ግንቦት ሰባት ሊንቀሳቀስበት የሚችላቸው አካባቢዎች አዲስ አበባ፣ ከሲዳማ ዞን ውጭ ደቡብ ክልልና የአማራ ክልል በመሆኑ፣ በአማራ ክልል ላይ ኢሳትን ካድሬዎቹን በመጠቀምም አብን ላይ ከፍተኛ ዘመቻ የጀመሩበት ሁኔታ ነው ያለው። የአማራ ክልልን ካጣ ግንቦት ሰባት የትም መድረስ እንደማይችል ስለተረዳ።

አብንና የአማራ ደርጅቶን “ዘረኞች ናቸው” እያሉ ይከሳሉ። “ዘረኝነት አያስፈልግም” እያሉ ያስተምራሉ። ግን ትልቁ ችግራቸው ዘረኝነትን የሚጸየፉት አማራው ጋር ሲሆን ነው። ለኦሮሞ፣ ለሲዳማ ሲሆን ዘረኝነት ለነርሱ ጽድቅ ነው። ኦሮሞው፣ ሲዳማው በጎጡ ሲደራጅ ችግር የለባቸውም። አማራው ሲደራጅ ግን ያንቀጠቅጣቸዋል።

እኔ እንዲህ እላለሁ፣ መርህ ይኑረን። ዘረኝነትም የጎሳ አደረጃጀትን የምንቃወም ከሆኑ ሁሉንም እንቃወም። ለአንድነት የቆምን ነን የምንል ከሆነ ሁሉንም ለማቀፍ፣ ሁሉም ጋር ለመድረስ እንስራ። የኦሮሞ ክልል ለኦነግ ወይም ለኦዴፍ አሳልፎ መስጠት ኢትዮጵያዊነት አይደለም።

ግንቦት ሰባት በአብን ላይ የከፈተውን ጦርነት ማቆም አለበት። አብን ውስጥ ብዙ የቀድሞ አንድነቶች አሉ። ተገፍተው እንጂ ነገሮች ከተመቻቹ ወደ ኢትዮጵያዊነት ፖለቲካ መምጣታቸው አይቀርም።

ይልቅ ግንቦት ሰባት ከኦዴፍና ኦነጎች ጋር ያለውን ትሥስር በመስበር፣ በኦሮሞ ክልል ለሚኖረው ማህበረሰብ ፣ ከሌሎች የአንድነት ሃይሎች ጋር በመሆን የተሻለ አማራጭ እንዲኖረው መስራት ቢጀመር የበለጠ ይረዳዋል። ቄሮዎች እያስፈራሯቸው ብዙዎች ጸጥ ብለዋል እንጂ በኦሮሞ ክልል የኢትዮጵያዊነት ሃይል ቀላል አይደለም። በቀላሉ ምን አልባት ከምእራብ ሸዋ የተወሰኑ አካባቢዎች በስተቀር እንዳለ የኦሮሞ ክልል የሸዋ ዞኖችን የአንድነት ሃይሉ ማሸነፍ ይችላል። የጂማ ዞን፣ የኢሊባቡር ዞንም እንደዚሁ የኢትዮጵያዊነት ሃይሉ ማሸነፍ ይችላል። ወለጋ፣ ሃረርጌ፣ ምእራብ አርሲ፣ ባሌ አስቸጋሪ ሊሆኑ ይችላሉ። ሆኖም አርሲ፣ ቦረና፣ና ጉጂ ዞኖች እንደ ሸዋና ጂማ ባይሆኑም እድሉ አለ። አማራ ክልልን አጣን ብለው አላስፈላጊ ሰጣ ገባ ውስጥ ከሚገቡ ትኩረታቸውን ወደ ኦሮሞ ክልል ያዙሩ። አማራጭ ያላገኛ የታፈነ ህዝብ በዚያ ብዙ አለና።