ኪዳኔ ዓለማየሁ

4002 Blacksmith Drive
Garland, TX 75044
USA

ነሐሴ 18 ቀን 2010 ዓ/ም

ግልጽ ደብዳቤ
ለብፁዓን ወቅዱሳን አቡነ መርቆሬዎስና አቡነ ማትያስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርኮች

አዲስ አበባ
ኢትዮጵያ።

ግልባጭ[i]

ለቸሩ የኢትዮጵያ አምላክ፥ ለእግዚአብሔር፤
ለእመቤታችን፣ ለቅድስት ማርያም፤
ለሊቃነ መላእክት ለቅዱስ ሚካኤልና ለቅዱስ ገብርኤል፤
ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶችና ምእመናን።

ጉዳዩ፤ በቤተ ክርስቲያናችን ስለ ተከሰቱ ችግሮች መፍትሔ ለማግኘት የቀረበ አቤቱታ፤[1]

በመጀመሪያ፤ ዝቅ ብዬ እጅ እየነሣሁ የአክብሮት ሰላምታዬን በትሕትና አቀርባለሁ፡፡

በመቀጠልም፤ ከዚህ ቀደም፤ ሚያዚያ 18 ቀን 2005 ዓ/ም በቤተ ክርስቲያናችን ላይ ተደቅነው ስለሚገኙት ልዩ ልዩ ችግሮች አቅርቤላችሁ የነበረውን አቤቱታዬን በማክበር እያስታወስኩ፥ የብፁዓን ወቅዱሳን አባቶችን ቀጥታ መልስ ባላገኝም፥ በቸሩ የኢትዮጵያ አምላክ እርዳታና በሀገራችን ጠቅላይ ሚኒስትር፥ በክቡር ዶር. ዐቢይ አሕመድ አማካኝነት አንደኛው እጅግ ከባድ የሰላምና የአንድነት ጉዳይ መፍትሔ በማግኘቱ እግዚአብሔርን፥ ጠቅላይ ሚኒስትራችንንና ብፁዓን ወቅዱስነታችሁንም በታላቅ ትሕትና አመሰግናለሁ። በዚህ አጋጣሚም፥ ስለ ሰላሙና አንድነቱ ጉዳይ ከፍተኛ ጥረት ያከናውኑ ለነበሩት ሁሉ በተለይም ለሚመለከታቸው ካህናትና ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዓለም አቀፍ የምእመናን ማኅበር ምስጋናዬን አቀርባለሁ።

ወጥ የሆነ አወቃቀርና የአመራር ምደባ የማከናወን አስፈላጊነት፤

ሰላሙና አንድነቱ ከተገኘ በኋላ በተለይ ውጭ ሀገሮች የሚገኘው የቤተ ክርስቲያናችን አገልግሎት በተቀናጀ ሥልት ወጥ በሆነ እንዲከናወን አወቃቀሩና አመራሩ እንዲስተካከል ስለሚያስፈልግ ቅዱስ ሲኖዶሱ መፍትሔ እንደሚያገኝለት ተስፋ አደርጋለሁ።

ሌሎች ችግሮች፤

በቤተ ክርስቲያናችን ባሁኑ ጊዜ የተገኘልን ሰላምና አንድነት ሌሎቹንም ችግሮች ለማስወገድ እጅግ ከፍ ያለ አስተዋፅኦ ሊኖረው የሚችል መሆኑን ስለማምን ከዚህ ቀደም አቅርቤላችሁ የነበሩትን አቤቱታዎች እንደ ገና ከዚህ በታች በዝርዝር አቀርባለሁ፤

ለቤተ ክርስቲያን ስለሚያስፈልገው እርዳታ፤

እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ብዙ ደብሮች፣ ገዳሞችና የአብነት ትምህርት ቤቶች እንዳሉ የታወቀ ነው። ነገር ግን፤ በተከሠተው የቀድሞ መከፋፈል ምክንያት፤ ምእመናን በቂ እርዳታ እያበረከትን አንገኝም። ለምሳሌ፤ በየዓመቱ ውጭ ሀገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወደ ሐገራችን የሚያስተላልፉት ገንዘብ መጠን ከ$3 ቢሊዮን እንደማያንስ ተገልጿል። ከዚህ ውስጥ ለቤተ ክርስቲያን የሚቀርበው እርዳታ እጅግ አነስተኛ መሆኑ ራሱ ብፁዓን ወቅዱሳን አባቶችን እንደሚያሳስብና ተገቢውን እርምጃ እንደሚያመነጭ ተስፋ አደርጋለሁ።

ስብከትና ትምርት፤

በቅርቡ በኢትዮጵያ በተከናወነው የሕዝብ ቆጠራ ውጤት መሠረት፣ የቤተ ክርስቲያናችን አማኞች ቁጥር እድገት ከሌሎች እምነት ተከታዮች አኃዝ ጋር ሲወዳደር ዝቅ ማለቱ ተገልጿል። በተጨማሪም፤ እንደ ኮፕቶች ያሉ እኅት ቤተ ክርስቲያኖች እንደ እንግሊዝኛ ባሉት የዓለም ቋንቋዎች በመጠቀም፤ እምነታቸውን ማስፋፋት ሲችሉ በኛ ቤተ ክርስቲያን በኩል ተመሳሳይ ጥረት ሲደረግ አይታይም። እንዲሁም፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ምእመናን ውጭ ሐገሮች እንደሚኖሩና በትውልድም እየተስፋፉ መሆናቸው ቢታወቅም፣ ተገቢ የሆኑ ማሠልጠኛዎችና ኮሌጆች አልተቋቋሙላቸውም። የዚህ ሁሉ ዋናው ምክንያት የቤተ ክርስቲያናችን መሪዎች ጊዜ የሚባክነው እንደዚህ ያለውን ከባድ ችግር ለማስወገድ አለመሆኑ ነው።

የቤተ ክርስቲያናችን የአስተዳደር ድክመት፤

ቤተ ክርስቲያናችን ላይ ተከሥተው ከሚገኙት ከባድ ድክመቶች የሚከተሉትን መጥቀስ ተገቢ ነው፤

1ኛ/ ግልጽ የሆነ የቤተ ክርስቲያናችን ለዘለቄታ የሚጠቅም ራእይ፥ ሥልት፥ እቅድና ፕሮግራም የለም፤

2ኛ/ አስተዳደሩ እጅግ ደካማ የሆነ፥ ግልጽነትና ተጠያቂነት/ቁጥጥር የጎደለበት፥ በሙስናና በጎሰኝነት የተተበተበ፥ ቃለ ዐዋዲው ተሻሽሎ የአሠራር ቅልጥፍና የሚያስፈልገው መሆኑ፤

3ኛ/ ለልዩ ልዩ የሥልጣን እርከኖች በግልጽ የተመዘገበ፥ ለሹመትና ለቁጥጥር የሚያመች ለሥራ ውጤት መለኪያ መስፈርት አለመኖሩ፤

4ኛ/ የቤተ ክርስቲያናችንን የፓትሪያርክ ምርጫ ሥርዓት በጥንቃቄ ለተመለከተው ጣልቃ ገብነትን የሚጋብዝ፥ እጅግ ውሱንና ደካማ በመሆኑ፥ ለ50 ሚሊዮን ምእመናን ተወካይ ሆነው የሚመርጡት 800 ብቻ ናቸው።

ስለዚህ፥ በአባቶች መሀል ሰላም ስለ ስፈነ፥ ባለሞያ ምሁራንን በማሰማራት በቤተ ክርስቲያናችን የተሟላና የቀለጠፈ አገልግሎትና ግልጽ ራዕይ፥ ሥልት፥ እቅድና መርሐ ግብር በማፍለቅና በመጠቀም ቀጣይ መሻሻል የሚያስገኝ እርምጃ እንዲወሰድ በትሕትና አሳስባለሁ።

የፖለቲካ ጣልቃ-ገብነት፤

በሐገር ቤትም ሆነ በውጭም የተከሰተው ሁኔታ በግልጽ የሚያሳየው፥ ፖለቲከኞች በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ውስጥ ጣልቃ-ገብ መሆናቸው ነው። ይህንንም ሁኔታ ያባባሰው በብፁዓን ወቅዱሳን አባቶች መሀል የተከሰተው ሁኔታ ነው። ስለዚህ፤ በዓለም አቀፍ መሠረታዊ መርሖና በኢትዮጵያም ሕገ መንግሥት መሠረት ቤተ ክርስቲያናችን ነፃነቷን እንድታረጋግጥ ማድረግ በአባቶች ሊታሰብበት የሚገባው ጉዳይ እንዲሆን በማክበር እማጸናለሁ።

የአጽራረ ቤተ ክርስቲያንን ችግር ስለ መመከት፤

እንደሚታወቀው፤ በውጭም በውስጥም የሚገኙ የቤተ ክርስቲያናችን ተቃዋሚዎች፤ በኛ በኩል በተከሰተው የመለያየት መዳከም በመጠቀም፤ እርስ በርሳችን እንድንጋጭና በሚከፈተው በር ለመግባት የሚያደርጉት ጥረት እየተጠናከረ ነው። ስለዚህ፤ የቀድሞ ክርስቲያን ሐገሮች ላይ የደረሰው በኛም ላይ እንዳይደርስ፥ ከወዲሁ ጥንቃቄ የሰፈነበት እርምጃ እንዲወሰድ በትሕትና አሳስባለሁ። በተለይ በሐገራችን በክርስቲያኑና በእስላሙ መሀል “የጠላትህ ጠላት ወዳጄ ነው” በሚል የተዛባ መመሪያ ሳይሆን ለዘለቄታው ጸንቶ የሚኖር መከባበር፤ መቻቻል፤ ለሐገር ልማት ኅብረት የሚያስገኝ ግልጽና ቋሚ የሆነ ሥልት እንዲሰፍን ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድ በማክበር አሳስባለሁ።

ቤተ ክርስቲያናችንን የሚመለከቱ ዓለም-አቀፍ ጉዳዮች፤

ተከስቶ በነበረው የአመራር ችግር ምክንያት፤ በቂ ትኩረት ያላገኙ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች አሉ። ከነዚህ ውስጥ ሊጠቀሱ የሚገባቸው፤

1ኛ/ ኢየሩሳሌም የሚገኘው ታሪካዊው “ዴር ሡልጣን” ገዳማችን፤ የግብጽ ኮፕቶች በፈጠሩት የይገባኛል ችግርና የእሥራኤል መንግሥትም በያዘው አቋም፤ ከሁሉም በላይ ግን በቤተ ክርስቲያናችን በኩል ተገቢው ጥረት ባለመከናወኑ፤ በቅርቡም በደረሰው የጣራ መፍረስ አደጋ ልዩ ጥረት ማስፈለጉ እንደ ቀጠለ ነው። ስለዚህ፤ ታሪካዊ ቅርሳችንን ለማዳን በኅብረት፤ ተግተን እንድንታገል መመሪያችሁ እንዲደርሰን በማክበር አሳስባለሁ።

2ኛ/ ሌላው ዓለም-አቀፍ ትኵረት የሚገባው ከባድ ጉዳይ፤ በቫቲካን ድጋፍ ፋሺሽቶች ለፈጸሙት ግፍ እስካሁን ድረስ     ሐገራችንም ሆነች ቤተ ክርስቲያናችን ተገቢ ካሣ ካላማግኘታቸው በላይ፤ የተዘረፉባቸው ንብረቶች አለመመለሳቸው፤ እንዲሁም ለወንጀሉ ተጠያቂ የሆኑት የኢጣልያ መንግሥትና ቫቲካን ይቅርታ አለመጠየቃቸው ነው። ከፈጸሙት ወንጀል ውስጥ፥ አቡነ ጴጥሮስን፥ አቡነ ሚካኤልን እንዲሁም በብዙ መቶ የሚቆጠሩ የደብረ ሊባኖስ ገዳምተኞችን፥ በአጠቃላይም አንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንን መጨፍጨፋቸው፥ 2000 ቤተ ክርስቲያኖችንና 525000 ቤቶችን ማውደማቸው፥ በቫቲካንም እጅ ክ500 በላይ የሆኑ ከሐገራችን የተዘረፉ ሰነዶች እንደሚገኙ የታወቀ ነው። ስለዚህ ከባድ ጉዳይ ዓለም አቀፍ ሕብረት ለፍትሕ – የኢትዮጵያ ጉዳይ (Global Alliance for Justice – The Ethiopian Cause) (www.globalallianceforethiopia.net) የተሰኘው ድርጅት ከፍተኛ ጥረት እያከናወነ እንደ ሆነ የታወቀ ነው[2]። ብፁዓን ወቅዱሳን አባቶች ለሐገራችንንና ለቤተ ክርስቲያናችን ክብርና ፍትሕ ከፍተኛ ጥረት እንዲከናወን መመሪያችሁ እንዲተላለፍልን በትሕትና አመለክታለሁ።

3ኛ/ ከፍተኛ ትኩረት የሚገባው ሌላው ከባድ ጉዳይ፤ የኢትዮጵያ ፓትሪያርክ የነበሩትን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስንና ሌሎችንም ሰዎች በግፍ በማስገደል ዋናው ተጠያቂ የሆነውን፤ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያምን ለፍትሕ የማቅረቡ አስፈላጊነት ነው። ለዚህ ጉዳይ ያላሰለሰ ጥረት በማከናወን ላይ ያለው “ፍትሕ ለኢትዮጵያ”[3] የተሰኘው ድርጅት ተገቢው ድጋፍ ይገባዋል። ኮ/መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ለፍትሕ እንዲቀርብ ተገቢው እርምጃ በብፁዓን ወቅዱሳን አባቶች እንዲወሰድ በትሕትና አሳስባለሁ።

ምእመናንን ከእግዚአብሔር ሕግ አፍራሽነት ስለ ማዳን፤

የብፁዓን ወቅዱሳን አባቶችን ልዩ ትኵረት የሚጠይቀው ሌላው እጅግ ከባድ ጉዳይ ከ90% በላይ የምንሆነው የቤተ ክርስቲያናችን ምእመናን ከንስሐውና ከቅዱስ ቍርባኑ በመራቃችን በመጽሐፍ ቅዱሱ፥ በቅዳሴውና በመጽሐፈ ቅዳሴው መሠረት ሕገ እግዚአብሔር አፍራሾች ሆነን መገኘታችን ነው።

የመንግሥተ ሰማያት መውረሻ የሆነውን ታላቅ የአምላክ ስጦታ፥ ቅዱስ ቁርባኑን በልዩ ልዩ ምክንያቶች ባለመቀበላችን፥ በቅዳሴው መጀመሪያ ራሳችን በምናዜመው፥ ከዚህ በታች በተጠቀሰው መሠረት፥ የእግዚአብሔርን ሕግ አፍራሾች ሆነን እንገኛለን።

“ሃሌ ሉያ! በቅዳሴ ጊዜ ክምእመናን ወገን ወደ ቤተ ክርስቲያን የገባ  ሰው ቢኖር፥ ቅዱሳት መጻሕፍትን ሳይሰማ፤ የቅዳሴው ጸሎት እስኪፈጸም ባይታገስ፥ ከቍርባኑም ባይቀበል፥ ከቤተ ክርስቲያን ይለይ (ይወገድ)፤ የእግዚአብሔርን ሕግ አፍርሷልና። የሥጋና የነፍስ ፈጣሪ በሚሆን በሰማያዊ ንጉሥ ፊት መቆምንም አቃሏልና። ሐዋርያት በሲኖዶሳቸው እንዲህ ብለው አስተምረውናል።”

ይህ ከባድ ሁኔታ ለምእመናን ብቻ ሳይሆን ለካህናትና ለቤተ ክርስቲያንዋ በአጠቃላይ መፍትሔ የሚያስፈልገው ግዙፍ ችግር መሆኑ የታወቀ ነው። የካሕን አገልግሎት የሥራ ውጤት መስፈርት አንደኛው ምእመናን ንስሐ እየገቡ ወደ ቅዱስ ቍርባኑ እንዲቀርቡ ማድረግ መሆን እንደሚገባው አያከራከርም። ይህ ባለመሆኑ፥ በቤተ ክርስቲያናችን የተከሰተው አሳዛኝ ሁኔታ ለምእመናን የነፍስ ማዳኛ የተደገሰውን የአምላክ ስጦታ፥ ሥጋ ወደሙን፥ በአብዛኛው የሚያጠናቅቁት ራሳቸው ካህናትና ዲያቆናት፥ እንዲሁም ኃጢአት የሌለባቸው ሕፃናት ብቻ ናቸው! ስለዚህ፥ ምእመናንን ከቅዱስ ቍርባኑ አርቀው የሚገኙትን የባህል ግንዛቤዎችና የማስፈራሪያ ሥርዓቶችና እንቅፋት የሆኑ ተግባሮች በጥልቀት በማጥናት፥ አመቺ በሆነ ቀልጣፋ የንስሐ አገልግሎት እንዲተኩና ምእመናን ከእግዚአብሔር ሕግ አፍራሽነት እንዲድኑ ማድረግ እጅግ የሚያስፈልግ አንገብጋቢ ጉዳይ ስለ ሆነ ብፁዓን ወቅዱሳን አባቶች የመፍትሔ እርምጃ እንድትወስዱልን በትሕትና አመለክታለሁ።

የቅዱስ ሲኖዶስ ሥልጣን

በ1991 ዓ/ም ሕገ ቤተ ክርስቲያን፥ አንቀጽ 5፥ ቁጥር 1፥ በተደነገገው መሠረት፥ “በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው ቅ/ሲኖዶስ የመንበረ ሐዋርያት ወራሽ ስለሆነ በቤተ ክርስቲያኒቱ የመጨረሻው ከፍተኛ ሥልጣን ባለቤት ነው።” ነገር ግን፥ እንደሚታወቀው፥ ከዚህ በታች ከተዘረዘሩት ምሳሌዎች መገንዘብ እንደሚቻለውም፥ የቅዱስ ሲኖዶሱ ሥልጣን በተገቢው ደረጃ እየተከበረ ነው ማለት አይቻልም። ምክንያቱም፥

1ኛ/ ቅዱስ ሲኖዶሱ እንዲፈርስ የወሰነው የአቡነ ጳዎሎስ ሐውልት አሁንም ቆሞ ይገኛል።

2ኛ/ በቀድሞው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ የሕሊና አቋም የያዙትን ጳጳሳት የደፈሩ ሰዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ አልተወሰደም።

3ኛ/ አንዳንድ ጳጳሶች ማዕረጉን ያገኙት በጎሳ፥ በጥቅምና በፖለቲካ ትስስር መሠረት ስለ ሆነና ከነዚሁ ውስጥ ጥቂቶቹ ደግሞ የሚኖሩት በምንኵስና ሥርዓት ሳይሆን እጅግ በተንዛዛ የቅንጦትና የሙስና ኑሮ መሆኑ ስለሚታወቅ፥ የመንፈሳዊ አገልግሎታቸውን አጠያያቂ አድርጎታል።

ስለዚህ፥ የቅዱስ ሲኖዶሱ ሥልጣን ሙሉ ክብር እንዲያገኝ ለመንፈሳዊ ግዴታቸው በጽንዓት የሚቆሙ ቤተ ክርስቲያኗን የማያስደፍሩ አባቶችና ለዚሁ ብቁ የሆነ ሥርዓት እንዲኖር ያስፈልጋል።

መደምደሚያ፤

ከ34 ዓ/ም ጀምሮ (ሐዋ.ሥ.ም/8 (26-39) በብዙ መሥዋዕትነት አባቶች ያቆዩልንን ክርስቲያናዊ አንድነት ለ50 ሚሊዮን መንጋዎቻችሁ ጠብቃችሁ እንድታቆዩልን በመማፀን፤ ለእግዚአብሔር ጭምር ግልባጭ በማድረግ ይህንን የአቤቱታ ደብዳቤ በትሕትና አቅርቤያለሁ።ሁለታችሁ ብፁዓን ወቅዱሳን አባቶች፥ አቡነ መርቆሬዎስና አቡነ ማትያስ፥ ከእግዚአብሔር በተቸራችሁ ማዕረግና ኃላፊነት፥ በቤተ ክርስቲያናችን የሰፈነው ሰላም፥ አንድነትና ፍቅር እንዲጠናከርና ዘላቂነት ያለው መሻሻል እንዲገኝ የበኩላችሁን ታሪካዊ ግዴታ እንድትወጡ እለምናለሁ። ለዚህም እጅግ ከፍተኛ ዓላማ ብቁ እንድትሆኑ ቸሩ የኢትዮጵያ አምላክ እንዲረዳችሁ እማፀናለሁ።

ከፍ ካለ የአክብሮት ሰላምታ ጋር፤

 

ኪዳኔ ዓለማየሁ

ምእመን።

[1] ይህንን ጽሑፍ ዶር. ጌታቸው ኃይሌ ተመልክቶልኝ የማስተካከያ ሀሳቦችን ስላጋራኝ ከልብ አመሰግናለሁ። የአቤቱታ ነጥቦቹ በሙሉ የራሴ መሆናቸውን አረጋግጣለሁ።

[2] ለበለጠ መረጃ፤ መጽሐፌን፤ “My Journey with the United Nations and Quest for the Horn of Africa’s Unity and Justice for Ethiopia”ን ይመልከቱ።

[3] “ፍትሕ ለኢትዮጵያ” በቅርቡ ለኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ለክቡር ዶር. ዐቢይ አሕመድ የተጻፈውን የአቤቱታ ደብዳቤ በhttp://www.yatewlid.com/images/Letter_to_Ethiopian_Prime_Minister.pdf መመልከት ይቻላል።