ከታሪክ መድረክ – የሰንደቅዓላማው ወንጀለኛ አርማ (ኀይሌ ላሬቦ)


ይኸንን ጽሑፍ ለመጻፍ ያነሣሣኝ በነዚህ ሁለት ሳምንቶች በኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማ ዙርያ የተነሡት አወዛጋቢ ጥያቄዎችና ክርክሮች ሲሆኑ፣ በተለይ ደግሞ የቀድሞው የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ሊቀመንበር የነበሩት፣ አሁን በጡረታ ያሉት ሊቅ (ዶር.) ነጋሦ ጊዳዳ የባሕርዳር ሕዝብ አዲስ ለተመረጠው ለኢሕአዴግ ጠቅላይ መሪ ለሊቅ ዐቢይ አሕመድ የደስታ ስሜቱን ሊገልጥ፣ ድጋፉን ሊሰጥ ሲል ይዞ በወጣው ሰንደቅ ዐላማ ላይ የሰጡት ኂሳዊ አስተያየት ነው። ሊቅ ነጋሦ የባሕርዳር ሕዝብ በነቂስ ይዞ የወጣው ምንም ምልክት ከላዩ የሌለበት ማለትም ልሙጡ የአረንጓዴ ብጫ ቀይ ቀለማት ሰንደቅዓላማ የአገሩን ሕገመንግሥት የሚፃረር ነው ብለው በመኰነን አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። በሳቸው እይታ ሰንደቅዓላማው ሁለት ከፍተኛ ሕጸቶች ያሉበት ሲሆን፣አንደኛው ዘውዳዊ ሥርዐትን የሚያንጸባርቅ የነአፄ ኀይለሥላሴና የነአፄ ምኒልክ ሰንደቅዓላማ፣ ሁለተኛ ደግሞ የዚህ ሥርዐት ፍሬ እንደመሆኑ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ አንድነት የሚፃረር፣ እኩልነቱንም የሚያናጋ ነው ብለው ያብራራሉ። ሊቅ ነጋሦ በርሳቸው ሊቀመንበርነት ሌሎች ኻያስምንት የኢሕአደግ አባላት ተሳትፈውበት ያጸደቁትንና፣ የሕገመንግሥቱ አካል ያደረጉትን ሰንደቅዓላማ ሕጋዊና “የሃገሪቱን ሕዝቦች እኩልነት የሚያረጋግጥ” ነው ብለው ያስተምሩናል። የአዲሱን ጠቅላይ መሪያቸውን “መደመር” የሚለውን መፈክረ ቃል በመጨመር፣ ሊቁ ይኸንኑ አቋማቸውን ሲያብራሩ የሰንደቅዓላማውንም አመጣጥ በመጨመር ነው። እንዲህ ነው ያሉት፤

ፕ/ር ኀይሌ ላሬቦ

“እነዚያ [ማለትም የነግሥታቱ] ባንድራዎች አንድ ሊያደርጉን እንደማይችሉ አይተን ፤ በ1987 ዓ.ም የኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ የሚደመር፣ ሃይማኖታችንን በሙሉ የሚደምር፣የተለያዩ ግለሰቦችንንና ቡድኖችን የሚያግባባና ሁላችንም አንድ የሚያደርግ ባንድራ የቱ ነው? ብለን በሕገ–መንግስቱ አንቀፅ ሦስት ላይ አስቀመጥን”።

የዛሬ ውይይቴ የሊቅ ነጋሦ ትረካ ምን ያህል እውነተኝነት አለው ብለው መጠይቅ ብቻ ሳይታገት፣ የትኛው ሰንደቅዓላማ ነው ሕጋዊ በሚለው ርእስ ላይ ደግሞ መወያየትን ይጠይቃል። አባቶቻችን “ነገር ከመጀመርያው፣ እህል ከመከመርያው” እንደሚሉ፣ የ‘ልሙጡ’ ሰንደቅዓላማ አመጣጥ ከ ‘ባለኮከቡ’ ጋር አስተያይቶ መናገሩ ሚዛናዊ ፍርድ ለመስጠት ተገቢ ይመስለኛል። ውይይቱን ከልሙጡ ልጀምር።

ሁላችንም እንደምናወቀው፣ አፄ ምኒልክ፣ በአፄ ቴዎድሮስ ዳግማዊ ተጀምሮ፣ በአፄ ተክለሃይማኖትና በአፄ ዮሐንስ ራብዓይ የቀጠለውን የኢትዮጵያን መልሶየመገንባት ሥራ፣ ከማንኛውም የቀደሟቸው ነገሥታት፣ የተሻለ ብልሃትና የበለጠ ፍቅር በመጠቀም እፍጻሜ ያመጡት መሪ ናቸው። ሕዝባቸውም በውድ እንጂ በግድ እንዳይገዛላቸው ስላልፈለጉ፣ እሳቸውን ከመውደድ የተነሣ፣ እንደንጉሥና እንደአባት ሳይሆን እንደወላጅ እናት ‘እምዬ ምኒልክ” ብሏቸው በመጥራት ፍቅሩን ገልጦላቸዋል። የዘመናቸውም ሆኑ፣ ከነሱ በኋላ የመጡ የዓለም ታሪክ ጸሐፊዎችና ገዢዎች የማስተዳደር ብልሃታቸውን አይተው “የወጣለት ጥሩ መሪ” በማለት አድንቋቸዋል። በጥበባዊ አስተዳደራቸው፣ የኢትዮጵያ ክብር አደገ። የዘመናዊ አስተዳደር መሠረትም ተጣለ። ዘመናዊነትን ለማስጨበጥ በአፄ ምኒልክ ዘመን ያልተነካ የአስተዳደር ዘርፍና መስክ አልነበረም ማለት ይቻላል። ሰንደቅዓላማም ከነዚህ ዘርፎች አንዱ ነው። ዛሬ የሚውለበለው የኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማ ቅርጹንና ሦስቱን የቀለማት ዐይነት ያገኘው በአፄ ምኒልክ ዘመነመንግሥት ስለሆነ፣ ሊቅ ነጋሦ “የአፄ ምኒልክ ባንዲራ” ቢሉት አይገርምም። ግን የረሱት ነገር ቢኖር፣ ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚወደው ባለሦስት ቀለማት ሰንደቅዓላማ በአፄ ምኒልክ ይጀምር እንጂ፣ የቀለማቱ አደራደር ንጉሠነገሥቱ ከወሰኑት ጋር አይገናኝም ብቻ ሳይሆን፣ ከአድዋ ድል ማግሥት በፊት አሁን ባለው መልክ በሕይወት መኖሩ ራሱ ያጠራጥራል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሰንደቅዓላማ በይፋ ተበሠረ የተባለው በአ.አ. በጥቅምት 1898 ዓ. ም. የነጭ ዐባይ ዙርያ ሊቃኝ በመዘጋጀት ላይ ለነበረው የፈረንሳይና የኢትዮጵያ ጓድ፣ አፄ ምኒልክ እንደአ.አ. በጥቅምት 1897 ዓ. ም.፣ የኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማ ብለው በሰጡት ድርጊት ላይ በመመሥረት ነው። ቀለማቱ አቀማመጣቸው አግዳሚ ሁኖ፣ ከላይ ቀይ፣ ከመኻል “ም” ፊደል የተለጠፈበት ብጫ፣ ከታች ደግሞ አረንጓዴ ነበር። “ም” የ”ምኒልክ” ምሕፃረ-ቃል ሲሆን፣ ዋናው ምክንያት በአካባቢው ለነበሩት ቅኝ ገዢዎች አገሪቷ በሳቸው ሥር መሆኗን እንዲያውቁት ሲባል ሆን ብሎ የተደረገ ይመስላል። ሰንደቅዓላማው በየምክንያቱ እንደየአስፈላጊነቱ በአፄ ምኒልክ ዘመን እጥቅም ላይ ቢውልም፣ በዐዋጅ የተነገረ ነገር ግን አልነበረም። የቀለማቱም አደራደር ግልጥ አልነበረም። አንዳንድ ጸሓፊዎች ብጫው እንዳለ በመኻል ሁኖ፣ አረንጓዴውን ከላይ፣ ቀዩን ከሥር ያዩበትም ሁናቴ እንደነበረ ይናገራሉ። ንጉሠነገሥቱ ቀለሞቹንና አደራደራቸውን እንዲሁም አግዳሚ አቀማመጣቸውን በምን ላይ ተመሥርተው እንደወሰኑ ግልጥ አልነበረም። የቀለሞቹንም ዐይነት የወሰኑት፣ በጥናትና በኢትዮጵያ ባህልና ታሪክ ተንተርሰው ሳይሆን፣ የነጭ ዐባይ ቃኝ ጓድ ጥያቄ እንደዱብ ዕዳ ሳይታሰብ የመጣባቸው ስለነበር፣ አሳቡን በቅርብ ከሚያውቋቸው ከፈረንሳይና ከኢጣሊያን ሰንደቅዓላማዎች ቀለማት በመዋስ ነው የሚል አስተያየት አለ[1]። ግን “ሦስቱን ቀለማት ባንድጋ የመስፋቱ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር፣ ቀለማቱ ለየብቻቸውም ቢሆኑ፣ ከጥንት ጀምሮ በተለያዩ ነገሥታት እንደኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማ እሥራ ላይ ይታዩ ስለነበር፣ የውጭ አገሮችን በማየት የተቀነባበሩ ናቸው የሚለው አባባል ውሃ አይቋጥርም። በጊዜው የነጭ ዐባይ ቃኝ ጓድ አባል የነበረው ፈረንሳዊው ቻርል ሚሼል ኮቴ የሦስቱ ቀለማት ጨርቆች እንዴት እንደተሰፉ ሲያብራራ፣

“እስከዚያ ቀን ድረስ ለየብቻቸው ይንጠለጠሉ የነበሩትን ሦስቱን የኢትዮጵያን ሰንደቅዓላማ ቀለሞች፣

ማለትም ቀይ፣ ብጫ፣ አረንጓዴ፣ ለመጀመርያ ጊዜ ባንድጋ እንዲሰፉ {አፄ ምኒልክ] ዐዘዘ፣”[2]

ሲል ቀለማቱ የተውሶ አለመሆናቸውን ያሳያል። ሁኖም በቀለማቱ አደራደር ጉዳይ ላይ ስምምነት ያልነበረ ይመስላል። ስለዚህም ከንጉሠነገሥቱ ዕረፍት በኋላ በቀለማቱ አሰላለፍ፣እንዲሁም ከጥንት የኢትዮጵያ ታሪክ ጋር ስላላቸው ግንኙነትና ትስስር የተጧጧፈ ክርክር መነሣቱ የግድ ሆነ። የአፄ ምኒልክ የግቢ ሚኒስቴርና የሥርዐተ መንግሥታቸው ዋና አቀናጅ የነበሩት፣ አቶ ኀይለማርያም ሠራቢዮን[3] በንጉሠነገሥቱ ወቅት የነበረውን ሲደግፉ፣ ሌሎቹ አልተቀበሏቸውም። ሁኖም ባለሟሉ የፈለጉት በላቲን አሜሪቃ ውስጥ በሚገኝ ቦሊቪያ በተባለ አገር በቅድሚያ በመወሰዱ የሰንደቅዓላማው ቀለማት አቀማመጥ አረንጓዴ፣ ብጫ፣ ቀይ ይሁን የሚለው ቡድን ክርክሩን አሸንፎ፣ የአፄ ምኒልክ ሰንደቅዓላማ ቀለማት ድርድር አገልግሎቱን አበቃና፣ በ፲፱፻፱ ዓ. ም. በአረንጓዴ፣ ብጫ፣ቀይ ተተካ።

እኔ እንደማውቀው ከኢትዮጵያውያን ደራሲዎች ስለኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማ በጽሑፍ ያስቀመጠልን ይኸ አሸናፊ ቡድን ብቻ ነው። ከመኻላቸው፣ ጐላ ያለ ሚና የተጫወቱት ራሱን “የኢትዮጵያ ልጅ” ብሎ የሚጠራ መምህር ጸጋዘአብ[4] ሲሆን፣ ሌላው ነጋድራስ ደስታ ምትኬ[5] ነው። እንደየቅደም ተከተላቸው፣ አንደኛው ሐምሌ ፪ ቀን ፲፱፻፲፯ ዓ.ም.፣ ሁለተኛው ደግሞ ጥር ፲፫ ቀን ፲፱፻፲፰ ዓ ም በብርሃንና ሰላም ጋዜጣ ላይ ባወጡት ጽሑፎቻቸው የኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማ ዘመናትን ያስቈጠረና ከትውልድ ወደትውልድ እየተላለፈ የመጣ መሆኑን ይገልጹልናል። ለምን የቀስተደመና ቀለማት ተመረጡ ለሚለው ጥያቄ በብሉይ ኪዳን በኦሪት ዘልደት ምዕራፍ ፱፣፲፪-፲፯ ታሪክ ጋር የተያያዘ መሆኑ ይነግሩናል። ይኸውም፣ እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ዳግመኛ በንፍር ውሃ ላያጠፋት ከኖኅ ጋር የተዋዋለው የዘለዓለም ቃልኪዳኑ ምልክት ነው ይላሉ። ከዚህም ባሻገር፣ኢትዮጵያም በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ አግኝታ ለዘላለም በባዕድ ሳትገዛ እንደምትኖር የሚያረጋግጥላት ከእግዚአብሔር የተሰጣት ምልክት ቀለማት ናቸው በማለት ከብሉይ ኪዳኑ ታሪክ ጋር ያጣጥማሉ።

ሌሎች ከኋላቸው የመጡት ምሁራን በበኩላቸው ሁለቱ ጸሓፊዎች ለሰንደቅዓላማ በሚሰጡት ምስጢር ቢስማሙም፣ በአጀማመሩ ግን ይለያሉ። በነሱ አባባል፣ “የኢትዮጵያ መንግሥት በተመሠረተበት ወቅት፣ ነገሥታቱና ምሁራኑ ተመካክረው ሲያበቃ፣ በሰንደቅዓላማው ምሥጢር ከተስማሙ በኋላ ሦስት ቀለማት እንዲሆኑ ተወሰነ። አፄ ገላውዴዎስ (1532-1551) ኢማም አሕመድን፣ አፄ ዮሐንስ(1864-1881) ግብፆችን፣ አፄ ምኒልክ(1882-1906) ኢጣሊያኖችን በአድዋ ድል” የመቱት በዚህ ትእምርተ ኀይል ነው ይላሉ።

ከዚህ መግለጫ ግልጥ የሆነ ነገር ቢኖር፣ የዛሬ ሰንደቅዓላማ ቀለማት በአፄ ምኒልክ ቢወሰኑም፣ አደራደራቸው ግን ቈይቶ እንደመጣ፣ ቀለማቸውና የቀለማቱ አሰላለፍ ከብዙ ውይይትና ግንዛቤ በኋላ እንደተከናወነ ነው። አፄ ምኒልክም ለመላው ዓለም የሰንደቅዓላማው ባለቤት ኢትዮጵያ መሆኗን ቢያሳውቁትም፣ ውሳኔው ግን በምንም መልኩ በይፋ አልታወጀም። ንጉሠ ነገሥቱ ቀለማቱን የመረጡት በታሪክ በመተንተራስና የቀለማቱንም ምስጢር በማገናዘብ ነበር ቢባልም፣ ከኋላቸው የመጡት ምሁራን አባባሉን አይቀበሉትም። ቢሆንም፣ የሰንደቅዓላማውን ታሪክ ስንመለከት፣ የመላ ኢትዮጵያን ሕዝብ ያዋሐደና ያስተሳሰረ ብቻ ሳይሆን፣ የአገሪቷን ምድር ጠባይና እምነት ያካተተ እንጂ፣ ሊቅ ነጋሦ እንደሚሉት የአገሪቷን ሕዝብ እኩልነት የሚያናጋ፣ አንድነቱን የሚፃረር ባሕርይ በፍጹም የለበትም። እንደዚህ ካልሁ በኋላ፣ ታሪኩን ባጭሩ መመልከት የግድ ይሆናል።

የኢትዮጵያን ሰንደቅዓላማ ታሪክ በሁለት መክፈል ይኖርብናል። አንደኛው፣ ያልተጻፈና፣ በአፈታሪክ ላይ ብቻ የተመሠረተ። ሁላችንም እንደምናውቀው፣ ኢትዮጵያውያን የመጻፍ ባህል እምብዛም ያላዳበርን ሕዝብ ነን። እኔ ራሴ የግእዝ ተማሪ ሳለሁ፣ በብዙ የኢትዮጵያ አብያተተክርስቲያናት በዓላት ከቦታ ወደቦታ እየነገድሁ እሳተፍ ነበርና፣ እጅግ በጣም የሚገርመኝ ነገር ቢኖር፣ በየበዓላቱ የሚቀኙት የቅኔ ዐይነቶችና ብዛት ሲሆን፣ ከነዚያ አንድም ሳይጻፍ እዚያው እተቀኘበት ተቀብሮ መቅረቱ ነበር። ከቅዱስ ያሬድ ጊዜ ጀምሮ ከተቀኙት ቅኔዎች መካከል ሁሉም ባይሆኑ፣ አንድ ሦስተኛው እንኳን ቢጻፍ ኖሮ፣ ኢትዮጵያ አፈራች መባል የሚቻለው የመጻሕፍቱ ብዛትም ሆነ፣ ዐይነትና ጥራት ማንኛውንም የምዕራባዉያን ቤተመጻሕፍት (የአሜሪቃን ኮንግረስንና የብርቲሽን ቤተመጻሕፍቶች ጭምር) እጅግ በጣም ባስናቀ ነበር። ምንም ሃይማኖትን ያማከሉ ቢሆንም፣ ቅኔዎቹ በቃላት አጠቃቀም ርቀት፣ በይዘታቸው ጥልቀት፣ ባዘሉት አሳባቸው ምጥቀት፣ በምሥጢራቸው ውስብስብነትና በአጻጻፋቸው ስልት ከፍተኛ የምዕራብ ዓለም የኪነጥበብ ደራሲያን የሚባሉትን እንደጣሊያኑ ዳንቴ አሊጌሪ፣ የእንግሊዙ ዊሊያም ሼክስፔር የመሳሰሉትን ዋጋ ባሳጣቸው ነበር ብዬ አምናለሁ። ባሕሉ ባለመዳበሩ ይኸ ሊሆን አልቻለም። ሁኖም ግን፣ ጉዳዮችን በጽሑፍ የመመዝገብ ልማድ አለመዳበር በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን፣ በአብዛኛው ዓለም የነበረ ችግር ነው ማለት ይቻላል።

ስለሰንደቅዓላማ ህልውናውም ሆነ ቀለማቱ መናገር አስፈላጊ ሁኖ ባለመታየቱ ይሁን፣ ወይንም በሌላ ለኛ ሥውር በሆነ ምክንያት፣ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ፣ በየዘመኑ የመጡት የኢትዮጵያ ጸሓፊዎች መዝግበው የተውልን ነገር ባይኖርም፣ መጠቀሙን ከጀመሩት አገሮች ኢትዮጵያ ከመጀመርያዎቹ፣ ማለትም በፊታውራሪነት ከመሩት አንዷ መሆን አለባት የሚሉ በርካታ ናቸው። ስለዚህ፣ሰንደቅዓላማ በአገሪቷ ውስጥ በጥቅም ከዋለ ዘመናት ያስቈጠረ መሆን አለበት ቢባልም፣ ከመቼ ጀምሮ እንደሆነ ግን በርግጥ የሚታወቅ ነገር የለም።

ሰንደቅዓላማን መጀመርያ ላይ እንደአገር መለዮና መታወቂያ ብዙውን ጊዜ ይጠቀሙ የነበሩት መርከበኞች ናቸው።

አክሱማውያን በዘመናቸው፣ ይልቁንም አፄ ካሌብ በስድስተኛ ዘመነምሕረት መካከል፣ የናግራንን ክርስቲያኖች ያሳድድ የነበረውን አይሁዳዊውን ድሁኔዎስን ሊወጉት ቀይባሕር አቋርጠው ወደዐረብ አገር ሲሄዱ፣ መርከቦቻቸው ብሔራዊ ሰንደቅዓላማ እያውለበለቡ እንደተጓዙ አይጠረጠርም። ሰለሰንደቅዓላማ የቀለማት ዐይነት መረጃ ባይኖረንም፣ ስለህልውናቸው ግን ቢያንስ ከዐሥራ አምስተኛ ዘመነምሕረት አንሥቶ እስከአጼ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት አልፎ አልፎ በነገሥታቱ ታሪከነገሥት ይታወሳል። አፄ ምኒልክ ሐረርን ከአራት መቶ ዓመታት በኋላ ማለትም በ፲፰፻፸፱ ዓ. ም. መልሰው በያዙበት ወቅት፣ ከተማውንና የመንግሥትን መዛግብት የሚቀበሉትን መልእክተኞቻቸውን ከሰንደቅዓላማ ጋር እንደላኩ ይገልጻል[6]።

ከኢትዮጵያ ወጣ ብለን የውጭ አገር ጸሓፊዎች ካየን፣ ቢያንስ ከ፲፭ኛ ዘ. ም. አንሥቶ፣ የሰንደቅዓላማ በኢትዮጵያ መኖር በሰፊውም ባይሆን በመጠኑ ተመዝግቧል። ስለቀለማቱ ግን የተናገረ የለም። ሐተታ ላለማብዛት ሲባል ከነዚህ ጸሓፊዎች ሦስት ጠቃሚዎች ናቸው ብዬ የማምናቸውን ብቻ ላንሣ። አንዱ የኢማም አሕመድ ዜና መዋዕል ደራሲ፣ የመናዊው ሺሐብ አድ-ዲን ነው። ሌላው በወቅቱ ኢትዮጵያን የጐበኙ የፖርቱጋል ዜጎችና፣ እንዲሁም እነሱ በሰጧቸው መረጃ በመመሥረት የካርታ ሥራ ባለሙያዎች ጠቃሚ መረጃዎች ትተውልናል።

ኢትዮጵያን ስለማሸነፍ በሚለው መጽሐፉ ሺሐብ አድ-ዲን[7] በእስላሞቹ በኩል ስለነበሩት ሰንደቅዓላማዎች ቀለማትና ቊጥር በዝርዝር ይገልጣል። ስለክርስቲያኖቹ ሲናገር ግን ጀብዱነታቸውን በማድነቅ፣ “አርማቸውን እንደለበሱ፣ ሰንደቅዓላማቸውን እያውለበለቡ” እንደሞቱ፤ ወይንም መኳንንቱ የእስላሞቹ ጥቃት እጅግ ቢያይልባቸውም፣ “እነሱም ሰንደቅዓላማቸውም እንደተራራ ገደል ቀጥ ብለው እንደቆሙ ነበር” ብሎ ከመናገር ውጭ ስለሰንደቅዓላማዎቹ መልክ፣ ቀለምና ቍጥር ያለው ነገር የለም። ስለኢማሙ ሰንደቅዓላማዎች ሲናገር ግን፣ ሦስት ነገሮች ግልጥ ይሆናሉ። የያንዳንዱ የጦር መሪ ሰንደቅዓላማ በኢማሙ የተሰጠ ሲሆን፣ ባለአንድ ብቻ ቀለምና፣ በሰንደቅ ላይ ሳይሆን በጦር ጫፍ ላይ የሚሰካ ነበር። ስለዚህ ሰንደቅዓላማው በወቅቱ በአጋጣሚ የተፈጠረ እንጂ ቀዋሚና የቈየ አገራዊ መለዮ እንዳልሆነ ያመለክታል። ሁለተኛው፣ ቀለማቱ “የኢትዮጵያ ቀለማት” ተብለው ከሚመደቡት በቀስተደመና ዙርያ ካሉት አረንጓዴ፣ ብጫና ቀይ ብቻ የተወሰነ አይደለም። ጥቊርንና ነጭንም ይጨምራል። በደራሲው እንደተመዘገበው፣ የኢማሙ ሰንደቅዓላማ ቀለም ብጫ ነበር። የኢትዮጵያም ነገሥታት አርማቸውን ብዙውን ጊዜ የሚለጥፉት በብጫው ላይ ስለሆነ፣ የግራኝም መለዮ ይኸው ቀለም መሆኑ፣ የሁለቱ መመሳሰል የአጋጣሚ ጉዳይ ነው ብሎ ማለፉ አስቸጋሪ ነው ብዬ አምናለሁ። ቀስተደመና ዓመቱን በሙሉ፣ በክረምት ወቅት ዝናም ሲዘንም፣ በበጋ ደግሞ በበርካታ ፏፏቴዎች አካባቢ የሚታይ ነገር በመሆኑ፣ የሰው ልጅ እንደሰንደቅዓላማ መጠቀም የጀመረው ምናልባትም “የቀስተደመና ቀለማት” ይሆናሉ ተብሎ ይታመናል። በኢማም አሕመድ እንዳየነው፣ አብዛኞቹ በኢትዮጵያ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ራስገዝ አስተዳደሮች ይጠቀሙት የነበረው ከነዚህ ቀለማት መካከል መርጠው ነው። ከዚህም የተነሣ፣

ባንዳንድ አካባቢ “የኢትዮጵያ ቀለማት” በመባል እስከመታወቅ ደርሰዋል።

ከፖርቱጋሎች በኩል ስለሰንደቅዓላማ ጉዳይ የተሻለ መረጃ የሚሰጠን ማኑኤል ባራዳ[8] ነው ማለት ይቻላል። በአ.አ. በሺ፮፻፴፬ ስለትግራይ ታሪክና ሥነምድር በጻፈው መጽሐፍ ኢትዮጵያውያን ሰንደቅዓላማቸውን በጦርነትም በሠርግም ወቅት እንደሚጠቀሙት፣ በአሣሣል፣ በመልክ፣ በዐይነትና በቁመት ሁሉም አንድ እንደሆነ፣ በቤተሰብ ሆነ ወይንም በመኰንን ማዕርግ ደረጃ ልዩነት እንደሌለ ያወሳል። ሌላው፣ ስለካህኑ ዮሐንስ ምድር የተሣሉት በርካታ ካርታዎች ናቸው። ከነዚህ መካከል በሺ፭፻፸፫ ዓ.ም. ላይ ዳቹ አብርሃም ኦርቴሊዩስ[9] በሠራው ካርታ ላይ ተንተርሶ፣ ዊልም ጃንሶን ብለው[10] በሺ፮፻፴፭ ዓ. ም. የሣለው ነው። ካርታው በግልጥ ኢትዮጵያ የካህኑ ዮሐንስ የግዛት አገር መሆኑን ይገልጣል። አማራ፣ ትግሬ፣ ዶባ፣ ደንከል የሚሉ የቦታ ስሞችም ተመዝግበዋል። ከውስጡ የአንድ ወንድና የአንዲት ሴት ሥዕል ከሁለት ጃንጥላ የያዙ ልጆች ምሥል ጋር ተሥሏል። ከሴትዮዋ ላይ ያለው ልብስ በቀለማቱ የኢትዮጵያን ሰንደቅዓላማ ያንጸባርቃል። ከላይ አረንጓዴ ሸሚዝ፤ ከመኻል ብጫ ጒርድ፣ ከታች እስከእግሯ የሚደርስ ቀይ ሽርጥ ለብሳለች። ዛሬም ቢሆን በኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማ ቀለማት ያጌጠ ቀሚስ፣ ሸማና ብሔራዊ ልብስ ተለብሶ ማየት የተለመደ እንደሆነ እናውቃለን። የብለው ካርታ ምሥል የኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማ የመቶ ዓመት ታሪክ ሳይሆን፣ ቢያንስ ከአራት መቶ ዓመት በላይ ዕድሜ አለው የሚለውን አቋም ይደግፋል ማለት ይቻላል።

ስለኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማ ብዙ የሚባል ነገር አለ። ግን የኢሕአዴግ መሪዎች እንደገለጹት ጨርቅም ቀለምም፣ እንጨትም እንዳይደለ ርግጥ ነው። ባጭሩ፣ ያንድ ሕዝብ የመሬቱ ባለቤትነት፣ የነፃነቱ ርግጠኝነት፣ (የጥሩም ሆነ የመጥፎ) ታሪኩና ርእዮተ ዓለሙ መግለጫ ነው ብሎ ማጠቃለሉ ይበቃል። ኢትዮጵያ ከዐምስት ዓመት ትግል በኋላ፣ፋሽስቶች ድል ሁነው አገሯን ጥለው እንደወጡ፣ ነፃ አገርና የመሬቱ ባለቤት መሆኗን ለመላው ዓለም ያስታወቀችው፣ በጭቈናቸውም ሥር ለነበረው ሕዝቧም ያበሠረችው፣ በመጀመርያ ሰንደቅዓላማዋን በመሬቷ ላይ በመትከል ነው። በቀስተደመና ምስል የተሣለው የኢትዮጵያ ባለሦስት ቀለም ሰንደቅዓላማ፣ እንዳየነው፣ በጥንታዊነቱም ሆነ ባዘለው ምሥጢር የሚያስደምም ነው ማለት ይቻላል። አረንጓዴ፣ ብጫ፣ ቀይ ቀለማት፣ ትርጒማቸው የአገሪቷን “ምድር፣መንግሥትና ሕዝብ” ሲያመለክት፣ ባሕርያቸውም አንድም ሦስትም መሆኑን ያሳያል። በአረንጓዴ ቀለም የተመሰለችው ምድር፣ የሁሉም ፍሬ ሕይወት ሲትሆን፣ ቀዩ ደግሞ ዜጐችዋ ላገርና ለወገን ፍቅር ሲሉ ካስፈለገ ሕይወታቸውን በጀግንነት ሊሠዉ ዝግጁ መሆናቸውን ያረጋግጣል። በብጫ የተመሰለው መንግሥት፣ የምድርና የሕዝብ ጠባቂ፣ የሁለቱም አንድነት ማተብና ሐረግ ሲሆን፣ ሕዝቡን አገር ለመከላከልም ሆነ ለልማት በኅብረት ማሰለፍ ግዴታውና አላፊነቱ እንደሆነ ይነግረናል። በአገራችን፣ ሦስት ቊጥር የፍጽምና ምልክት ነው። የቀለማቱ ሦስትነትም ባንድ በኩል የምድሯንና የሕዝቧን ፍጽምና ሲያንጸባርቅ፣ በሌላው ደግሞ ልዩ ልዩ የአየር ጠባይ፣ የመሬት አቀማመጥ፣ ሀብትና ፍሬያማነት እንዳላት ይመሰክራል። በሕዝቧም መኻል ያለውን የእምነት፣ የቋንቋና የባህል ልዩነት ያመለክታል። የቀለማቱ ባንድነት መያያዛቸው፣ ምድር፣ መንግሥትና ሕዝብ በዓላማ፣ በአቋምና በግብር ያላቸውን ውሕደትና እኩልነት ብቻ ሳይሆን ሕዝቡም በታሪክ፣በደም፣ በኑሮ እንዲሁም በማንኛውም ማኅበራዊ ዘርፍ ርስበርሱ የተሳሰረና የተዋሐደ እንደሆነ ያስረዳል።

ይኸ በ፲፱፻፱ ዓ. ም. ብሔራዊ የሆነው ሰንደቅዓላማ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የአንድነቱና የነፃነቱ ምልክት ከመሆን አልፎ፣ አገልግሎቱን ለሌላውም ሰፊ ዓለም በማበርከት በታሪኩ ከፍተኛ አስተዋፅዖ አድርጓል። በምዕራባውያን ጭቈና ይማቅቅ የነበረው ጥቍር ሕዝብ ፈታኝና እልህ አስጨራሽ ትግሉ ወቅት፣ በኢትዮጵያዊነት ዙርያ በመሰለፍ ብቻ አልነበረም የታገለው። ሰንደቅዓላማዋንም የትግሉ መከታ፣ የነፃነቱ ፋና፣ የድሉ ዋስትና አድርጎ ነበር የተመለክተው።

ከአስድናቂው የአድዋ ድል በኋላ፣ ጥቊር ሕዝብ በተለይም የኢትዮጵያዊነት መግለጫና የማንነቷ መለዮ ሁኖ ለዓለም የተበሠረውን የኢትዮጵያን ሰንደቅዓላማንም፣ የነፃነትና የእኩልነት ትግሉ ወቅት፣ እንደትእምርተ ኀይልና እንደትእምርተ መዊዕ ያውለብለብ ነበር። የአሳቡ ጠንሳሽ የመላውን ዓለም ጥቊር ሕዝብ፣ ለዚህ ዓላማ ባንድጋ ያሰባሰበው፣ ስመጥሩው የጃማይካው ተወላጅ ማርኩስ ጋርቬይ[11] ነው። አቶ ጋርቬይ፣ በአ. አ. በ፲፱፻፳ ዓ.ም. “ተመልከት ዓላማህን፣ ተከተል አለቃህን” ሲል የጥቊር ሕዝብ ማንነት መግለጫ፣ የትግሉ ተስፋ እንዲሆንለት የሰጠው የኢትዮጵያን ሰንደቅዓላማን ቀለማት ነው[12]። ወደሠላሳ ዓመታት ቈይተው፣ ነፃነታቸውን የተጐናፀፉት አብዛኞቹ የአፍሪቃ መንግሥታትም፣ የአገራቸው ክቡርና አኩሪ ታሪክ፣ የነፃነታቸው ማረጋገጫ፣ የመሬታቸው ባለቤትነት ማስመሰከርያ እንዲሆን የመረጡት፣ እነኚሁኑን የኢትዮጵያን ሰንደቅዓላማ ሦስቱን ቀለማት በመዋስና፣ መሠረት በማድረግ ስለነበር፣ ዛሬ “የመላዋ አፍሪቃ ቀለማት” በመባል ይታወቃሉ።

የኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማ ከፍተኛ አድናቆት በዚህ ብቻ አላበቃም። የአድዋ ድል፣ የጥቁር ሕዝብ ተጋድሎ ደጋፊ የነበረውንና በዘመናዊ ፈጠራው የታወቀውን፣ ጋሬት አውጉስቱስ ሞርጋን[13]ን ከኢትዮጵያ ጋር ሊያተሳስር በቅቷል። የመኪናና የተለያየ ተሽከርካሪ በዓለም ላይ ብቅ ማለት፣ መጓጓዣ መንገዶቹን እጅግ በጣም አጨናንቆ፣ ብዙ ሕዝብ ለአደጋ ሲያጋርጥ፣ ለሞት ሲዳርግ፣ ብዙ ቢሞከርም ፍቱን መፍትሔ ሊገኝ አልተቻለም። የተቻለው፣ በአ. አ. በ፲፱፻፳፪ ዓ. ም. ላይ፣ አቶ ሞርጋን የኢትዮጵያን ሰንደቅዓላማ ቀለሞች ለትራፊክ መብራት አገልግሎት በማዋሉ ነው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ፣ ሦስቱ የኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማ ቀለማት፣ ዘመናዊ ተሽከርካሪ በሚጓዝበት መንገዶች፣ በመላው ዓለም ከዳር እስከ ዳር፣ የሰውን ልጅ መመላለሻ ጠባይ ተቈጣጣሪ ሁነዋል። ሦስትዬው ቀለማት የትራፊክ መብራት በያለበት፣ የሕግ አስጠባቂና አስከባሪ ኀይል ብቻ ሳይሆን፣ አገልግሎቱን ከጀመረበት ወቅት ጀምሮ፣ የብዙውን ሰው ሕይወት ከሞት አድነዋል፤ ትርምስምስና ጭንንቅ ከየመገናኛ መንገዱ አስወግደው ዘርና አካባቢ፣ ቋንቋና ባህል፣ እምነትና የትምህርት ደረጃ፣ መደብና ማዕርግ፣ ዳራና ፆታ ሳይለዩ፣ ሁሉንም በእኩልነትና በትክክል፣ በሥነሥርዐትና በመከባበር እያስተናገዱ ይገኛሉ።

እንግዴህ ሊቅ ነጋሦ የሚያጥላሉት ሰንደቅዓላማ በኢትዮጵያ ረጅም ታሪክና ጥልቅ ምሥጢር ያለው ብርቅ ቅርስ ብቻ ሳይሆን፣ ለብዙ የዓለም ክፍሎችም የነፃነታቸውና ያገራቸው ባለቤትነት ምልክት ሁኖ ያገለገለ ነው። ከኢትዮጵያ ገጸምድር አላንዳች ማመነታት መጥፋት ያለበት ሰንደቅዓላማ ቢኖር ልሙጡ ሳይሆን ባለኮከቡ ነው። ይኸ ሰንደቅዓላማ እጅግ በጣም አስከፊ ታሪክ ውጤት መሆኑ አይካድም። ለመረዳት ከፈለግን የሕወሓትን ታሪክ መመልከት ግድ ይሆንብናል።

በየካቲት ወር በ፲፱፻፷፰ ዓ. ም. ባወጣው በመጀመርያ እትም መግለጫው፣ ሕወሓት የትግራይ የተፈጥሯዊና ማኅበራዊ ችግሮች መሠረታዊ ምክንያት የሆኑት ሦስቶቹ ኢምፐርያሊዝም፣ ባላባታዊ ሥርዐትና የአማራብሔረሰብ መሆኑን እንደዚህ ሲል ይገልጣል።

“የትግራይ ሕዝብ ለረጅም ዘመን ሰብኣዊና ፖለቲካዊ መብቱ ተነፍጎ ሲጠላና ሲናቅ” የኖረበት ምክንያት “ጨቋኝዋ የአማራ ብሔር ሆነ ብላ እንደመንግሥት መመሪያዋ አድርጋ” ስለሠራችበት ነው። እንዲሁም ደግሞ በትግራይ ሥራ ታጥቶ “ሕዝቡ በሽርሙጥናና በስደት”፣ እንዲሁም “በረኀብ፣ በድንቊርናና በበሽታ እየተሠቃየ” ያለበት “መሠረታዊ ምክንያት ኢምፐርያሊዝምና ባላባታዊ ሥርዓት.…ጨቋኝዋ የአማራ ብሔር የምታደርገው የኤኮኖሚ ብዝበዛና የፖለቲካ ጭቈና” ነው። ስለዚህ “ጨቋኝዋ የአማራ ብሔር ጭቈናዋ እስካላቆመች ድረስ ኅብረተሰቧ ዕረፍት አታገኝም።

የሕውሓት መግለጫ ያስቃል ብቻ ሳይሆን፣ ያሳዝናልም። በሐሰትና የተዛባ ርእዮተ ዓለም የተመሠረተ ስለሆነ። ልክ ሒትለር የጀርመኖችን ችግር በአይሁዶች፣ እንዲሁም የግራዘመም ርእዮተዓለም ባላቸው ግንባሮችና ግለሰቦች ላይ እንደጣለ ሁሉ፣ ሕወሓትም በጭንቅላቱ እንጂ በትግራይ ውስጥ በውን ህልውና በሌላቸው ምክንያቶች ላይ ነበር የትግሬ ሕዝብ ጠላቶች ብሎ ይጮህ የነበረው።

ኢምፐርያሊዝም፣ ጥቅማጥቅም ሊገኝባቸው ይቻላል በተባሉት አገሮች በቅኝ ግዛት፣ ወይንም በጦር ኀይል፣ ወይንም ሌላውንም ዐይነት ስልት በመጠቀም አንዱን አገር በግልጥ፣ ካልተቻለም በሥውር መቈጣጠር ይገባል በሚል ርእዮተ ዓለም የተገነባ የፓለቲካ ሥርዐት ነው። ሁላችንም እንደምናውቀው፣ ብዙውን ጊዜ ይኸ አስተሳሰብ ከምዕራባውያን መንግሥታት ጋር ተቈራኝቶ ይገኛል። ምን ሊያገኙ ሲሉ ነው ምዕራባውያን ትግራይን ለመቈጣጠር ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን የሚያጠፉት። ይኸንን ያህል ደደቦች ስላልነበሩ አላደረጉም፤ ሊያደርጉም አልሞከሩም። ኢምፐርያሊዝም ሌላው ቀርቶ፣ ትግራይ የምትባል አገር መኖሯን እንኳ እንደሚያውቅ ማስረጃ ያለ አይመስለኝም።

የባላባታዊ ሥርዐትስ። ባላባታዊ ሥርዐት በአብዛኞቹ የአውሮጳ አገሮች በመካከለኛ ዘመነምሕረት ላይ የተከሠተ የመሬትና የሥልጣን አደላደል ነው። በዚህ ሥርዐት ንጉሡ ለመሳፍንቱ መሬት ያድላል፤ እነሱም በለውጡ የውትድርና አገልግሎት ይሰጡታል፤ ከሥራቸው ያሉት ደግሞ በተራቸው ጢሰኞቻቸው ሲሆኑ፣ አራሹ ክፍል ለይስሙላም ቢሆን ከጌቶቹ ለሚለገሥለት የጥበቃና የጸጥታ አገልግሎት ውለታ ሲል በመሬታቸው ላይ ለመኖር፣ እጅመንሻ ለመስጠትና ከምርቱ የተመደበለትን ሊከፍል ይገደዳል። ታዲያ ይኸ ዐይነት ሥርዐት በትግራይ ነበር ወይ ቢባል ስለመኖሩ ምንም ዐይነት ማስረጃ የለም። በትግራይ ቀርቶ በማንኛውም የኢትዮጵያም ሆነ የአፍሪቃ ክፍል መኖሩን የሚያረጋግጥ ሰነድ የለም። መግለጫው በወጣበት ወቅት እየተጠናከረ ይሄድ የነበረው የድልብ ማለትም የካፒታሊስም እንጂ ባላባታዊ አልነበረም።

አማራስ። ለመሆኑ አማራ ምንድር ነው። ስለዚህ ብዙ ተጽፏል፣ ብዙም ተነግሯል። እኔም በተለያዩ ወቅቶችና መድረኮች በጉዳዩ በመጠኑ ጽፌአለሁም ተናግራለሁም። ሰፋ ያለ ማብራርያ የፈለገ እዚያ እንዲያነብብ ይጋበዛል[14]። እንዲያው ለነገሩ ያህል፣ አጠር ያለ ገለጣ ልስጥና ልቋጭ። ሕወሓት ሥልጣን እስከያዘበት ዘመን ድረስ፣ አማራ የሚለው ቃል መቼም ጊዜ ከአንድ ብሔረሰብ ጋር ተቈራኝቶ አይታወቅም። ኢትዮጵያውያንም ሆኑ የውጭ አገር ደራሲዎች አማራ ሲሉ የሚያመለክቱት፣ አሁን ወሎ በመባል የሚታወቀውን ክፍለአገር፣ ወይንም አሁንም ቢሆን እዚያው ጠቅላይ ግዛት ውስጥ የሚገኘውን የአማራሳይንትን ምድር ነው፤ አለበለዚያም ኢትዮጵያዊ የሆነውን በሙሉ ነው። በአማራ ምድር ይኖር የነበረው ሕዝብ የመጣው ደግሞ ከአክሱም ነው ይባላል።

ሕወሓት አማራ ሲል ነገሥታቱን ይሆን የሚያመለክተው። ነገሥታቱ አማርኛ ይናገሩ እንጂ፣ የመጡት ከተለያዩ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ መሆኑ ግልጽ ነው። ትግራይ ደግሞ ይተዳደር የነበረው ከማንኛውም የኢትዮጵያ ግዛቶች ይበልጥና በተሻለ ሁናቴ በገዛ ራሱ ምድር ተወላጆች እንጂ ከሌላ አካባቢ በመጡት ሹሞች አልነበረም።

ሕውሓት አማራ የሚሉት አማርኛ ተናጋሪውን ከሆነ፣ አማርኛ ቋንቋ እንጂ ብሔረሰብ አይደለም። ሕወሓት ሥልጣን ይዞ አገሪቷን በብሔር እስከወቃቀረ ድረስ፣ አማርኛ ተናጋሪ የብሔረሰብ አመለካከት ስላልነበረው፣ ራሱን እንደጐሣ ቈጥሮ አያውቅም። አማርኛ ይልቅስ የኢትዮጵያ ሕዝብ ርስበርሱ ሊግባባ የፈጠረው የመላ ኢትዮጵያውያን የጋርዮሽ ቋንቋ ነው። የኢትዮጵያን ብሔረሰቦች በሙሉ ለማንኛዉም ሳያዳላ የሚወክል፣ ከማንኛውም ጋር የማይተሳሰር፣ ሲናገሩት ጉሮሮ የማይከረክር፣ ምላስ የማያዶለዱም፣ ገለልተኛ፣ ግልጽና ጥርት ያለ ቋንቋ ነው።

አማራም ሆነ፣ ትውልዱ ትግራይ ያልሆነ አማርኛ ተናጋሪ፣ ወደትግራይ ሄደ ቢባል፣ በጣት የሚቈጠር መሆን አለበት። ከሄደም በተሰጠው የሥራ አላፊነት ተገድዶ እንጂ፣ በፈቃዱ ወዶ ነው ማለቱ ይከብዳል። በተለይም ከአፄ ምኒልክ ዘመነመንግሥት ጀምሮ የሕዝብ ፍልሰት የነበረው ከሰሜን ወደደቡብ እንጂ ከደቡብ ወደሰሜን አልነበረም። ስለዚህ የትግራይ ተወላጆች በተለያዩ ምክንያቶችና ጊዜ፣ የመላዋን የኢትዮጵያ መሬት ከጫፍ እስከጫፍ አዳርሰዋታል። በቀረው የኢትዮጵያ ምድር እነሱ ያልረገጡት መንደር፣ ያልተሰማሩበት የሥራ ዘርፍ የለም ማለት ማጋነን አይሆንም። ታዲያ እውነቱ እንደዚህ ከሆነ፣ የትኛው የአማራ ብሔረሰብ ነው ትግራይን የበዘበዘው፤ እንዴትስ ብሎ ነው ወደትግራይ የደረሰው፣ ምንስ ፈልጎ ነው ብሎ መጠየቅ ተገቢ ይመስለኛል። እዚያ ካልሄደ፣ የሚበዘበዝ ነገር ባገሩ ከሌለ፣ እንዴት ነው ሕውሓት ከመሬት ተነሥቶ የአማራን ብሔረሰብ ደመኛ ጠላቱ ሊያደርግ የበቃው። የሕወሓት መግለጫ ያነበበ ድርጅቱን አዙሮ የማያይ የጥራዘነጠቆች ወይንም የአእምሮ ቀውስ ያላቸው ሰዎች ጥርቅም ነው ቢል የተሳሳተ አስተያየት ነው ማለቱ በጣም ይከብዳል። ትክክል አይደለም ብሎ መሟገትም ያዳግታል። እውነቱን ለመረዳት ብዙም ርቆ መሄድ አያስፈልግም። መግለጫው ራሱ ይበቃል።

እንግዴህ ሕወሓት ከመነሻው የአማራ ብሔረሰብ ዋና ጠላቱ መሆኑን ለይቶ ከወሰነ በኋላ ነው፣ አገሩንም ሕጉንም ያወቃቀረው። አወቃቀሩም ይኸንኑ ብሔረሰብ ለማጥቃትና ለማጥፋት በሚያመቻችልለት መንገድ ነበር ቢባል በተከታታይ የፈጸማቸው ሥራዎች በእማኝነት ሊጠሩ ይችላሉ።

በመጀመርያ ደረጃ፣ በትግራይ የበላይነቱን ካረጋገጠ ወዲያ፣ የተዛባ ርእዮተ ዓለሙን በግብር ላይ ለማዋል የሚረዱትን አቋሞች ለማደላደል፣ ሕወሓት ሁለት ግንባር ከፈተ። ባንድ በኩል አጋር ድርጅቶችን በአምሳሉ ጠፍጥፏቸው ሊፈጥር አስቦ አባላት የመመልመል ዘመቻውን ተያያዘበት። ለዚህም ሲል፣ ባላንጣው ከነበረው የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ(ኢሕአፓ)ና መሰሎቹ ግራዘመም ድርጅቶች፣ መርሃግብሩን ለማሳመን የቻላቸውን ግለሰቦች ከራሱ ጋር ቀላቀለ። እምቢ ያሉትን በመደምሰስና ከአካባቢው በማባረር አስወገዳቸው። ድርጅታዊ መዋቅር ለሌላቸው ብሔረሰቦች ደግሞ፣ በእጁ ያሉትን የጦርሠራዊት ምርኮኞችንና በብሔረሰብ ልሂቃን ስም ከየቦታው ያጠራቀማቸውን ግለሰቦች፣ የየአካባቢያቸው ተወካዮች እንደሆኑ በማሰብ ድርጅታዊ ዕውቅና ሰጣቸው። እነዚህን ሕወሓት የመርሀግብሩ አስፈጻሚ ይሆናሉ ብሎ ያቋቋማቸውን አጋር ድርጅቶች፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) የሚል ጉራማይሌ ስም ሰጣቸው።

በዚህ መልክ የኦሮሞ ብሔረሰቦች ተወካይ እንዲሆን፣ ሕወሓት ከፈጠራቸው የኢሕአዴግ ድርጅቶች አንዱ፣ የኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲአዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ነው። ሊቅ ነጋሦም ለኢሕአዴግ አባልነት የበቁት በዚህ ድርጅት ጥላ ሥር በመሆን ነው። እንግዴህ ሊቁ ከጥንስሱ አንድ የተለየ ብሔረሰብን ነጥሎ ለማጥፋት የተቋቋመው ሕወሓት ዋና አዋላጅ ከሆኑት አንዱ መሆናቸው አይካድም።

የኢሕአዴግን አወቃቀር ያካሄድ በነበረበት ወቅት፣ ሕወሓት ከመሰል የትግል ጓዶቹ፣ ማለትም በአቶ ኢሳይያስ በሚመራው የኤርትራ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር ሊቀመንበርነት፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አጋፋርነት፣ ድርጅቱ በ፲ሺ፱፻፹፫ ዓ.ም. በጋ ላይ በኤርትራ ውስጥ ተሰነይ በተባለ ከተማ በተካሄደው ስብሰባ ኢትዮጵያን በጐሣ በሚሸነሽን ሕገመንግሥት ተስማማ። የሕገመንግሥቱን ቊልፍ ነጥቦች አርቅቆ ለሕወሓት መሪ ለአቶ መለስ ዜናዊ ሰጠው የሚባለው ከኦነግ ዋኖች አንዱ የሆነው አቶ ሌንጮ ለታ ነው።

የዚህ ሁለቱ ርምጃዎች መጨረሻው ውጤት የክልሎች መንግሥታት መፈጠርና የ፲፱፻፹፮ ዓ. ም. ሕገመንግሥት መጽደቅ ነው። ሁለቱም ድርጊቶች ሕወሓት አማራን ነጥሎ በማነጣጠር የመምታት ዓላማውን ለማሳካት ከመርሀግብሩ አስፈጻሚ ኢሕአዴግ ጋር ሁኖ የገነባው የአስተዳደር መዋቅር አካል ናቸው።

በመጀመርያ ደረጃ፣ ሕወሓት ከኢሕአዴግ ጋር ሁኖ ክልል በመባል የሚታወቀውን የአስተዳደር መዋቅር ገነባ። የኢትዮጵያን ሕዝብ በሰማንያ ያህል የትውልድ ዝርያ ከፋፍሎ አንዱን ብሔር፣ ሌላውን ብሔረሰብ፣ የቀረውን ሕዝብ በማለት በትርጒምየለሽ ቃላት አማትቶ ሲያበቃ፣ አገሪቷን ሸንሽኖ ዘጠኝ ክልሎች ፈጠረ። በየክልሉ የሚኖረውን የሕዝብ አንድነትና እኩልነት ያረጋግጣል በማለት፣ ኮከብ ያለበትን አርማ በሰንደቅዓላማው ላይ ለጠፈበት።

የክልል ዓላማ ሕዝቡ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር ነው። እውነቱ ግን ከላይ እንደገለጽሁት ለሕወሓት ክልሎች የመግለጫውን ዓላማ የሚያሳካባቸው ረጃጅም ቀኝ እጆቹ ናቸው። ስለዚህ ክልሎች ሥራችን ብለው የያዙት፣ አማርኛ ተናጋሪውን በስመ “ነፍጠኛ”፣ “የምኒልክ ሰፋሪ”፣ “ጨቋኝ” ወይንም “የጨቋኝ ቡድን” እያሉ በማሳበብ፣ ልሕቅና ደቂቅ፣ ወንድና ሴት፣ ሕፃንና ሽማግሌ፣ ነፍሰጡርና አሮጊት ሳይለዩ በጅምላ ልዩልዩ ስልትና መሣርያ እየተጠቀሙ ሲገድሉ፣ ሲጨፈጭፉ፣ ሀብቱንና ንብረቱን ሲነጥቁ፣ ግለሰቦችን ሲያፈናቅሉ እስከዛሬ ድረስ ኑረዋል። ልክ በአውሮጳ ከጀርመን ቊጥጥር ሥር የነበሩ ግዛቶች በናዚዎች የተዛባና የሐሰት ስብከት ተመርተው፣ በአይሁዶች ላይ የፈጸሙትን ግፍ፣ ክልሎችም በሕወሓት በሚንቀሳቀሰው የኢሕአዴግ መሪዎች ቅስቀሳ፣ በአማርኛ ተናጋሪው ሕዝብ ላይ ከዚያ የማይተናነስ ኢሰብኣዊ ጭካኔና የዘር ማጽዳት ተግባር እንደፈጸሙ መታወቅ ይገባል።

ሕወሓት አማርኛ ተናጋሪውን ያሳደደው በመግደል፣ ንብረቱን በማውደም፣ በማፈናቀል ብቻ አይደለም። ባንድ በኩል፣ የክልሉን አስተዳደር መስፈርቱን በማያሟሉ ግለሰቦች ሞላ። አስተዳዳሪዎቹ አማርኛ ቢናገሩም፣ ወይንም በአማራ ክልል ቢወለዱም፣ በትውልድ ሐረጋቸው ከሌላ አካባቢ የመጡ ወይንም የአማራን ጥቅምና መብት ከማስጠበቅ ይልቅ ራሳቸው አሳዳጆቹ ከመሆን አልተቈጠቡም። በሌላ በኩል፣ ሕወሓት ክልሉን እየሸረሸረ እጅግ በጣም ሰፊ መሬት ወደትግራይ አስገብቷል። ከዚያ ባሻገር፣ በብዙ ሚሊዮን የሚቈጠሩ አማርኛ ተናጋሪዎች በቀሩት ስምንቱ ክልሎች መኖራቸው እየታወቀ፣ ዜግነታዊ መብታቸውን አስገፍፎባቸዋል። በያሉበት ምንም ውክልና የላቸውም። በቋንቋቸው ሊማሩና ሊያስተምሩ አይችሉም፤ የመምረጥና የመመረጥ መብት ተነፍጎባቸዋል። በማንኛውም ጊዜ አስተዳደሩ ከፈለገ ከክልሉ ቢያባረር የሚጠይቀው የለም።

ባለኮከቡ የኢሕአዴግ ሰንደቅዓላማ እንደተባለው የእኩልነትና የአንድነት ምልክት መሆኑ ቀርቶ፣ ልክ እንደየጀርመን ናዚ እስዋስቲካ የጥላቻ፣ የስደት የግድያ ምንጭ ሆነ። ሊቅ ነጋሦም የኢሕአዴግ አባል ድርጅት አካል የሆኑት የኢትዮጵያን ታሪክ በተንሻፈፈና በተዛባ የሕወሓት ጠማማ መነጽር ብቻ ለማየት ዝግጁ በመሆናቸው ይኸንን እውነት ሊረዱ የቻሉ አይመስልም። የታሪክ ምሁር ቢሆኑም ዕውቀቱ የላቸውም ብቻ ሳይሆን የማሰላሰል ችሎታቸው ምን ያህል ዝቅተኛ መሆኑን አንድ ወቅት በድርጅታቸው ርእዮተ ዓለም ላይ ከመሪያቸው አቶ መለስ ጋር አለመግባባት ተፈጥሮ ሊቁን ሁለትና ሁለት አራት መሆኑን የማያውቅ መሃይምን መሆናቸውን በማሽሟጠጥ እንደነገራቸው ራሳቸው “የነጋሦ መንገድ” በሚለው መጽሐፋቸው ያጫወታሉ። እኔም በበኩሌ ስለሳቸው ያለኝ አስተያየት ከዚሁ የማይለይ መሆኑን በጽሑፌም፣ በንግግሬም ገልጫለሁና[15] እዚህ ብዙ መለፍለፍ አያስፈልገኝም።

ሊቅ ነጋሦ እጅግ አድርገው የሚያጣጥሏቸው አፄ ምኒልክም ሆኑ አፄ ኀይለሥላሴ በአስተዳደር ብቃትም ሆነ፣ በሕዝብ ዘንድ ባላቸው ተቀባይነት፣ እንዲሁም የሥልጣናቸው መሠረት ከድርጅታቸው እጅግ በጣም የተለየ መሆኑን የተረዱ አይመስሉም። በዚህ ረገድ፣ ስለአፄ ምኒልክ ታላቅነት ከዚህ በላይ በቂ ስላልሁ ሌላ መጨመሩ አስፈላጊ አይመስለኝም። ስለሳቸው ታላቅነት ያለኝን ግንዛቤና ዕይታ ማወቅ ለሚፈልግ “ምኒልክን ብትወቅሱ ማንነታችሁን ትረሱ” በሚል ርእስ የጻፍሁትን ንኡስ መጽሔት እንዲያነብ እጋብዛለሁ። አሁን ግን ብዙም ያልሁት ስለሌለ ወደአፄ ኀይለሥላሴ ልግባ።

አፄ ኀይለሥላሴ ወደኢትዮጵያ ዙፋን የወጡት የሰው ደም ሳይፈስ፣ ንብረት ሳይነካ፣ በዘመኑ በነበረው በምርጫ ሥርዐት በታላቅ ክብርና ማዕርግ በሕዝብ በጎ ፈቃድ ነው። መኳንንቱና ቤተክህነቱ፣ ሕዝቡም ከሊቅ እስከደቂቅ ባንድ ላይ ሁኖ ባንድ ድምፅ በእልልታና በደስታ መርጧቸዋል። ይኸም ማለት፣ እንደደርግ ሰላማዊ ሕዝብ እየጨፈጨፉ፣ ንብረት እያወደሙ ሥልጣን አልያዙም። እንደ ሕወሓት ደግሞ ዐሥራሰባት ዓመት በጫካ ተዋግተው፣ ንብረት አውድመው፣ ደም አፍስሰው አለውድ በግድ በጠመንጃ ኀይል በሕዝብ ላይ አልተጫኑም። በዚህ የታሪክ መነጽር ካየን፣ የኮከቡ ሰንደቅዓላማው ሕጋዊነት ዋጋ-ቢስ ይሆናል። በዚህ መልክ ወደሥልጣን የመጣ መንግሥት የደነገገውን ሰንደቅዓላማ መቀበል ማለት ደግሞ በግፍ በጠመንጃ ኀይል በሕዝብ ላይ ተጭኖ በጡንቻው ለሚገዛው መንግሥት ሕጋዊ ዕውቅናን መስጠት ይሆናል።

ብዙ ጊዜ አንዳንድ ጸሓፊዎች በሕወሓት የሚመራውን የኢሕአዴግን መንግሥት ከጀርመኑ ናዚና ከኢጣሊያኑ ፋሺዝም ሲያመሳስሉ አነብባለሁ። እኔ ራሴ ከላይ እንዳልሁት ንጽጽሩ ተገቢ ነው። ግን የሦስቱም ዐመፃቸውና ግፋቸው እንዳለ ሁኖ፣ ኢሕአዴግ በብዙ መልኩ ከሁለቱም የከፋ መሆኑን አስተያየት ሰጪዎቹ የተገነዘቡ አይመስልም። ናዚዎችም ሆኑ ፋሺስቶች ሥልጣን የጨበጡት በሕጉ ደንብ በምርጫ ተወዳድረው በማሸነፍና የሕብን ውክልና አግኝተው ነው። ኢሕአዴግ ግን ዙፋኑን የተቈናጠጠው በጠመንጃ ኀይል ነው። ናዚዎች እሥልጣን ላይ ሲወጡ ወደአርባ ዐምስት ከመቶው የጀርመን ሕዝብ ሥራ ፈት ነበር። ሥልጣን ከያዙ ሦስት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አንድም ሥራ-ፈት ጀርመን አልነበረም ይባላል። የኢሕአዴግ መንግሥት ግን የተሰማራው ሥራ በመፍጠር ሳይሆን ያገሩን ሀብት በመበዝበዝና በመግፈፍ ነው።

የባለኮከቡን ሰንደቅዓላማ ሕጋዊነት ለመረዳት ሕጉን ራሱን መመርመር የግድ ይሆንብናል። ሕግ በተደገነነለት ሕዝብ መካክል አድልዎና ልዩነት ሳያሳይ፣ ለሁሉም እኩል አገልግሎት መስጠት ይኖርበታል። ሕግ የማንም የአገሪቷ ዜጋ የመጨቈኛ መሣርያ ሁኖ መገኘትም መታየትም የለበትም። አለበለዚያ ሕግነቱ ዋጋ ስለሌለው፣ ተጨቋኙ ብቻ ሳይሆን የቀረው የአገሪቷ ሕዝብ የተቻለውን መሣርያ በመጠቀም መዋጋት ይኖርበታል። የኢሕአዴግ ሕገመንግሥት ሕወሓት የአማራ ብሔረሰብን ለማጥፋት ያቀናጀ መሣርያ መሆኑን ዐይተናል። በዚህ ሥርዐትና ደንብ የጸደቀውን ሰንደቅዓላማ ነው ሊቅ ነጋሦ የነፃነት፣ የእኩልነትና የአንድነት አርማ ብለው የሚፈርጁ። የኢትዮጵያ ሕዝብ የተገነዘበው ግን እሳቸው በሚሉት መልክ አይደለም። ለኻያ ሰባት ዓመት የተጋረጠው የግፍና የሰቈቃ፣ የእስራትና የግድያ ምልክት አርማ ነው። ስለዚህ በየቦታው ታሪካዊውንና ከአያቶቹ የወረሰውን፣ ከኢትዮጵያ አገሩ አልፎ የዓለም ግርማ የሆነውን ክቡር ሰንደቅዓላማ በየከተማው በነቂስ ይዞ እየወጣ ኢሕአዴግን ወግድ እያለ ነው።

ሕወሓት የፈጸመው ግፍ ብቻውን እንዳላደረገው ተደጋግሞ ተነግሯል። በዚህ እኩይ ተግባሩ ዋና ጀሌውና ቀኝ እጁ ሕገመንግሥቱን አብሮ አርቃቂው ኦነግ እንደነበረ፣ ዓለም ያወቀው ፀሓይ የሞቀው ጉዳይ ነው። ኦነግ ልክ እንደሕወሓት፣ ኢትዮጵያን ማፍረስና አማርኛ ተናጋሪውን መጨረስ እንደዋና ዓላማው አድርጎ ይንቀሳቀስ የነበረ ድርጅት ነው። በቅርቡ አማርኛ ተናጋሪ ሕዝብ በቀመሰው ግፍ ኦነግን ከደሙ ንጹሕ አስመስሎ ለማቅረብ ዘመቻ ተሞክሯል። እውነቱ ግን በኢትዮጵያና በማንኛውም የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ለደረሰው ታላቅ እልቂት ሕወሓትም ሆነ፣ ኦነግ ከነመሪዎቻቸው (አሁን በአዲስ ድርጅት ስም የሚጠሩ እነሌንጮ ለታ የመሰሉትን የዱሮ የኦነግ መሪዎችን ጭምር) በትክክል ተጠያቂ መሆናቸው መረሳት ያለበት አይመስለኝም። ሕወሓት እሥልጣን ላይ ሲወጣ፣ ኦነግ በጊዜው የነበረውን የፖለቲካ ቀውስ በመጠቀም፣ ክልሌ ነው በሚልበት አካባቢ፣ በኤርትራው ሻቢያ ችሮታ እየተንቀሳቀሰ፣ ይዞታውን ለማስፋፋት ይሯሯጥ በነበረበት ወቅት፣ አማርኛ ተናጋሪውን ብቻ ሳይሆን፣ መጤ ብሎ የፈረጀውን ኢትዮጵያዊ በሙሉ፣ ያባርርና የሰው አንደበት መግለጥ በማይቻል ጭካኔ ይገድል እንደነበር በሰፊው ተመዝግቧል። ሕወሓትም በአምሳሉ በጠፈጠፈው በኢሕአዴግ አማካይነት፣ ሥልጣኑንም ሆነ ጭፍጨፋውን የተቋደሰው ከኦነግ ጋር ነው። ሊቅ ነጋሦ የባሕርዳር ሕዝብ የአራጁን ድርጅት ሰንደቅዓላማ ሳይዝ ቢወጣ ሳይዘገዩ የዜና አውታሮችን ጠርተው ተቃዉሟቸውን አሰምቷል። ኦነግ ግን ኢትዮጵያን አፍርሶ ነፃ አገር ለማቆም ያዘጋጀውን ሰንደቅዓላማ አንግቦ ሰልፍ እንደወጣ አልሰሙም ማለት ያዳግታል። ከሰሙ ለምን አንዲትም የተቃዉሞ ቃል አልተነፈሱም ብሎ መጠየቁ አስፈላጊ ነው። ሰምተው ዝም ብለው ክከሆነ ርካሽ ስብከትና ፍርደገምደልነት ማለት እንደዚህ ነው። ካንድ ምሁር ቀርቶ ከማንም አላፊነት ከሚሰማው ተራ ዜጋ የሚጠበቅ አይመስለኝም።

ንግግሬን ከአሁን አሁን እቋጫለሁ ብል አልሆነልኝም። ግን በጥቂት ቃላት ልደምድመው። እኔ እንደምረዳውና ከዚህም በላይ በተጨባጭ እንደተገለጸው፣ የኢሕአዴግ ክልልና ሕገመንግሥት ለመስማት የሚቀፍ፣ ለማሰብ የሚሰቀጥጥ፣ ለማየት የሚያስበረግግ፣ ለመጻፍ የሚያስደነግጥ በሰው ኅሊና የማይታሰብ ግፍ ሠርተዋል። ሰንደቅዓላማው የሚያሳስበው ይኸንን እውነታ ነው። ከናዚዎቹ እስዋስቲካ የሚለይበት ምክንያት በምንም መልክ አይታየኝም። ሁለቱም የክፋት ዐዘቅት ምልክት ናቸው። የዚህ ዐይነት ኢሰብኣዊ ጭካኔ ማስታወሻ የሆነውን ሰንደቅዓላማ በእጁ እንዲይዝ ከኢትዮጵያን ሕዝብ መጠበቅ፣ ልክ አይሁዶችን የናዚዎችን እስዋስቲካ በደስታ እያውለበለቡ ሠርግቤት እንዲሄዱ እንደማስገደድ ነው። ፍትሕና ርትዕ፣ አንድነትና እኩልነት፣ ሰላምና ፍቅር የሚመኝ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በእጁ ሊነካው አይገባውም። እንደዚሁ፣ ማንም ኅሊና ያለው ግፍ የሚጠላ መሪ ደግሞ፣ ሳይውል ሳያድር ሕወሓት ለዘር ማጽጃ ዓላማው ማስፈጸሚያ የሸረባቸውን ሦስቱን መዋቅሮች እስክነአካቴአቸው ማጥፋት ይጠበቅበታል። እነሱም የሕወሓት ክልል፣ ሕገመንግሥትና ሰንደቅዓላማ ናቸው። ልክ የናዚ ተቋማትና ሥርዐት እንደተደመሰሱ ሁሉ፣ የኢሕአዴግንም ማውደም አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ።

ቸር ይግጠመን።

[1] Stanislaw Chojnacki, “Third Note on the History of the Ethiopian National Flag: The Discovery of Its First Exemplar and the New Documents on the Early Attempts by Emperor Menilek to Introduce the Flag,” Rassegna di studi Etiopici, vol. 26 (1980-1981) ገ. 34-36. [2] . C. H. Michel, Vers Fachoda à l’encontre de la Mission Marchand à travers l’Ethiopia (Mission de Bonchamps), (Paris, 1900) ገ. 247. [3] . ኀይለማርያም ሠራቢዮን (አ. አ. 1863-1929) [4] . ጸጋ ዘአብ፣ የኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማ ትርጒም [5] . ነጋድራስ ደስታ ምትኬ፣ የኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማ የተመሰለው ትርጓሜ [6] ጸሐፌ ት እዛዝ ገብረሥላሴ፣ ታሪከ ዘመን ዘዳግማዊ ምኒልክ ንጉሠነገሥት ዘኢትዮጵያ፣ (አዲስ አበባ፣ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት)፣ገ. ፻፵፮። [7] . Šihab ad-Din Ahmad bin abd al-Qadr [8] . Manoel Barradas (1572-1646) [9] . Abraham Ortelius (1527-1598). [10] . Wllem Janszoon Blaeu (1571-1638). [11] . Marcus Mosiah Garvey, 1887-1940. [12] . ማርኩስ ጋርቬይ (Marcus Mosiah Garvey, 1887-1940) የኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማ ቀለማት መስለውት፣የመላው ጥቊር ሕዝብና አገር የማንነት መለዮና መግለጫ እንዲሆኑ ያወጃቸው ቀለማት ጥቁር፣ አረንጓዴ፣ ቀይ ናቸው። በኢትዮጵያው ብጫ ቀለም ቦታ በስሕተት ጥቊር መጠቀሙን የተረዳው ቈይቶ ነው ይባላል። [13] .Garrett Augustus Morgan, 1875-1963. ሞርጋን ብጫ ቀለም እንደማስጠንቀቂያ በመጨመሩ፣ ዘመናዊው ተሽከርካሪ ያደርስ የነበረው አደጋ በከፍተኛ ደረጃ በመቀነሱ፣ የፍልሰፋውን መብት፣ ጀነራል ኤለክትሪክ ኩባንያ በአ. አ. በ፲፱፻፳፫ ዓ. ም. በአርባሺ የአሜሪቃ ብር ገዝቶት፣ ሦስቱ የኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማ ቀለማት የመላው ዓለም ዘመናዊ መጓጓዥ ዋና ተቈጣጣሪ ቀለማት ሁነዋል። [14] . የፈለገ “ከታሪክ መዝገብ !ለመሆኑ አማራ ማነው?”
https://welkait.com/wp-content/uploads/2016/08/8-12-2016-Who-Are-The-Amhara.pdf“ከታሪክ መድረክ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ትላንትናና ዛሬ።”

https://www.zehabesha.com/amharic/wp-content/uploads/2018/06/ETHIOPIA-AND-ETHIOPIANISM-6-19-2018-1.pdf

የሚሉትን ንኡሳን ጽሑፎች ያንብብ።

[15] . የፈለገ የሚከተሉን ማንበብ ወይንም ማየት ይችላል።
https://ethsat.com/2017/01/esat-special-ethiopians-prof-haile-larebo-10-jan-2017/
https://ethsat.com/2017/01/esat-special-ethiopians-prof-haile-larebo-part-two-21-jan-2017/ ;ምኒልክን ብትወቅሱ ማንነታችሁን ትረሱ

https://welkait.com/wp-content/uploads/2014/02/emperorMenelikIsTheGreat.pdf

ፌስቡክዎን በመጠቀም እዚህ ላይ አስተያየት መስጠት ይችላሉ