23 ኦገስት 2018

 

የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ፕሮፌሰር መረሳ ፀኃየ
MERESA

ወቅታዊ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ለብዙዎች ይህ ነው ብሎ ለመግለጽ የሚያስቸግር መልክ ይዟል።

በዚህ ምክንያት አገሪቷ ተመልሳ ከ1983 ዓ.ም በከፋ መልኩ ወደ መስቀለኛ መንገድ መመለሷን የፖለቲካል ሳይንስና ስትራቴጂካዊ ጥናት ሙሁሩ ረዳት ፕሮፌሰር መረሳ ጸሃየ ይናገራሉ።

የዚህ ችግር መሰረታዊ ምክንያት በኢህአዴግ ውስጥ የተፈጠረው አለመግባባት፣ በኦሮሚያ ክልል ተነስቶ መላ አገር ያዳረሰው ፖለቲካዊ ተቃውሞን መንግስት መፍታት ባለመቻሉና በመጨረሻም ህዝቦች ወደ ብሄር ተኮርና ሌሎች ግጭቶች ማምራታቸው እንደሆነ ያስቀምጣሉ።

በኢትዮጵያ የመንጋ ፍትህ የሰው ህይወት እየቀጠፈ ነው

በመቀሌው አውሮፕላን ማረፊያ ታግተው የነበሩት የፌደራል ፖሊስ አባላት ተለቀቁ

.ዶ/ር አብይ በግላቸው ለውጥ ያመጣሉ?

የእነዚህ ችግሮች ድምር ውጤት አገራዊ አንድነትና ደህንነትን አደጋ ላይ የጣለ ከባድ ፖለቲካዊ ችግር እንደተፈጠረ የሚናገሩት ረዳት ፕሮፌሰር ጸሃየ በዚህ ወቅት የአገሪቱ እጣ ምን ይሆን? የሚለው የብዙዎች ጥያቄ እንደሆነ ምሁሩ ይናገራሉ።

እነዚህን ውስብስብ አገራዊ ችግሮች መንግስት እንዴት መፍታት ይችላል? የአገሪቷ ፖለቲካዊ አስተሳሰብስ ወዴት ያመራ ይሆን?

ቢቢሲ፡ በእርስዎ እይታ የኢትዮጵያ ፖለቲካ በምን ደረጃ ይገኛል?

ረዳት ፕሮፌሰር መረሳ፡ ያለው ፖለቲካዊ ሁኔታ ኢትዮጵያ መስቀለኛ መንገድ ላይ የጣለና ነገን መገመት የማይቻል ሆኗል።

የኢህአዴግ አጋር ድርጅቶች ዉስጥ ያለው ችግር ለአገራዊ ቀውስና የአመራር እጦት ምክንያት ሆኗል።

መንግሥትም ህግና ስርአትን ለማስከበር የተቸገረበት፣ ዜጎች ለአካላዊና ስነ ልቦናዊ ጥቃት የተጋለጡበትና የተፈናቀሉበት ሁኔታ ስላለ በሚያስፈራ መልኩ አገሪቷ መስቀለኛ መንገድ ላይ ነች ማለት ይቻላል።

ሌላው በፌደራልና ክልል መንግስታት መካከል ያለው ግንኙት ጥሩ አይደለም። በኤርትራ የነበሩ ተቃዋሚ ሃይሎች ደግሞ በሙሉ ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል።

እነዚህ ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የሚጣጣም ፖለቲካዊ ፍልስፍና እና ራዕይ የሌላቸው ሲሆኑ መንግሥት ያለው ተቀባይነት እንዲዳከም ህግና ስርአት ለማክበር የሚፈተንበት ለዜጎች ለጥቃትና መፈናቀል ምክንያት የሆኑ ችግሮች እየተፈጠሩ አሉ። ለዚህ ነው መስቀለኛ መንገድ ላይ ነን ያልኩት።

“ሽብር ምንድን ነው ፣ አሸባሪ ማን ነው?” ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ

ቢቢሲ፡ “ብሄር ተኮር” ጥቃቶች አገሪቷ ላይ እየተፈጸሙ ነው ? ይህ ከምን የተነሳ ይመስልዎታል?

ረዳት ፕሮፌሰር መረሳ፡ አንደኛ ኢትዮጵያ በታሪክ የአገር ግንባታ ችግር ያለበት ናት። የብዙ ብሄሮች አገር ስለሆነች አገራዊ ግንባታ (ኔሽን ቢዩልዲንግ) የሚባለው ሂደት ሊያግባባን አልቻለም። ለዚህ አንድነቷንና ተቀባይነቷን የሚፈታተኑ ሦስት የፖለቲካ አስተሳሰቦች አሉ።

የመገንጠል ፖለቲካዊ አስተሳሰብ አንዱ ነው። ኢትዮጵያ ልማትና ዲሞክራሲ ማምጣት የምትችል አገር አይደለችም፤ ጊዜ ሳንወስድ የራሳችን አገራዊ ነጻነት ሊኖረን ይገባል የሚል ፖለቲካዊ አስተሳሰብ አለ።

በሌላ በኩል ብዝኃነት አደጋ ስለሆነ ኢትዮጵያ አንድ ብሄር፣ ቋንቋና ህዝብ ማስተናገድ አለባት የሚል አሃዳዊ አስተሳሰብ ሲኖር ሁለቱንም ጫፍ ኢትዮጵያ ካላት ነባራዊ ሁኔታ ጋር የሚጣጣም ባለመሆኑ ፌደራላዊ ስርአት ነው የሚያዋጣን የሚሉም አሉ።

እነዚህ ሦስቱን ማስታረቅ አለመቻሉ ኢትዮጵያ ሁሉም የሚቀበላት አገር እንዳትሆን አድርጓታል።

ላለፉት 27 አመታት የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ አመራር ይዞ የቆየው የፌደራሊዝም ስርአት አገሪቷ ላይ ለሚነሱ ጥያቄዎች ህገ መንግስታዊና ፖለቲካዊ እውቅና ቢሰጥም እንኳ ላለፉት ሦስትና አራት አመታት ግን ይህን ህልዉና በሚፈትን መልኩ የፌደራሊዝም አስተሳሰብ ችግር ውስጥ ወድቋል።

ስለዚህ ፌደራሊዝም ስርዓቱ ለጊዜውም ይሁን ለዘለአለሙ ተዳክሟል ማለት ይቻላል።

ሌላው ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ አቅም ችግር ያለባት አገር ናት። ብዙ የተማረና ስራ የሚፈልግ የሰው ሀይል ቢኖርም እንኳ መንግስት ስራ ሊፈጥርለት አልቻለም። የአገሪቷ ኢኮኖሚ አድጓል ቢባልም ህዝቡን የሚመግብና ስራ የመፍጠር አቅም ያለው አልሆነም።

ሙስጠፋ ኡመር የሶማሌ ክልል ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት ሆነው ተሾሙ

ተቃውሞ ሲጀምር የአዲስ አበባ ማስተር ፕላንና የስራ እጦት ምክንያቶች ነበሩ። ወጣቱ ስራ እያጣ በሄደ ቁጥር መንግሥት ያለው ተቀባይነት እየተዳከመ ወጣቱ በብሄር እንዲደራጅና የራሱን ጥቅም ሌሎች እንደወሰዱበት አድርጎ በመረዳት ወደ ጥፋት እንቅስቃሴ እንዲሄድ ምክንያት ይሆኗል።

ያለንን አገራዊ አቅም ከአገራዊ ግንባታው አለመመጣጠኑኢትዮጵያ በህዝቦቿ ዘንድ ያላትን ተቀባይነት ፈተናላይ በመጣል መንግሥት ደግሞ ህግና ስርአት ለማክበር ተቸግሮ በርካታ የዜጎች መፈናቀልና ብሄር ተኮር ጥቃቶች ሲደርሱ እየታየ ነው።

በአጠቃላይ ኢህአዴግ ተዳክሞ በሚገርም መልኩ አንድ መሆን አቅቶት የዜጎች ደህንነት አደጋ ላይ ወድቆ የአገር መከላኪያውም የዜጎቹን ደህንነት እንዳይጠብቅ ጠንካራ ፖለቲካዊ አመራር ሳያገኝ ቆይቷል።

በኦሮሚያ ክልል የነበረው ተቃውሞ Image copyright Getty Images

ቢቢሲ፡ ይሄ ሁሉ ግን ባንዴ የመጣ ሳይሆን ያለፉት 27 አመታት ዉጤት ነው ይባላል?

ረዳት ፕሮፌሰር መረሳ፡ ኢትዮጵያ ሦስት መሰረታዊ ጥያቄዎች ነበሯት። የብሄር እኩልነት፣ መሬትና የዲሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ሲሆኑ፤ እነዚህ የአገር ግንባታው ችግር አካል ናቸው።

በአጼ ሚኒሊክ ኢትዮጵያ ለመጨረሻ ጊዜ አሁን የያዘችውን ቅርጽ ስትይዝ እነዚህ ችግሮች ይዛ ነው የተፈጠረችው።

ሌላው አርሶ አደሩ ከእርሻ ተነስቶ ወደ ኢንዱስትሪያል ካፒታል ሊሸጋገር እየተገባ፤ እስከ አሁን በእርሻ የተመሰረተ ኢኮኖሚ ነው ያለን።

ወጣቱ ስራ አጥቶ ተስፋ ቆርጧል ሲባል መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር ስለሌለ፤ የተማረው ስራ አጥ እየሆነ ስለሆነ ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያ ያላት ኢኮኖሚያዊ ችግር አሁን ላለው ፖለቲካዊ ሁኔታ ምክንያት ሆኗል።

ጎዳና ተዳዳሪዎችን በህክምና መታደግ

በዚህ ምክንያት ላለፉት 25 አመታት አድጓል ሲባል የነበረው ኢኮኖሚ ትክክለኛ ኢኮኖሚያዊ እድገት አለመሆኑና ይልቁንም በረድኤትና ምጽዋት የተመሰረተ መሆኑ ችግር ፈጥሯል።

ሌላዉ መሰረታዊ የኢትዮጵያ ችግር የምንለው ረዥም ታሪክ አለን ህገ መንግስታዊና ዲሞክራሲያዊ ባህል የለንም።

ህገ መንግስቱ ለነበሩት ጥያቅዎች እዉቅና ቢሰጥም አቶ መለስ ዜናዊ “ቢግ ማን ፖሊስ” ገንብቶ ነው ያለፈው።

በዚህ ጊዜ ክልሎች ቋንቋቸዉን ባለማሳደጋቸው፣ ኢኮኖሚያዊ አቅምና ስራ ባለመፍጠራቸው፣ ዲሞክራሲ ባለማስፋታቸው፤ ገዢው ፓርቲ ደግሞ ለዲሞክራሲያዊ ሽግግር በሚጠቅም መልኩ ባለመደገፉ ባለፈው ምርጫ መቶ በመቶ አሸንፌአለሁ ሲል ከአሁን በኋላ መንግሥትን በምርጫ መቀየር እንደማይቻል በማሳየት ተስፋ የሚያስቆርጥ ሁኔታ ተፈጠረ።

ስለሆነም መንግሥት በምርጫ ሳይሆን በአመጽ ነው የምንቀይረው የሚል ስሜት ፈጠረ። ከአቶ መለስ በኋላ የመጡት አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ደግሞ የነበረው ስርአት ለማስቀጠል አቅም ስላነሳቸውና አራቱንም ድርጅቶች አስተባብረው መምራት አልቻሉም ነበር። 10ኛ የድርጅቱ ጉባኤ በተካሄደ በአንድ ወር በኦሮሚያ ክልል ተቃውሞ ተቀሰቀሰ። ስለሆነ ችግሩ የኢህአዴግ አመራሮች የፈጠሩት ችግር ነው።

ችግሩ የህገ መንግሥት ሳይሆን ዲሞክራሲ ባለመስፋቱ፣ የኢትዮጵያ ህልውና ከኢህአዴግ ህልዉና ጋር በመተርጎሙ፤ ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ማዳከም ላይ ሲሰሩ የነበሩ ስራዎች፣ ዜጎች ምርጫ ላይ እምነት ማጣታቸዉና ከአመጹ በኋላ ኢህአዴግ ችግሩን የሚፈታበት አቅም ማጣቱ ናቸው።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ ለማ መገርሳ፣ ዶክተር ደብረፅዮን ገብረ ሚካኤልና ደመቀ መኮንን Image copyright PM Office facebook

ቢቢሲ፡ ምን መደረግ አለበት ይላሉ?

ረዳት ፕሮፌሰር መረሳ፡ አሁን፡ የኢህአዴግ ህጋዊ የፖለቲካል ኢኮኖሚ አስተሳሰብ በተግባር ደረጃ አለ ብሎ ለመናገር ይከብዳል። አብዮታዊ ልማታዊ ነው ሊበራል አይታወቅም። አንድ የሚገለጽበት “ፖፕሊዝም” ነው።

አለ የሚባለው ዲሞክራሲም የሰበር ዜና ዲሞክራሲ ነው። ሰበር ዜና እያሉ ህዝቡን ከአንድ አጀንዳ ወደ ሌላ አጀንዳ ሲያሸጋግሩት ነው እያየን ያለነው። ኢህአዴግ እስከ ምርጫ ጊዜ የቀሩትን ጊዜያት ቢያጤን ነው የሚሻለው።

አገር ቀውስ ላይ ነች፤ ህዝብ ግጭት እየለመደ በሄደ ቁጥር መንግስት ላይ ያለውን እምነት እያጣ የራሱን አማራጭ እየወሰደ ይሄዳል። መንግሥት እንዳለውም ሰፊ የጦር መሳርያ መስፋፋት አለ። ይህ ወደ እርስ በእርስ ጦርነት እንዳንገባ ያሰጋል።

የብዙ ዜጎች መፈናቀልና ብሄር ተኮር ጥቃቶች ሲፈፀሙ እያየን ነው። ወደ አገር ቤት የገቡት ሀይሎችም ታሪካዊ ቅራኔ አላቸው። ይህን ለማስታረቅ የሽግግር መንግስት መምጣት አለበት።

መንግሥት በአገሪቷ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲ ድርጅቶችን በማስተባበር አገሪቷን ማዳን ካልቻለ መጨረሻው ከባድ ነው። ይህ የዜጎችንና የአገር ደህንነትን ወደ ነበረበት ይመልሳል የሚል ተስፋ አለኝ።

ቢቢሲ፡ በፌደራል መንግስትና በትግራይ ክልል መካከል ክፈትት ያለ ይመስላል?

ረዳት ፕሮፌሰር መረሳ፡ የኢትዮጵያውያን የፍትህና የዲሞክራሲ ትግል ለ17 አመታት የተሸከመው የትግራይ ትግል ነበር።

ይህ የህወሃት ትግል በሌሎች ብሄሮች በሁለት መንገድ ታየ። ይህ ትግል እራሳችንን ለማስተዳደርና ማንነታችንም ለማሳደግ ጥሩ ነገር አድርጎልናል የሚሉ ሲኖሩ ፤ በሌላ በኩል ታሪካችንን ወስዶብናል የሚሉም አሉ።

ህወሀት ፌደራል ላይ ተቀምጦ የትግራይን ጥቅም ጨፍልቋል።

አገራዊ ቀዉሱ ሲፈጠር ሁሉም የትግራዋይና የህወሀት ጠላት ሆነ። ህወሀት አሁን ስልጣን ስለሌለው ማድረግ የሚችለው ክልሉን ማስተዳደር ስለሆነ ወደ አፈራው ክልል ተመልሷል። የትግራይ ህዝብ ደግሞ ዲሞክራሲን በማስፋት መሰረታዊ ጥቅሞቹን የምታከብር አገር ነው የሚፈልገው።

የህወሀት አመራሮች ችግር የለባቸውም እያልኩኝ አይደለም። አሁን የህወሀት መሪዎችን እየወቀሱ ያሉትን ግን አብረው ሲያጠፉ የነበሩ ናቸው።

ስለዚህ ፍጥጫው ህወሀትን ማዳከምን ያለመ ነው።

SOURCE      –   BBC/AMHARIC