26 August 2018

ዘካርያስ ስንታየሁ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (/) ወደ ሥልጣን ከመጡ ለመጀመርያ ጊዜ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ በሶማሌ ክልል ሰዎች ከአንበሳ፣ ከጅብና ከነብር ጋር ይታሰሩ እንደነበር ገልጸዋል:: በሶማሌ ክልል የነበረው ሰብዓዊ መብት ጥሰት በፊልም የሚታይ ልብ ወለድ እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረግ አይመስልም ብለው፣ ታሳሪዎች የሚጠበቅባቸውን ብቻ ሳይሆን ከሚጠበቅባቸው በላይ እንዲናዘዙ ለማስፈራራት ይህ ድርጊት ይፈጸምባቸው እንደነበር ተናግረዋል::

በቅርቡ በክልል በነበረው ግጭት ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በዜጎች ላይ ሲደርስ የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ ለመግባት ለምን ዘገየ በሚል ተጠይቀው፣ በክልሉ የሚደረገው ጣልቃ ገብነት ከፍተኛ ጥንቃቄና ብስለት ካልተደረገበት በስተቀር ክልሉን ብቻ ሳይሆን ቀጣናው ሊታወክ ይችል እንደነበር ተናግረዋል:: ለዚህም እንደ ማስረጃ ያነሱት ድሬዳዋ ላይ ሆን ተብሎ የጂቡቲ ዜጎች እየተመረጡ ጥቃት የደረሰባቸው ሲሆን፣ ይህም ግጭቱ ቀጣናዊ ይዘት እንዲኖረው ለማድረግ ታስቦ መሆኑን ጠቁመዋል:: ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድርጊቱ እንዴት እንደሆነና እነማን ፈጸሙት የሚለው በሒደት ወደፊት ተጣርቶ እንደሚገለጽ አክለዋል::

በክልሉ የተፈጸመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት እጅግ አሳፋሪ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሥልጣን ላይ ያሉ ባለሥልጣናት ከዚህ ክስተት እንዲማሩ ጥሪ አቅርበዋል:: ‹‹ማንም ሥልጣን ላይ ለዘለዓለም መቆየት ስለማይችል፣ ባለሥልጣናት ከኃላፊነታቸው ሲነሱ የማያፍሩበት ሥራ ሊሠሩ ይገባል፤›› ብለዋል::

በሶማሌ ክልል ያለው የመንግሥት አወቃቀር በቤተሰባዊ ትስስር መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸው፣ መንግሥት በአፋጣኝ ጣልቃ ያልገባው ተዳክሞ ሳይሆን፣ ግጭቱ ወደ ከፋ ቀውስ እንዳይለወጥ ጥንቃቄ በመደረጉ መሆኑን ተናግረዋል:: የክልሉ የቀድሞ ፕሬዚዳንት አብዲ መሐመድ ዑመር (አብዲ ኢሌ) ዕጣ ፈንታ በሕግ እንደሚወሰን ጠቁመዋል::

በአገሪቱ በቅርቡ የመጣውን ለውጥ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች እንዴት ተቀብለውታል ተብለው የተጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለውጡን ሙሉ ለሙሉ የተቀበሉና ያልተቀበሉ ድርጅቶች እንደሌሉ ተናግረዋል:: ‹‹ኦሕዴድ ለውጡን ሙሉ ለሙሉ ተቀብሎ ሕወሓትን ግን የዚያ ተቃራኒ አድርጎ መመልከት ስህተት ነው:: በሕወሓት ውስጥ ለውጡን የሚደግፉና ከለውጡ ጋር የቆሙ አሉ:: ለውጡን የማይቀበሉት ኃይሎችም አሉ፤›› ብለዋል::

ትግራይ ክልልን እየመሩ ያሉት አመራሮች ለውጡን ከልብ እንደሚደግፉ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በጡረታ የተሰናበቱትና የቀድሞውን ሥርዓት እንዲቀጥል የሚፈልጉት ለውጡን ላይደግፉት ይችላሉ ብለዋል:: ሁለቱን ቡድኖች ግን አንድ ላይ ጨፍልቆ ማየት ስህተት ነው ብለው፣ ሕወሓትን የለውጡ ተቃዋሚ አድርጎ መመልከት አያስፈልግም ብለዋል::

ከለውጡ ጋር በተያያዘ ኢሕአዴግ እንደ ፓርቲ የሚመራበትን አይዲዮሎጂ ቀይሯል ወይ ለሚለው ጥያቄ፣ ‹‹ኢሕአዴግ በመጀመርያ ታድሷል:: በመቀጠልም በጥልቅ ተሃድሶ ውስጥ ነው ያለው:: ይህንን ማድረግ ያስፈለገው ኢሕአዴግ በማርጀቱና በመሻገቱ ነው:: ስለዚህ የዴሞክራሲ አውዱን አስፍቷል:: ይህም ማለት አሸናፊ ሐሳብ እንዲገዛ ተደረገ እንጂ፣ የአይዲዮሎጂ ለውጥ አልተደረገም፤›› ብለዋል::

ኢሕአዴግ በተለያየ ጊዜ ራሱን ሲለውጥ የነበረ ፓርቲ መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ፓርቲው በ1983 .. ከኮሚኒስት ወደ ካፒታሊስት ሥርዓት ተቀይሯል:: ሁልጊዜ አዳዲስ ሐሳብ ሲመጣ የሚያኮርፉ ሰዎች በፊትም አሉ፣ አሁንም ይኖራሉ:: አዲስ ሐሳብ አሁንም እየጨመረ ይሄዳል:: ኅብረተሰቡም በየጊዜው ሐሳቡ እያደገ ስለሚሄድ ኅብረተሰቡን መቅደም ካልቻለን ችግር ውስጥ ነን፤›› ብለዋል:: በአገሪቱ ያለው የለውጥ ፍጥነት አንዳንዶችን በማስደንገጡ ነው እንጂ ምንም ዓይነት የአይዲዮሎጂ ለውጥ አላደረግንም ብለዋል::

ከዚህ ቀደም የህዳሴ ግድብ በአሥር ዓመትም ላይጠናቀቅ ይችላል ብለው ስለተናገሩት ተጠይቀው፣ ግድቡን በአምስት ዓመት እንጨርሳለን ብለን ማጠናቀቅ ያልቻልነው በሁለት መሠረታዊ ችግሮች ነው ብለዋል:: የመጀመርያው የፕሮጀክት ማኔጅመንት ድክመት ሲሆን፣ ሁለተኛው ከግድቡ ዲዛይን ጋር በተያያዘ መሆኑን ተናግረዋል::

የፕሮጀክት ማኔጅመንት ድክመት በህዳሴ ግድቡ ላይ ብቻ ሳይሆን በበርካታ የመንግሥት ፕሮጀክቶች ላይ የሚታይ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህም በተለይ ከደካማ የሥራ ባህላችን ጋር አያይዘውታል:: ከህዳሴ ግድቡ ዲዛይን ጋር በተገናኘም ከመጀመርያውኑ የጠራ ዲዛይን ተይዞ ወደ ሥራ አልተገባም ብለዋል:: ‹‹ህዳሴ ግድቡን ሊሠሩ ቀርተው፣ እንደ ህዳሴ ግድብ ዓይነት ዓይተው የማያውቁ ሰዎች ተሰባስበው በሞራል ብቻ ሊሠሩት አይችሉም፤›› ብለዋል:: በህዳሴ ግድቡ የሚሳተፈው ሜቴክም ከፍተኛ የሆነ የአቅም ውስንነት እንዳለበት ገልጸው፣ አሁንም ሥራው ከሜቴክ ተወስዶ ለሌሎች ኩባንያዎች ካልተሰጠ እሳቸው ባሉት ጊዜ ስለመጨረሱ አሥጊ መሆኑን ተናግረዋል::

በተመሳሳይም በአገሪቱ ያሉ ግዙፍ የስኳር ፕሮጀክቶችም ከሜቴክ ተነጥቀው ለሌሎች ኩባንያዎች ተሰጥው ፕሮጀክቶቹን ለማጠናቀቅ እየተሞከረ መሆኑን ገልጸዋል::

ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲኖር ለማድረግ እየተሠራ መሆኑንም ተናግረው፣ የቀጣዩ ምርጫ ምዝገባ በዘመናዊ መንገድ እንዲከናወን ከተቻለም ሙሉ የምርጫ ሒደቱ ዘመናዊ አሠራርን እንደሚከተል ጠቁመዋል:: ‹‹የምርጫ ኮሮጆ ጥርጣሬ ከኢትዮጵያ ውስጥ መጥፋት አለበት:: ሳይመረጡ ማገልገል አይቻልም፤›› ብለዋል:: ይህንንም ለማድረግ የምርጫ ተቋሙን በኢሕአዴግም፣ በተቃዋሚዎችና በሕዝቡም ጭምር እንዲታመን አድርገን እንዲደራጅ እየሠራን ነው ብለዋል::

በአገሪቱ ውስጥ የተለያዩ ወንጀሎች ሠርተው የተሸሸጉ ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ገልጸው፣ ወንጀል ሠርቶ ግን ዕድሜ ልክ መሸሸግ አይቻልም ብለዋል:: ሕዝቡ ውስጥም ገብተው የተሸሸጉ ወንጀለኞችን ሕዝቡ ባወቀ ጊዜ አሳልፎ ይሰጣቸዋል ብለዋል:: መንግሥት ወንጀል የሠሩ ሰዎችን በሚገባ አጥንቶ ተጨባጭ ማስረጃ ሲኖረው፣ ውጤቱን ለሕዝቡ ይፋ ያደርጋል ብለዋል::