በቦሌ፣ በባህርዳር፣ መቀሌ፣ ጋምቤላ ፤ አሶሳ፣ ጎንደር፣ ጅማ፣ ላሊበላ እና ድሬዳዋ በሚገኙ አየር ማረፊያዎች የሚሰሩ የኢትዮጵያ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪ ባለሙያዎች አድማ አደረጉ። የኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኮሎኔል ወሰንየለህ ሁነኛው አድማ ቢደረግም የበረራ አገልግሎት አለመቋረጡን ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል።

በረራ አልተስተጓጎለም-ኮሎኔል ወሰንየለህ ሁነኛው

የኢትዮጵያ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪ ባለሙያዎች የስራ ማቆም አድማ መቱ። ባለሙያዎቹ አድማውን የመቱት “በተደጋጋሚ ላነሷቸው የሙያ ዕውቅና፣ የደሞዝና ጥቅማ ጥቅም ጥያቄዎች ተገቢ የሆነ ምላሽ ባለማግኘታቸው” እንደሆነ አስታውቀዋል።

የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪ ባለሙያዎች በማህበራቸው አማካኝነት ለኢትዮጵያ ሲቪል አቭዬሽን ባለስልጣን ባስገቡት ደብዳቤ ለጥያቄያቸው ምላሽ ካላገኙ ከዛሬ ጠዋት አንድ ሰዓት ጀምሮ በረራዎችን እንደማያስተናግዱ አስጠንቀቀው ነበር። የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ፍጹም ጥላሁን ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት ባለሙያዎቹ ዛሬ ስራ አቁመዋል።

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኮሎኔል ወሰንየለህ ሁነኛው “ዛሬ ከአንድ ሰዓት ጀምሮ እንደማያስተናግዱ ባስገቡት ወረቀት እና ባደሙት መሰረት አድማውን ቀጥለዋል። ነገር ግን ለአንዲትም ደቂቃ ምንም ባልተናነሰ እንዲያውም በተሻለ ሁኔታ መሔድ የሚገባቸው አውሮፕላኖች ወጥተዋል። ማረፍ የሚገባቸው አርፈዋል። ሥራው በአግባቡ እየተሰራ ነው። ምንም አይነት እንቅፋት የለም። መቶ ፐርሰንት እንደቀድሞው እያስተናገደ ነው” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

እንደ አቶ ፍጹም ገለጻ የትራፊክ ተቆጣጣሪ ባለሙያዎች ጥያቄ ላለፉት ስምንት ዓመታት ሲንከባለል የመጣ ነው። “የአሁኑ የተነሳው ጥያቄ የዕውቅና የደመወዝ እና የጥቅማ ጥቅም ነው። ማኔጅመንቱ እና የመንግስት አካላት እየተከተሉ ያለው፤ ማኔጅመንቱ አሳስቷቸው ይሆናል፤ ጥያቄውን ለመፍታት እየሄዱበት ያለው አካሄድ ሰራተኛውን ስላላሳመነው እና ጥያቄዬን በመሰረታዊነት ይፈታልኛል ስላላለ ነው ወደዚህ የተገባው” ሲሉ የማህበሩ ፕሬዝዳንት ከስራ ማቆሙ ጀርባ ያለውን ምክንያት አስረድተዋል። ለጥያቄያዎቻችን ምላሽ አላገኘንም” ያሉ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ባለፈው ሚያዝያ ወር ለሰዓታት ስራ በማቆማቸው በቦሌ አየር ማረፊያ በረራ ተስተጎሎ እንደነበር ይታወሳል።

የዛሬውን የስራ ማቆም አድማ የመቱት በቦሌ፣ በባህርዳር፣ መቀሌ፣ ጋምቤላ ፤ አሶሳ፣ ጎንደር፣ ጅማ፣ ላሊበላ እና ድሬዳዋ በሚገኙ አየር ማረፊያዎች ያሉ ባለሙያዎች እንደሆኑ ገልጸዋል። በኢትዮጵያ 120 ገደማ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪ ባለሙያዎች የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ሰማንያ አራቱ በቦሌ አየር ማረፊያ የሚያገለግሉ ናቸው ተብሏል። ሁሉም ባለሙያዎች በዛሬው የስራ ማቆም አድማ መሳተፋቸው ቢነገርም በረራ ግን አልተቋረጠም ተብሏል። የሲቪል አቭዬሽን ባለስልጣን በኃላፊነት ደረጃ ያሉ ባለሙያዎችን፣ ጡረተኞችን እና ከስራው የተገለሉ ሰዎችን በመጠቀም በረራ እንዳይቋረጥ ማድረጉን አቶ ፍጹም አስረድተዋል።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ ባወጣው “ጥብቅ ማስታወቂያ” የስራ ማቆም አድማ ለማድረግ የወሰኑ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች በቀጣይ ቀናት በምድብ ስራቸው ላይ እንዲገኙ የማይገኙ ከሆነ የስራ ውላቸውን ለማቋረጥ ዝቶ ነበር። ባለሙያዎቹ ዛሬ በስራ ገበታቸው ላለመገኘታቸው አንዱ ምክንያት ይህ ማስጠንቀቂያ እንደሆነ የማህበሩ ፕሬዝዳንት ተናግረዋል። የስራ ማቆም እርምጃው የ“ወታደራዊ፣ የVIP  እና የአምቡላንስ በረራዎችን” እንደማያካትት ማህበሩ ቀደም ብሎ አስታውቆ የነበረ ቢሆንም መስሪያ ቤቱ ባወጣው ማስታወቂያ ምክንያት ይህንንም ለማድረግ እንዳልቻሉ አቶ ፍጹም አብራርተዋል።

ባለስልጣኑ ከቅዳሜ ጀምሮ በመስሪያ ቤቱ ቀርበው አዲስ ድልድላቸውን የማይቀበሉ ሰራተኞችን የስራ ውል ያለተጨማሪ ማስታወቂያ እና ውይይት እንደሚያቋርጥ አስጠንቅቆ ነበር። ቦሌ አየር ማረፊያ አቅራቢያ በሚገኘው የባለስልጣኑ መስሪያ ቤት ዛሬ ጠዋት የተገኘው ዘጋቢያችን ቅጽር ግቢው አቅራቢያ በርካታ የፌደራል ፖሊስ አባላትን ተመልክቷል። ፖሊሶቹ ወደ መስሪያ ቤቱ የሚገባውን ሰራተኛ ከያዙት ዝርዝር ጋር ሲያመሳክሩ አስተውሏል። ጋዜጠኞች ወደ ግቢው እንዳይገቡም ተከልክሏል።

ተስፋለም ወልደየስ

ጌታቸው ተድላ ኃይለጊዮርጊስ

አርያም ተክሌ