አብዲ ኢሌና ተባባሪዎቹ ለፍርድ ይቅረቡ!” ብላቹህ ብትጠይቁ የአገዛዙ ምላሽ ምን የሚሆን ይመስላቹሃል???

መሰንበቻውን ወያኔ የሶማሌ ክልል በሚለው የሀገራችን ክፍል ለተፈጠረው አውዳሚና ዘግናኝ ቀውስ ተጠያቂ የሆነው አብዲ ኢሌ መታሠሩን ግልጽ ባልሆነ መንገድ የኮሚውኒኬሽን (የተግባቦት) ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊው አቶ አሕመድ ሽዴ በወቅቱ አስታውቆ ነበር፡፡ ከአብዲ ኢሌ ጋር የታሰሩ ሌሎች ወንጀለኞች ስለመኖራቸው የሰማነው ነገር የለም፡፡

አብዲ ኢሌን በተመለከተም እስከአሁን ባለው ጊዜ ፍርድ ቤት አልቀረበም፡፡ የታሰረበት ቦታም አይታወቅም፡፡ ሕገመንግሥታቸው አንድ እስረኛ በታሰረ 24 ሰዓት ባልበለጠው ጊዜ ውስጥ ፍርድ ቤት እንዲቀርብ ያስገድዳል፡፡

እኔ የምሠጋው አቶ አብዲ ኢሌ ፍርድ ቤት ቀርቦ ለሰሞኑ ብቻ ሳይሆን ለዘመናት ለፈጸመው አረመኔያዊ ግፍ ሁሉ ፍርዱን ያገኛል ብለን ስንጠብቅ አንባሳደርነት መሾሙን እንዳንሰማ ነው፡፡ ምክንያቱም አገዛዙ እስከ አሁን የዚህን ግፈኛና አውሬ ሰው ያለመከሰስ መብት ያላነሣው ሰውየውን ተከሳሽ ለማድረግ ባለማሰቡ ነውና፡፡

አየ የኛ ሕዝበኛ (populist) ዐቢይና አሥተዳደሩiii

የዐቢይን አሥተዳደር የሕግ የበላይነት፣ ተጠያቂነትና ፍትሕ የሌለበትና ይኖራል ተብሎም የማይጠበቅበት አሥተዳደር ወይም ዘመን በመሆኑ ዘመነ ምሰና ብንለው አይሻልም ትላላቹህ???

እና በዚህ ዘመንና አሠራር ነው ታዲያ የሕዝብ መብት የሚከበረው??? የሕዝብ ጥያቄ የሚመለሰው??? ሕዝብ ነጻነቱን የሚያገኘው??? ሕዝብ የሥልጣን ባለቤት የሚሆነው???

የሕግ የበላይነት፣ ተጠያቂነትና ፍትሕ በሌለበት ሀገርና ለፍትሕ፣ ለሕግ የበላይነትና ለተጠያቂነት ቁርጠኛ የሆነ የመንግሥት አሥተዳደር በሌለበት ሀገር ሥርዓት አልበኝነት፣ ብጥብጥ፣ ሁከትና ቀውስ እንጅ ሰላም፣ መረጋጋትና ደኅንነት የሚባል ነገር ፈጽሞ አይኖርም!!!

ይሄንን ጉዳይ በተደጋጋሚ ዐቢይ በይቅርታ ስም የወያኔን ግፈኛና አረመኔ ባለሥልጣናትን ከተጠያቂነት ነጻ ለማድረግ በማሰብ ትርጉም የለሽ ይቅርታን በለፈፈ ቁጥር ሳስጠነቅቅ ቆይቻለሁ፡፡

ለዚህም ነው አሁን በየቦታው የምናየው ሰዎች በራሳቸው ውሳኔ የመሰላቸውን እርምጃ የመውሰድ ድርጊቶች እየተስፋፉ የመጡት፡፡ ሕዝቡ የሕግ የበላይነትና ተጠያቂነት መኖሩን ማየትና ማረጋገጥ ካልቻለ ሁኔታው ከዚህም እየከፋ ይሔዳል እንጅ ሰላምና መረጋጋት ይኖራል ብሎ ማሰብ ዘበት ነው!!!

አገዛዙ ግን ይሄንን የፈለገው ይመስላል፡፡ አገዛዙ ግፈኛ፣ ወንጀለኛ፣ አረመኔና ሌባ ባለሥልጣናቱ ተጠያቂ ሆነው ለፍርድ መቅረባቸውን ፈጽሞ አይፈልግምና ሕዝቡን በቀውስ ከምንናጥስ በቃ እነሱን ብንምራቸው፣ በነጻ ብንለቃቸውና ሰላም ብናገኝ ይሻለናል!” እንዲል ለማድረግ ነው በየቦታው በማበጣበጥ በርትተው እየሠሩ ያሉት፡፡ በሶማሌ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ቦታዎች እየተቀሰቀሱ ካሉ ቀውሶች ጀርባ ያለው ምሥጢር ይሄው ነው፡፡ ሕዝቡ ግን ይሄንን ቁማር ልብ ያለው አይመስለኝም፡፡

የወያኔ ባለሥልጣናትን በተመለከተ አንዳንድ ምሁራን ተብየ የወያኔ ሎቢዎች (አግባቢዎች) “ለሀገር ሰላም ሲባል ተጠያቂ ሳናደርጋቸው ሁሉንም ነገር እንተውና እንደ አዲስ እንጀምር!” የሚሉና ሕዝብን ለማግባባት ጥረት የሚያደርጉ አሉ፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ሁለት መታወቅ ያለባቸው ነጦቦች አሉ፡፡ በምንም ተአምር ቢሆን የሕግ የበላይነትን ደፍልቆ፣ የፍትሕ ጥያቄን ረግጦ ወይም ጨፍልቆ ተጠያቂነትን አስወግዶ ፈጽሞ ሰላም ሊሰፍን የማይችል መሆኑንና ኢአመክንዮአዊ አስተሳሰብ መሆኑን በሚገባ መገንዘብ ያሻል፡፡ እንዲህ ዓይነት የሕግ የበላይነትንና የፍትሕ ጥያቄን የጨፈለቀ የረገጠ፣ ተጠያቂነትን ያላካተተ እርቅም እስከዛሬ ድረስ በዓለማችን በየትኛውም ስፍራ ተፈጽሞ አያውቅም! ከቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ እስከ ደቡብ አፍሪካ እና ሩዋንዳ እንኳ ብትጓዙ ተፈጻሚ አልተደረገም፡፡ ዝርዝሩ ካስፈለገ ሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ፡፡

ሌላው ነጥብ ደግሞ ምንድን ነው ወያኔ የዘረፈውን እንደያዘ እንሸኘው!” ማለት ከዚህ በኋላ ሥልጣን የሚይዘው ማንም ይሁን ማን የወያኔዎችን አለመከሰስ አለመጠየቅ የተቀበለ እስከሆነ ጊዜ ድረስ ከዚህ በኋላ ባለው ዘመን ወያኔ የዘረፈው ሀብት ሁለንተናዊ የበላይነት እንዲኖረው አድርጎ እንዲቀጥል ስለሚያስችለውና ይሄም ፍትሐዊ ተጠቃሚነትና ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እንዳይኖር ስለሚያደርግ ወይም እንደተዛባ እንዲቀጥል ስለሚያደርግ ለግጭትና ለአለመግባባት ምክንያት ሆኖ አዙሮ ችግር ላይ የሚከተን ስለሚሆን ይህ አማራጭ መፍትሔ ሊሆን እንደማይችል መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

በመሆኑም ጥቅመኛ የወያኔ ደላሎች አርፋቹህ ተቀመጡ!!! የሕግ የበላይነትና ፍትሕ ለድርድር አይቅረቡ!!!

ሕዝባችንም ነጻነቱን ማግኘትና የሥልጣን ባለቤት መሆን ከፈለገ ይሄንን የአገዛዙን ፍጹም ኃላፊነት የጎደለው አረመኔያዊ ሸፍጥ በመረዳት የፈለገ ተአምር ቢፈጠር እርስበርስ ላለመበጣበጥ መወሰንና አገዛዙ ከስሩ ተነቅሎ እንዲወገድ ቆርጦ መታገል ይኖርበታል!!!

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

amsalugkidan@gmail.com