በአፈታሪክ ይሁን በታሪክ ብዙም ባይገባኝ የኢትዮጵያ ነገስታት ከንጉስ ሰሎሞን የወረሱት ደም እንዳለ ተደርጎ ሲነገር ቆይቷል በዛም የሰሎሞናውያን ሥርወ-መንግስት ሲባል ቆይቷል፡፡ ብዙዎች ይሄ ዝም ብሎ ተረት ተረት ነው ቢሉትም አሁን ሳይንስ የደረሰበት የሞለኩላር ጄኔቲክስ ጥናት ውጤት በእርግጥም ሲባል የነበረውን በንግስት ማክዳ (የሳባ ንግስት) በኩል የሰሎሞን ዘር ወደ ኢትዮጵያ እንደገባ እየመሰከረ ይገኛል፡፡ ነገስታቶቹ ብቻ ሳይሆኑ ኢትዮጵያውያን በአጠቃላይ ግማሽ አካባቢ የሚሆነው ደማቸው ከንጉሱ ሰሎሞን ዘር ጋር እንደሚገናኝ ነው የሳይንስ ውጤቱ እየተናገረ ያለው፡፡ ባለፈው ይህን አስመልክቶ ያስነበብኳችሁን የሳይንስ ምርምር ውጤት ተመልከቱ፡፡ https://www.satenaw.com/amharic/archives/62859 በምስሉ የምታዩት ሰማያዊው የሌቫንት ድርሻ የሰሎሞን ዘሮችን ነው የሚያመለክተው፡፡
ዛሬ ስለ ሰሎሞናውያን ለማውራት ሳይሆን የዛሬው የኢትዮጵያ መሪ(ንጉስ) አብይና የንጉስ ሰሎሞን ልጅ የሆነው የሮብዓም ታሪክ ጉዳይ ስላስገረመኝ ነው፡፡ ሮብዓም የሰሎሞን ልጅ በአባቱ በሰሎሞን ምትክ ሲነግስ የአባቱ ዘመን ሽማግሌዎችን ሰብስቦ ሕዝቡን እንዴት ማስተዳደር እንደሚገባው ምክር ይጠይቃቸዋል፡፡ እነሱም ይህ ሕዝብ ራስህን ዝቅ አድርገህ በትገዛለትና ብታገለግለው ፍጹም ላንተ ይገዛልሀል ብትበድለው ግን ያምጽብሀል አባትህ የከበደበትን ቀምብር አቅልልለት ብለው ይመክሩታል፡፡ እሱ ግን ከእነሱ በኋላ በእድሜ እንደሱ የሆኑትን ይሰበስብና እንደገና ያማክራል፡፡ የእሱ እኩዮች የሆኑት ታዲያ የምን ለሕዝብ ማጎብደድ ነው፡፡ ለሕዝቡ ማለት ያለብህ እንደውም ከአባትህ የበለጠ ቀምበር መጫን እንዳለብህ ነው ስለሆንም የእኔ ትንሷ ጣቴ ከአባቴ ወገብ ትወፍራለች፣ አባቴ በጅራፍ ገረፋችሁ እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ…… ብለው ለሕዝቡ ንገረው አሉት፡፡ እሱም የሽማግሌዎቹን ምክር ቸል ብሎ የእሱ ቢጤ ጎረምሶችን ምክር ሰማ፡፡ በሕዝቡም ላይ በደልንና ግፍን አበዛ ሕዝቡም አመጸበት መንግቱም ተከፈለች፡፡ የጠቢቡ የሰሎሞን ልጅ የናቀውን ምክር አብይ ከሽማግሌዎቹ በደንብ የሰማው ነው የሚመስለው፡፡ እና ምን ትላላችሁ የጠቢቡ ሰሎሞን ልጅ ጅሉ ሮብዓም ነው ወይስ ብልሁ አብይ?! የአብይና አጋሮቹ ዛሬ ላይ እያደረጉት ያሉት በእርግጥም እነዚያ ለሮብዓም ሲናገሩ የነበሩ የሽማግሌዎቹን ምክር አንደወረደ ነው የሚመስለው፡፡ ዛሬ ሚስኪኗ እማሆይ ቤት ከአዲስ አበባው ከንቲባ ሌላው አጋሩ ታከለ ኡማ ጋር ተገኝተው ምግብ ሲበሉ የታዩበታዩበትን ክስተት እንደቀድሞዎቹ (ሮብዓሞች) ቢታሰብ እንኳን በእውን በሕልምም የሚመጣ አይመስልም፡፡ እንዲህ ያከበራችሁት ሕዝብ ለዘላለም ብትገዙት ምን ገዶት፡፡
ሰሞኑን ብዙ ለውጥ እንደሚኖር እንጠብቃለን፡፡ ወሮበሎቹ ሲጫወቱበት የነበረው ፕሮጄክት ሁሉ የአባይን ግድብ ጨምሮ ከዚህ በኋላ በሚኖር ጠንካራ ሥምሪት በፍጥነት ተጠናቀው እንደምናያቸው ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ከዚህ በኋላ የሕዳሴ ግድብ የሚል ቃል መነሳት የለበትም፡፡ ለነገሩ አንዲት የሆነች አባይ ላይ እሷም በጃፓኖች የተንጠለጠለች ድልድይ ትልቅ ሆና የሕዳሴ ድልድይ በሚል ሲጨፍሩብን ኖረዋል፡፡ ያበሳጫል፡፡ ዓለማችን በብዙ ኪሎሜትሮች የሚለኩ ድልድዮችን በየአገራቱ በምትሰራበት በዚህ ዘመን ለእኛ ያቺ አባይ ላይ ያለች መሸጋገሪያ ሕዳሴ ተባለች፡፡ ከዛ ግድብ በሚል የእኛንው ገንዘብ ለመበዝበዝ ሕዳሴ በሚል እየዘፈኑ አጃጃሉን፡፡ ያናድዳል፡፡ የኢትዮጵያን ሕዳሴ እንዲህ በኮልኮሌ የሚለኩትን አስተሳሰቦች ከዚያች ምድር መንቀል ግድ ይለናል፡፡ የአባይ ግድብ አገሪቱ ከሚያስፈልጓት አንዱ እንጂ ሕዳሴ አደለም፡፡ የእኛ ሕዳሴ አሁን ነው ጭላንጭሉ እየታየ ያው፡፡ የዜጎች ተስፋ፣ ደስታ፣ ቁጭት፣ …ወዘተ፡፡ ትውልድ እያመከነ የወሮበላ ምድር ያደረጋት ያ ወሮበላ ቡድን ላያንሰራራ መወገዱ ነው የእኛ ሕዳሴ፡፡ እኛ ለእኛ የሚያስፈልገውን ሁሉ ለመስራት ሙሉ አቅሙ አለን፡፡
አሁን ሁሉም በሙያው ምን መሥራት እንደሚችል ያስብ፡፡ አብይ ሆይ አንድ ነገር ላንሳ፡፡ እንዲህ በቀላሉ እንደማይሆን አውቃለሁ፡፡ ግን ወደፊት መግፋት ግድ ይለናል፡፡ ከዚህ በኋላ የቡድን እየተባለ ማጭበርበሪያ የሆነው የኮታ መብት ጉዳይ በጽኑ ይታሰብበት፡፡ ከምንም በላይ የዜጎች መብት ጽኑ መሠረት ላይ ሊቆም ይገባዋል፡፡ በቁጥር ብዛትና የሆነ ብሔር ወኪል ነኝ በሚል ሳይሆን ሙሉ የሆነ የዜግነት መብት ያላቸው ኢትዮጵያውያንን መፍጠር ነው ግብ ማድረግ ያለብን፡፡ ብሔር፣ ባሕል፣ ቋንቋ ምናምን እየተባሉ የወሮበሎች መደበቂያ የሆኑ ዋሻዎች በሕግ ለፖለቲካ መጠቀሚያ እንዳይሆኑ መከልከል ያስፈልጋል፡፡ ይህ አካሄድ የሕዝቦችን ነጻነት በሚል የወሮበሎች መፈንጫ አድርጎናል፡፡ ብሔር ሆነ፣ ባሕል ወይም ቋንቋ የአገሪቱ እሴቶች እንደመሆናቸው መንግስት አንደመንግስት ሕግ አውጥቶ ባለቤቱ ከሆነው ሕዝብ ጋር ሊያበለጽጋቸውና ሊጠብቃቸው የሚገቡ እንጂ በምንም መልኩ የፖለቲካ ፓርቲ ሴረኞች መደበቂያ መሆን የለባቸውም፡፡ ስለዚህ ከብሔር ፖለቲካ ተላቀን ወደ ፍጹም የዜጎችን (የእያንዳንዱን) መብት ሙሉ በሙሉ ማስከበር መምጣት አለብን፡፡ ያኔ መሪዎች በኮታ ሳይሆን መሪ የሚሆኑት ቢያንስ አብዛኛው ሕዝብ በመሪነት ሲመርጣቸው ነው፡፡ አብይ አንተም ይህን ጉዳይ ጠቆም አድርገህዋል፡፡ ኢትዮጵያን ለመምራት የኦሮሞ፣ ወይም የአማራ ሕዝብ መረጠውና ፓርላማ መግባት ስለቻለ መሆን የለበትም በፍጹም፡፡ ከየትኛውም ብሔር በሉት ዘር ይምጣ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ ሊያቅፍ የሚችል አስተሳሰብና ብስለት ሲኖረው ብቻ ሊሆን ይገባል፡፡ ለአማራ ሕዝብ እታገላለሁ የሚል የኢትዮጵያ መሪ ሊሆን አይችልም፡፡ ለኦሮሞ ሕዝብ እታገላለሁ የሚል የኢትዮጵያ መሪ ሊሆን አይችልም ሌላም በቁጥር ትልቅ ኮታ አለኝ በሚል መሪ መሆን መቆም አለበት፡፡ ይህ በኮታ የሚደለደል አካሄድ አደጋ አለው፡፡ ይታሰብበት፡፡
ሌላው አሁን እያሳከረ ያለው የቋንቋ ጉዳይ ነው፡፡ እዚህም ላይ መምታታት አለ፡፡ ወሮበሎቹ ስልጣን እንደያዙ ብዙ አገሪቱን አሁን ወዳለንበት ምስቅልቅል የከተቱን ብዙ የወሮበሎች ውስኔዎች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ሁላችንንም ሊያግባባ የሚችል ቋንቋ የግድ ይላታል፡፡ ሆኖም ግን ከአንድ በላይ ቋንቋ በሚነገርባቸው አካባቢዎች እንደ አስፈላጊነቱ (መስፈርት ወጥቶ በሕግ በተቀመጠ አግባብ) መስፈርቱ በሚፈቅደው ሁኔታ የሚታዩ ቋንቋዎች ለሕዝብ አገልግሎት እንዲውሉ ማድረግ አስፈላጊነቱ ለሕዝቡ ብቻም ሳይሆን ለአሰራር ቅልጥፍናና ጥራትም ስለሚበጅ ነው፡፡ ለምሳሌ በአሜሪካ የአገሪቱ ቋንቋ በግልጽ ኢንግሊዘኛ እንደሆነ ቢታወቅም በብዙ ሥፍራዎች በርከት ያለ አንድ ሌላ ቋንቋ የሚናገር ማህበረሰብ ባለበት ያ ቋንቋ በመንግስት የአግለግሎት መስጫዎች በሕግ አገልግሎት የሰጣል፡፡ ለምላሌ በደሲ የእኛው አማርኛ አገልግሎት ከሚሰጥባቸው አንዱ ነው ይባላል፡፡ ይህ አይነት አሰራር በኢትዮጵያም ቢታቀድ፡፡ ተጨማሪ የፌደራል ቋንቋ የሚባለውን ለብዙ ጊዜ ቢሆን ከሚሉት ነበርኩ፡፡ አሁን ላይ ሳስበው ግን ብዙ ሌላ ውጥንቅጥ ያለው ችግር ነው፡፡ ሁላችንንም ሊያግባባ የሚችል ቋንቋ ያስፈልገናል፡፡ በአጋጣሚ አሁን በአለው ሁኔታ በብዙ ሥፍራ አማርኛ ለመግባቢያነት እየዋለ ነው፡፡ አማርኛን ከአማራ ጋር እያያዙ ከመተቸት እውነታውን በደንብ ማስተዋል ግድ ይላል፡፡ በሕንድ ብዙ ቋንቋ ይነገራል፡፡ ሕዝባቸው ከአለውም ሥፋት አኳያ የሚግባባበት ወጥ የሆነ ቋንቋ የለውም፡፡ ብዙ ሕንዶች ከተለያየ የአገሪቱ ክፍል ከመጡ የሚግባቡት በኢንግሊዘኛ ነው፡፡ አሁን ላይ ግን መንግስት የሒንዱን ቋንቋ በአገሪቱ ሁሉ ለማዳረስ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው፡፡ ብዜም ስኬት እያመጣ ነው፡፡ ይህ ማለት ሌሎች ቋንቋዎች ይከስማሉ ማለት አደለም፡፡ እነሱም በሚነገሩበት አካባቢ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸው ይሰራሉ፡፡ እሳቤው ኢንግሊዘኛን በሒንዱ ለመተካት ነው፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ውስጥ ሌላ አንድ የቋንቋ ስልት በሥርዓተ ትምህርቶች መካተት ያሉንን ቋንቋዎች ከመጠበቁና ከማሳደጉም በላይ በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት መፋጠንን ይፈጥራል ብዬ የማምነው በየክልሉ ተማሪዎች ቢያንስ አንድ ተጨማሪ ቋንቋ እንዲማሩ ማድረግ ነው፡፡ ለምሳሌ አማራ ክልል የሚማሩ ተማሪዎች መርጠው ኦሮምኛ ወይም ሶማሊኛ ወይም ትግሪኛ ወይም ሲዳምኛ ሊማሩ ይገባል፡፡ ሌላውም እንደዛው፡፡ ይህ በብዙ አገራት ዛሬ እየተሰራበት ያለ አሰራር ነው፡፡ ለምሳሌ በአውሮፓ ብዙ አገራት ኢንግሊዘኛና ተጨማሪ ፈረንሳይኛ ወይም ስፓኒሽ መማር በብዛት የሚሰራበት ነው፡፡ ልብ በሉ አገራቱ የራሳቸው ቋንቋ አላቸው ኢንግሊዘኛን ብዙዎች በወጥነት ነው የሚያስተምሩት፡፡ ፈረንሳይኛና ስፓኒሽ እንደ ቅደም ተከተላቸው ነው፡፡ ይህም ሆኖ ተማሪዎች ተገደው ሳይሆን ወደፊት የሚኖራቸውን አለም አቀፍ ግንኙነትና የሥራ እድል ከግንዛቤ በማስገባት ነው እንዲማሩ የሚደረጉት፡፡ በኢትዮጵያም የቋንቋዎችን አስፈላጊነት ከዚህ አንጻር ቢታይና ስርዓተ ትምህርቶቹ ቢቀረጹ፡፡ ለእኛ ከአገር ውስጦቹ በተጨማሪ ኢንግሊዘኛ በእርግጥም ግድ ይለናል፡፡ እኛ ከአለም አናመልጥምና፡፡ አሁን ቻይናና ጃፓንም እየሞከሩት ናቸው፡፡ ቢቻል እንደውም ጥራቱን የጠበቀ ኢንግሊዘኛ ቢሰጥ፡፡ የአንዱ ክልልን ቋንቋ ለሌላው በማስተማር ምን አልባትም በፌደራል ደረጃ ተጨማሪም ሆነ ራሱን ችሉ ቋንቋ ሊሆን የሚችል ሆኖ ሊያድግ የሚችል ቋንቋ ይፈጠራል፡፡ ያኔ ሕዝቦች ስለሚግባቡበት ራሳቸው የሚወስኑት እንጂ የእንትና ክልል ስለፈለግና ስላልፈለግ አይሆንም፡፡
ሌላው ከፊደል አጠቃቀም በተመለከተ ነው፡፡ እንደ እውነቱ ይህ የእኔ አስተሳሰብ እንጂ ይሁንም እያልኩ አደለም፡፡ ግን በስሜታዊነት ሳይሆን ቢሆን መልካም ነው ብዬ የማስበውን ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሁኔታ ለአገር ውስጥ ቋንቋዎች የግዕዝን ፊደል መጠቀም ብዙም ወጭ አያሶጣም የሚል እምነት አለኝ፡፡ ግን አሁን ብዙዎች ላቲን በመጠቀም የየራሳቸውን የተደራጀ አጻጻፍ ስለፈጠሩ ተመለሱና ግዕዝ ተጠቀሙ ማለት አንዱ አስቸጋሪ ጉዳይ ነው፡፡ ከመነሻው ችግር የነበረው የግዕዝ ፊደል የፖለቲካ ሰለባ በመሆኑ በስሜትና በጥላቻ የላቲንን መጠቀም እንደተወሰነ ነው የማስተውለው፡፡ ይህ በሆነበት ወቅት ብዙዎች ወደ ላቲን ቀየሩ፡፡ አንዳንዶች ላቲኑ አላዋጣ ሲል ወደ ግዕዝ የተመለሱ አሉ ለምሳሌ ሀረሪ፡፡ ግዕዝን የፖለቲካ ኢላማ አላደረግንውም ብሎ ለማሳመን የግዕዝ ፊደል ለእኛ ቋንቋ ምቹ አደለም የሚለው በቋንቋ ምሁራኖች አከራካሪ ነው፡፡ በእርግጥም የላቲን ፊደል ለብዙ ቋንቋዎች አገልግሎት ይሰጣል ሆኖም ሙሉ ሆኖ ሳይሆን እንደ አስፈላጊነቱ ሌሎች ምልክቶች እየተጨመሩበት ነው፡፡አብዛኞቹ የሚጠቀሙት እኛ ከ ኤ እስከ ዜድ ከምናውቃቸው ምልክቶች ተጨማሪ በማካተት ነው፡፡ ለምሳል β ይህ ምልክት በጀርመንኛ እንደ ረዥም ኤስ ይውላል፡፡ ለምሳሌ Straße የሚለው Strasse እንደማለት ነው፡፡ ግን ሙሉ በሙሉ ማለት አደለም፡፡ እና የግእዝም ፊደል እንደ አስፈላጊነቱ ሌሎች ፊደላትንም ሆነ ምልክቶችን በመጨመር ለየትኛውም ቋንቋ በሚፈለገው ሁኔታ ማዘጋጀት ሲቻል ነው ወደ ላቲን የተሄደው፡፡ በኢትዮጵያ ሁኔታ ለተማሪዎች የአገር ውስጥ ቋንቋዎችን በግዕዝ ፊደላት መጠቀሙ ጥቀሙ
- አገሪቱ ውስጥ በስፋት በዚህ ፊደል የሚታተሙና ከጥንት ጀምሮ ሲታተሙ የኖሩን ለማንበብ ያስችላል
- ተማሪዎች የላቲንን ፊደል በኢንግሊዘኛና በአገር ውስጥ ቋንቋ በመጠቀማቸው ምክነያት የሚመጣ ውዥንብርን ያስወግዳል
- ዛሬ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ሳይቀር የራሳቸውን ቋንቋ በላቲን የሚማሩ ተማሪዎች ኢንግሊዘኛ ሲጽፉ በዛው ለራሳቸው ቋንቋ በለመዱት አጻጻፍ የመጻፍ ዝንባሌ ይታይባቸዋል፡፡ በዚህም የተነሳ የኢንግሊዘኛ ቃላትን በትክል መጻፍ ይቸገራሉ
- ሶስተኛ በእርግጥ የግዕዝ ፊደል በቀጥታ ድምጽን መጻፍ ስለሆነ ቋንቋውን የማያውቅ እንኳን ቢሖን ፊደላቱን ከአወቀ ሊያነብ ይችላል
- የራስ መሆኑና ተጨማሪ ፍደል እውቀትም መሆኑ ጠቀመታ አለው፡፡ በአላም ላይ የራስ ፊደላት ያላቸው ብዙ አገሮች አሉ ከአፍሪካ ግን እኛ ብቸኛ ሳንሆን አንቀርም፡፡ አብዛኛው አለም እኛን የሚያየን ምንም ታሪክና መሠረት እንደሌለን ነው፡፡ ግን ይህን መሰል ሀብታችንን ስናሳይ በእርግጥም ያልጠበቁት ስለሚሆን ለእኛ ለራሳችን የሚኖራቸው ምልከታ ሳይቀር ይቀየራል፤፡ ይህ አይነት እውነት በራሴም ገጥሞኛል፡፡
ሁሉም ልብ ሊለው የሚገባ የግዕዝ ፊደል እንደተባለው የሳባውያን ሊሆን ይችላል ግን ሁላችንም ስንጀምር ሳባውያን እንደሆን ከላይ ሊንክ ያደረኩላችሁን በደንብ አስተውሉ፡፡ ይህ ፊደል በተወሰኑት ወገኖች ሲቀር ሌሎች ተውት እንጂ ከጅምሩ አመጣጡን ከራሳችን አመጣጥ አስተውሉት፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ታሪካዊ ቅርስ በሉት የጥንት ስልጣኔ አሻራ ትግራይ ውስጥ ስላለ የትግሬ፣ አማራ ውስጥ ስላለ የአማራ፣ አይምሰላችሁ፡፡ እውነታው ፍጥጥ ብሎ የሚታየው ከላይ ሊንክ ያደረኩላችሁን በደንብ ስታስተውሉት ነው፡፡ የአክሱም ሀውልት ሲሰራ ትግሬ የሚባል ነግር አልነበረም የላሊበላ ፍልፍል አብያተክርስቲያናት ሲሰሩ አማራ የሚባል አልነበረም፡፡ ዛን ወቅት ምን አልባትም ዛሬ ሲዳማ የተባለው ሕዝብ አክሱማዊ ነበር፡፡ ዛሬ ኦሮሞ የተባለው የማክዳ መንግስት ነበር፡፡ ልብ በሉ አስተውሉ ማንም የራሱን ታሪክ የሌላ አያስመስል፡፡ በዛ ቀጠና እኛ ለዘመናት ነበርን፡፡ ከባሕር ወጣ ከማዳጋስካር መጣ ብለው የጻፉብን ከአሉ ይሄው እኮ በደማችን ያለው ማንነት ውሸት ነው እያለ ግልጹን ይነግረናል፡፡ አስተውሉ ሶስቱን የዘር ግንዶች የኢትዮጵያና አካባቢዋን (ሶማሌ፣ ሱዳን፣ ኤርትራና ጂቡቲን) ጨምሮ፡፡ አሪ፣ ሌቫንት(ምናልባትም ሰሎሞናዊያን)፣ ሌላው የማሳይ አባት፡፡ ይህ ዘር ማዳጋስካር የለም! ባህር ውስጥ የለም! ከማሳይና ታንዛንያ ውስጥ ከአለ አንድ ሕዝብ ውጭ የእኛን ደም ያለው ሕዝብም የለም! ታንዛንያ ሂዱ የዚህ ደም በለቤቶች እኛ ከኢትዮጵያ ነው የመጣንው ሲሏችሁ ትሰሙታላችሁ፡፡ በጥናቱ ሩዋንዳውያን አልተካተቱም ግን እኛን ሊመስሉ ይችላሉ፡፡ ሁሉም ከሰሜን ወደ ደቡብ ነበር የሄደው፡፡ የኦሮሞን ታሪክ የጻፉት አስመሮም ኦሮሞን ከመዳወላቡ ሳይሆን ከሰሜን ቀይ ባሕር አካባቢ እንደመጣ ይጠቁማሉ፡፡ በስሜት አንነዳ ሰሜን ያለውን ቅርስ ለአማራና ትግሬ ማስረከብ ራስን መካድ ነው፡፡ እንደው የሚታወቀውን የላሌበላን ጉዳይ እናንሳ፡፡ ላሊበላ በግልጽ እስከዛሬም አገው እየተባል በሚጠራ ሕዝብ የተሰራ ነው፡፡ ዛሬ ግን ላሊበላ የት ነው፡፡ ለሰቆጣ መቅረቡ አንድ ነገር ሆኖ ሙሉ በሙሉ ግን በአገው ሕዝብ መሀል አደለም፡፡ ወደ አክሱም የመመዘዘውም ታሪክ እውነት ይሄው ነው፡፡ በእነዛ ዘመናት ዛሬ በለቤት የተደረጉት አማራና ትግሬ ከእነጭርሱም አልነበሩም፡፡ በቀላሉ የዜይን ሕዝብ አስቡት፡፡ የዜይ ሕዝብ ደቡባዊ ነው ግን የግዕዙም ፊደል ሌሎቹም ምልከቶቹ ከሰሜን ተከተለውት መጥተዋል፡፡ በተመሳሳይ የወንጭን አካበቢ ሕዝብ አስተውሉ፡፡ ዛሬ ለእያንዳንዳችን ባሕል ምናምን የመሰለንን እናስተውል፡፡ ኢሬቻን ጨምሮ፡፡ ከዚህ በፊት ጠቁሜዋለሁ ኢሬቻ የኦሪት ሥርዓት ምልክት ሊሆን እንደሚችል፡፡ ምሁር ነን የምትሉ እዚህ ምርምር ውስጥ ግቡ ሕዝቡ የገነባችውን ባህልና እሴቶችን መደበቂያ አድርጋችሁ መርዝ አትርጩ፡፡
እነ አብይ ሕዝቡን በዚህ ታሪካዊ መሠረት ላይ እንዲያስቀምጡት ተጨማሪ ጉልበት ቢሆናቸው ብዬ ነው፡፡ ስለሆንም በአለማስተዋል የምንሄድባቸውንና የምንወስንባቸውን ነገሮች ቆም ብለን እናስብ፡፡ መሠረታችን ሩቅ ነው፡፡ አባቶቻችን በአለፉበት ያለው ሁሉ የእኛ ነው፡፡ ግዕዝም በማያሻማ ሁኔታ የአማራ ወይም የትግሬ ፊደል እንዳልነበረ ግልጽ ነው፡፡ ከመነሻው የፊደሉ ፈላስፎች የሁላችንም አባቶች የሆኑት የመጀመሪያዎቹ እንደነበሩ እናስተውል፡፡ በመሆኑም ከመንም በላይ ግዕዝ ፊደል የእኛ ነው! የአፍሪካም ነው! ወደፊት እንደውም ለሌሎች አፍሪካውያን ሳያቀር ማስተማር ቢታሰብ፡፡ አፍሪካውያን በፍቅር እንደሚቀበሉት አምናለሁ! ያኔ የእኛ ይሉታልና! የአፍሪካ የፊደል በለቤትነት በእኛ ይወከላል! በዚህ ሁሉ እሳቤ የግዕዝን ፊደል መጠቀምን አሁንም ቢታብ፡፡ የግዕዝ ፊደላትን ለየቋንቋዎቹ እንደሚስማማ ሁኔታ ተጨማሪ ሆሄያትንም ሆን ሌሎች ምልክቶችን በማካተት በባለሙያዎች ቢሰራበት፡፡ ያኔ የግዕዝ ፊደል አደለም የኢትዮጵያን ቋንቋዎች የወፍ ድምጽ ሳይቀር የሚመዘገብበት ይሆናል፡፡ የዚህ ሁሉ ቋንቋ ድምጾች ማካተት ከቻለ በእርግጥም ከሰው ድምጽ ውጭ የሆኑ ልዩ ድምጾችንም ለማስተናገድ የሚችል ልዩ ፊድል ይሆናል፡፡ ያኔ ሌሎች ፈልገውት ይመጣሉ፡፡ ይህ ሊሆን የሚችል ነገር ነው፡፡
ቅዱስ እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ! አሜን1