አቶ ታማኝ በየነ

እልል አለች ኢትዮጵያ – እጆቿን ዘርግታ ወደ ሰማይ፣
ታማኝ ውድ ልጇ ዘወትር – እንዳልተለያት ስታይ፤

“ይደልዎ!” አለ ሕዝቡ – ያገር-አድን ቅኔ እንደተዘረፈ ሁሉ
በ”አቋቋም”፣ በአካሄዱ… ተማርኮ በውብ ቃሉ፤

የጥበብ ነው ተፈጥሮው – ውበት ማስተዋልን የታደለ፣
ላገር፣ ለሕዝብ በእምነት አድሮ፣ – የፍቅር ህያው ሃውልት የተከለ፤

ታማኝ ለሙያው ክህሎት – የመድረኩ ጸዳል አብሪ፣
በፈጠራው መንፈስ-አዳሽ – አገር ወዳድ ወገን አኩሪ፤

“የትዕይንተ-ጥበባት” ሞተር – የብሔራዊ ትያትር ዋልታ፣
የመድረኩ መሪ ተዋናይ – ጥበብ ለተጠማ አለኝታ፤

በ”ዘመነ-ውጥረት” ማግስት – የታዳሚው ሳቅ አፍላቂ፣
ኢትዮጵያዊው ብላቴና – ትኩስ ህይወት ተፍለቅላቂ፤

ባለቅባት፣ ባለጸጋ – ተሰጥዖ ለኪነት፣
በቀልዳ-ቀልድ እያዋዛ – አሳላፊ ክቡር እውነት፤
ከ”ፋሲሊደስ”..እስከ “ሕዝብ ለሕዝብ”…
ከ”ሮሃ” እስከ “ደመራ”፣
አንጸባራቂ ኮከብ – በኪነቱ አለም ጎራ።

…የሕዝብን ድምጽ አስተጋቢ – ሃሳቡን ተንታኝ ያለፍርሃት፣
ከ”ስቴድዮም” እስከ “ዲሲ” – ከ”ሲ-ኤን-ኤን” እስከ “ኢሳት”፤
ከ”አኬልዳማ” እስከ “ፌዝ-ራሊዝም” – በመልሶ ማጥቃት ዝና፣
በመረጃ እሚያጋልጥ – የ”ኢቲቪ”ን ጉድ ገመና፤
ከአሜሪካ እስከ አውሮፓ – ከኦሺያንያ እስከ አፍሪካ፣
እንደ አበባ ጽጌረዳ – በየዕለቱ እሚፈካ።

የመጥምቁ አምሳያ – ጭው ባለው በረሃ ጯኺ፣
ከድቅድቅ ጨለማ ውስጥ አሻግሮ – መጪዋን የብርሃን ቀን ጠቋሚ።
“እኔ በቃላት አጠምቃችኋለሁ፤ በመንፈስ የሚያጠምቃችሁ ከኋላ ይመጣል፤”
እያለ ለኢትዮጵያውያን – እሚረጭ ያንድነት ፈዋሽ ጸበል።

ከባድ ሸክም ያረፈበት – የትውልዱ መሪ አውራ፣
ብሩህ ተስፋን ሰንቆ – ለጨለመበት እሚያበራ፤
የጭንቅ አጋር.. ያገር ሲሳይ – የወገኑ ባላደራ፤

የአንድነት ምልክቱን – ሃገራዊ ክቡር ዓርማ፣
ሕዝብ በእምነት ያስረከበው – የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ፤

ምንኛ መታደል ነው – ለሕዝብ አደራ መታጨት፣
ለካስ ይሄ ነው ምስጢሩ – “ስምን መልዓክ ያወጣዋል” ማለት፤

ወድቃ-ደቃ እንደማትቀር ስታውቅ – እልል አለች አገሬ፣
አዕላፋት አፍርቶ – ተስፋ ሲሆናት ‘አጅሬ’!
የአንድነት ዋስ ጠበቃ – ሁሉን-አቀፍ አንጋቹ፣
በኪነቱ፣ በ”አክቲቪስቱ” – ለሰው ልጅ መብት ተሟጋቹ፤

“የሕዝብ ጆሮ፣ የሕዝብ ዐይን” ነጻ ሚዲያ ለመገንባት፣
ቤት፣ ንብረቱን፣ ልጆች፣ ሚስቱን፣ – ትቶ ባለም ሲንከራተት፣
ላንድ ራሱ ያለው ጸጋ – የሚያፈራው ዕንቁ ዋጋ፣
ጭብጨባ ነው ወረቱ – አጀብ-ድምቀት ንብረቱ፣
ህሊናዊ እርካታ ነው – ሰላም እንቅልፍ መተኛቱ፤
(ለኛም አዟል ይቺን “ኪኒን” – በዘወትር ስብከቱ)።

ባለም ዙሪያ በሕዝብ ነግሦ፣ በሄደበት ፍቅር አፍሶ፣
የትውልዱ ዕሴት ዋጋ – እማይገኝ በፍለጋ፤

እልል አለች ኢትዮጵያ—እጆቿን ዘርግታ ወደ ሰማይ፣
ታማኝ ውድ ልጇ ዘወትር— እንዳልተለያት ስታይ፤

“ይደልዎ!” አለ ሕዝቡ— ያገር-አድን ቅኔ እንደተዘረፈ ሁሉ፣
በ”አቋቋም”፣ በአካሄዱ… ተማርኮ በውብ ቃሉ፤

የጥበብ ነው ተፈጥሮው— ውበት ማስተዋልን የታደለ፣
ላገር፣ ለሕዝብ በእምነት አድሮ – የፍቅር ህያው ሃውልት የተከለ!

ጌታቸው አበራ
የካቲት 2005 ዓ/ም
(ፌብሯሪ 2013)
========================================================================

የሕዝብ “ሃብት” ለሆንውና ለተወዳጁ ታማኝ በየነ መታሰቢያነት ከዛሬ አምስት ዓመታት በፊት ፣ የጫርኳትን ይህቺን ግጥም ዳግም ለንባብ ለማብቃት የወደድኩት፤ ታማኝን፣ ቤተሰቡን፣ መላውን አገር-ወዳድ ደጋፊዎቹንና አክባሪዎቹን እንኳን ደስ ያላችሁ፣ እንኳንም ለዚህች ዕለት አበቃን ለማለት ነው።

(እንደ አቤ ቶክቻው በቅንፍ ውስጥ ጥቂት ለማከል ያህል፤ ከአምስት ዓመታት በፊት ይህችን ግጥም ስጭር፣ “ያጋነንኩ” የመሰላቸው ነበሩ፤ ይሁንና አሁን “የባሰው” ቀን መጣላቸው፤ እንዴትስ ሊሸከሙት ይቻላቸው ይሆን?)