ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ ዛሬ በሰጡት የመጀመሪያው ጋዜጣዊ መግለጫቸው ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ልዩ ልዩ ጥያቄዎች የሰጧቸው ምላሾች ፤

• አሁን ላይ ለአዲስ አበባ ከንቲባ እንደተሾመ የሚወራው ስህተት ነው፡ ቀጣዩ ምርጫ እስኪደርስ ከተማዋ በባላደራ አስተዳደር ከምትመራ ሶስት ወጣት ፖለቲከኞች ተቀምጠዋል፡፡ ለጊዜው የተቆጠሩ የህዝብ ስራዎችን ይዘው ወደ ስራ ገብተው ውጤት እያሳዩ ነው፡፡

• በቀጣዩ ምርጫ የአዲስ አበባ ህዝብ የራሱን ከንቲባ ይሾማል፡፡

• በአለም ላይ ከአንድ በላይ ቋንቋዎች በአንድነት የብዙ አገራት የስራ ቋንቋ ሆነው ያገለግላሉ፡፡በኢትዮጵያም አፋን ኦሮሞ የስራ ቋንቋ ይሁን የሚል ጥያቄ አለ፤ሀሉም ወገን ከአንድ በላይ ቋንቋ ለማወቅ ቢጥር መልካም ነው፡፡ይሁን እንጂ አፋን ኦሮሞን የስራ ቋንቋ ለማድረግ የህገ መንግስት ማሻሻያ ስለሚፈልግ አሁኑኑ ይሁን የሚባለው ተገቢ አይደለም፡፡አማርኛን ጨምሮ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከአንድ ቋንቋ በላይ ለማወቅ መጣር አለበት፡፡ሁሉም ነገር ህግና አሰራርን ተከትሎ የሚታይ ጉዳይ ነው፡፡

• የታጠቁ ኃይሎች ወደ አገር ቤት የተመለሱት ነፍጣቸውን ጥለው በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ነው፡፡እነሱን የሚደግፍ ተቋምም ይደራጃል፡፡

• ኢትዮጵያዊነት የአቃፊነት ባህል ነው ያለው እንጂ አግላይ አይደለም፡፡አልፎ አልፎ የታዩት ጥፋቶች መታረም ያለባቸው ናቸው፡፡የተፈናቀሉም ወደየቀያቸው እንዲመለሱ እየተደረገ ነው፡፡

• ወጣቶች ለስርዓት መታገል እንጂ ራሳቸው ፈራጅ መሆን የለባቸውም፡፡

• የኢትዮጵያና ኤርትራ የሰላም ስምምነት ማንም ያሳካው ጅማሮውን እና የታየውን በጎ ፍላጎት ያማረ ፍፃሜ እንዲኖረው ማድረግ የሁሉም ድርሻ ነው፡፡

• ሀብት በማስመዝገብ ሌብነት አይጠፋም፣ ዋናው ጉዳይ ሌብነትን የሚጠየፍ አገልጋይ ትውልድ መፍጠር ላይ ትኩረት ሊደረግ ይገባል፡፡

• ኢትዮጵያ ክብሯንና ትልቅነቷን የሚመጥን የውጭ ድፕሎማሲና ግንኙነት ስራ እየተሰራ ነው፤አገራትም ይህን በማጤን ነው ወደኛ እየመጡ ያሉት፡፡

• ህዳሴው ግድብን ለመስራት ወደ ስራ ስንገባ የጠራ ግንዛቤና አቅም ይዘን አይደለም የገባነው፡፡ህዳሴው ግድብ በሜይቴክ አቅም የሚጨረስ ፕሮጀክት ባለመሆኑ ሂደቱን እየተጠና ግንባታው በተሻለ አቅም ፈር የሚይዝበት መንገድ ለመቀየስ እየተሰራ ነው፡፡

ከሰኔ 16ቱ የቦንብ ጥቃት እና የኢንጅነር ስመኘው ሞትን እንዲሁም የእሳቸውን ጤንነት አስመልክቶ ለተነሱላቸው ጥያቄዎች የሰጧቸው ምላሾች፤

• የሰኔ 16ቱ ጥቃት በሚመለከት ውጤት በሚመለከት ባለሙያዎች የደረሱበትን ማስረጃ ለህዝብ ያሳውቃሉ፡፡

• የምርመራ ውጤቱ ገለፃ የዘገየው የተጣራ መረጃ ለህዝብ ለማቅረብ ሲባል ነው፡፡
• የኢንጅነር ስመኘው ሞት የሚያሳዝን ነው፤ስለአሟሟቱ ጥብቅ ክትትል ተደርጓል፡፡ይህም ጉዳይ በምስራቁ የአገሪቱ ክፍል በተከሰተው አለመረጋጋት የምርመራ ውጤቱ ገለፃ ዘግይቷል፡በቅርቡ ባሙያዎቹ የደረሱበትን ውጤት ለህዝብ ያሳውቃሉ፡፡

• በእኔ ጤንነት ጉዳይ የተወራው አሉባልታ ነው፣ሙሉ ጤነኛ ነኝ፡፡በተለይ ከአሜሪካ ከተመለስኩ በኃላ ሙሉ ጤነኛ ሆኘ ስራ ላይ ነው ያለሁት፡፡

በቅርቡ በሶማሌ ክልል ከተፈፀመው ጥፋት ጋር ተያያዥ ለሆኑ የጋዜጠኞች ጥያቄዎች የሰጧቸው ምላሾች፤

• የማህብረሰብን ደህንነት ለማስከበር የህግ የበላይነት ማስከበር ወሳኝ ነው፡፡ከመረጃዎች ውስንነት አንፃር በተፈለገው አንፃር ባይሄድም በሁሉም አካባቢዎች ወደፊት ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

• በአገሪቱ እየታየ ላለው የኢኮኖሚ አሻጥር መፍትሄ የሚያፈላልግ ግብረ ኃይል ወደ ስራ ገብቷል፡፡

• መንግስት በሱማሌ ክልል የተፈጠረውን ግጭት ለማስቆም በጥንቃቄ ላይ የተመሰረተ ስራ ተሰርቷል፡፡በተፈለገው ፍጥነት ባለመሄዱ ነው ጥፋቱ ገኖ የወጣው፡፡

• በሱማሌ ክልል ለተፈጠረው ጥፋት ከነበራቸው ኃላፊነት አንፃር የቀድሞው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አብዲ ሙሐመድ ኦማር ጉዳይ ወደፊት በህግ የሚታይ ይሆናል፡፡

• ኢህአዴግ እስካሁን የርዕዮተ ዓለም መስመር ለውጥ አላደረገም፡፡ጥልቅ ተሃድሶ መስመር ላይ ነው

• ኢህዴግ በቅርቡ ባካደው ጉባኤ ይዟቸው በገባቸው አጀንዳዎች ላይ በመግባባት ነው የተለያየው፡፡ልዩነት አለ የሚባው መሰረት የለውም፤ልዩነት ቢኖር እንኳን መሰል ድምፆች እንዲደመጡ ነው የምንፈልገው፡፡

• ኢህአዴግ ከላይኛው አመራሩ ሙሉ ለሙሉ ታድሷል ማለት አይቻልም፡፡ጅምሩን አጠናክሮ ለመሄድ እየጣርን ነው፡፡

• ወንጀል ሰርተው ማህበረሰቡ ውስጥ የተደበቁ ባለስልጣናት ጊዜው ይረዝማል እንጂ ከመጠየቅ አይድኑም፡፡የተሟላ ማስረጃ ሲገኝ ወደ አደባባይ ይወጣሉ፡፡

• ኢህአዴ ቀጣዩን የምርጫ ጊዜ የማራዘም ሀሳብ የለውም፡፡ስለማራዘምም አልተወያየም፡፡

• ምርጫው ያለምርጫ ኮረጆ በዘመናዊ የኤሌክትሮኒክ መንገድ በተያዘው ጊዜው እንዲካሄድ ነው ፍላጎታችን፡፡

• በሁሉም ዘነድ ቅቡልነት ያለው የምርጫ ተቋም እንዲፈጠር እንሰራለን፡፡