ደረጀ ተፈራ

 

) መግቢያ

ቋንቋን መሰረት ያደረገ  የጎሳ ፌዴራል ስርዓት ባለበትና በክልል ተቧድነው ሃገሪቷን እንደ እራፊ ጨርቅ ቦጫጭቀው ከዚህ መስመር አትለፍ፣ ይህ የኔ ነው አንተን አይመለከትህም፣ መጤዎች ከክልላችን ውጡ፣ ወደ ሃገራችሁ ሂዱ፣ እየተባሉ ዜጎች በሃገራቸው ላይ ሁለተኛ ዜጋ ሆነው በሚፈናቀሉበትና ተሳቀው በሚኖሩበት ሃገር፣ በተለይም በአማራው ህዝብ ላይ የተቀነባበር የጥላቻ ዘመቻ ተደርጎበት ለጥቃት በተጋለጠበት በዚህ አስቸጋሪ ወቅት እራሱን ከጥፋት ለመከላከል የአማራው መደራጀት ጥያቄ ውስጥ የማይገባ መራራ ሃቅ ነው። ምናልባት አማራውን ሊያስወቅሰው ይችላል ብዬ የማስበው እራሱን ከጥቃት ለመከላከል መሰባሳቡ ሳይሆን ይህ ሁሉ ግፍና በደል በአማራነቱ ምክንያት እየደረሰበት እስካሁን ድረስ ባሳየው የተራዘመ ትእግስቱ ነው። አማራው በአማራነቱ አይደራጅ ማለት ላለፋት 27 ዓመታት የደረሰበትን በደልና እንግልት፣ ሞትና ስደት፣ የዘር ማጥፋትና ማጽዳ፣ የኢኮኖሚና የፓለቲካ መገለል ይቀጥል እንደ ማለት ነው።

….

የአማራን የህልውና ትግል የሚቃወሙት እነማናቸው በሚል ዙሪያ በግሌ ባደረኩት ዳሰሳ የተገነዘብኩት ነገር ቢኖር አማራን በፖለቲካ ፕሮግራማቸው ጠላታችን ነው ብለው ካስቀመጡት ወይም በጠላትነት ከፈርጁት የብሄር የፖለቲካ ድርጅቶች በተጨማሪ ያ- ትውልድ አባል የሆኑ በጎልማሳና በጡረታ እድሜ ክልል የሚገኙ ግለሰቦች የሚመሩ በርካታ የአንድነት ፓለቲካ አራማጆች እና በእነሱ ርዕዮተ ዐለም ያደጉና ግለሰቦች በዋናነት ይገኙበታል። እነዚህ እድሜ ጠገብ የሆኑ አፈቅቤ የሴራ ፓለቲከኞች አብዛኛዎቹ በተማሪው እንቅስቃሴ ወቅት ተሳተፎ የነበራቸው ሲሆን የኮሚኒስት አስተሳሰብን ያራምዱ ነበር። በወቅቱ ተማሪው ውስብስብ የሆነውን የኢትዮጵያን ችግሮች ዙሪያ በአግባቡ ምንም ዓይነት ጥናትና ትንታኔ ሳይደረግበት የኢትዮጵያ ችግር በአንድ መስመር ብጫቂ ወረቀት ላይ የጨቋኝና የተጨቋኝ ችግር ነው በማለት የደመደመ ነው። ተማሪው በዚህ ቁንፅልና እንጭጭ ድምዳሜው አማራን ጨቋኝ፣ ሌሎች ብሔረሰቦችን ደግሞ ተጨቋኝ ናቸው በማለት አማራውን ለጥቃት ያአጋለጠ ኢትዮጵያን አሁን ለደረሰችበት ምስቅልቅል ሁኔታ የዳረገ ነው።

እንደሚታወቀው በቀዳማዊ አፄ ኃይለ ስላሴ ንጉሳዊ መንግስት ላይ ይካሄድ በነበረው የተማሪዎች የአመጽ እንቅስቃሴ ወቅት የተፈጠሩ የፓለቲካ ድርጅቶች አብዛኛዎቹ ግራ ዘመም በሆነው በኮሚኒስት አስተሳሰብ የተቃኙ ነበሩ። ከነዚህም ውስጥ ኢህአፓ፣ መኢሶን፣ኦነግ፣ ወያኔ፣ ሻዕቢያ/ ጀብሃና እራሱን ደርግን (ሰደድንና ኢሰፓን) መጥቀስ ይቻላል። ኮሚኒስቶች የሚታወቁበት ዋና ዋና ባህሪያቸው በመደብ ትግል የሚያምኑ፣ ፈጣሪ የለም የሚሉ፣ በፕሮፓጋንዳና በውሸት ጠላቶቻቸውን ስምና ታሪክ በማጉደፍ የሚያጠቁ፣ በመግደል የሚያምኑ፣ በሴራ ፓለቲካ የተካኑ መሆናቸው ነው። በኮሚኒስቶች ትርጉም መደብ ማለት ቡድን ማለት ሲሆን የመደብ ትግል (Class Struggle) ሲሉ ደግሞ ህዝቡን በጾታ፣ በፓለቲካ አመለካከት፣ በብሔር እና በመሳሰሉት በቡድን በመከፋፈል አንዱን በዳይ ሌላውን ተበዳይ አድርጎ ማታገል/ ማፏከት ማለት ነው።

የኮሚኒስት ርዕዮተ ዓለም አራማጆች ስለ ማህበራዊ ለውጥ (Socia Change) ያላቸው አመለካከት ከግጭትና ከአመጽ ጋር የተያያዘ ነው። ይኸውም በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ ለውጥ ወይም እድገት ይከሰታል ብለው የሚያምኑት በአብዮት፣ በግጭት፣ በአመጽ ወይም በመደብ ትግል ነው። በመሆኑም የኢትዮጵያን ህዝብ ለጋራ ሃገራዊ እድገትና ብልጽግና በፍቅር፣ በወንድማማችነትና በህብረት ከማሰለፍ ይልቅ በመሃሉ ልዩነት በመፍጠር በዝባዥና ተበዝባዥ፣ ጨቋኝና ተጨቋኝ፣ አብዮተኛና ፀረ አብዮተኛ፣ ተራማጅና ጎታች፣ ኪራይ ሰብሳቢና ልማታዊ ባለሃብት፣.. ወዘተ እያሉ ግጭትን በሚጋብዙ በተቃራኒ (በተጻራሪ) መደቦች ይከፋፍሏቸዋል። በዚህ ሁኔታ ህዝቡን መሃል ልዩነት በመፍጠር አንዱን የራሳቸው ወገን በማድረግና ሌላውን በጠላትነት በመፈረጅ በህዝቡ መሃል ልዩነትንና ጠላትነትን ያስፋፋሉ፣ በማህበረሰቡ ውስጥ አለመረጋጋትንና እርስ በርስ መጠራጠርን በመፍጠር በስልጣን የሚቆዩበትን፣ በሙስና ሃብት የሚያፈሩበትን የግል ዝናቸውን ከፍ አድርገው ቆራጡ መሪ፣ ባለ ርዕዩ መሪ፣ የነጻነታችን አባት፣ ጓድ ሊቀመንበር ወዘተ እየተባሉ ከሰው በላይ በውሸት እየተኮፈሱ በአምባገነንነት የሚኖሩበትን ሁኔታ ያደላድላሉ። በመሆኑም አሁን አማራ በደል አድርሶብናል፣ ምኒልክ እንደዚህ አድርጎናል እያሉ ያለምንም ታሪካዊ መረጃና ማስረጃ የሚያቀርቡት ውንጀላ በጠላትነት የፈረጁትን የአማራን ህዝብ በውሸት ትርክትና በፕሮፓጋንዳ ጋጋታ የበዳይነት ስሜት ተሰምቶት እንዲሸማቀቅ ያቀነባበሩት የኮሚኒስቶች የማጥቂያ ስልት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።

….

ላለፋት 50 ዓመታት በአማራ ህዝብ ላይ የተሰራው የጥላቻና የስም ማጥፋት ዘመቻ ምክንያት ማመዛዘን ይችላሉ የተማሩ ናቸው የሚባሉትን እንኳን ሳይቀር ፕሮፓጋንዳው ሰለባ አድርጓቸዋል። በመሆኑም በያ- ትውልድ የሚመሩ ህብረ ብሄር የፓለቲካ ድርጅቶች፣ በእነሱ የሚፈጠሩ ህብረቶችና ግንባሮች የሚቀርፁት የፓለቲካ ፕሮግራሞች አማራን አግላይ ወይም በቀጥታ ጠላት የሚያደርግ ነው። በመሆኑም እነዚህ ቡድኖች የአማራዉንም ሆነ የኢትዮጵያን ችግሮች በተገቢው መንገድ በመረዳት የመፍታትም ሆነ ታግለው የማታገል ቁመና የሌላቸው፣ ለሰርጎ ገቦች የተጋለጡ በዚህም የተነሳ በችግር የተተበተቡና ምንም ሳይሰሩ የሚፈርሱ፣ ሚስጥር አባካኞች ስለሆኑ ለሃገሩና ለባንዲራው ቅን አሳቢ የሆነውን የዋሁን አማራ የበግ ለምድ በለበሱ ተኩላዎች ሲያስበሉ ኖረዋል።

….

ወደሚቀጥለው ርዕስ ከመሄዴ በፊት ወያኔ በፈጠራ ታሪክ አማራን ይከስና ይወነጅል እንደነበር ትንሽ ልበል። ህወሃት/ ትህነግ ጨቋኟ የአማራ ብሔር ትግራይን በዘበዘች፣ ጨቆነችን ደሃ ያደረገችን ሴቶቻችን በሽርሙጥናና በሌብነት ላይ እንዲሰማሩ ያደረገችን እያለ ይከሳል። ይህን ሁሉ ያደረገችን ጠላታችን ስለሆነች አማራን ማህበራዊ ሰላም አንነሳለን በማለት የአሸባሪነት ወይም የብቀላ የጦርነት በህዳር ወር በ1968 ባጸደቁት በትህነግ ማኒፌስቶ ላይ እንደተገለጸው በአማራ ህዝብ ላይ አውጀዋል። በጣም የሚገርመው (1ኛ) አካባቢው በተፈጥሮው የተራቆተ ስለሆነ መጀመሪያ እነሱን ለመበዝበዝ የሚሄድ አይኖርም። በቀ/ኃ/ስላሴ ዘመንም ይሁን በደርግ መንግስት የትግራይ ክፍለ ሃገር እራሷን መቻል ስላቃታት ከማዕከላዊ መንግስት ነበር ለሰራተኛ ደሞዝም ሆነ ለሌሎች ወጪዎች የበጀት ድጎማ የሚደረገው። (2ኛ) ደግሞ ከድሮ ጀምሮ ትግራይ ውስጥ አማራም፣ ኦሮሞም ሆነ ሌላ ኢትዮጵያዊ እንዲያስተዳድር ተልኮ አያውቅም፣ ትግራይ ሁሌም በትግሬ ብቻ ነው ትተዳደር የነበረው። ታዲያ እንዴት ሆኖ ነው አማራ ትግሬን የሚጨቁነው። የማይመስል ነገር። እንደሰማሁት ድሮ ወደ ትግራይ የሚመደቡ መምህራንና ሌሎች የመንግስት ሰራተኞች ብዙዎቹ ወደ ትግራይ መስራት ስለማይፈልጉ ከሌላው አካባቢ የበለጠ እርከን ( የደሞዝ ጭማሪ) ት/ት ሚኒስቴር (መንግስት) እያደረገላቸው ነበር በስንት ማባበልና ልመና የሚመደቡት። በአንድ ወቅት ወያኔ ባንክ እየዘረፈና ድልድይ እያፈረሰ ቢያማርረው እነዚህ የትግራይ ወንበዴዌች ምን እንሁን ነው የሚሉት? መንግስት ከትግራይ የሚያገኘው አንዲት ስባሪ ሳንቲም የለም ነገር ግን ለቾክ (ጠመኔ ወይም ኖራ) እንኳን መግዣ እንኳን መሸፈን አቅቷቸው ከማዕከላዊ መንግስት እየተገዛ ነው የሚላክላቸው በማለት ተናግሯል። በሌላ ጊዜ ደግሞ ምንም ቢደረግላቸው ከወቀሳ በቀር ምስጋና የሌላቸው ሁሌ ተበድለናል የሚሉ ስለነበር ወርቅ ሲያነጥፋላቸው ፋንድያ ነው የሚሉት በማለት ከሃዲነታቸውን መንግስቱ ኃ/ማርያም በብሽቀት ገልጿል።

….

) ክልል ምስረታ

እንደሚታወቀው በ1885 (እኤአ) የአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች አፍሪካን ለመቀራመት ጀርመን በርሊን ላይ ስብሰባ አድርገው የአፍሪካ ካርታን እንደ ምግብ በመካከላቸው ጠረጴዛ ላይ ዘርግተው አፍሪካን እንደ ቅርጫ ስጋ ያለከልካይ ተከፋፈሏት። ይህም የበርሊኑ አፍሪካን የመቀራመት ጉባኤ «Scramble of Africa» ተብሎ ይታወቃል። በተመሳሳይ ሁኔታ በ1983 ዓ.ም ወያኔና ኦነግ የሽግግር መንግስት በጋራ እንደመሰረቱ ባለው የህዝብ ብዛትም ይሁን ለሃገር አንድነትና ስልጣኔ ዋጋ የከፈለውን የአማራን ህዝብ አግልለው ይህንን ወሳኝ የህልውና እና የሃገር የባለቤትነት ጉዳይ ህዝቡን ሳያወያዩ ብቻቸውን ቢሯቸውን ዘግተው እንዳሻቸው ኢትዮጵያን በክልል ሸነሸኗት። የኢትዮጵያን ካርታ ጠረጴዛ ላይ ዘርግተው ሽንሸናውን ሲያከናውኑ ሳይንሳዊና በተጠና መንገድ ማለትም የወቅቱን የኢትዮጵያን ህዝብ ብዛት፣ የህዝቡን ፍላጎትና ስብጥር፣ አሰፋፈር፣ የተፈጥሮ ወይም ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ፣ የህዝቡን ኢኮኖሚያዊ ትስስር፣ ስነልቦና፣ ቋንቋ፣ ታሪክና ዝምድናን እና የመሳሰሉትን ግምት ውስጥ ያስገባ አልነበረም። በጣም የሚገርመው በወቅቱ  እራሳቸው ወረቀት ላይ ባስቀመጡት የቋንቋና የጎሳ መስፈርት መሰረት እንኳን ያልተከናወነ ነበር። እንደነሱ የቋንቋና የጎሳ መስፈርት መሰረት በትክክል ቢሰራ ኖሮ ትግራይ ቢያንስ 4 ወይም 5 ክልሎች ማለትም የትግሬ፣ የኩነማ፣ የይሮብ፣ የአገውና የሳሆ (አፋር)  ክልል ይወጣት ነበር። ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋም ሆነ ብሔረሰብ እንደ ሰው እኩል መብት እስካለው ድረስ በኢትዮጵያ አጠቃላይ በጎሳዎቻ ቁጥር ወይም ቋንቋዎች ብዛት ስንሄድ በኢትዮጵያ ከ85 ክልል በላይ በተፈጠረ ነበር። ነገር ግን ወያኔና ኦነግ በወቅቱ የነበራቸው ዋና ዓላማ ወደፊት ለመመስረት ላቀዱት ለትግሬ ወይም ለኦሮሞ ነፃ መንግስት ኢኮኖሚ ምንጭነት ይጠቅመናል ብለው ያሰቡትን ለምለም አካባቢዎችንና የተፈጥሮ ሃብቶችን (Natural Resources) በህግ ሽፋን ወደ እነሱ ክልል ማከማቸት ነበር።

በ1982ዓ.ም ኤርትራ ተሰኔ በሚባል ቦታ ወያኔ፣ ኦነግና ሻዕቢያ ከደርግ ወድቀት በኋላ 1ኛ. ኢትዮጵያን በቋንቋ በጎሳ እንደሚያዋቅሯት፣ 2ኛ የኤርትራን ነፃ መንግስትነት እንደሚቀበሉና አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርጉ አስቀድመው በድርጅቶቹ መሪዎች በሆኑት በመለስ ዜናዊ፣ በሌንጮ ለታና በኢሳያድ አፈወርቄ በሚመሩ ልዑካን ቡድኖች ስምምነት አድርገው ነበር። በተለይም ወያኔና ኦነግ ባደረጉት ስምምነት መሰረት ስልጣን እንደያዙ መጀመሪያ ያደረጉት ኢትዮጵያን ለዘጠኝ ክልሎች መከፋፈል ነበር። ስለዚህ ክልሎች የተፈጠሩትም ሆነ ድንበራቸው የተወሰነው ህዝቡ ተጠይቆ፣ ተወያይቶበትና ድምጽ ሰጥቶበት ሳይሆን በወያኔና በኦነግ አመራሮች መሃል በተደረገ ስምምነት መሰረት ነው።

በመሆኑም ኦነግና ወያኔና የእሱ ተለጣፊ ድርጅቶች የህዝቡ ፍላጎት ሳይጠየቅና ድምጽ ሳይሰጥበት በፈጠሩት አዲስ ክልል የተቀራመቱትን መሬት ለህዝባቸው ታግለን ያስገኝንልህ የክልልህ ካርታ ይህ ነው በማለት አስተዋወቁ፣ ባዘጋጁት በክልላዊ ህገ መንግስታቸው ላይ ድንበራችን ከዚህ እስከዚህ ነው በማለት አሰፈሩ፣ ካርታም ሰርተውና አትመው ለህዝቡ አሰራጩ፣ በትምህርት ካሪኩለም ውስጥ በማስገባት የክልሉ ተማሪዎች እንዲማሩትና ካርታውን እንዲለምዱት አደረጉ። በኢትዮጵያ የብሔር ጭቆና ነበር ከሚሉት በላይ በወያኔና በኦነግ የሽግግር መንግስት አስፈሪ የሆኑ የማንነትና የድንበር ጥያቄዎች መነሳት ጀመሩ። እኔ ሌላ ሳልሆን አማራ ነኝ የሚሉ የማንነት ጥያቄዎች በወልቃይት፣ በራያ፣ በመተከልና በተለያዩ አካባቢዎች ተነሱ፣ ይህ መሬት የኦሮሞ ሳይሆን የጉጂ፣ የሶማሌ፣ የአማራ ወዘተ ነው የሚሉ ጥያቄዎች በየቦታው ተቀጣጠሉ። ባጠቃላይ ይህ በቋንቋ ላይ የተመሰረተ የጎሳ ፌዴራሊዝም ገና ከመነሻው ችግር የነበረበት፣ ህዝቡን እርስ በርሱ መቋጫ ወደሌለው ጦርነት ውስጥ የሚከት፣ በሃገሪቷ ውስጥ ቀድሞ ያልነበረ አዲስ የድንበርና ማንነቴ ይይከበርልኝ የኔ ጎሳ እናንተ ያላችሁት ሳይሆን ሌላ ነው ማንነቴን አክብሩልኝ ከፋኝ ለሚሉ ጥያቄዎች ተነሱ። የወያኔና የኦነግ ቅንነት የሚጎለው፣ በተንኮል የታጀለ የጎሳ ፌዴራሊዝም ግጭቶችን እዚህም እዛም በማስነሳት ሃገሪቷን መቋጫ ወደሌለው ውዝግብ ውስጥ ከተታት። እዙህ ላይ ሊነሳ የሚገባው ነገር  የኢትዮጵያን ህዝብ ባልመከረበትና ባልተወያየበት፣ የህዝቡን ይሁኝታ ባላገኘ ኢፍትሃዊ በሆነ ሁኔታ የተፈጠረን ክልል ለእነሱ ጥቅም ስለሰጣቸው ብቻ በርካታ የኦሮሞ የጎሳ ፖለቲከኞች ችግሩ የፌዴራሉ ስርዓት ሳይሆን ወያኔ ዲሞክራሲያዊ ስላልሆነ ነው በማለት ጉዳዩን ለመሸፋፈን ይከጅላሉ። መጀመሪያውኑ ወያኔና ኦነግ ኢትዮጵያን ለዘጠኝ ክልል ሲከፋፍሉ ህዝቡ ተወያይቶና ወዴት መካለል ትፈልጋለህ ተብሎ ተጠይቆ ወይም ድምጽ ሰጥቶበት ሳይሆን ከዚህ ተራራና ወንዝና መለስ ትግራይ ይባላል፣ እስከዚህ ወንዝ ድረስ ደግሞ ኦሮሚያ እያሉ በማን አህሎኝነትና በዘፈቀደ እንዳሻቸው ያለከልካይ ያደረጉት ዝርፊያ ስለሆነ አሁን ለሚነሱ የማንነትና የድንበር ጥያቄዎች በእነሱ በሌቦቹ ህገ መንግስት መሰረት ነው የሚፈታው ማለት ማፌዝ ነው።

 

የት/ ፓሊሲ፤

ወያኔና ኦነግ የመሬት ነጠቃና ቅርምቱን እንደጨረሱ በመቀጠል በ1983 ዓ.ም  አዲስ የትምህርት ፓሊሲ ተማሪዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ መማሪያ አወጡ። ልጆች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መማራቸው መልካም ሆኖ ሳለ በማር እንደተለወሰ መርዝ አዋጁ ብዙ ችግር ይዞ መጣ። በነገራችን ላይ የአፍ መፍቻ እና የክልሉ የስራ ቋንቋ ሊለያይ ይችላል፣ በአንድ ክልል ከአንድ በላይ ቋንቋ በህዝቡ ሊነገር ይችላል። በመሆኑም ልጆች በአፍ መፍቻ ወይም በእናታቸው ቋንቋ ይማሩ የሚለው የተባበሩት መንግስታት ህግ እና በክልሉ ቋንቋ ማስተማር ይለያያል ስለዚህ ይህ ህግ በኦሮሚያም ሆነ በትግራይ አጠቃላይ በኢትዮጵያ ደረጃ ተግባራዊ ሆኗል ማለት አይቻልም። ለማንኛውም በየአካባቢው የክልሉ የስራ ቋንቋ ይህ ነው ተብሎ በፓለቲከኞቹ በተወሰነው መሰረት የተማሪዎች መማሪያ መፃህፍት በክልሉ የስራ ቋንቋ መዘጋጀት ተጀመረ። እዚህ ላይ አንድ ነገር ግልጽ ማድረግ የሚገባ ነገር ያለ ይመስለኛል እሱም ከገነት ዘውዴ በፊት ማለትም በሽግግሩ መንግስቱ ወቅት የኢትዮጵያ የትምህርት ሚኒስቴር የነበረው የኦነጉ ኢብሳ ጉተማ ሲሆን ምክትሉ ደግሞ የደቡቡ የሃዲያው ተወካይ አማራ ጠሉ ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ ነበር። ኦነግ በሽግግሩ ጊዜ አማራ የጋራ ጠላታችን ነው በማለት ከወያኔ ጋር በፈጠረው ወዳጅነት ፓለቲካውን ወደ ህዝቡ ለማስረጽና የኦሮሞን ወጣቶችን በዘረኝነትና በአማራ ጥላቻ ለመበከል ተጠቅሞበታል። ኦነግ፣ ወያኔ እና በአካል የወያኔ በመንፈስ የኦነግ ፍጥረት የሆነው ኦህዴድ የመንግስት መገናኛ ራዲዮ፣ ቴሌቪዥንና ጋዜጦችን በመጠቀም እንዲሁም በአካል ካድሬዎቻቸውን በየቀበሌውና ገበሬ ማህበሩ በመላክ ከጎረቤቶቻቸው የነጠቁትን መሬት ለህዝባቸው ታግለን ያስገኝንልህ የክልልህ ካርታ ይህ ነው በማለት አስተዋወቁ፣ “በክልላዊ ህገ መንግስት” ላይ ድንበራችን ከዚህ እስከዚህ ነው በማለት አሰፈሩ፣ ካርታም ሰርተው ለህዝቡ አሰራጩ፣ በትምህርት ካሪኩለም ውስጥ በማስገባት የክልሉ ተማሪ እንዲማረውና ካርታውን እንዲለምደው አደረጉ።

ወደ ጀመርነው የሽግግር መንግስቱ የት/ት ፓሊሲና አተገባበሩ ስንመለስ በወቅቱ የነበረው በኢብሳ ጉተማ የሚመራው የትምህርት ሚኒስቴር የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ የተማሪዎችን መማሪያ መፃህፍትና የመምህራንን መመሪያ (Students Text Book and Teachers Guide) እንዲያዘጋጁ ውክልና ለክልሎች ሰጣቸው። በዚሁ መሰረት የክልል የትምህርት ቢሮዎች ካድሬ መምህራንን በመመልመልና ስልጠና በመስጠት በየክልላቸው ለሚማሩ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የሚያገለግል የሙከራ (Trail Edition) መማሪያ መፃህፍት ማዘጋጀት ጀመሩ። ባዘጋጁትም የታሪክ፣ የቋንቋና የጂኦግራፊ (የህብረተሰብ) መፃህፍት ውስጥ በፊት በደርግ መንግስት ታትሞ በነበረው መጻህፍት ውስጥ እንደ አብዲሳ አጋ፣ አድዋና የመሳሰሉትን ስለሃገር ጀኞችና ስለአንድነት የሚያስተምሩ ጽሁፎች ከታሪክና ከቋንቋ ማስተማሪያ ጽሁፎች (Passages) ውስጥ ለቅመው በማውጣት ነፍጠኛ ይህንን ያንን አደረግ ትርክቶች ተኳቸው። ካድሬዎች የፈጠሩት የተዛባ ትርክቶች፣ የቦታ ስያሜዎች፣ በህዝቦች መሃል ግጭት ሊፈጥሩ የሚችሉ ሴረኛ አመለካክርቶችን፣ አንዳንዴም አንድ ተራራ ወይም አካባቢንና ወንዝን የኔነው በሚል ስሜት በሁለት ክልሎች ውስጥ በማካተት ለተማሪዎች መማሪያነት አዘጋጁ። ይህ ታሪክን ማዛባትና በህዝቦች መሃል ግጭትንና ጠላትነትን የሚያስተምር፣ የድንበር/ የወሰን መጋፋት መጽሃፍቱን በሚያዘጋጁት በየክልሎቹ ካድሬዎች ሆን ተብሎም የሚፈፀም ቢሆንም ችግሩን ት/ት ሚኒስቴር በምንቸገረኝነት ስሜት ወይም ሆን ብሎ የሚከታተልበትና የሚያርምበት አሰራር አልዘርጋም ነበር። በተለይ ኦሮሚያን፣ ደቡብን፣ ሶማሌና ትግራይ አንድ የሚያደርጋቸው አማራውን ለክልላቸው ህዝብ ጠላት አድርገው በየተማሪው መፃህፍት ውስጥ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ማካተታቸው ነበር። አማራ ነፍጠኛ ጠላታቸው እንደሆነ፣ ኦርቶዶክስ የነፍጠኛ ሃይማኖት መሆኑ፣ የምኒልክ ይህንን ያንን አድርጓል፣ እገሌ የሚባል ከአማራ አገር የመጣ ራስ ወይም የጦር አለቃ እዚህ አካባቢ ጦርነት ከፍቶ ይህንን ጉዳት አድርሷል የሚሉ የፈጠራና የውሸት ትርክቶች በተማሪው መፃህፍት ውስጥ ተካተቱ። በተቃራኒው ደግሞ እገሌ የሚባል የኦሮሞ፣ የሲዳማ ወይም  የ… ተዋጊ ወይም አባ ገዳ ነፍጠኛን ተዋግቶ እዚህ ቦታ አሸንፎታል በማለት እራስን የማጀገንና ታሪክን የማዛባት ስራ በሰፊው ተሰራ። ባጠቃላይ በዚህ መንግስት የጎለመሰውን ሃገር ተረካቢውን (የተረከበውን) ትውልድ ላለፋት 27 ዓመታት ጥላቻን፣ በቀልንና ውሸትን በተቀነባበረ ሁኔታ አስተምረው አሳድገውታል። ይህን ትውልድ ቤተሰቡ ካላስተማረው በስተቀር ከክልሉና ከጎጡ ውጪ የሚያውቀው ነገር የለም። በየ ትምህርት ቤቱ የሚሰቅለውና የሚያወርደው ባንዲራም ሆነ የሚዘምረው የህዝብ መዝሙር የክልሉን እንጂ የኢትዮጵያን አይደለም። … ኦነግ በወያኔ ስልጣኑን ተቀምቶ ከተባረረ በኋላ በኦነጉ በኦቦ ኢብሳ ጉተማ ተይዞ የነበረውን የት/ት ሚኒስቴርን የተካችው የብአዴኗ ወ/ሮ ገነት ዘውዴ ነበረች። ገነት ዘውዴ ኦነግ በአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ት/ት ቤቶች በሙከራ (Trail Edition) ስም ጀምሮት የነበረውን ትውልድ አምካኝ፣ ሃገር አፍራሽ፣ ጸረ አማራ፣ ጸረ ኢትዮጵያ፣ ጸረ ኦርቶዶክስ፣ የሆነው የትምህርት ስርዓት እስከ ዩኒቨርስቲርስቲ ድረስ በመቀጠል አጠናቀቀችው።

ወያኔ፣ ኦነግና ተባባሪዎቻቸው በተማሪው ላይ እንዳደረጉት ሁሉ ህዝባችን የሚሉትን የማህበረሰብ ክፍልን በዘረኝነት ለመበከል ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም። በካድሬዎቻቸው አማካኝነት እታች እስከ ገበሬ ማህበር ድረስ ፀረ አማራ፣ ፀረ ኢትዮጵያ ቅስቀሳ በማድረጋቸው የተነሳ ከኦሮሚያ፣ ከደቡብ ህዝቦች፣ ከቤንሻንጉልና ከመሳሰለው አካባቢዎች በአማራ ህዝብ ላይ ተነግሮ የማያልቅ አሰቃቂ ግፍ ተፈፅሟል። የአማራ ገበሬም ሆነ ለፍቶ አዳሪ የኢትዮጵያ ዜጋ እንዳልሆነ ሁሉ ወደ ሃገርህ ሂድ ተብሎ ከወለጋ፣ ከአርሲ፣ ከጉራ ፈርዳና ከመሳሰሉት በጠ/ሚሩ መለስ ዜናዊ ሳይቀር ህዝቡን መጤ ዛፍ ቆራጭ እያሉ በማሸማቀቅ ንብረቱን ቀምተው አባረሩት። የህዝቡን ስነልቦና/ ሞራል ለመስበር ከዚህም በላይ በመሄድ ለዚህች ሃገር ነፃነት ሲሉ ከጠላት ጋር የተዋደቁ ደማቸውን ያፈሰሱ፣ ህይወትና አካላቸውን የገበሩ፣ በየጫካውና ሸንተረሩ የተንከራተቱ የአማራ ጀግኖችንና ነገስታትን በአደባባይ መስደብና ማዋረድ ስራቸው ሆነ።

ሌላው ደግሞ ህወሀት፣ ኦነግ፣ ኦህዴድ፣ ደህዴንና የመሳሰሉት በጎሳና በቋንቋ ላይ የተመሰረቱ የዘር የፓለቲካ ድርጅቶች መዋቅራዊ በሆነ ሁኔታ የመንግስትን በጀትና እንደ ሬዲዮና ቴሌቪዥንና ሌሎች የህዝብ መገናኛ፣ መኪናና ቢሮ በመጠቀም በሚችሉት መጠንና አቅም የፀረ አማራ ዘመቻ አድርገዋል። በተለይም በየክልላቸው በወጣቱ ላይ ጥላቻንና በቀልን ዘርተዋል። ከአንድነት ይልቅ ልዩነትን አስተምረዋል። ኢትዮጵያም ከሰው ልጅ መፈጠር ጀምሮ በሂደት የተገኘች የሰው ልጅ መገኛ የአለም እምብርት ሳትሆን በድንገት የተከሰተች፣ ታሪኳ ከአንድ እድሜ ጠገብ ከሆነ ሰው ከመቶ አመት እንኳን የማይበልጥ ታሪክ የሌላት፣ ባዶ የህዝቦች ጥርቅምቅሞሽ የሆነች፣ ህዝቦቿም ዝምድና፣ የጋራ ታሪክና እሴት የሌላቸው፣ ባንዲራዋም ጨርቅ እንደሆነ በአደባባይ ሰብከዋል።

እዚህ ላይ ሳልገልጽ ማለፍ የማልፈልገው የአማራ ባህልና ታሪክን በፈጠራ ታሪክ ጥላሸት ሲቀቡና የጥላቻ ሃውልት በየአካባቢውና ከተማው ሲያቆሙ፣ አማራውን ሲገሉና ሲያፈናቅሉ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ የቆምን ነን የሚሉት ህብረ ብሔራዊ የአንድነት የፓለቲካ ድርጅቶችም ሆኑ ፊደል ቆጥረናል የሚሉ የየትኛውም ጎሳ የሆኑ ምሁራን፣ የሃይማኖት መሪና አማኝ ነን ለእውነትና ከተገፋት ጎን እንቆማለን የሚሉት ሳይቀሩ ፍርደ ገምድል በመሆን ሰብአዊ መብቱ ለተገፈፈው፣ በዘሩ ጥቃት ለተደረገበት የአማራ ህዝብ በሰባዊነት አንዲት የአዘኔታ ቃል ሲናገሩም ሆነ በሰው ዘር ላይ የተፈፀመን ወንጀል ሲያወግዙ አልተሰሙም። በመሆኑም የአማራን ህዝብ ጠላት አድርገው ምንም ሳያጠፋና ሳይበድል፣ የትኛውንም የሃገሪቱን ህግ ሳይተላለፍ በገደሉትም ይሁን ዳር ቆመው በምንቸገረኝነት የተመለከቱት፣ ወይም ባፌዙበት ላይ የአማራ ህዝብ ተስፋ ቢቆርጥ ወቃሽ ያለው አይመስለኝም።

“ሊበሏት የፈለጓትን አሞራ ጅግራ ናት ይሏታል” እንደሚባለው አንዳንድ ብልጣብልጥ ካድሬዎች እኛ ጨቋኝ ጠላታችን ነው ያልነው የአማራን ገዢ መደብ እንጂ የአማራን ህዝብ አይደለም ሲሉ መሰማታቸው ለወንጀላቸው ሽፋን ለመስጠት እንጂ በተግባር እየታየ ያለው አማራ የተባለን ሁሉ ከህጻን እስከ ሽማግሌ በአማራነታቸው እየተለቀሙ ገበሬ፣ ነጋዴው፣ የእለት ጉርሱን ተሯሩጦ የሚሸፍነው ደሃ ሸቃጭ፣ ቱሪስት አስጎብኚው፣ ጋዜጠኛው፣ ሹፌሩ፣ ቄሱ፣ አስተማሪው፣ ተማሪው፣ በመንግስት መስሪያቤትም ይሁን በግሉ የሚሰራው፣ ህፃናት፣ እርጉዝ ሴቶችና ሽማግሌዎች ሳይቀሩ ሲሰደቡ፣ ሲፈናቀሉ፣ ሲረሸኑ፣ ሲታረዱ፣ ቤት ተዘግቶበት እስከ ህይወታቸው ሲቃጠሉ፣ እርጉዞች ሆዳቸው በሳንጃ ሲቀደድና ቀሳውስቱ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሲታረዱ ነው ያየነው። የአማራን ገዢ መደብ የሚሉት የፓለቲካ ቁማር እንጂ በጠላትነት ፈርጀው በኢኮኖሚ፣ በፓለቲካውና በማህበራዊ ህይወቱ መዋቅራዊ በሆነ ስልት ያጠቁትና ያደቀቁት ደሃውን የአማራ ህዝብን እንጂ ገዢ መደብ የሚሏቸው በዚህ ዘመንና ጊዜ በህይወትስ የት አሉ? እንደ እውነቱ ከሆነ በወቅቱ በነበረው ህኛ ህዝቡም አምኖ በተቀበለው መሰረት ንጉሶች በአብዛኛው ከአማራ ይወለዱ እንጂ በዘውዳዊው አስተዳደር በየአካባቢው የሚሾሙት የሃገሩ ተወላጆች ነበሩ። ለምሳሌ የወላይታው ንጉስ ጦና፣ የጅማ ኦሮሞው አባ ጂፋር፣ የትግሬው ራስ መንገሻና የወለጋ ኦሮሞው ደጃዝማች ገ/እግዚአብሔር ጆቴንና የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል (እራስን በራስ ማስተዳደር አሁን የተጀመረ ሳይሆን ጥንትም በንጉሶች አስተዳደር የነበረ ነው፣ ልዩነቱ በንጉሶቹ ጊዜ ህዝቡ በክልል ያልታጠረ፣ በኢትዮጵያ ምድር በየትኛውም አካባቢ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ የመስራትና የመኖር ያልተሸራረፈ ሙሉ መብት የነበረው መሆኑ ነው)። በኢትዮጵያ ታሪክ ከታች ከጭቃ ሹሙ እስከ ራስ ወይም ፊታውራሪና ቢትወደድ ሹመት ድረስ ባለው የንጉሳዊ መዋቅር ከአማራ ብቻ ሳይሆን ከኦሮሞም፣ ከትግሬም፣ ከጉራጌም፣ ከሲዳማም፣ ከከንባታም፣ ከሃድያም፣ ከሶማሌም፣ ከጋንቤላም፣ ከሃረሪም፣ ከሁሉም በድሮ ማእረግ የማይጠራ የብሔረሰብ አባል አይገኝም ነበር።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ማከል የምፈልገው ነገር በ60ዎቹ ዓ/ም በተማሪው እንቅስቃሴ ወቅት የጨቋኝ፣ ተጨቋኝ ፕሮፓጋንዳ ያደጉ ትውልዶች ከንግግራቸው፣ ከስራቸውና ከሚወስዱት አቋማቸው መገንዘብ የሚቻለው አሁንም ቢሆን በውስጣቸው የአማራ ጥላቻ ያለቀቃቸው መሆናቸው ነው። የአማራው ሞትና ቁስል የማይሰማቸው፣ ስደትና እንግልቱ ግድ የማይሰጣቸው፣ በአማራ ህዝብ ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን አይተው እንዳላየ ሆነው የሚያልፋ፣ ሲያመቻቸውም የአማራውን ሞትና እንግልት ለራሳቸው Advantage መጠቀም የሚፈልጉ፣ በአማራ ሞትና ኪሳራ የፓለቲካ “ጌም” የሚጫወቱ “የድሮ ጊዜ ቁማርተኞች” ናቸው። ላለፋት 27 ዓመታት በአማራው ላይ ሲዘመትበት ዳር ቆመው ተመልካች የነበሩ፣ የአማራው መበደልና ስቃይ የማይሰማቸው፣ ሃገር ማለት መሬቱ እንጂ ህዝቡን የሚያካትት የማይመስላቸው ደካሞች በእርግጥ ኢትዮጵያን እወዳለሁ ካሉ ጊዜ ሰጥተው የመጡበትን መንገድ እና ያላቸውን አስተሳሰብ (አቋም) ጊዜውን የዋጀ ነወይ በማለት ቢፈትሹ መልካም ይመስለእኛል። ለኢትዮጵያ አንድነት ቀናኢ የሆነውን የአማራን ህዝብ እራሱን ከጥፋት ለማዳን በሚያደርገው የህልውና ተጋድሎ እንቅፋት ከመሆን መቆጠብ አለባቸው። ይህንን ጨዋ ሃገሩንና ባንዲራውን የሚወድ ህዝብ ባያስከፋት ጥሩ ነው።  … በአማራ ሞትና ኪሳራ “የፓለቲካ ጌም” መጫወት ከሚፈልጉት “የድሮ ጊዜ ቁማርተኞች” በስተቀር በጠራ መስመር ለሃገር አንድነት የሚታገሉትን የአማራ ህዝብ ተቃውሞ አያውቅም ነገር ግን ለህዝቡ በተቃራኒው የሚሰጠው ምላሽ ኝ ጥሩ አይደለም። በተለይ ለሃገር አንድነትና ለህዝቦች እኩልነት ቆመናል የሚሉ አንዳንድ የፓለቲካ ድርጅት መሪዎች ፍርደ ገምድልነታቸው የበዛ ነው። የኦሮሞን፣ የትግሬን፣ የሲዳማን፣ የአፋርን፣ የሶማሌን  ወዘተ በብሔራቸው መደራጀትን ሳይቃወሙ አማራው ላይ ሲደርሱ ግን ወገቤን ይላሉ። ሌሎች ብሔሮች በጎሳቸው ሲደራጁ የደገፉ ሰዎች፣ አማራውን ግን አትደራጅ ኢትዮጲያዊነት ይሻልሀል ማለታቸው አንተ ስለራስህ አታውቅም እኔ አውቅልሃለሁ እንደማለት ነው። ይህ ደግሞ የአማራን ህዝብ መናቅ ነው። ይልቁኑ የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማን እንደ ማህተቡ አጥብቆ ወደ ያዘው ወደ አማራው መመላለሳቸውን ለጊዜው ተወት አድርገው የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ተረግጦና ተጥሎ የኦነግ ባንዲራ ወደተሰቀለበት፣ የኢትዮጵያ ታሪክና ጀግኖቿ ወደሚሰደቡበት፣ የሃገር ባለውለታዎች ወደሚንቋሸሹበት፣ የባለፈው አልበቃ ብሏቸው ዛሬም የአማራን ደም ለማፍሰስ የጦርነት ነጋሪት ወደሚጎሸምበት፣ በቃኝ የማያቁ የቀን ጅብ ዘራፊዎችና ደም አፍሳሾች ወደ ተከማቹበት፣ ዘረኝነት ጠዋት ማታ ወደሚሰበክበት ክልሎችና ከተሞች ሄደው ስለ ኢትዮጵያዊነት፣ ግብረገብና አብሮ የመኖርን ጥበብን ቢያስተምሯቸው ጥሩ በሆነ ነበር። ከዚህ በተረፈ በአማራ ኪሳራና ደም በወያኔ፣ በኦነግና በሻቢያ የፈረሰች ኢትዮጵያን ዳግም ለማቆም የሚመኙ ሰዎችን ተዉ በሏቸው። እንደ ዘመነ መፍሳንት የተከፈፋለችን ሃገር ዳግም ቴዎድሮስና ምኒሊክ ተነስተው በአማራ ደም አንድ እንዲያደርጓት የሚመኙ ሰዎች አሉ። ኢትዮጵያዊነትን የሁሉም እንጂ የአማራው ብቻ አይደለችም። ሁሉም ኢትዮጵያነቱን ይዞ ወደ ጠረጴዛ ይምጣ፣ ከዛ በኋላ መነጋገር ይቻላል። ከዚህ በፊት አማራው ለኢትዮጵያ ነፃነትና አንድነት መሞቱ፣ ለእድገትና ስልጣኔዋ መድከሙ፣ በዚህ ስርዓት ሽልማትና ምስጋና ሳይሆን በደልና እንግልት ነው ያገኘው፣ አማራ ለሃገሩ ያለው ፍቅር እንደ ክርስቶስ በከሃዲያን እና ጊዜ ባነሳቸው የባንዳ ልጆች አሰቀለው፣ አዋረደው፣ አፈናቀለው፣ በድህነት እንዲጎሳቆል፣ በሃገሩ ላይ ሁለተኛ ዜጋ አደረገው፣ ያባቶቹን ርስት ቀምተው አፈናቀሉት እንጂ በዚህ ዘመን ያገኘው መልካም ነገር የለም።

ነገሩን ግልጽ ለማድረግ በመጨረሻ አንድ ነገር ልበልና ጽሁፌን ላጠናቅ አማራው ልደራጅ ያለው ኢትዮጵያዊነቱን ጠልቶ ወይም ክዶ፣ አባቶቹ ለዚህች ሃገር የከፈሉትን ዋጋ ዘንግቶ አይደለም፣ እንደሌሎቹም ለመገንጠል፣ ሃገር ለመዝረፍ ሳይሆን ጥቃት፣ መገለልና በደል ስለበዛበት እራሱን ከጨርሶ ጥፋት ለመከላከል በአልሞት ባይ ተጋዳይነት የገባበት የህልውና ትግል ነው። ስለዚህ ከዚህ በፊት የአማራን መደራጀት ትቃወሙ የነበራችሁ በአንድነትም ይሁን በሌላ ጎራ የተሰለፋችሁ ሁሉ የአማራው ተጋድሎ ፍትሃዊና ምክንያታዊ መሆኑን ተገንዝባችሁ ቢቻላችሁ የትግሉ አጋዥ ሁኑ፣ ካልሆነላችሁ ግን እንቅፋትነታችሁን ብትተው የተሻለ መሆኑን ወንድማዊ ምክሬን እለግሳለሁ። የአማራ ተጋድሎ ላይቆም ተጀምሯል። —//—

ድል ለአማራ ህዝብ!

ደረጀ ተፈራ