በህውኃት ሰማይ ሥር (መጽኃፍ) ከታዘብኩት፤

ክፍል ፪

{ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳል ራሱንም የሚያዋርድ ሁሉ ከፍ ይላል} ማቲዎሰ 23፣12

  • ስለ ራስ ማውራት፡፡  ቅዱስ መጽኃፍ “ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳል ራሱንም የሚያዋርድ ሁሉ ከፍ ይላል” ማቲዎሰ   23፣12) ቢልም የመንፈሳዊ ኮሌጅ ምሩቁ ኃብታሙ ግን በእያንዳንዱ ክፍል ለራሱ ራሱ ምስክር ሆኖ ቀርቧል፡፡ሌላ ሰው ይመስክር እንጂ ሰው ለራሱ እንዴት ተጨበጨበልኝ ብሎ ያውም በመጽኃፍ ይጽፋል፡፡ሌሎቹን በየቦታቸው ወደ ፊት እናያቸዋለን፡፡
  • ተጨበጨበልኝ፡መጋቢት 5/1997 ዓ ም ቅንጅት በወረዳ 19 ብሔረ ጽጌ ፊት ለፊት ሜዳ ላይ ባደረገው ስብሰባ ላይ አቶ ጌታነህ አለም የወረዳው አስተባባሪ ጋብዞት ተገኝቶ ባደረገው ንግግር ደማቅ ጭብጨባ እንደተቸረው ለዛ ንግግር ያነሳሳውም የሻ/ ጌታቸው ንግግር መሆኑን ይገልጻል፡፡ 9 ገጽ 31)ይሁን እንጂ ጌታነህ ዓለም እኔ አስተባባሪም አልነበርኩም ስላልሆንኩም አልጋበዝኩትም ይላል፡፡የወረዳው ኮሚቴ ጸኃፊ የነበረው አቶ አንተነህ ሙሉጌታ ደግሞ ሁሉንም የተካሄዱ ስብሰባዎች አስታውሳለሁ፤እንግዳ የጋበዝነው እኔና ሊቀመንበሩ ዶ/ር ሽመልስ ነበርን፤እነናም ሻ/ቃ ጌታቸውን አልጋበዝንም ይላል፡፡እኔ የማውቀው ደግሞ ሻ/ቃ ጌታቸው የተወዳደሩት ሰሜን ሸዋ መርሀቤቴ በመሆኑ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት እዛ እንደነበሩ ነው፤

 

  • ሚያዚያ 30/97 ወደ መስቀል አደባባይ ላመራው የወረዳ 19 የቅንጅት ደጋፊ ፤ “የዚህ ሰልፍ ፊት አውራሪ እኔ ነበርኩ ይላል፡” (ገጽ 65)ይህ እውነት ከሆነ ቅንጅትን ለመምረጡም ሆነ ለመደገፉ የማይታወቅ ወጣት ሳይቀር በገፍና በግፍ እየታፈሰ በየማጎሪያ ካምፕ ሲታሰር ፊት አውራሪው እንዴት ተረፈ? የምትል ነገር ሽው ትላለች፡፡ እዚህ ላይ ዋናው ትዝብቴ ግን ይህ አይደለም፡፡ በ1997 ዓም ባልታወቀ ወር አዲስ አበባ መግባቱን፣ ከመቅጽበት በቅንጅት መንፈስ መለከፉን፤መጋቢት 5/97 የወረዳ 19 ስብሰባ ላይ ተገኝቶ የመጀመሪያው በሆነው የፖለቲካ ንግግር ደማቅ ጭብጨባ ማግኘቱን፣ ሚያዝያ 30 የሰልፉ ፊት አውራሪ መሆኑን ሳትዘነጉ ተከተሉኝ፡፡ የ 1999 ዓ.ም መጨረሻ ወርሀ ነሀሴ ግን እጄን ይዛ ወደ መለስ ጓዳ መራችኝ፡፡( ገጽ  155) አብዩ ጥያቄ የሚመጣው እዚህ ጋር ነው፡፡ከላይ እንደተገለጸው በመንፈሱ ተለክፌ ሆንኩለትም አደረኩለትም ያለው የቅንጅት አመራሮች ከእስር የተፈቱት ሐምሌ 13/1999 ዓም በእለተ አርብ ነው፡፡ ኋላ በተፈጠረው ነገር ብናስከፈውም ነሀሴ የደጋፊው የደስታ ስሜት ገና ያልቀዘቀዘበት ግዜ ነበር፡፡መስከረም  ደግሞ የምሊኒየም ድግስ፡፡ በቅንጅት መንፈስ የተለከፈና ፊት አውራሪ እስከመሆን የደረሰ ሰው ታዲያ በዚህ ወቅት እንዴት ለምንና ስለምን ወዘተ መለስ ጓዳ ለመግባት በቃ ቻለስ? አይን የራሱን አያይ ሆነና  እንዲህ ያለው ጸኃፊ ገጽ 249 ላይ ቀላል የማይባሉ ማሊያ እየቀየሩ የገዢውን ቡድን ተቀላቅለዋል በማለት ሌሎችን ይወቅሳል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ወያኔ ጉያ ከመግባት ፓርላማ መግባት የከፋ ወንጀል ሆኖ ..ልጆቻንን ከጥይት እናተርፋለን ብለው መንገድ የቀሩ ወላጆች ደም ሳይደርቅ ፓርላማ ለመግባት ያሳዩት ጥድፊያ በእርግጥም አከራካሪም አስወቃሽም ነው! ይላል፡፡( ገጽ 88) ፕ/ር መረራ ጉዲና  የቡዳ ፖለቲካ የሚሉት መሆኑ ነው!
  • ሚያዝያ 30 የወረዳ 19 ሰልፈኛ ወደ መስቀል አደባባይ ያመራው ሰንደቅ ዓላማ በለበሱ ሶስት ሞተር ሳይክሎች መሪነት ከሀያ በሚበልጡ ተሸከርካሪዎች ተጭኖ እሱ ፈት ውራሪ ሆኖ መሆኑን ይገልጽል፡፡ (ገጽ 65) አቶ አንተነህ የተነሳነው ዳማ ሆቴለል አጠገብ ነበረው ቢሮአችን ሲሆን የሄድነው በእግራችን ነው እንዲህ ብሎ ጽፎ ከሆ ውሸት ነው ሲል አቶ ጸጋየ አላረው ደግሞ እውነት ለመናገር ይህን በአይኔ አላየሁም ብሏል፡፡አቶ ጌታነህም አለማየቱን ነው የነገረኝ፡፡
  • ቀደም ሲል ደቡብ አፍሪካ የኖርኩ ስለሆነ የሥራ ቪዛም ነበረኝና ስደትን ካቆምኩበት ለመቀጠል ወስኜ የዓለም ዋንጫው የስታዲዮም ሁካታ ሲጀመር ወደ ደቡብ አፍሪካ አቀናሁ፡፡(ገጽ 267) ቀንም ወርም ዓ.ም አልተገለጸም፡፡ይሁን እንጂ ገጽ 257 ላይ በረባ ባልረባው ሁሉ ቦርድና ቡድን ባደራጁ ቁጥር ይሰጡኝ የነበርኩት ( ይህችንም ልብ በሏት)እኔም የኮሚቴው አባል መሆኔን የምትገልጽና በ20/05/2002 ዓ/ም ከቀኑ 7.30 በታላቁ ቤተ መንግሥት  ኢዩበልዩ አዳራሽ በሚደረገው የኮሚቴው የመጀመሪያ ስብሰባ እንድታደም የምታሳስብ ደብዳቤ ደረሰችኝ የሚለውን ስናነብ የደቡብ አፍሪካው ጉዞ ከዚህ በኋላ መሆኑን እንረዳለን፡፡ ጥያቄ የሚያስነሳው ይሄ ሳሆን እዛው ገጽ ላይ ከዚህ ቀደም ብሎ የሰፈረው እና እረፍት ስለምፈልግ ልቀቁኝ የሚል መልእክት ያለው ደብዳቤ ለኢህአዴግ ጽ/ቤት አስገባሁ የሚለው ነው፡፡ የመጀመሪያው ጥያቄ -የተጻፈለትን ደብዳቤ ቀን ወርና ዓ.ም አይደለም እሱ ጋር የደረሰበትን ሰአትና ደቂቃ ያስታወሰና የከተበ ሰው እንደምን እሱ የጻፈውን መልቀቂያ ሌላው ቢቀር ዓ.ም አልገልጽም?ለምን?

ሁለተኛው ጥያቄ ገጽ 245 ላይ እንደዘረዘረው 13 ሥልጣኖች ነበሩኝ ያለውና ኢህአዴግ ከ 97 የምርጫ ውድቀት በኋላ በ2002 ዓ.ም በአዲስ አበባ አዲስ ታሪክ ለማስመዝገብ አብዝቶ ከሚተማመንባቸው ሰዎች መካከል አንዱ ነበርኩ የሚለን ሰው እረፍት እፈልጋለሁ በቃኝ ሲል የሚሸኝ ያውም እስከ ደቡብ አፍሪካ ያ የምናውቀው ወያኔ ወይንስ ሌላ?

ሶስተኛ – ነገሩ በዚህ ብቻ አያበቃም ከላይ በተገለጸው ሁኔታ ተሸኘሁ ብሎን ገጽ 270 ላይ ደግሞ እሁድ ቀን ሚያዝያ 2003 ዓ.ም ማዘጋጃ በተካሄደ የኢህአዴግ ወጣት ፎረም ጉባኤ ላይ በድንገት ተከስቶ  ንግግር ማድረጉንና ደማቅ ጭብጨባ እንደተለገሰው ይገልጻል፡፡ ወያኔ እንዲህ ደግና ዴሞክራት ነበር እንዴ! አናውቀውም ነበር ማለት ነው ?

  • ለሁለት ዓመታትም ቢሆን ገራፊ ሥርዓት ሲገነባ ጠጠር ስለማቀበሌ…(ገጽ 17) ግዜውን በትክክል ባይነግረንም የባለ ራዕይ ወጣት ማህበር ቆይታውንና  አንድነት የገባበትን ግዜ በግርድፉ ወስደን ብናሰላ ሁለት ዓመት የተባለው እውነት ሆኖ አይገኝም፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን ይህ ሳይሆን ጠጠር የተባለው ነው፡፡ ራሱ እንደነገረን አስራ ሶስት ኃላፊነቶች የነበሩትና  ወያኔ አብዝቶ ከሚተማመንባቸው ሰዎች አንዱ የነበረ ሰው ተግባሩ በጠጠር የሚለካ ይሆናል? ማንም ሰው አሌ ሊለው የማይችለው ሀቅ በወያኔ ዘንድ ለኃላፊነት ለመብቃት አይደለም ከከተማ ለተቀላቀሉ ታግለው ለመጡትም ታማኝነት ቀዳሚውና ዋናው መስፈርት ነበር፡፡ በስመ ዴሞክራሲ ወንበር ያምራችኋል ለምን እንደኛ ታግላችሁ አትመጡም የሚለው በተራ ተጋዩ ጭምር ሲነገር የነበረው የሚረሳ አይመስለኝም፡፡ መለስም ታማኝ እስከሆነ ድረስ መሀይምም ቢሆን እንሾማለን ነው ያለው፡፡ ስለሆነም ከከተማ የገቡት ያውም ወያኔ በምርጫ መሸነፍ እንዳለ ባወቀበት እና ዳግም አንደዛ አይነት እድል ለተቀዋሚዎች ላለመስጠት መሹለኪያየ
  • ሆነዋል ያላቸውን ቀዳዳዎች ሁሉ በደፈነበት ወቅት ለተጠቀሱት የበዙና የከበዱ የኋላፊነት ቦታዎች  ለመብቃት መስለው አይደለም በተግባር ከጳጳሱ ቄሱ ይሉ አይነት ሆነው መገኘት አለባቸው፡፡ እናም ድርጊታቸው አይደለም ጠጠር ከጡብም ይገዝፋል፡፡
  • ባለ ራዕይ ወጣቶች፣ በቀሉ እጥፍ ድርብ መሆኑን ባውቅም እንደ ጎልያድ የገዘፉትን የቀድሞ አጋሮቼን ልታገል እንደ ዳዊት ጠጠር ይዤ ወጣሁ፡፤ ( ገጽ 16) አጋሮቼን ወይንስ ጌቶቼን ? ይህ ማህበር መቼ እንዴት ለምን ዓላማ ወዘተ እንደተቋቋመ አልተገለጸም፡፡ገጽ 271 ላይ ጉዞ ወደ ባለ ራዕይ ወጣቶች ማኅበር የሚል ንዑስ ርእስ ቢኖርም አንድ ገጽ በማይሞላ ያለቀ ለዛውም ስለ ማህበሩ የማይገልጽ ነው፡፡ ለምን? ገጽ 250 ላይ የህውኃት ኢህአዴግን ቤት ከተሰናበትኩ በኋላ ወደ ተቃውሞው ጎራ ከመሄዴ በፊት ከቅርብ ወዳጆቼ ጋር ባለ ራእይ የሚባል የወጣቶች ማህበር መስርተን..የሚለው ለምን እዛ ቦታ እንደገባ ባይገባኝም ቦታው በንኡስ ርእሱ ስር ይመስለኛል፡፡ ያውም ያነሳኋቸው ጥያቄዎች የሚመልስ ሆኖ፡፡

ሌላው የሚነሳው ጥያቄ ከወያኔ ተሰናብቼ ወጣሁ ያለ ሰው እንዴት ነገሮች አልጋ በአልጋ ሆነውለት በአጭር ግዜ ማህበር ለማቋቋም ቻለ? የሚለው ነው፡፡ እስከ ዛሬ የሚጮኸለትን የምህበራት አዋጅ ልብ ይሏል፤

እነዚህና መሰል ጉዳዮች ሲደማመሩ ነው ወደ ፊት እንደምናየው ባልነበረበት ፓርቲ ውስጥ እየገባ ያልነበረና ያልሆነ ነገር ለመጻፍ የደፈረ ሰው አቋቋምኩት ስለሚለውና መሪው ስለነበረ ድርጅት ከመናገር የገታው ምንድን ነው? ለማለት የሚያበቁት፡፡ ደፍረው ሊገልጹት የማይችሉትን ነገር ከመነሻው አለመንካት ከነኩ ደግሞ ፍርጥ አድርጎ ማሳየት ተገቢ ነው፤ ለትውልድ የሚተላለፍ ለታሪክ የሚቀመጥ መጽኃፍ ነውና፡፡ ጠልቆ የሚያይ የለም በሚል አንባቢን መናቅም ይመስለኛል፡፡

  • እስከዚህ የተመጣበትን መንገድ በአስተውሎት ተገንዝባችሁታል ብዬ ስለማምን መድገም አያሻኝም፡፡ ግን አንድ ነገር ልበል ከአንድነት ፓርቲ ሰዎች ጋር መገናኘቱን የነገረን ገጽ 251 ላይ ሲሆን ጉዞ ወደ ባላራዕይ ወጣቶች የምትለዋ ባለ አንድ ገጽ ንዑስ ርዕስ የምትገኘው ገጽ 271 ላይ ነው፡፡ ይህ መሰል የቅደም ተከተል መፋለስ ብዙ ቦታ ያለ ሲሆን ሆን ብሎ የተደረገ የአጻጻፍ ዘይቤ፤ወይንስ ባለማስተዋል፣ ወይንስ አንባቢው የታሪኩን ፍሰት ተከትሎ ነገሮችን በደንብ እንዳይረዳ ከመፈለግ የሚል ጥያቄ ያጭራል፡፡ ይህ የበለጠ ትኩረት የሚስበው ዋና ዋና ጉዳዮች ቀንና አመተ ምህረታቸው አለመገለጹን ልብ ሲሉ ነው፡፡ሲፈልግ ሰአትና ደቂቃ ሳይፈልግ እንኳን ቀን ወርም አለመገለጹ ተራ የመዘንጋት ጉዳይ ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም፡፡
  • ከህውኃት ወደ አንድነት፤ ከላይ በመጠኑ ለማየት በተቻለው ሁኔታ ህውኃት ውስጥ የነበረው ኃብታሙ የአንድነት ሰዎች ከፍተኛ ዝግጅት አድርገንበት ነበር በሚሉት ምርጫ 2007 ዋዜማ አንድነት ፓርቲ ውስጥ ተከሰተ፡፡ መቼም አባል የሆነበትን ቀን ማስታወስ ለኃብታሙ የሚገድ ነገር ሆኖ  ነው ቀኑን ያልገለጸው ለማለት የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ለሀብታሙ አንድነት መግባት መንገድ ጠራጊ መሆኑ የተገለጸው ወዳጄ ጸጋየ አላምረው ደግሞ ኃብታሙን ፎርም ያስሞላው ገና ባለራዕይ ውስጥ እያለ መሆኑን ይናገራል፡፡ይህንስ ምን ይሉታል፡፡ በአንድ ግዜ ሁለት ቦታ አባልነት፡፡

2.2,-ሰው የነገረኝ የተባሉ አሉ ጉዳዮች፡፡ አበው ነገርን አረጋግጦ እህልን አላምጦ ይላሉ፡፡

ነጋሪው ማንም ይሁን ምን ሰሚው አይደለም በመጽኃፍ ለማስፈር በቃል ለሌላ ሶስተኛ ወገን ከማስተላለፉ በፊት የሰማው ነገር ምን ያህል ለእውነት የቀረበ መሆኑን መመዘን ማመዛዘን ይኖርበታል፡ ህሊና ለምን ተሰጠን ታዲያ፡፡አቶ በረከት የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ምኒስትር ሆኖ መረጃና ማስረጃ ላይ ተኝቶ አሉ፤ነገሩኝ እያለ ነበር የሁለት ምርጫዎች ወግ የሚል መጽኃፍ የጻፈው፡፡በዚህ መጽኃፍ ሰማሁ ነገሩኝ ተብለው ከተጻፉት ለማሳያ ያህል ጥቂት እንመልከት፤

  • -የቅዳሜው ማዕበልና የእሁዱ ሱናሚ በሚለው ርእስ ስር ከገጽ 58-64 የሰፈረው እስር ቤት አገኘሁት የሚለውና የሀገር ውስጥ ደህንነት ኃላፊ የነበረው ወልደስላሴ ወልደሚካኤል ነገረኝ የሚለው ነው፡፡ሚያዚያ 30/97 የቅንጅትን ሰልፍ ለመከታተል ሶስት አመራሮች ወልደሥላሴን ጨምሮ መስቀል አደባባይ አንበሳ ሕንጻ ላይ እንደነበሩ፤የህዝቡን ብዛት ሲያዩ አጥወልውሎአቸው ራሳቸውን ስተው ስልክ ተደውሎ ወደ ሕክምና መወሰዳቸው ሰፍሯል፡፡ ይቀጥልናም በዚህ ባልተጠበቀ ክስተት መለስ ዜናዊና በረከት ስምዖን ተረብሸው ነበር፡፡መለስ የሚይዝ የሚጨብጠውን አጥቶ ብቻውን ያለ አጃቢ በቤተ መንግሥት ግቢ ውስጥ ከወዲያ ወዲህ ሲንቆራጠጥ፣በረከት በበኩሉ መኪና ይዞ በመውጣት ሰልፈኛውን ይቃኝ ገባ ተብሎ ተገልጾአል፡፡እግዜር ያሳያችሁ እንግዲህ ራሱን ስቶ ሆስፒታል ሄደ የተባለው ሰው ነው እንግዲህ ይህን አለ የተባለው፡፡ ጥያቄው የተባለው ሰው ማለት አለማለቱ ላይ አይደለም፡፡ጸሀፊው  በርግጥ ተነግሮት ከሆነ ነጋሪው ማንም ይሁን የቱንም ሥልጣን ይኑረው ሳይመዘንና ሳይመዛዘን መጻፍ ተገቢ አይደለም ፤ምን አልባት የህሊናን ጥያቄን ወደ ጎን ማለት ከተቻለ አብዝተን እደምናየው ስምን ደብቆ ፌስ ቡክ ላይ ይጻፍ ይሆናል፡፡ ስምን ጠቅሶ በመጽኃፍ፡ ለማቅረብ ግን ትልቅ ድፍረት ይጠይቃል፡፡

ከዚህ በላይ ከረዘመ አንባቢን ማሰልቸት ይሆናል፤ቁም ነገሩም ትኩረት ያጣል፣እናም ሞልቶ ከተረፈው እድሜ ካልነፈገን ነገም ሌላ ቀን ነውና በይደር እንገናኝ ስል በታላቅ ይርታ ትእግስታችሁን በመጠየቅ ነው፡፡

በህውኃት ሰማይ ሥር (መጽኃፍ) ከታዘብኩት፤ ክፍል ፩ (ታምራት ታረቀኝ)

ታምራት ታረቀኝ ነሐሴ 2010ዓ.ም ክፍል ፩ «ሕይወትን ሊወድ መልካሞችንም ቀኖች ሊያይ የሚፈልግ ሰው ምላሱን ከክፉ ከንፈሮቹንም ተንኮልን ከመናገር ይከልክል፣ ከክፉ ፈቀቅ ይበል»2ኛ ጴጥሮስ 3/10 ቅድመ ንባብ ፣ ሀ- የዛሬ አመት በወርሀ ነሐሴ በድረ ገጾች ለንባብ የበቃው የኢ/ር ግዛቸው ጽሁፍ በሁለት ምክንያት ቀልቤን ስቦት ነበር ያነበብኩት፡፡ አንደኛው ምክንያቴ የተጠቀሙበት “የሀብታሙ አያሌው ቅጥፈትና የባዶ ቅል መንኳኳት”  የሚለው … Continue reading በህውኃት ሰማይ ሥር (መጽኃፍ) ከታዘብኩት፤ ክፍል ፩ (ታምራት ታረቀኝ)