በአርበኞች ግንቦት 7 እና በኢትዮጵያ አንድነትና የሕዝብ አብሮነትን የሚደግፉና የሚታገሉ አክቲቪስቶች መምጣት ያስደስተኛል:: በተለይ የሚቆጠቁጠኝ የሐገሬ ህልውና ለማስጠበቅ ከሚሰሩ እነዚህ ሃይሎች ጋር የሃሣብ እንጂ የመርህ ልዩነት ስለማይኖረኝ በሰላም ሃገራችሁ ግቡ እያልኩ አክብሮቴን እገልፃለሁ::

የኔ ምንነቴም ሆነ ማንነቴ ኢትዮጵያዊነት ብቻ ነው። ብቸኛ ሠፈሬ፣ መንደሬና ሐገሬ ኢትዮጵያ ናት። ያለ ጎሣ ፓለቲካና ድርጅት ነፃነት የለም ቢሉኝ እንኩዋን በገዛ ፈቃዴ በባርነት መኖርን እመርጣለሁ። ወደ እንሠሦች እርከን ደረጃ ከመውረድ ከሠውነት ጋር ማለፍ እመርጣለሁ።

ማንኛውም ዓይነት ፅንፈኝነት ልክ አለመሆን ብቻ ሣይሆን አደጋም ነው:: ማንኛውም ዓይነት የጎሣ አክራሪነት ከየትም ይሁን ከየት ይምጣ የአስተሳሰብ መላሸቅ፣ መጥበብና መውረድ ምልክት ነው። ከልጅ ጋር መጫወት ልጅን ለመምሰልና ልጅን ማስደሰት እንጂ ልጅ መሆን አይደለም።

ሊገባኝ የማይችልና እንዲገባኝም የማልፈልገው በአርበኞች ግንቦት 7 እና በተለይ በጎንደር አክቲቪስቶች፤ ታማኝን በየነ እና የጎንደር ህብረትን ላይ የሚካሄደው መጠነ ሠፊ አፍራሽ ቅስቀሣ እጅጉን አሣፋሪ ነው:: በማንኛውም መስፈርት የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላት ወያኔ እንጂ አርበኞች ግንቦት 7 እና እነዚህ አክቲቪስቶች አይደሉም።

በጎሣ መደራጀትና አደረጃጀቱን የጎሣ ፓለቲካ ማድረግ በማህበር ማሰብን፤ መውደድንና መጥላትን ያመጣል:: የአስተሳሰብ አድማስን ማጥበብ ብቻ ሣይሆን እንደ ከብት መታጎርንና መነዳትን ይተገብራል:: ሻነን ኤል አልደር “ብዙ ጊዜ ሌላውን የሚተቹ በራሳቸው ውስጥ ያለውን ጉድፍና ጉድለት ያጋልጣሉ” (“Often those that criticise others reveal what he himself lacks.”) ይላል::

ቀጣፊና ውሸታም እንደሚዋሽ ያውቃል:: በእርግጥ ዘለላ እውነትን ይዞ የሚጋልብ የጥፋት መሃንዲስ ነው::

አርበኞች ግንቦት 7 እና እነዚህ አክቲቪስቶች ለኢትዮጲያ አንድነት፤ ለህዝቧ መብትና ነፃነት ብሎም የዴሞክራሲ ስርዓት መስፈን ጉልህ ሚና ተጫውተዋል:: የግልና የቡድን መስዋዕትነት ከፍለዋል:: በወያኔ እስር ቤት ማቀዋል:: ቆስለዋል:: ተሰውተዋል:: ለዚህም ቀዳሚ ምስክሩ አንዳርጋቸው ፅጌ ነው። እነዚህ የሕዝብ ልጆች ክብር እንጂ ውርደትን አያስተናግዱም:: ክብር እንጂ ሥም ማጥፋትና ዘመቻ አያስፈልጋቸውም። ለወያኔ አፓርታይዳዊ የጎሣ ፓለቲካዊ ስርዓት መንገዳገድ ወታደራዊና ከሁሉም በላይ ያደረጉት ስነልቦናዊ ትግል ውጤት ይመዘናል:: ውጤቱም ታይቷል::

ግንቦት 7 እና አክቲቪስቶቹ በተለይ የኢትዮጵያ ግዛታዊ አንድነትና የሕዝብ መስተጋብር እንዲፈጠር በፅናት የቆሙ አርበኞች ናቸው:: ክብርና ምስጋና እንስጣቸው::

እንደኔ እምነት በተለይ የጎሣ ፓለቲካና “በጎሣ ፌደራሊዝም” ርዕዮት መርዝ ቫይረስ የተለከፉ ከዘቀጡበት ኢትዮጵያዊ ማንነትን በጎሣ ምንነት የመተካት አባዜ ሃገሬ ኢትዮጵያን አደጋ ጋርጦባታል:: በጎሣ ፓለቲከኞች የሚዘወር መንጋና አደረጃጀት ተወደደም ተጠላም የወያኔያዊው “የጎሣ ፌደራሊዝም” ርዕዮት መርዝ ቫይረስ ተሸካሚ ነው:: የአንድነቷ መሠረት በሆነው ሕዝብ ውስጥ ይህን መርዝ መዝራት ተያይዘዋል:: ያልተጠበቀ ጦስና መዘዝን (unintended consequences) ለማስላት ተስኗቸዋል:: የሐገር ጉዳይን የሕፃን ጨዋታ አድርገውታል:: የኩታራና የባለዕድሜ ግጥሚያ አድርገውታል:: በእብሪትና በጀብደኝነት ታጭቀዋል።

የጎሣ ፓለቲከኞቻችንና ድርጅቶች እጅግ ፅንፈኛ አስተሳሰብን በሚያራምዱ የጎሣ አክራሪዎች መዳፍ ሥር ወድቀዋል:: የጥፋት ሃይል እየሆኑ ባልወከላቸው ሕዝብ ስም መመፃደቅ ጭራሹንም ትውልድንና ምሁራንን እያብጠለጠሉ ድንቁርናቸውን ለመጫን አሰፍስፈዋል::

እኔ ኢትዮጵያዊ ብቻ ነኝ:: ወያኔ ሠራሽ የዳቦ ስምን በኢትዮጵያዊነቴ አልቀይርም:: እውነትን በመረጃና ማስረጃ መዝኜና ገምግሜ ስረዳ ስለእውነት እናገራለሁ። የማንም ድርጅት አባል፣ እስረኛ ወይም መንጋ አይደለሁም። በማህበርም አላስብም። አልደግፍም ወይም አልቃወምም። ሃሣቤን በነፃነት ያለተፅዕኖ አስባለሁ። ገልፃለሁ።
እኔ ግንቦት 7ን አውቀዋለሁ። ግንቦት 7 ግን አያውቀኝም። እውነትን ለመድፈርና ለማወጅ መተዋወቅን አይጠይቅም።

ለማንኛውም በኢትዮጵያ ሉዐላዊነት፤ በሕዝብ አብሮነትና መስተጋብር፤ በመብት፤ ነፃነትና እኩልነት እንዲሁም የነዚህ ማረጋገጫ በሆኑት የሕግ የበላይነት የሚሰፍንበት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሚያምን ሃይል ድጋፌን እሰጣለሁ::

ባጭሩ የግንቦት 7 እና አክቲቪስቶቹ መምጣት ፓለቲካችን ውስጥ የምናየውን ቁማር ለማረቅና የጎሣ ፓለቲካን ቫይረስ ለማምከንና ኢትዮጵያዊ ምጥቀትን ለማምጣት መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል ብዬ አስባለሁ::

የግንቦት 7 አባላትን እና አክቲቪስቶቹ በጠላትነት የፈረጀ ወያኔ ነው:: ይህን ፍረጃ ተቀብሎ የሚያስተጋባ ወያኔ ውክልና የሰጠው ብቻ ነው:: ወያኔ ሞቷልና ውክልናውም በሕግ አይሰራም:: ግንቦት 7ን ማብጠልጠልና ስሙን ማጉደፍ ጠላት ወያኔን መታደግ ነው። ለአማራውም ይሁን በኢትዮጵያ አንድነት ለሚያምን ሕዝባችን ከግንቦት 7 የተሻለ ወዳጅ የለውም። ግንቦት 7ን በዘመቻ የሚያጥላላ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ እሣት የሚለኩስና የጎሣ መንግስት መስርቶ የጎሣ ባላባትነት ያማረው ነው።

ሞት “ለጎሣ ፌደራሊዝም”!

መብትና ነፃነት ማግኛና ማረጋገጫው ጎሣዊ አደረጃጀት ሣይሆን ዴሞክራሲና የሕግ የበላይነት ብቻ ነው!

በነፃነት ፋኖነታቸው የግንቦት 7 እና አክቲቪስቶቹ ክብርና ሞገስ ይገባቸዋል!