አብረሃም ፈቀደ 

Aug 27, 2018  141

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 212010 (ኤፍ..) ዕድሜያቸው 14 ዓመት ለሆናቸው ልጃገረዶች በመደበኛነት የማህጸን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት ከመጪው ጥቅምት ጀምሮ እንደሚሰጥ ተገለጸ፡፡

ክትባቱ በትምህርት ቤቶች፣ በጤና ተቋማትና በጊዜያዊ የክትባት ማዕከላት የሚጀመር መሆኑን ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ይህ የተባለው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በክትባቱ አጀማመር ላይ ያተኮረ መርሃግብር ባዘጋጀበት ወቅት መሆኑ ተገልጿል፡፡

ሚኒስቴሩ የማህጸን በር ካንሰር ክትባትን ከወጪና ከተፈጻሚነት አኳያ በሙከራ ደረጃ ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲያካሂድ መቆየቱ ይታወሳል፡፡

የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተወካይ አቶ አስናቀ ዋቅጅራ በኢትዮጵያ የማህጸን በር ካንሰር ከጡት ካንሰር ቀጥሎ በስፋት በወሊድ ዕድሜ ክልል የሚገኙ ሴቶችን የሚያጠቃ በሽታ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ በየዓመቱ በበሽታው የሚጠቁ ሰዎች ቁጥርም ከ4 ሺህ 600 በላይ ይደርሳል ብለዋል፡፡

በበሽታው ከተጠቁት ውስጥም ከ3 ሺህ 200 በላይ የሚሆኑት ህይወታቸው እንደሚያልፍ አቶ አስናቀ ገልጸዋል፡፡

የማህጸን በር ካንሰር የሚተላለፈው በሽታው ከያዘው ሰው ጋር በሚደረግ የግብረ ስጋ ግንኙነት ነው ተብሏል፡፡

በኢትዮጵያ የክትባት መርሃግብር መሰጠት ከተጀመረ ወዲህ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ህጻናትን ህይወት መታደግ መቻሉን ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በዓለም ላይ ከ200 በላይ የካንሰር አይነቶች የሚገኙ ሲሆን ከነዚህ ውስጥም የማህጸን በር ካንሰር አንዱ ነው ተብሏል፡