መንግስት ስርዓት አልበኝነትን አይታገስም። ጠ/ሚነስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ
መንግስት ስርዓት አልበኝነትን አይታገስም። ጠ/ሚነስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ
ሕግና ሥርዓት የማህበረሰባችን መሰረት እና ያስተሳሰረን ነው። መንግሥት አሁን ላይ እየተስተዋለ ያለውን ከህግ በላይ የመሆን ዝንባሌና ሥርዓት አልበኝነትን አይታገስም።(ጠ/ሚነስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ)
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር በአዛዥነት እና ስታፍ ኮሌጅ ያሰለጠናቸውን ከፍተኛ መኮንኖችን ሲያስመርቅ ከተናገሩት ዋና ዋና ነጥቦች:-
• ነፃነትና ስርዓት አልበኝነት ባለመለየት መረን የወጣ ሕግና ስርዓትን የማያከብር የመንጋ ፖለቲካ ኢትዮጵያ ውስጥ መቆም ይኖርበታል፡፡
• ሕጋዊ ስርዓትን እያደከምን በመንጋ የሚሰጥ ፍትሕ ተከትለን በግል ስሜት መነዳት የለብንም፡፡
• ሕግ አልባና አመጽን የሚታገስ ስርዓት እንደ አገር መቆጠራችንን ከንቱ ስለሚያደርግ አገራዊ አንድነታችንን በሕግ አግባብ ማስጠበቅ የዘወትር ተልዕኮአችን ይሆናል፡፡
• ዘመናዊነት የሕግ የበላይነት ማክበር ነው፡፡
• እንደመር፣ በይቅርታ አንድ አገር እንገንባ ስንል ከመረን እንውጣ፣ ሕግ አናክብር በየከተማው ሽፍታ ይበራከት ማለት አለመሆኑን በአንክሮ ማስገንዘብ እፈልጋለሁ፡፡
• የይቅርታው ዓላማ ባለፍንበት መንገድ ያጣናውን ለማግኘት እንጂ የገነባነውን አገር ለማፍረስ ስላልሆነ እያንዳንዱ ዜጋ ይህ ከአብራኩ የወጣውንና በአነስተኛ ደሞዝ ሕይወቱን እየገበረ የአገር አንድነትን የሚያስጠብቀውን ኃይል የመውደድ፣ የማክበር፣ የሞራል ድጋፍ የመስጠት ኃላፊነት አለበት፡፡
• በጄኔራል ሰዓረ መኮንን ያየነውን የመከላከያ አንድነት እና የለውጥ ኃይል መሆንን የማስቀጠል ፍላጎት በሁሉም ጄኔራል መኮንኖች እንዲደገም፣ በጡረታ የተገለሉ ጄኔራሎች ለወታደር ጡረታ ስለማይሰራ በየትኛውም ጊዜ ችግር ካጋጠመን እናት አገር ጥሪ ልታቀርብላቸው ስለምትችል ቀርባችሁ ሁኔታውን እያያችሁ በመምከር፣ በማገዝ፣ በመደገፍ፣ ወገናዊነታችሁን ማሳየት እንድትችሉ እንዳትበተኑ፣ አንድ ሆናችሁ አንዲት ኢትዮጵያን እንድታጠናክሩ አደራ ማለት እፈልጋለሁ፡፡
