የ2012ቱ ምርጫ በ2 ዓመት ቢራዘምስ?


••••
ብሩህ ዓለምነህ
••••
በአራት ምክንያቶች ቀጣዩ ምርጫ በ2 ዓመት መራዘም አለበት ብዬ አምናለሁ።

1ኛ – የሽግግር ባሕሪ ነው። በአሁኑ ወቅት ሀገራችን ሽግግር ላይ ናት። በሽግግር ላይ ያለ ህዝብ ምን ዓይነት ባህሪና መንፈስ ይኖረዋል? የሚለው ጥያቄ በጣም ወሳኝ ነው። ሽግግር ሁልጊዜ ተስፋንና ስጋትን አጣምሮ ስለሚይዝ በህዝቦች ላይ የባህሪና የመንፈስ አለመረጋጋትን ይፈጥራል። ይሄም አለመረጋጋት እስኪሰክንና “ተስፋ በስጋት ላይ ድል እስኪቀዳጅ ድረስ” ልክ አሁን በሀገራችን እየታየ እንዳለው የሥርዓት አልበኝነት መልኮች በየቦታው ይፈነዳሉ። ይሄንን አለመረጋጋት ለማስተካከል ጊዜ ይወስዳል።

ምርጫ ደግሞ ሽግግር ነው። የተደራጁ አዳዲስ አስተሳሰቦችና ፍላጎቶች ወደ አደባባይ ወጥተው የሚጫረቱበት ወቅት ነው ምርጫ። በዚህም የተነሳ ምርጫ ሁልጊዜ ተስፋና ስጋትን ይዞ ይመጣል። በመሆኑም፣ አሁን ባለንበት ያለመረጋጋት መንፈስ ላይ ምርጫ ማካሄድ ማለት የህዝቡን ተስፋ ከመጨመር ይልቅ ስጋቱን ማባዛት ነው የሚሆነው።

2ኛ – መንግስት ባቀረበላችው “የሰላማዊ ትግል ጥሪ” መሰረት ለዓመታት በውጭ የነበሩ ድርጅቶች በብዛት ወደ ሀገር በመግባት ላይ ይገኛሉ። እነዚህ ድርጅቶች እርስበርስ እና ሀገር ውስጥ ካሉ ፓርቲዎች ጋር ያላቸው የርዕዮተ ዓለም አንድነትና ልዩነት (አሰላለፋቸው) ገና አልታወቀም። እርስበርስ የሚወያዩበት፣ የሚጣመሩበትና ሐሳባቸውን ለህዝቡ የሚያቀርቡበት ጊዜ ያስፈልጋቸዋል። ለምርጫው የቀረው 20 ወራት ደግሞ ለዚህ በቂ አይደለም።

3ኛ – የመጫወቻ ሜዳው (የምርጫው ህጉና ተቋማት) ላይ እስከ አሁን ገና መግባባት ላይ አልተደረሰም። ውይይት ተደርጎበት ሁሉም መተማመን ላይ መድረስ አለባቸው። ሆኖም ግን፣ በእንደዚህ ዓይነት ድንግዝግዝ ላይ ወደ ምርጫ መግባት ማለት ወደ ሌላ ስጋት፣ አለመረጋጋትና ጭቅጭቅ ውስጥ መግባት ማለት ነው።

4ኛ – የዶ/ር አብይ መንግስት የመጀመሪያዎቹን አራት ወራት በዲፕሎማሲያዊ ሥራዎች እና ክፍተት ያለባቸውን የህግና የፖሊሲ ጥናቶችን በማድረግ ነበር ያሳለፈው። በአሁኑ ወቅት እነዚህ ጥናቶች በመጠናቀቅ ላይ እንደሆኑና አንዳንዶቹም ወደ ውይይት እየመጡ እንደሆነ እየሰማን ነው (ለምሳሌ የት/ት ፖሊሲው፣ የበጎ አድራጎትና የፀረ ሽብር አዋጁ)። እነዚህ ውይይቶች እንዲቀጥሉ፣ እንዲሰክኑ፣ ተግባራዊ እንዲደረጉና ለውጡ በደንብ መሬት እንዲረግጥ ጊዜ መስጠት ስለሚያስፈልግ ምርጫው በ2 ዓመት ቢራዘም ጥሩ የሚሆን ይመስለኛል።