- ጠቅ/ሚኒስትሩም፣ አስተማሪ የሕግ ተጠያቂነት እንደሚረጋገጥ አስታወቁ፤
- መከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ መቃሳ፣ከቅዱስ ፓትርያርኩ ጋራ ተወያዩ፤
- የርዳታ አቅርቦቱን፥ በትራንስፖርትና በሰው ኃይል እንዲሁም በእጀባ ያግዛል፤
- ለምእመኑ የኑሮና የመንቀሳቀስ መብት ትኩረት እንዲሰጥ ፓትርያርኩ ጠየቁ፤
†††
- “በማረጋጋቱ ቤተ ክርስቲያንም ትልቁን ሚና እንድትወጣ እንሻለን፤”/ሚኒስትሩ/
- “ያልደረስንባቸው ቦታዎች ስላሉ አሁንም ከለላ እንፈልጋለን፤”/ሥራ አስኪያጁ/
- በተገደሉትና በተጎዱት የካሳ ጥያቄ የሚቀርብበት ኹኔታ ስለመኖሩ ተጠቆመ፤
- የዐቢይ ኮሚቴ፣ቀጣይ ዙር የጊዜያዊ ርዳታ አቅርቦት ነገ ወደ ክልሉ ያመራል፤
†††
በኢትዮ ሶማሌ ክልል በተፈጸመ አረመኔያዊ ግድያ፣ የንብረት ውድመትና ዘረፋ የተጎዱባትን ካህናትና ምእመናን ለመርዳትና መልሶ ለማቋቋም እንዲሁም መንፈሳዊ አገልግሎቷን ለማስቀጠል ቤተ ክርስቲያን ለምታደርገው ጥረት፣ የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር የበኩሉን ድጋፍና እገዛ እንደሚሰጥ፣ ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ መቃሳ አስታወቁ፤ ሕዝቡን በማረጋጋትና ሰላም በማስፈን በኩልም፣ ቤተ ክርስቲያን ቀዳሚ ሚናዋን እንድትወጣ ጠየቁ፡፡
የመከላከያ ሚኒስትሩና ባልደረቦቻቸው፣ ዛሬ ዓርብ፣ ነሐሴ 18 ቀን 2010 ዓ.ም. ረፋድ፣ በመንበረ ፓትርያርኩ ተገኝተው ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋራ የተወያዩ ሲኾን፤ ቤተ ክርስቲያን የምታጓጉዘውን ጊዜያዊ ርዳታ፣ ተጎጅዎችን በዘላቂነት ለማቋቋምና የተቃጠሉባትን አብያተ ክርስቲያን ዳግም ለመገንባት ወደ ስፍራው የምታደርገውን እንቅስቃሴ በማጀብ፣ ተሽከርካሪና የሰው ኃይል በማቅረብ እንደሚያግዝ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡
“ለምታደርጉት እንቅስቃሴ ስጋት አይግባችሁ፤ የሚያስፈልጋችሁን የጥበቃ ኃይል በምትጠይቁት ጊዜና ቦታ እናቀርባለን፤ እናሰማራለን፤” በማለት ሠራዊቱ የሚያደርገውን እገዛ ገልጸዋል ሚኒስትሩ፡፡
ጸጥታን ለማስፈን፣ የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ከማንሣት ጀምሮ በክልሉ አመራርና በመከላከያ ሠራዊቱ የተወሰዱ ርምጃዎችን ለቅዱስ ፓትርያርኩ ያብራሩት አቶ ሞቱማ፣ በጥፋቱ የተሳተፉ ተጠያቂ አካላትን ተከታትሎ በቁጥጥር ሥር የማዋሉ ተግባር እንደቀጠለ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ “አሁንም ያልተያዙ አካላት ስላሉ ከፍተኛ ጥንቃቄ እያደረግን እንረባረባለን፤” ያሉት ሚኒስትሩ፣ ቤተ ክርስቲያን ተጎጅውን ሕዝብ በማረጋጋት የጎላ ሚናዋን እንድትወጣ ጠይቀዋል፡፡
“በወታደር ጥበቃ ብቻ አይኾንም፤ ቤተ ክርስቲያንም ትልቁን ሚና እንድትወጣ እንፈልጋለን፤” ብለዋል አቶ ሞቱማ፡፡ ነውጠኞቹ እንዳሰቡት ባይሳካላቸውም የሃይማኖት ግጭት ለማስነሣት ዐቅደው እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ ያለሃይማኖት አባቶች ተሳትፎ የሰላም ጥረቱ የተሟላ ሊኾን እንደማይችል አስገንዝበዋል፡፡
በመከላከያ ኃይሉ ስለሚደረገው እገዛና ሚኒስትሩ ስለሰጧቸው ማብራሪያ ቅዱስነታቸው አመስግነው፣ ቤተ ክርስቲያን ለሀገር ሰላምና የሕዝቡ አንድነት በመጸለይና በማስተማር የኖረ ሚናዋን አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጸዋል፤ ለካህናቱና ለምእመናኑ የመኖር ዋስትና፣ የመንቀሳቀስ መብት መጠበቅ ትኩረት እንዲሰጥም አሳስበዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ ዐቢይ ኮሚቴ አቋቁማ ጊዜያዊ ርዳታ በማድረስና ለመልሶ ማቋቋም እያደረገች ስላለችው ጥረት ያስረዱት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ፣“ሕዝባችን እንዲረጋጋ እኛም ጥረት እናደርጋለን፤” ብለዋል፡፡
በውይይቱ ወቅት፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ፣ የኢትዮጵያ ሶማሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ፣ ብፁዕ አቡነ መቃርዮስና ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ ተገኝተዋል፤ አስተያየቶችና ጥያቄዎችም ተነሥተዋል፡፡ “ቤተ ክርስቲያን ስትቃጠል አስቸኳይ መግለጫ አልሰጣችሁበትም፤” የሚለው አንዱ ነው፡፡
ሁከቱና ጥፋቱ፣ ከቀድሞው ፕሬዝዳንት ብልሹነት ጋራ የተያያዘና እርሱን ለማረም ጥረት እየተደረገ በነበረበት ወቅት ከተጠያቂነት ለማምለጥ የተፈጠረ መኾኑን ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡ “የነበረው አረመኔ ነው፤አሁን የተተኩትን ም/ል ፕሬዝዳንት ወንድምና ሌሎችንም የገደለ ነው፤ እርሱን ለማንሣት በሒደት ላይ እያለን ይህ ተከሠተ፤ኹኔታዎች መልክ እስከሚይዙ፣ እስከምናጣራና እስከምንተካ ድረስ ነው የዘገየነው፤ መንግሥት እስከ አሁን እየሠራ ነው፤ በቅርቡ ግን መግለጫ እንሰጣለን፤” ብለዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያንን በመዝረፍና በማቃጠል የተፈጸመው ድፍረት በሶማልያ ጦርነት ወቅት እንኳ ያላጋጠመ ድፍረት እንደኾነ አቶ ሞቱማ አውስተው፣ በካሳ ደረጃ የሚቀርብ ጥያቄ ቢኖር መብቷን እንዲከበር ለማገዝ በሚኒስቴሩ በኩል ዝግጁነቱ እንዳለ ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል፣ በጠቅላይ ጽ/ቤቱ ዐቢይ ኮሚቴ ሥር የተቋቋመው የጊዜያዊ ርዳታ አሰባሳቢ ኮሚቴ፣ ነገ ቅዳሜ፣ በርካታ ደረቅ ምግቦችንና አልባሳትን ጭኖ ወደ ክልሉ እንደሚያመራ ታውቋል፡፡ አስቸኳይ ርዳታን በየመጠለያው ለሚገኙ ወገኖች የሚያደርስበት ቀጣይ ጉዞ ሲኾን፣ የጉዳት መጠኑን አጥንቶና የሚያስፈልገውን ዘላቂ ድጋፍ ለይቶ ግምቱን በመወሰን ሪፖርት የሚቀርብበት እንደሚኾን ተነግሯል፡፡
ልኡካኑን በመምራት የሚጓዙት የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ መልአከ መዊዕ አባ ኃይለ ጊዮርጊስ ተረፈ፣ “ጠረፋማ ቦታዎች ላይ መግባት አልቻልንም፤ አሁንም ከለላ እንፈልጋለን፤” በማለት የመከላከያ ሠራዊቱ እጀባና ድጋፍ እንደሚሹ አስታውቀዋል፡፡ እየተሰበሰቡ ያሉ ርዳታዎች ለተጎጅዎች ሊዳረሱ ካልቻሉ፣ ቤተ ክርስቲያን ካሳ የምትጠይቅበት ኹኔታ እንደሚኖር ሥራ አስኪያጁ ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡
በተያያዘ ዜና፣ በሶማሌ ክልል ወንጀል በፈጸሙ አካላት ላይ አስተማሪ የሕግ ተጠያቂነትን የሚያረጋግጥ ርምጃ መንግሥት እንደሚወስድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ያስታወቁ ሲኾን፤ የተፈናቀሉ ወገኖችንም በዘላቂነት ለማቋቋም መፍትሔ እንደሚፈለግም ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በዛሬው ዕለት ከክልሉ የሕዝብ ተወካዮች ጋራ በጽ/ቤታቸው በተወያዩበት ወቅት፣ የሕግ ጥሰት የፈጸሙ አካላት እንዲጠየቁና ርምጃ እንዲወሰድባቸው ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ፥ መንግሥት ያለፈውን ስሕተት በማይደግም አኳኋን እንደሚሠራ፤ የሕግ የበላይነት፣ መነጋገርና መቻቻል ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ መኾኑን አስታውቀዋል፡፡ ግለሰቦች ወንጀል ፈጽመው ከሥልጣን ሲወርዱ ብሔርና ጎሣ ውስጥ ገብተው እንዳይደበቁ፣ ፍትሕ ለሁሉም እንዲረጋገጥ ሕዝቡ መንቃትና ማወጣት እንደሚጠበቅበት ዶ/ር ዐቢይ አስገንዝበዋል፡፡
በክልሉ ተፈጥሮ በነበረው ኹኔታ ኅብረተሰቡ ያሳየውን ትዕግሥት አድንቀው፣ አስተማማኝ ሰላም ማረጋገጥ የመንግሥት ትኩረት እንደሚኾንና ይህንም በተቋም ግንባታ ማጽናት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡ የሀገር ሽማግሌዎችና ምሁራን የበኩላቸውን ሓላፊነት እንዲወጡ አሳስበው፣ የተፈናቀሉ ወገኖችንም ለማቋቋም ዘላቂ መፍትሔ እንደሚፈለግ ገልጸዋል፡፡