼን አፈንድቶ ፊቴ በእንባ ጎርፍ እንዲታጠብ አደረገኝ፡፡ ረዳቴም ትንሽ ግራ ሳትጋባ አልቀረችም፡፡ እንዲህ ብዙ እንባ የፈሰሰኝ መቼ ነበር? ዛሬስ ይህን ያህል ያስለቀሰኝ ምንድነው?
ስሜቴን ኮርኩረው ያስለቀሱኝ የFacebook ጓደኞቼ ናቸው፡፡ መነሻው ጧት ላይ “በኢትጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እንኮራለን” በሚል ንዑስ ርዕስ ሥር ከ IbrahimMulushewa ገፅ ወስጄ የለጠፍኩት ነው፡፡ በጽሁፉ ሥር የተሰጡ አስተያየቶች ስሜትን የሚነኩ፣ ብሶትን የሚቀሰቅሱና እንባን የሚያፈስሱ ናቸው፡፡ ስለሆነም እንደእኔ በለጋ ዕድሜው ከ10ኛ ክፍል ትምህርቱን አቋርጦ ለተሰደደ፣ ከባድ ርሃብና ጥምን ችሎ በርሃ አቋርጦ ለተጓዘ፣ ህግና ሥርዓት በሌለበት በ”ተጋዳላይ” እጅ ላይ ወድቆ በእስር ለተሰቃዬ፣ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ገብቶ ሲዳክር ለኖረ ሰው፣ አስተያየቶቹ ሊፈጥሩ የሚችሉትን ስሜትና እንባን መቆጣጠር በጣም ከባድ ነው፡፡ ስላልቻልኩም ካፌ በረንዳ ላይ ተቀምጨ ብዙ አነባሁ፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ ጨዋነትና ቅንነት መገለጫዎቹ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ የዚህ ቅንነትና ጨዋነት ምንጭ የሚከተላቸው እምነቶች መሆናቸው አያጠያይቅም፡፡ በተለይ ቀደምትነት ያላቸው የኦርቶዶክስና የእስልምና እምነቶች አስተምሮዎች የህዝቡን መንፈሳዊ ባህሪ በመግራትና በመቅረፅ ረገድ የተጫወቱት ሚና የማይተካ መሆኑ እሙን ነው፡፡ በዚህ ውስጥ የሌሎች እምነቶች ድርሻም አሌ የሚባል አይደለም፡፡ እምነቶቹ ህዝቡ (በእያንዳንዱ ሰው ውስጥ) ፈሪሃ እግዚአብሔር/አላህ እንዲያድርበትና የመልካም ሥነ-ምግባራት ባለቤት እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡ በመሆኑም ቅንነት፣ በጎ አድራጊነት፣ ቸርነት፣ ጨዋነት፣ ሰው አክባሪነትና ትህትና የ”ኢትዮጵያዊነት” መገለጫና መታወቂያ እስከመሆን ደርሰዋል ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ምናልባትም ይህ ግንዛቤ “ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ” እንዲሉና ከአጉል “መታበይ” የመነጨ እንዳይመስል በዘመናት ሂደት ያዳበርናቸውን ማህበራዊ እሴቶች በቅጡ መዳሰስና እውነቱን ማረጋገጥ ይቻላል፡፡
የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሚና፣
====================
የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ማዕከላዊ መንግሥቱን ከተቆጣጠረው ወገን በመሆኗ ካለፉት ሥርዓቶች ጋር ተያይዛ መነሳቷ የማይቀር ነው፡፡ በእርግጥም የሥርዓተ መንግሥታቱ ፍልስፍናም ሆነ ቅቡልነት (legitimacy) የሚመነጨው ከቤተ-ክርስቲያኗ መሆኑ ቤተ-ክርስቲያኗ አብራ ልትወቀስም ሆነ ልትወደስ ትችላለች፡፡ በአንፃሩ ሌላው ወገን አሸናፊ ሆኖ ማዕከላዊ መንግሥቱን ቢቆጣጠር ኖሮ የአገዛዙ መሠረትና ፍልስፍና አሸናፊው ኃይል የወጣበት ማህበረሰብ የሚከተለው እምነት መሆኑ አይቀሬ ነበር፡፡ በተለይም የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ፍልስፍና (በጽንሰ-ሀሳብ ደረጃ እንኳን) በማይታወቅበት በዚያ ዘመን ተቀናቃኝን በኃይል ከማንበርከክ ባለፈ ህዝቡ አገዛዙን እንዲቀበል (indoctrinate) ለማድረግ የእምነት ተቋማትን ከመጠቀም ሌላ ምን የተሻለ አማራጭ ይኖራል?
ይህም ሆኖ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ካጠፋችው ይልቅ ያለማቸው እንደሚበልጥ ከወገናዊነት ነፃ ሆኖ መከራከር ይቻላል፡፡ ቤተክርስቲያኗ በሀገረ-መንግሥቱና በአገዛዝ ሥርዓቱ ላይ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም አኩሪ ብሔራዊ እሴቶቻችን ላይ የጎላ አሻራ እንዳላት አይካድም፡፡ ለአብነት ያህል በሀገር ነፃነትና ሉኣላዊነት፣ በጀግንነት፣ በአርበኝነት፣ በመስዋዕትነት፣ በታማኝነት፣ በህግ አክባሪነት ወዘተ … ዙሪያ የተገነቡ አስተሳሰቦችን በማስረፅና የኢትዮጵያውያን መገለጫ እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ የእምነቱ አባቶች የተጫወቱትን ሚና ሥመ-ጥሩን ሰማዕት አቡነ ዼጥሮስንና ሌሎችንም መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከዚህም በመለስ ከሌሎች ጋር በመመካከርና በመከባበር ላይ የተመሠረተ ግንኙነትን ጠብቆና አጠናክሮ በመኖር ረገድ የእምነቱ አባቶች የነበራቸውን ገንቢ ተሞክሮ መምህር አካለ ወልድንና ሼህ ሁሴን ጅብሪልን በመጥቀስ ማስረገጥ ይቻላል፡፡
ይሁንና በአገዛዝ ሥርዓት ውስጥ ወሳኝ ድርሻ እንደነበረው ተቋም ቤተ-ክርስቲያኗ ላበረከተችው የምትወደሰውን ያህል የምትወቀስባቸው ነገሮችም ይኖራሉ፡፡ ጠቅለል አድርጎ ለማዬት ያህል ቤተ-ክርስቲያኗ የንጉሣዊ ሥርዓቱ ባለሟል፣ ባለርስት፣ ልዩ ተጠቃሚና በየደረጃው ተሰሚ እንደነበረች መካድ አይቻልም፡፡ ይህም በሌሎች እምነቶች/ተከታዮች ዘንድ የመገፋት/የመገለል ስሜትና ቅሬታ መፍጠሩ አልቀረም፡፡ ከዚህም በመነሳት ባለፉት ሥርዓቶች ተገልለናል/ተገፍተናል የሚሉ እምነቶች/ተከታዮች በሥርዓቶቹ ውስጥ ባለድርሻና ልዩ ባለሟል የሆነችውን የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በተጠያቂነት ደርበው ቢያቀርቡ አያስገርምም፡፡ ቤተክርስቲያኗ ከንጉሳዊ ሥርዓቶቹ ጋር ተደርባ መጠየቋና መወቀሷ ግን እጅግ አመዝኖ የሚታየውን በጎ አስተዋፅኦዋንና ገንቢ ሚናዋን በዜሮ ሊያባዛው ይቅርና ሊቀንሰውም አይችልም፡፡
የሙስሊሞች መገፋትና ቅሬታ፣
==================
በተለይም ቀደም ባሉት ዘመናት፣ በየትኛውም ዓለም የሃይማኖት ተቋማት እንደሰልፋቸው የድል ትሩፋቶች ወይም የሽንፈት ጽዋ ተቋዳሽ መሆናቸው አይቀሬ ነው፡፡ በእኛ ሀገርም ከዚህ የተለዬ ነገር እንዲሆን አይጠበቅም፡፡ መሠረቱ ክርስትና በሆነው ማዕከላዊ መንግሥትና የእስልምና እምነት ተከታዮች በሆኑት የዳር አገር አሚሮችና ሱልጣኔቶች መካከል በሚደረጉ ፍልሚያዎች አሸናፊው ወገን የተሸናፊው ወገን መገለጫና መሠረት የሆነውን እምነትና/ተከታዮቹንና የእምነት ተቋማትን በጥርጣሬና በርቀት ማዬቱ የሚጠበቅ ነው፡፡
ከዚህም ባለፈ የተፅዕኖ ክበባቸውን (sphere of influence) ለመቀነስ በኢኮኖሚ ማዳከምን ጨምሮ የተለያዩ አስተዳደራዊ ተፅዕኖዎችን ሊፈጥር ይችላል፡፡ ሁሉንም አንድ አድርጎ ለመግዛት ካለው ፍላጎት አንፃር፣ ይህን ሊያደግ የሚችለው በግልፅና በአዋጅ ሳይሆን በረቀቀ ስልትና “ፊውዳላዊ” ሴራ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ስለፍትህና ዴሞክራሲ የዳበረ አስተሳሰብ ባልነበረበት በዚያ ዘመን የትኛውም ወገን የራሱ ለሆነ ነገር ይበልጥ መቆርቆሩና ማድላቱ ተፈጥሯዊና የሚጠበቅ ሲሆን፣ ከሃይማኖታዊ ወገንተኝነት ይበልጥ የሚያሳስበው ግን የሌላው እምነት/ተቋም የአገዛዙን ቅቡልነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባና የሥልጣን ተቀናቃኙ ኃይል መሠረት ሊሆን መቻሉ ነው፡፡
ከዚህ በመነጨ ሙስሊሞች “ባለፉት ሥርዓቶች በረቀቀ ስልትና “ፊውዳላዊ” ሴራ ተገፍተናል/ተገልለናል” በሚል የሚያቀርቡትን ቅሬታ “ጆሮ ዳባ” ብሎ ወይም እንደተራ “ስሞታ” አይቶ ለማለፍ መሞከር ዘላቂ መፍትሔ ሊሆን ካለመቻሉም በላይ የእርስ በርስ መቃቃር መፍጠሩ አይቀርም፡፡ የምር እርስ በርስ መተሳሰቡ ካለ፣ አንዱ ወገን “ቅሬታ አለኝ” ሲል፣ ሌላው ወገን ቢያንስ በጥሞና ሊያዳምጠው ይገባል፡፡ ከማዳመጥም ባለፈ በእሱ ጫማ ውስጥ ሆኖ ማሰብም ያስፈልጋል፡፡ ወደኋላ ተመልሶ ያለፈውን መቀየር ባይቻልም፣ አሁን ላይ በተጨባጭ የሚነሱ ችግሮችን በጋራ መፍታት፣ ስለወደፊቱ መመካከር፣ ይበልጥ ተግባብቶና ተሳስቦ መኖር ይቻላል፡፡
ያለፉት ሥርዓቶች ከፈጠሯቸው አስተዳደራዊና ሥነ-ልቦናዊ ተዕኖዎች በመለስ፣ ሙስሊምና ክርስቲያኑ እንደ ህዝብ በቀላሉ ተግባብቶና ተዋድዶ ለመኖር የሚችል መሆኑ በተግባር የተፈተነ ነው፡፡ ይሁንና የእምነት ልዩነቶችም ሆኑ ቅሬታዎች የሚስተናገዱበት አግባብ ዘመኑ በሚጠይቀውና በሚፈቅደው ደረጃ፣ እንዲሁም ከጋራና ዘላቂ ጥቅሞቻችን አንፃር የተቃኘና በመተሳሰብ ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት፡፡ ተወደደም ተጠላም፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ሙስሊምና ክርስቲያኑ ተከባብሮ፣ ተመካክሮና አንድነቱን አጠናክሮ ከመኖር ሌላ አማራጭ ሊኖረው አይችልም፡፡ የሀገራችን ህልውናም በሁለቱ ታላላቅ ቤተ-እምነቶች (ሌሎችንም ጨምሮ) መግባባትና አንድነት ላይ የተመሠረተ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡
የኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያንን የጥቃት ዒላማ ማድረግ፣
==================================
የወያኔ/ህወሓት ህልውና የታነፀው ብሶትን በማስተጋባትና በወቅቱ ወጣት በነበሩት ታጋዮች አእምሮ ውስጥ የበቀል ስሜትን መዝራትና ኮትኩቶ ማሳደግ በሚሉ እሳቤዎች ላይ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ የብሶታቸውን ምንጭ በውል መረዳት ባይቻልም፤ አስተሳሰቡን አምጠው የወለዱትና ለፍሬ ያበቁት የትግሉ ፊታውራሪዎች “ኢትዮጵያዊነትን” ማዳከምና የኢትዮጵያ አንድነትን መሠረት መነቅነቅ የሚያስችላቸውን ስልት ቀይሰዋል፡፡
በእነሱ እይታና ግምገማ የ”ኢትዮጵያዊነት”ና የኢትዮጵያ አንድነት መሠረቱ በኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን አይዲዮሎጂና በአማራው ሥነ-ልቦና ላይ የተገነባ ነው ብሎ ያምናል፡፡ ስለሆነም ገና ከጧቱ መሣሪያ አንስተው ጫካ ሲገቡ አማራውን “በጠላትነት” በመፈረጅ “መልሶ ማንሰራራት በማይችልበት ሁኔታ አከርካሪውን መስበር” የሚል ግብ አስቀምጠዋል፡፡ ከዚሁ ጋር፣ አማራውን ጨምሮ በተለያዩ ማህበረሰቦች መካከል የአስተሳሰብ መተሳሰርንና አንድነትን፤ እንዲሁም የጋራ እሴቶችን ጠብቆ በማቆየት ረገድ ቁልፍ ድርሻ አላት ከሚል በመነጨ የኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያንን የጥቃት ዒላማ አድርገዋታል፡፡ ግን እንዴትና ለምን?
ኢትዮጵያ “የአብዮት ማዕበል” እያላጋት በነበረበት፣ ሁሉም ወገን በየፊናው በሚቀዝፍበት፣ ሁካታና ትርምስ በነገሰበት በዚያ “አሳሳች” ወቅት የሀገራችንን ዕጣ-ፈንታ ለመወሰን “ማገብት” በሚል ጥላ ሥር እየተሰባሰበ የሚመክርና የሚያሴር ቡድን እንደነበር ልብ ያለው ወገን ይኖር ይሆን? የቡድኑ አባላት የቅድመ-ዝግጅት ሥራቸውን ጨርሰው ደደቢት በረሃ ከወረዱ በኋላስ በተለይ አማራውን በጠላትነት መፈረጃቸውና ህልውናውን ጥያቄ ውስጥ ማስገባታቸው ምን ያህል ይታወቅ ነበር? አማራውስ “ተጋዳላዮቹን” መንገድ እየመራና ልጆቹም ትግሉን እንዲቀላቀሉ እያበረታታ ወደ መሐል አገር እንዲገቡ ሲያግዛቸው ልቦናው ምን ይነግረው ነበር? ሀገር ከተቆጣጠሩ በኋላስ ሁሉም በአማራው ላይ እንዲዘምትና እንዲረባረብ ሲያደርጉስ እንዴት አይበጅም ባይ ጠፋ? በዘመናት ሂደት ያዳበርናቸውን የጋራ እሴቶች ጠብቀን ማቆየትስ እንዴት አቃተን?
ወያኔ/ህወሓት ከቀየሰው ስልት አንዱ እነዚህን እሴቶች ጠብቀው ሊያቆዩ የሚችሉ ተቋማትን ማዳከምና በሌሎች ዘንድ በጥርጣሬ ሊታዩ የሚችሉበትን ሁኔታ ማጉላት ነበር፡፡ ከዚህ አንፃር ከኢትዮጵያ ሀገረ-መንግሥት ግንባታና ከሥርዓተ-መንግሥቱም ፍልስፍና ጋር በተያያዘ፣ እንዲሁም የጋራ ሀገራዊ እሴቶችን በማዳበር ረገድ የጎላ ደርሻና አሻራ የነበራት የኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን ከተለያዬ አቅጣጫ ስልታዊ ጥቃት በመክፈት ወከባና ውጥረት እንዲፈጠርባት ተደርጓል፡፡ በውስጥ የእምነቱን ተከታዮች በመከፋፈልና የእርስ በርስ ሽኩቻ እንዲነግስ በማድረግ፣ እንዲሁም “አይበጅም” የሚሉና የሚገስፁ፤ በህዝበ ክርስቲያኑ ዘንድ ተሰሚነት ያላቸውን የእምነት አባቶች በመለየት፣ በማግለልና በማሳደድ ክብርና ሞገሷን እንዲታጣ በዕቅድና በተከታታይ ተሰርቷል፡፡
ከውጭም; ቤተ-ክርስቲያኗን ካለፉት ሥርዓቶች ጋር በማያያዝ፣ ገንቢ ሚናዎቿን ጥላሸት በመቀባት፣ ባለፉት ሥርዓቶች የነበሩ ጥፋቶችን በማጉላት፣ ቤተክርስቲያኗ የጥፋቱ ሁሉ ተጋሪ እንደሆነችና; ያለፈ ሥርዓት ለመመለስ እንደምትሠራ አድርጎ በመሳል ሌሎች በጥርጣሬና በዓይነ-ቁራኛ እንዲመለከቷት ተደርጓል፡፡ በዚህ መንገድ ቤተ-ክርስቲያኗ የነበራትን ክብርና ተሰሚነት ጠብቃ መቆየት እንዳትችል፣ እንዲሁም ከሌሎች ቤተ-እምነቶች ጋር አዎንታዊ መስተጋብር ፈጥራ የይቅርባይነት፣ የእርቅና የፍቅር መንፈስ በመፍጠርና በማጠናከር ረገድ ዘመኑን የዋጀ ሚና እንዳይኖራት የተፈፀመው ደባ የጎዳውና ዋጋ ያስከፈለው ሁሉንም ወገን ነው፡፡ ስለሆነም የቤተ-ክርስቲያኗ የውስጥ ችግር መፈታትም ሆነ በሀገር ደረጃ ልትጫዎት የምትችላቸው ገንቢ ሚናዎች ሁላችንንም የሚመለከቱ የጋራ ጉዳዮች መሆናቸው ሊሠመርበት ይገባል፡፡ ይህም ሆኖ የእምነቱ ተከታይ ያልሆንን ሰዎች የቤተ-ክርስቲያኗ የውስጥ ችግር በመፈታቱ የተሰማንን ደስታ በመግለፃችን በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ የፈጠረው ስሜት በጣም የሚያስደምም ነው።
አልቅሼም አይወጣልኝ፣
==============
ለምን ታለቅሳለህ አትበለኝ! ለምን አላለቅስም? የህዝቡ ሁኔታኮ ሆድ ያባባል፡፡ ይኸ ህዝብኮ ብዙ ነገር አጥቷል፡፡ ተስፋውን ተነጥቋል፡፡ ፍቅር ተርቧል፡፡ ስለአንድነቱ፣ ስለጋራ እሴቶቹ፣ ስለታላቅነቱ የሚናገሩ ሰዎችን ይናፍቃል፡፡ ስለፍቅርና አንድነት ከተናገርክ ጆሮውን ብቻ ሳይሆን ልቡን ጭምር ከፍቶ ይሰማሃል፡፡ ልቡ ለፍቅር ክፍት መሆኑን ያረጋግጥልሃል፡፡ እናም ተስፋህ ይለመልማል፡፡
ለመሆኑ ይኸ ሁሉ ፍቅርና ቅንነት ወዴት ነበር የተነነው?እንዲህስ በቀላሉ እንዴት ወደ ቦታው ሊመለስ ቻለ? አሁን ደግሞ ያ ሁሉ ጭንቀትና ስጋት ወዴት ተነነ? ይህን ስታስብ ሞተህ እንደተነሳህ ሁሉ ሊሰማህ ይችላል፡፡ በእዝነ-ልቦናህ “የኢትዮጵያ ትንሳኤ” ሲበሰር ይሰማሃል፡፡ ብቻ ግን እንደዚያ ዓይነት ስሜት በውስጥህ ሊያንሰራራና ሁለመናህን ሊቆጣጠረው ይችላል፡፡ እናም ሳታስበው እንባህ ግድቡን ጥሶ ሊፈስ ይችላል፡፡ በውስጥህ ብዙ ነገር ቢኖርም አልቅሰህ አይወጣልህም …
ብቻ ግን ፍቅራችንን ዘላቂ ያድርገው! መዋደድና መተሳሰባችን የምር ይሁን! እኛ ፍቅርን ታድለን ፍቅርን የተራብን እንቆቅልሽ ህዝቦች ነን። የኢትዮጵያ ትንሳኤ በቅርብ እየታዬን የሚርቅብን አሳዛኝ ተጓዦች ነን። ፈጣሪ-አምላክ ቀኑን ያቅርብልን!!!
እስቲ የጂጂንና የቴዲን ዜማዎች ተጋበዝልኝማ!
“እኔን የራበኝ ፍቅር ነው …”
“ቅርብ ነው አይርቅም የኢትዮጵያ ትንሳኤ. ..”
አስተያዬት (comment) ከ M Dawit Solomon
ጽሁፉ ለእኔ በጣም አጥሮብኛል።ምክንያቱም ያነሳኸው ሀሳብ እጅግ እውነት ግን ለዘመናት እንዳይነገር የተደበቀ እውነታ ነው። በቅርቡ እንደው ነብዩ መሀመድና የኛ ንጉስ ምን አይነት ደብዳቤ ተጻጽፈው ነው የተግባቡትና የተስማሙት የሚለውን ለመመርመር ትንሽ መንገድ ሄድኩኝ። ነብዩ ወደ ሀበሻ ሀገር ሂዱ በዚያም በክርስቲያኖች ሀገር ፍትህና እውነት የሚያውቅ ንጉስ አለ። የሚለው አረፍተ ነገር ሲተነትን ብዙ ነገር ይከስታል። ንጉስ አርማህም የቡድኑ መሪ ጃእፋር ለቁረይሾች የመለሰውን መልስ ከሰሙ በኋላ እናንተ ከምትሉት ይልቅ እሱ የሚለው ከእኔ እምነት ጋር ይቀርባል ብለው ቁረይሾቹን አባረሩአቸው። እዚህ ላይ ብዙ ነገር ማየት ይቻላል። ካህን እና ንጉስ የነበሩ መሆናቸው፣ ለሁለቱም የፍርድ ወንበር መዘርጋታቸው እና እንደት እስልምናና የኢት. ኦርቶዶክስ ተመሳሰለ? ነው ጃእፋር ንጉሱን አታሏቸዋል? ይህንን ለማጣራት ትንሽ መንገድ ሄድኩ። ስለ ነገረ ድንግል ማርያም ሁለቱ እምነቶች ምን ይላሉ። በድንግልና ያለ ወንድ ዘር እንደወለደች፣ ፍጹም የሰው ዘር መሆኗ፣ ዬሴፍ የእሷ ጠባቂ ብቻ እንደነበር፣ እጅግ ትሁት ሰው እንደነበረች….. ይህንን አባባል ሙሉውን በሌሎች የክርስትና ዘርፎች ሙሉውን የሚቀበል የለም። በቁርአኑ ላይ ስለ ዬሴፍ ወክሊመትሁ አልቀሀ…..ወኢሳ…የሚለው አንተ ህጻኑንና እናቱን ልትጠብቅ ነው ነው እሚለው። ስለዚህ ጃእፋር ያቀረበው መረጃ ሁሉ ንጉሱን እንደሚያሳምን አያጠራጥርም። ወደተነሳሁበት ነጥብ ስመጣ በዘመን አመጣሾቹ የእስልምና ምሁራን የሚጽፉትን ሁሉ እስከቻልኩ ድረስ አነባለሁ አንዱም ግን እውነታውን መናገር አይፈልጉም። በቀደም አንዱ ወንድማችንና አንተ የጻፍከውን ሳነበው በቃ የኢት.ትንሳኤ ቀርቧል የተደበቁ እውነቶች እየወጡ ነው ነው ያልኩት። ያለፈው መንገዳችን አልጋ ባልጋ ነው ማለት ግን አይደለም። ግን ሙሉ በሙሉ ጨለማ እንዳልነበረ ግን ብዙ መረጃ አለ። በአጼ ዩሀንስ ዘመን የወሎ ቤተክርስቲያን አለቃ የነበሩት መምህር አካለወልድ ለንጉሱ ያቀረቡት ተቃውሞ፣ የወሎ ክርስቲያኖች ከሙስሊሙ ወንድማቸው ጋር አብረው የመከላከል ውጊያ ያለቁትና ላለመማረክ እራሳቸውን በገደል እየጣሉ ንጉሱ ያደረጉት አዋጅ ሁሉ በጋራ የከፈልነው መስዋእትነት ነው። ነገር ግን ጸሀፊወቹ ይችን ቢሞቱም መጥቀስም እንዲነሳም አይፈልጉም። ክፋትን ለመዝራት የምንሄድበትን ሩብ መንገድ ሳንሄድ እውነቱን እናገኛለን።