በትግራይ የመሸጉት ህውሃቶች ያለፈውን ሁሉ በመፋቅ፣ የወደፊቱን መገንባት አይቻልም ይላሉ፡፡ በኢኮኖሚው የተመዘገበው ፈጣን ዕድገት፤ የመሰረተ- ልማት ግንባታ፣ አብዮታዊ ዲሞክረሲ ፣ የብሄር ብሄረሰቦች መብትና እኩልነት፣ ህገ መንግስቱና ሰንደቃላማ ወዘተ  እያሉ ነው፡፡ በተመሳሳይ አቶ በረከት በቅርቡ ያሳተሙት መፅሃፍ የኢትዮጵያ ትንሳኤ፣ ከመንታ መንገድ  እስከ አፍሪካ ኩራትነት የመፃኢ ሁኔታው ዕድሎችና ተግዳሮቶች የሚል ርዕስ አለው፡፡ ዛሬ ካለው ለውጥ ጋር እድሜዋ የእንጨት ሽበት በሆነባት ሃገር ታሪክ በሃገሪቱ መሪወችና ልሂቃን የነበሩ ተያያዥ የገዘፉ ችግሮችና ጥቂት ትሩፋቶች በአጠቃላይ ፣ በተመሳሳይ በተመሳሳይ ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት እንደ ሃገር ብንቀጥልም በህወሃት ኢህአዴግ የተፈፀሙ ኢ- ሰብዓዊ ድርጊቶች፣ ዘረፋና ሙስናወች፣ የኢኮኖሚ አሻጥሮች፣ የጥቅመኛ ሹሞች ባህሪና ድርጊቶቻቸው በዝርዝር ከሚመለከቷቸው ባለስልጣናት ጋር ቀርበው ትምህርት ሊወሰድባቸው አልቻለም፡፡ ለውጡን በይቅርታ መዋጀት፣ ቂምና በቀል አንድ ቦታ መቆም እንዳለበት በፅኑ ባምንም ሾላን በድፍኑ በመሆኑ ከታሪክ አጋጣሚው አብዛኛው ተገቢውን ትምህርት ሳይወስድበት እንዳይቀር ስጋት አለኝ፡፡ የነበረው የህወሃት ኢህአዴግ ፖለቲካ ትላንት የብዙ ችግሮች ምንጭ ቢሆንም የዛሬ ጥቅሙ ከተማርንበት ብቻ ነው፡፡

ያለፈው አልፏል፣ ዋናው ወደ ፊት መቀጠል ነው፣ ይቅርታና ፍቅር ይበልጣሉ የሚሉት አማላይ ሃሳቦች የነበሩትን የችግሩን ባለቤቶች አዳክመው ከነበሩበት አስተሳሰብ ጋር አዳፍነው እንድንቀጥል ቢያስችሉን እንኳ ጥቂቶች የሃገሪቱ ቀጣይ መሪወችና ልሂቃን የማይማሩበት፣ ብዙሃኑ በብዥታ ውስጥ የሚቆዩበት አጠቃላይ ውጤቱ በመጨረሻ በታሪካችን እንደነበረው የቀርፋፋ ሃገራዊ ጉዞ ባለቤት እንደሚያደርገን መረዳት ተገቢ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የነበረው አጠቃላይ ሃገራዊ ችግር ቁንጮ ባለቤቶች፣ ዛሬ የነበረውን ችግር፣ የቀረበላቸውን የይቅርታና የፍቅር መንገድ ተረድተው፣ አምነውና ተቀብለው አወንታዊ በሆነው የለውጥ  ጎዳና የመጨረሻቸው የሆነውን ሚና ለመጫወት አልደፈሩም፡፡ እንደ ነበረው፣ “ግብር እስከመቃብር፤” ብለው ባልሞት ባይ ተጋዳይነት፣ ለቀጣይ መሪወችና ልሂቃን መጥፎ ዓርአያ መሆን ብቻ ሳይሆን ስጋቶችን ሆን ብሎ ለመፍጠር፣ ከብዙሃኑ መካከል የቻሉትን በብዥታ ውስጥ ለማስቀጠል በመስራት ላይ ናቸው፡፡ የእነዚህ ሃይሎች ተግባርና ዓላማው ከብዙሃኑ የተሰወረ ባይሆንም የተወሰኑትን አያሳስትም ማለት አይቻልም፡፡ የእኛ አማራጭ ዕኩይ የሆነውን ባህሪ፣ ሃሳባቸውን በትኩረት እየመከትን፣ ከትላንቱ፣ ከዛሬው፣ ነገም ከምንጠብቀው እና ወደ ፊት ከምናየው እስከ መጨረሻቸው ድረስ ከስህተቶቻቸው ሁሉ በጥንቃቄ መማር ብቻ ሁኗል፡፡

በስልጣን ጥምና ጥቅመኝነት ባህሪ ምክንያት ከላይ በተገለፁት የተለያዩ እንቶፈንቶወች የሚገለጠት የህወሃት ባለስልጣናት ያዙኝ ልቀቁኞችን ጨምሮ በአቶ በረከት ተመሳሳይ ባህሪ በተንሸዋረረ ዕይታ የአዋቂና የምሁር ለዛን ከላይ ተቀብተው የቀረቡትን ትንተናወች መመከት ያስፈልጋል፡፡

በቀላሉ ሰንበት ለሰው ልጅ ተፈጠረ እንጀ የሰው ልጅ ለሰንበት አልተፈጠረም ይላል መፅሃፉ ፡፡ ብዙ ሽህ ዜጎችን ካላግባብ በእስር ቤት ከታጎሩበት አውጥቶ፣ ከተሳደዱበት ወደ ሃገራቸው መልሶ፣ በሃገራቸው ጉዳይ እንዲሳተፉ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ መሞከር፣ አንድ እንሁን፣ እንደመር፣ ይቅር እንባባል ብሎ ተስፋ ያለውን ጅምር መጀመር ተገቢና ቅዱስ ተግባር መሆኑን የሚረጋግጡት ሰው፣ ዜጋ መሆን ብቻ እንጅ ፖለቲከኛ ህገ-መንግስትና የአብዮታዊ ዲሞክራሲ መስመር ሊሆኑ አይገባም ነበር፡፡ መነሳትም አልነበረባቸውም፡፡ በመሰሪ ፖለቲከኞች ባይሸፋፈን ሃገር የህወሃት ብቻ ናት፣ ለሃገራችን ያገባናል ከሚሉ ብዙሃኑ ዜጎች ባህሪ፣ ሃሳብና ዓመለካከት ጋር ተወዳድረን መቀጠል አንችልም ስለዚህ ጋሻና መከታችን የነበረው፣ የተለየው የእኛ ብቻ የሆነው ግገ-መንግስትና አፈፃፀሙ፣ በተመሳሳይ እንደፈለግን የምንተረጉመው የአብዮታዊ ዲሞክራሲ መስመር ይቀጥል ብሎ እንደ መጠየቅ ማለት ነበር፡፡ እያስመሰልን የቀጠልንበት፣ አቶ በረከትና አቶ ልደቱ አያሌው የተወኑበት የፖለቲካ ፓርቲወች ትያትር፣ ያቀረብንለትን ህግ ብቻ የሚያፀድቅን ፓርላማ፣ የእኛ ብቻ ልሳን የሆነን ሚድያ፣ ለይስሙላ ምርጫ ብቻ የሚጠቅምን ምርጭ ቦርድን፣ ይቀጥሉ ማለት ነበር፡፡ እኛ ብቻ የምንዘውረውን የፍትህና አስተዳደር ስርዓት፣ ያለ ተጠያቂነት አዛዥና ናዛዥ የምንሆንባቸው፣ በራሳችን፣ በሚስታችን፣ በአጋሮቻችን ስም ከቀረጥ ነፃ ንብረት የምናስገባበት፣ የባንክ ብድር የምናገኝበት፣ በሸሪኮቻችን ስም ህንፃና ሆቴል የምንገነባበትን፣ የኢኮኖሚ  ስርዓትና ተቋማትን ደክመንባቸዋል፣ ለፍተንባቸዋልና አትንኩብን ማለት ነበር ፡፡

የሱማሌ ክልሉን መሪ አብዲ ኢሌ በሱማሌ ዜጎቻችን ላይ አንግሰው፣ ለክልሉ ህዝብ ግፍን ለእነርሱ ጥቅምን እያተረፉ ከባጁ፣ ችግሩ ሞልቶ ከፈሰሰ በኋላ፣ ገደቡን ሲያልፍና በዜግነት ምንም በማይተረፍባት ምስኪን ሃገርና ስርዓት በመጨረሻ የተደረገን መልክ የማስያዝ ሙከራ ተመልክቶ በሃገርና ስርዓታችን ማፈር፣ እንደ ሰው እንደ ዜጋ መቆጨት እንጅ ፖለቲከኛ መሆን አያስፈልገውም ነበር፡፡ እኛ በዚህ አንገት ደፍተን( በመስከረም አበራ  በዘ-ሃበሻ ድህረ ገፅ የወጣውን ፅሁፍ ያነበበ ዜጋ ሁሉ የሚሰማው ስሜት ይመስለኛል፡፡)  ለብዙሃኑ በነበረው ጥቅም ሳይሆን ለተፈለገው ዓላማ ውጤታማ በነበረው፣ በጥንቱ፣ የፌዴራል ስርዓቱ፣ የብሄር ብሄረሰቦች መብት ብሎ ማላዘን ሁሉንም ዝቅ አድርጎ መገመት ብቻ ነው፡፡ ምን ጥሎ ክንብንብ እንዲሉ የምንሰማቸው ሪፖርቶች የሚያመለክቱት ጦር ልከን ከምናደራጃት መንግስት አልባዋ ሶማሊያ የበለጠ የሰው ልጅ የተዋረደው በፌዴራለዊ ዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ስር በሱማሌ ክልል ነው፡፡ ለነገሩ በትክክል የተሻልን ብንሆን ጦር ከመለካችን በፊት ሱማሌወች ወንድሞቻችን ሁሉ ወደ እኛ ይመጡ ነበር፤ አካባቢውን ስለማውቀው ድንበርና ከልካይ ሊያቆማቸው አይችልም፣ የተሻልን ብንሆን ደግሞ ለሁሉም እንበቃ ነበር፡፡

ባለ ኮከቡ ባንዲራ፣ ሰንደ ቃላማ የሚሉትም ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ሁሉም ጨርቅ ቢሆኑም በዜጎች ልቡና በሰረፀና ወደ ፊት በሚሰርፅ  ስሜት በዜጋው አዕምሮ ውስጥ ብቻ ከፍተኛ ቦታና ዋጋ ያላቸው ምልክቶች ናቸው፡፡ ሞኞች አሁንም ጨርቁ ላይ ናቸው፣ የሰውን ስሜት ወረቀት ላይ ባለ ህግ ብቻ ለማስረፅ ይሞግታሉ፤- በህገ መንግስቱ፡፡ ራስን በራስ ማስተዳደር እስከ መገንጠል የሚፈቅድ ህገ-መንግስት ራሳቸው ጀባ ካሉ በኋላ፣ ቢፃፍም ባይፃፍም አይቶ እንዳላዩ ማለፍ ሲቻል፣ ጥቂቶች ብዙሃኑ በአንድ ሰልፍ ላይ የሚይዘውን ሰንደቃላማ እንደ አንድ ሃገር ፖሊስና ዳኛ ለመዳኘት መሞከራቸው በእራሱ  የሚገርም ነው፡፡ ሁሉም ግን ባህሪ የማይታረምበት፤  ለውጡን ፣ የተፈጠረውን፣ የአንድነት፣ የእኩልነት ጎዳና በብዥታ ውስጥ ለመክተት ችግርን ለማራዘም የሚደረግ በሰፊው የትግራይ ህዝብ ላይ አነጣጥሮ የሚነዛ የጥቂት ህወሃት ባለስልጣናት ሴራ ነው፡፡ የትግራይ ህዝብ ያሉትን ለጊዜው ቢሰማም መመርመሩ፣ መፈተኑ፣ መመዘኑ ስለማይቀር ከንቱ ሙከራ ነው፤ – በመጨረሻ ራሳቸው ይቀላሉ፡፡

አቶ በረከት በመፅሃፋቸው ከመንታ መንገድ ወደ አፍሪካ ኩራትነት በተሸጋገረችው  ሃገርና ትንሳኤ ጀምረው የህወሃት ኢህአዴግንና የመሪውን መለስ ዜናዊ ስኬት በማወደስ የወቅቱን ለውጥ ተግዳሮት በነበረው የአተያይ ችግር ተጠፍረው ይተነትናሉ፡፡ ሁለት ምሳሌወችን አቅርበው በሃገራችን የተጀመረውን ለውጥና ስጋታቸውን ቢገልፁም፣ ትንተናቸውን ቢያስተካክሉት ንድፈ ሃሳባቸውና ምሳሌወቻቸው ፍንትው አድርገው የሚያሳዩት የራሳቸውን ጨምሮ የጓዶቻቸውን፣ የህወሃት ኢህአዴግን ያለፉት ዓመታ ሂደትና መጨረሻቸውን ነው፡፡

የመጀመርያው እኛ በቂ አይደለም፣ ግልፅነት ይቀረዋል፣ ብዥታ ነግሶበታል፣ ከነበረው ሙሉ ትምህርት መውሰድ አለብን፣ በምንለው የለውጥ ጅምር፣ በኢህአዴጎች መካከል የተፈጠሩት ልዩነቶች፣ ልዩነቶች ከድርጅቱ በተወሰነ መልኩ ወደ አደባባይ መውጣታቸው አስደንብሯቸው ይመስላል አቶ በረከት ራስ ወዳድነት፣ ሩጫና ፍክክር ያጠፋናል ብለው የሚከተለውን ይላሉ፡፡

 “በሃገራችን በመገንባት ላይ ያለው ስርዓት በዚህ ረገድ ያጋጠመውን ፈተና ለመገንዘብ የራስ ወዳድነት አይነተኛ ምሳሌ የሆነውን የአይጦች እሩጫ እሽቅድድም (Rat Race) ማንሳት ጥሩ ይሆናል፡፡”  የሚሉት አቶ በረከት ሲቀጥሉ ፣ “ በዚህ ሩጫ ውስጥ የገቡ የአይጥ መንጋወች ከአንድ ነገር ለመሸሽ ወይም አንድ ነገር ለማግኘት በድንገት በመረጡት አንድ መንገድ ግር ብለው ይጓዛሉ፤ አንተ ትብስ አንች ትብሽ የሚል መተሳሰብ በሌለበት አንዱ በሌላው ላይ ተረማምዶ ለመቅደም ይሞክራል፡፡ ለአቅመ ደካማ፣ ለትንንሾች አይጦች ማሰብ ብሎ ነገር የለም፡፡ ጉልበት ወይም ብልጠት  ያለው በውድ ጓደኛው ወይም በአገሩ ልጅ አይጥ ላይ እየተረማመደም ቢሆን ሌላውን ጥሎ ይሮጣል፡፡ በዚህ አይነቱ የጋራ ዕብደት ውስጥ ሲገቡም ራሳቸውንና ማህበረ አይጣቸውን ለከፋ አዳጋ ያጋልጣሉ፡፡ በመረጋገጥ ብዛት የሚሞተው ላካልና ለመንፈስ ጉዳት የሚዳረገው ይበዛል፤ የማታ ማታ ደግሞ ወደ ተዘጋጀላቸው ወጥመድ ሰተት ብለው መግባታቸው የማይቀር ይሆናል፤ ይህን በመሰለው የአይጦች እሩጫ እሽቅድድም መርህ የሚመራ ማንኛውም ፍጥረት ከዚህ ክፉ ዕድል ሊያመልጥ አይችልም፡፡ ቤተ-ሰብም ይሁን ማህበረሰብ ካፒታሊዝምም ይሁን ሶሻሊዝም መንግስትም ይሁን ፓርቲ በዚህ ራስን የማስቀደም መርህ እስከተመራ ድረስ በመጨረሻ የስኬትን ሳይሆን የውድቀትን አዝመራ ማጨዱ የማይቀር ይሆናል፡፡ በሃገራችንም ከዚህ የተለየ አይሆንም ፡፡ ይህ ቋሚ የተፈጥሮና የማህበረሰብ ህግ ነውና፡፡

አቶ በረከትና መሪወቻችን ከልጅነት እስከ ዕውቀት ጥርሳቸውን ነቅለው ባደጉበት ፖለቲካም ምን ያህል ቀላል እንደሆኑ፣ በአይናቸው ስር ኩልል ብለው ካለፉት ሂደቶች እንኳ ትክክለኛውን ግንዛቤ ለመረዳት የማይችሉ መሆኑን የአቶ በረከት ሃሳብ ያረጋግጣል፡፡ እራሳቸውና ጓዶቻቸው እንደ ነገሩ ተጋብቶባቸው ባገነገኑት የስልጣን ጥምና በሽታ፣ በትንሹ ልሰው በጀመሩት አጉል ጥቅም የጥቅም ሃራራ ሰለባ ሁነው፤ ከኢህአፓ እስከ ኢህዲንና ብአዴን፣ ከህወሃት እስከ ኢህአዴግ በደቦ ለሃምሳ ዓመታት በልዩነቶች መታረም ሳይሆን፣ ሳይነሳ፣ የበላውን እየበላ፣ እያሳደደ፣ እያገለለ ውሾን ያነሳ ውሾ ይሁን ተብሎ፣ ብልጦችና ጉልበተኞን ይዞ መስመሩን፣ የተፈጥሮ ወዙን በሳተ የሰው ልጅ ባህሪ፣ ሃሳብና ፍላጎት ውስጥ ሁነው መዝለቃቸው ዛሬም አልገባቸውም፡፡ አሁንም በዚህ ባህሪ ውስጥ ትክክለኛ ነገር መጠበቅ አይቻልም፡፡ ምሳሌውንና በጎውን የሰውን ልጅ ራስ ወዳድነት ባህሪ ያነሱት አንድ ጊዜ የከፋ ባህሪ ውጤት የሆነውን መሰሪ ሃሳብ በአዋቂና በምሁር ትንተና በማጀል ለማቅረብ በመፈለግ ይመስላል፡፡

ምሳሌያቸውማ የሚያሰገነዝበው ከአንድ ነገር ለመሸሽ ወይም አንድ ነገር ለማግኘት በደመ ነፍሳቸው ወደ አንድ አቅጣጫ ከመንጎድ ውጭ ተፈጥሯዊ የሃሳብና የልዩነት አቅም ከሌላቸው አይጦች በላይ ከፍተኛ አቅምና ልዩነት ያለው የሰው ልጆች ባህሪ በተመሳሳይ ችግሮች ተጠፍሮ፣ ከመገፋፋትና ከመረጋገጥም በላይ ሲተናነቅና ሲተላለቅ መባጀቱን ነው፡፡ ፖለቲካ፣ ርዕዮተ ዓለም፣ ህግና ስርዓት እየተነበነበ፣ ለሰፊው ህዝብ፣ ለጭቁኑ እየተባለ እንደ ሰው ሳይሆን እንደ እንስሳትም መሆን እንዳልተቻለ ነበር፡፡

የያዘ አይለቅም፣ አይፈተሸም እንጅ፣ ወቅታዊ በሆኑ ጥናቶች የሚያመለክቱት የሰው ልጅ በባህሪው ራስ ወዳድም፣ ማህበራዊ እንስሳም እንደሆነ ነገር ግን ቀደም ብሎ  እነ ሲግመን ፍረውድን ጨምሮ በዘርፉ ባለሙያወች  የሰው ልጅ ከማህበራዊ ባህሪው ባላይ እጅግ ራስ ወዳድ ባህሪ ባለቤት እንደሆነ የተያዘው ግንዛቤ ትክክል እንዳልነበረ ነው፡፡ የሰው ልጅ ራስ ወዳድ ቢሆንም የተወሰነ መጠን (Level) ያለውና ከገደቡ እንዳያልፍ በእራሱ ፈቃድና ፍላጎት ብቻ በሌላውና ለሌሎችም እንዲገደው በሚያስገድደው ማህበራዊ የተፈጥሮ ባህሪው የሚገታው መሆኑን ነው፡፡ ስለዚህ ተፈጥሯዊ የሆነውን የሰው ልጅ ራስ ወዳድነት ባህሪ ሙሉ ለሙሉ ገሸሽ ለማድረግ ፈፅሞ አይቻልም፤ ነገር ግን ከመጠኑ እንዳያልፍ በሌላው ማህበራዊ ተፈጥሮ መከላከል ይቻላል፡፡ አቶ በረከት ቤተ-ሰብም፣ ማህበረሰብም ካፒታሊዝምም ፣ ሶሻሊዝምም ቢሆን ለውጥ የለውም እራስ ወዳድነት ያጠፋል ይላሉ፡፡ መቼም ቤተ-ሰብና ማህበረሰብ የሰውን ልጅ ራስ ወዳድነት በሚቀንስና በሚከላከል አብዮታዊ ፓርቲና መንግስት አንድ ለአምስት የተደራጁ ኮሚቴወች አይደሉም፡፡ መጀመርያ አንድ ሰው ከሌለና ራሱን ችሎ መኖር ካልቻለ፣ ብቸኝነቱን መጀመርያ ሌላው ማህበራዊ ባህሪውና ፍላጎቱ ጎደሎ ካላደረገው እንዴት ቤተ ሰብ ሊቀጥል ይችላል፣ መጀመርያ ቤተ ሰብ ከሌለ የሰው ልጆች ማህበራዊ ባህሪና ፍላጎቶቻቸው አንድ ዓይነት የሆነውን ቤተ ሰብ አሁንም ጎደሎ ካላደረገው ማህበረሰብ፣ ሃገር ዕውን ሊሆኑና ሊቀጥሉ  አይችሉም፡፡

አቶ በረከት ሊረዱት የሚገባ የሰው ልጅ እጅግ ራስ ወዳድ እንደሆነ ቀደም ብሎ በተያዘው ግንዛቤ መሰረት ሃገር፣ ህግንና ስርዓት የግዴታ አስፈላጊወች እንደሆኑ በማሰብ በብዙሃኑ ፍላጎትና ጥቅም ላይ ሳይሆን በጥቂቶች መረን በለቀቀ ራስ ወዳድነት ላይ ስለጫኑት ነው የካፒታሊዝም ስርዓት ዕውን የሆነው፡፡ በብዙሃኑ ላብ ጥቂቶች በሃብት ሰማይ መድረሳቸውን ከላይ የተመለከተው ሶሻሊዝምና የእርስወ አመለካከት ተገቢውን ባህሪ ራስ ወዳድነትን አውግዞ ብቻ በመነሳቱ፣ በቀደምት ባለሃብቶች የነበረውን ከራስ ወዳድነት የሚከፋውን ባህሪ የወረሰው በስልጣንም ፣ በጥቅምም አሻሽሎ ነው፡፡ ከራስ ወዳድነት በላይ የከፋን የስልጣን ጥምና ጥቅመኝነት ባህሪን ሰፊው- ህዝብ፣ ወዛደሩ፣ ፓርቲው በሚሉ መሸፈኛወች ለጊዜው ማሽሞንሞን ቢቻልም በመጨረሻ ከነበረውም ካፒታሊዝም በላይ የአንድ ቤተ-ሰብ ስርዓቶችን ዓለም የተቀበለቸው በዚህ አብይ ምክንያት ነው፡፡ የእርስወና የጓዶችወም እንዳለመታደል ሁኖ የሚከፋ ነበር፡፡

ጥቅመኛና ጉልበተኛ በነበሩት ፊውዳሎች ላይ ብቻ ጣታችሁን ቀስራችሁ ተነሳችሁ፣ ከዓመታት የእርስ በእርስ መተላለቅ የወጣትነት ዘመንን ጫካ ከበላው በኋላ፣ በጉልምስናችሁ በከተማ ጠጅና ጮማን፣ በውስኪና በኮክቴል፣ ጠገራ ብርን በስዊዝ ባንክ ዶላር፣ ሰንጋ ፈረስን በኮብራና በአውሮፕላን ራሳችሁን በነበሩት ባህሪ፣ ፀባይና እግር ተካችሁ፡፡ ይህም ከዚያ የሚያልፍ የከፋ በሽታ እንጅ ራስ ወዳድነት እንዳልሆነ ልብ ይበሉ፡፡ ጥንት ጠጅና ጮማ፣ ጠገራ ብርና የሚጫን ሰንጋ ፈረስ የጭሰኛው አርሶ አደርና አርብቶ አደር አልነበሩም፡፡ ፀለምተኛ አይደለሁም! ዛሬ እነዚህ በቅደም ተከተል በውስኪና ኮክቴል፣ በስዊዝ ባንክ ዶላር፣ በኮብራና በአውሮፕላን ተቀይረዋል፡፡ የድሃ ሀገር ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እንኳ ሊሸከማቸው ያልቻለ እንደ ጥንቱ የጥቂቶች ሃራራ ማስታገሻ፣ የብዙሃኑ የመከራ ቀንበር ናቸው፣ ስለዚህ ለውጥ የለም፡፡

ወደ ሁለተኛው ስናቀና በእርሳቸው ዘመን ህወሃት ኢህአዴግ ከህዝባዊ ቅቡልነትና ስምምነት ሃይልንና ጉልበትን ስለመረጠበት ለማስረዳት፣ እና ከዚህ ተቃራኒ በሆነው ስርዓቱን በብዙሃኑ ስምምነትና መልካም ፈቃድ ላይ ለማቆም የተጀመረውን ለውጥ ላይ ጥያቄን ለማንሳት፤  መሪወችን በባለ ዋሽንትና ተመሪውን ብዙሃኑን ህዘብ በነብር መስለው አቅርበዋል፡፡ ይበልሃል ለማለት ሳይሆን አይቀርም “…..ስኬታማ ፓርቲወች የራሳቸው ድል እስረኞች ናቸው፡፡ ነብር በዋሽንት ይመሰጣል ሲባል ሰምቶ ይህን አደገኛ ፍጥረት ጥኡም የዋሽንት ዜማ ያስለመደ ከብት ጠባቂ ትንፋሽ ያጠረው ጊዜ በነብር እንደሚበላው ሁሉ፣ ህዝብን መልካም ነገር ያቀመሰ ፓርቲ ትንፋሽ ያጠረው ጊዜ ዕጣው ተመሳሳይ ይሆናል፡፡ ተሳክቶልኛል ብሎ በመኩራራት ወይም ችግር የለውም ብሎ በመዘናጋት መልካም ለመስራት የተዘናጋ እንደሆነ፣ አልፎ ተርፎም ህዝብን ከማገልገል መስመር ወጥቶ የግል ምቾቱን ያሰቀደመ ለት ከለውጥ ፈላጊው ማህበረሰብ ጋር ከመላተምና ይህን ከመሰለው አደጋ ማምለጥ አይቻልም፡፡ ” ይላሉ አቶ በረከት፡፡

ሃያ ሰባት ዓመት ከተጨማለቁበት ፖለቲካና በመጨረሻ ከጠበቃቸው አያያዝ ጋር የማይሄድ፣ ስኬትን ማጣጣም ባይጠላም ችግርን የሚጋራውን፣ የሚያስታምመውን ታጋሽ ህዝብ በዚህ ምሳሌ መገለፅ  አይችልም ፡፡ ችግርን የሚረዳ፣ የደከመውን የሚያበረታ፣ የሚያግዝ፣ ካሳተፉት አብሮ የሚሰራ ካልሆነ በተሻለው ለመተካት የሚፈልግና የሚጥር እንጅ ያፈራቸውን ልጆቹን የሚበላ አደገኛ ፍጡር በሆነ የሚመሰል ህዝብ በአቶ በረከትና ጓዶቻቸው አዕምሮ ውስጥ ብቻ እንጅ ዓለም ላይ የለም፡፡ ዛሬ አቶ በረከትም ጓዶቻቸውም ከስንፍናቸው፣ ከጥቅመኝነታቸው፣ ከዘረኝነታቸው፣ ከሴራቸው ጋር ተከብረው የተቀመጡት በህግና በስርዓት አቅም ብቻ ከመሰላቸው ተሳስተዋል፡፡ ህግን ስርዓትን በሚያከብር፣ ቂምንና በቀልን በሚንቅ ይቅርታንና ፍቅርን በሚስቀድም ህዝብ ምክንያት ነው፡፡

አቶ በረከት ቢረዱት ነብር እንስሳ ነው፣ በደመ ነፍሱ መጀመርያ የተፈጥሮ ጥያቄውን ለመመለስ፣ ለመመገብ፣ ፍላጎቱን ለማርካት ፊት ለፊት አደኑን ከማሳደድ፣ ያገኘውን ከመዋጥ  ውጭ ሌሎች አማራጮች የማይታዩት፣ እርስወ እንደሚሉት አረመኔ ሳይሆን ጠባዩ የባህሪው በመሆኑ ምስኪን እንስሳ ነው፡፡ በተመሳሳይ የሰው ልጅ በተፈጥሮው መጀመርያ የነፃነት፣ የእኩልነት፣ የአውነትና የፍትህ ባሪያ ነው፡፡ ወደ እንስሳት የሚያወርዱት ተመሳሳይ ባህሪወች ቢኖሩትም ሁሉንም ፍላጎቶቹን ለማሳካት አማራጮችን የመመዘን፣ የመመልከት የማማተርና የመፍጠር ተሰጥኦ ባለቤት የሆነው የሰው ልጅ እንደ ነብሩ ምስኪን እንስሳ አይመስልም፡፡ ዳይኖሰር ሲጠፋ የሰው ልጅ የቀጠለው በዚህ ምክንያት ሲሆን ከላይ እንደ ገለፅኩት የሰው ልጅ በተፈጥሮ ባህሪው ሳይሆን በሚያንጋድዳቸው ባህሪወቹ ላይ አቆጥቁጠው፣ አድገው፣ ፍሬ የሚያፈሩ እርጉም ጠባይወችን ሊያሳይ ይችላል ፡፡  በእርስወ ምሳሌ መሰረት እንዳለ መታደል ሁኖ በመጨረሻ እንደነበረው ድርጅትወ ኢህአዴግና ብዙሃኑ ህዝብ፣ ሰውና ነብሩ ተፋጠጡ፡፡ ሰውን መቼም አይስቱትም ዕጣ ፈንታውን ላለመቀበል፣ አጉል ባህሪውን ለማራዘም፣ የነብሩን እውነተኛና የመጀመርያ ፍላጎት ለመንፈግ የብሄር ብሄረሰቦች እኩልነትን ፖለቲካ፣ የልማታዊ መንግስትና አብዮታዊ ዲሞክራሲ የፖለቲካ መስመር፣ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት፣ መሰረተ ልማት የተሰኙ ዋሽንቶችን ይነፋል፤ ትንፋሽ እስከሚያጥረው ድረስ፣ ትንፋሽ ቢያጥረውም ባያጥረውም ህወሃት ኢህአዴግን ግን ህዝብ አልዋጠውም፤- ህዝብ ነብር ስላልሆነ፡፡ በህዝብ መልካም ፈቃድ ላይ የቆመና አሳታፊ የሆነ መንግስት፣ ሲያንቀላፋ የሚያነቃው፣ ሲሳሳት የሚያርመው፣ ህዝብና ሲደክም የሚቀየርበት ስርዓት ያለው መሪም ህዝብም ከእርሰወ ሟርት ነፃ ነው፡፡ ጅምሩ በትክክለኛው ጎዳና ላይ ስለሆነ ስጋት አይግባወት፣ የተፋጠጡት ነብርና ባለ ዋሽንቱ ሰው ተለያይተዋል፣ ነብሩ ባለወሽንቱን ሳይበላውና ነብሩ ሳይረክስ መሆኑ ደግሞ ደስ ይላል፡፡

በአጠቃላይ ከአቶ በረከትም ይሁን የህወሃት ጓዶቻቸው  ስህተት ብዙ ተምረናል፣ ለወደፊትም እንማራለን፣ የበለጠ የምንማርበት ዛሬ ራሳቸው በትክክል የሚሰማቸውን ስሜት ቢናዘዙልን ነበር፡፡ ወደራሳቸው ተመልክተው፣ የገባር ጭቁኖች ግፍ፣ የፊውፋዳሎች የመከራ ቀንበር ያባነነውን ወጣት በረከትና እንዳለመታደል ሁኖ የፊውዳሎች ባህሪ ያዶለዶመውን፣ ያሰናከለውን የሽማግሌውን በረከት እውነተኛ ስሜትና ተመሳሳይ እውነተኛ ስሜቶች እንጅ የአልሞትባይ ተጋዳይወች ቀጣይ ሀሳብ ብዙ ዋጋ የላቸውም፡፡ ለእናንተ የህሊና ዕረፍትና ሰላም፣ ለቀጣዩ ትምህርት የሚሆነው እርሱ ብቻ ነው፡፡ ስለማይቀር ሳይጨልም ብትሳተፉበት ደግሞ አንድ ሌላ ነገር ነው እላለሁ፡፡