ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ የቀድሞው የኢትዮጵያ መሪ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ምኅረት እንደማያገኙ ገለጹ።

ጠቅላይ ምኒስትሩ በዛሬው ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “አዋጅ ከሕገ-መንግሥት በታች የሆነ ሕግ ነው። ህገ-መንግሥቱ በምኅረት አዋጅ የቀይ ሽብር ጉዳይ እንደማይካተት በግልፅ ያስቀምጣል።
ስለዚህ አሁን ባለው ሁኔታ ኮሎኔል መንግሥቱ በምኅረት ወደ ኢትዮጵያ አይመጡም” ሲሉ አስረግጠው ተናግረዋል።

 

በስደት ዚምባብዌ የሚኖሩት ኮሎኔል መንግሥቱ ምኅረት ሊያገኙ የሚችልበት ዕድል ሊኖር እንደሚችል ግን ፍንጭ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ምኒስትር አብይ “ሕገ-መንግሥቱ ይኸን አንቀፅ አሻሽሎ እንደዚህ አይነት ወንጀሎች የሚያካተትበት ዕድል ወደ ፊት ካጋጠመ እሳቸውም ሊካተቱ ይችላሉ።

አሁን ባለው ሁኔታ ግን ሕገ-መንግሥቱ በግልፅ በቀይ ሽብር የተሳተፉ ኃይሎችን በምኅረት አዋጅ ማስተናገድ እንደማይቻል ስለሚገልፅ እና አዋጅ ከሕገ-መንግሥቱ በታች ስለሆነ በአጭር ጊዜ አይጠበቅም” ብለዋል።
DW AMHARIC