ብአዴን ህወሓት ለሱዳን አሳልፎ በተሰጠው መሬት ላይ መግለጫ ሰጥቷል። እነ አባይ ፀሀዬ ፈርመው የሰጡትን መሬት የሚመለከተው አካል ያልተሳተፈበት ነው ብሎታል!

ጌታቸው ሽፈራው

………………
“በመተማ ወረዳ ልዩ ስሙ ደለሎ በተባለው አካባቢ ታሪካዊ ዳራውንና ነባር የይዞታ መብታችንን ያላስጠበቀ፣ የሚመለከታቸውን አካላት ያላሳተፈና የጋራ አቋምም ያልተያዘበት ውሳኔ ተሰጥቶ እንደነበር አውቀናል፡፡ ይህ ውሳኔ ብአዴንና አመራሮቹ ለረጅም ጊዜ በህዝብ ዘንድ ባልተገባ መልኩ ሲታሙና ሲጠረጠሩ እንዲቆዩ አድርጓል”
………………………………………
” በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ያለው የድነበር ማካለል ጉዳይ በዘላቂነት እስኪፈታ ድረስ የሁለቱም ወገን አርሶ አደሮች የያዙትን የእርሻና የደን መሬት እንደያዙ እየተጠቀሙ እንዲቆዩ በሁለቱ ሃገራት መንግስታት መካከል ስምምነት ተፈርሞ መቆየቱ ይታወሳል፡፡
ይሁን እንጅ በተለይ በመተማ ወረዳ ልዩ ስሙ ደለሎ በተባለው አካባቢ ታሪካዊ ዳራውንና ነባር የይዞታ መብታችንን ያላስጠበቀ፣ የሚመለከታቸውን አካላት ያላሳተፈና የጋራ አቋምም ያልተያዘበት ውሳኔ ተሰጥቶ እንደነበር አውቀናል፡፡ ይህ ውሳኔ ብአዴንና አመራሮቹ ለረጅም ጊዜ በህዝብ ዘንድ ባልተገባ መልኩ ሲታሙና ሲጠረጠሩ እንዲቆዩ አድርጓል፡፡

በመሆኑም ውሳኔው በፌደራል መንግስት በኩል አስቸኳይ ማስተካከያ እንዲደረግበት እንጠይቃለን፡፡ ለጋራ የጸጥታ ማሰከበር ስራ ይጠቅማል የሚለውን ስምምነት ምክንያት በማድረግ በቋራ ወረዳ ልዩ ስሙ ነፍስ ገበያ በተባለው አካባቢ ለጊዜው ሰፍሮ የነበረው የሱዳን ወታደርም ይዞታ እያሰፋፋና ቋሚ ካምፕ እየገነባ ከያዘው ጊዚያዊ ይዞታ ሳይለቅ መቆየቱ ተገቢ እንዳልሆነ መዕከላዊ ኮሚቴው ገምግሟል፡፡

የካመፑም መኖር የድንበሩን ጉዳይ የበለጠ እያወሳሰበውና የክልሉ አርሶ አደሮችም የእርሻ ስራቸውን በሰላም እንዳያከናውኑ እንቅፋት እየሆነ ይገኛል፡፡ ከዚህ አኳያ የሱዳን ወታደር እስካሁን ድረስ ከያዘው ይዞታ ለቆ አለመውጣቱ ተገቢ ባለመሆኑ በፍጥነት ከይዞታችን ለቆ እንዲወጣና የፌደራል መንግሥትም ይህንኑ እንዲያሰፈጽምልን እንጠይቃለን፡፡ ብአዴን በክልላችን የሚገኘው ይህ የኢትዮ ሱዳን የድነበር ጥያቄ የነዋሪወችንና የአርሶ አደሮቻችንን ይዞታ መሰረት አድርጎ፣ ታሪካዊ ዳራውን ሳይለቅና የሃገርን ሉዓላዊ ጥቅም ባስከበረ መንገድ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድበት ጥረት ማድረግ እንደሚገባ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡