ከውጭ የሚገቡ ፓርቲዎቸን ከዕቃ ጋር አመሳስላችሁ እንዳታዩብኝ። በርግጥ በተለምዶ ከውጭ ለሚገቡ ዕቃዎች ከፍተኛ ግምት; ቅድሚያና ዋጋ እንሰጣለን። ለነገሩ ከውጭ ይገባሉ/ገቡ ለተባሉ ፓርቲዎችም ቅድሚያ መስጠታችን አልቀረም። ምናልባትም ከውጭ ሲገቡ ከሌሎች አገሮች ልምድና ተሞክሮ የተሻለ የተሻለ ነገር ይዘውም ሊሆን ይችላል። በአንፃሩ እዚሁ አገር ውስጥ ተቋቁመው የነበሩትን ለማጠናከር ያልሞከርነው እኩል ዋጋ ስለማንሰጣቸው ወይም ብዙም የተለዬ ነገር ስለማንጠብቅ ይመስለኛል። አንዳንዶቹ ይህንኑ ተገንዝበው (ይመስላል) ከውጭ ከሚመጡት ጋር ተቀላቅለው ራሳቸውን ለፖለቲካ ገበያው ለማቅረብ መንገድ እየፈለጉ ነው። ተቀላቅሎ ወደገበያው መግባት የማይነቀፍ ቢሆንም በዚህ ሩጫ ውስጥ ያገኙትን ሁሉ ሳያላምጡ መዋጥ ግን አደጋ ሊኖረው ይችላል።
ከዚህ አንፃር; ቆም ብሎ ነገሮችን ማጤንና ተገቢ ጥያቄዎችን ማቅረብ ያስፈልጋል። ለመሆኑ የፖለቲካ ገበያው (የህዝቡ) ፍላጎት ምንድነው? ፓርቲዎችን የሚቀበለው እዚሁ አገር ውስጥ የተቋቋሙ ወይም ከውጭ የገቡ በሚል ወይስ በያዙት አጀንዳ? ለመሆኑ ከውጭ የገቡት/የሚገቡት በአግባቡ ተፈትሸዋል/ይፈተሻሉ? እነሱስ ምን ያህል ራሳቸውን ገምገመዋል?
ቀደም ሲል ሲተከተሉት የነበረውን የትግል ስልትና ስትራቴጂ አዋጭነት/ውጤታማነት ዛሬ ላይ እንዴት ነው የሚገመግሙት? እነዶ/ር አብይ ወደሥልጣን ባይመጡና ከኤርትራ መንግሥት ጋር እርቅ ባይፈጠር ኖሮ በተለይ ኤርትራ ውስጥ የነበሩት ኃይሎች የትግል አቅጣጫቸው ምን ይሆን ነበር? በሌላ በኩል ከኢሳያስ መንግሥት ጋር እርቅ የፈጠረው የቀድሞው ህወሓት/ኢህአዴግ አመራር ቢሆን ኖሮ (the other scenario) በኤርትራ የመሸጉት የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ኃይሎች ዕጣ-ፈንታ ምን ይሆን ነበር? የሚሉት ጥያቄዎች አነጋጋሪ ናቸው።
ስለሆነም ሁሉም ወገን ከተሰቀለበት ወደመሬት ወርዶ ራሱን በአግባቡና በሐቅ መገምገም አለበት። እነዚህ ወገኖች (አብዛኞቹ) ከዚህ በፊት በአንድ ወይም በሌላ መንገድ በትግል ውስጥ የነበሩ ናቸው። ስለሆነም በነበሩባቸው የትግል መስመሮች ውስጥ ስኬቶችና ውድቀቶቻቸውን አንድ – ሁለት ብለው መለየት አለባቸው። ለዚህ አስተዋፅኦ ያደረጉ የትግል ስልትና ስትራቴጂዎቻቸውንም በቅጡ መፈተሽ አለባቸው።
ከዚህም ባለፈ የትግል አጀንዳዎቻቸውን በግልፅ ማስቀመጥ አለባቸው። ራሳቸውን አገዝፈውና ጠንካራ ተፎካካሪ ሆነው ከመውጣት ባለፈ ወዴት ሊወስዱን ይፈልጋሉ? ይህች አገር በተለያዩና (ባብዛኛው) ተቃራኒ ፍላጎቶችና (conflicting interests) ህልውናዋን በሚፈታተኑ ጥያቄዎች የተወጠረች መሆኗም መዘንጋት የለበትም። ችግሮችችንን ከዚህ በፊት በተሰለቸው ጩኸትና በተለመደው አካሄድ ለመፍታት መሞከር እንደማይቻል መገንዘብም ያስፈልጋል።
ችግሮቻችንን መፍታት የሚቻለው የኢትዮጵያን ነባራዊና ተጨባጭ ሁኔታ በመገንዘብና እሱን መሠረት አድርጎ በመነሳት ብቻ ነው። አሁን ላይ በሆያ-ሆዬና እርስ በርስ በመደናቆር የትም መድረስ እንደማይቻል በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ስለሆነም ሁሉም ወገን “ኳስ በመሬት” በማድረግ በተረጋጋና በሰከነ መንፈስ መነጋገር ይኖርበታል። በዚህ መንገድ የሀሳብ ብዛህነትን ሊያስተናግድ የሚችል ዴሞክሪያሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባት ጠንካራ መሠረት መፍጠር ይቻላል።
ለማንኛውም በግልም ሆነ በቡድን ከውጭ የገባችሁ ኃይሎች እንኳን ደህና መጣችሁ!
ኢትዮጵያዊነት ይለምልም!!!
—
“
ከሞሐመድ ዓሊ ሞሐድ ፌስቡክ ገጽ የተገኘ