የኢትዮጵያ አየር መንገድ
AFP

ትላንት የአዲስ አበባ፣ ባህርዳርና መቀሌ አውሮፕላን ማረፊያ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች የስራ ማቆም አድማ መትተዋል።

የትራፊክ ተቆጣጣሪዎቹ ከደሞዝ ጭማሬ፣ እውቅናና ከጥቅማጥቅም ጥያቄ ጋር በተያያዘ ነው ከላይ በተጠቀሱት አውሮፕላን ማረፊያዎች አድማ የመቱት።

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን ዳይሬክተር ጀነራል ኮሎኔል ወሰንየለህ ሁነኛው «እስከዛሬ ድረስ በመሰል ደረጃ የወጣ ጥያቄ አልነበረም» ይላሉ።

«ከዚህ ቀደም የነበሩት ጥያቄዎች ከደረጃ አሰጣጥ (ሬቲንግ) ጋር የተያያዙ ነበሩ፤ እኒህ ጥያቄዎች ደግሞ በዓለም አቀፍ አሰራር መሰረት የሚመለሱ ናቸው። ለዚህ ኮሚቴ ተቋቁሞ እነሱንም የኮሚቴ አባል አድርገናቸዋል» በማለት ኮሎኔል ወሰንየለህ ሁኔታውን ያስረዳሉ።

«እውቅና የመስጠት ጉዳይም ሌላው ነገር ነው፤ በዚህ በኩል ደግሞ መንግሥት የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎችን ሥራ እውቅና በመስጠት በተወሰነ መልኩ ከፍ ያለ ደሞዝ እየከፈለ ነው ያለው።» በማለት እዚህ ጉዳይ ላይ መግባባት ያልተቻለው የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎቹ እውቅናን ከገንዘብ ጋር ስላያያዙት እንደሆነ ለማስረዳት ይሞክራሉ።

«ሃገሪቱ ልትከፍል በምትችለው አቅም ጥናት አስደርገን ኮሚቴ አቋቁመን እነሱም የኮሚቴው አባል ሆነዋል። ነገር ግን እነሱ እየጠየቁ ያሉት 1 ሺህ በመቶ (አስር እጥፍ) የደሞዝ ጭማሪ ይደረግልን ነው።»ይላሉ።

ኃላፊው ጨምረውም «ደመወዛችን አንሷል፤ መንግሥት እኛ በፈለግነው መጠን ካልከፈለን አድማ እንመታለን ብሎ መንግስትን ማስገደድ ተገቢ ነው ወይ? በሌላው ዓለምስ ይሄ ያስኬዳል ወይ?» ሲሉ ይጠይቃሉ።

. «ወይዘሮ ጎሜዝ፤ እርስዎ አያገባዎትም! አርፈው ይቀመጡ በልልኝ»

. አብዲ ሞሃመድ ያለመከሰስ መብታቸው ተገፈፈ

. የብአዴን መግለጫ፡- ከስያሜ መቀየር እስከ ኢትዮ ሱዳን ድንበር

የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎቹ ላለፉት ዓመታት አለብን የሚሉትን ችግር ሲያሰሙ እንደነበር በማስመልከት ጥያቄ ያቀረብንላቸው ኃላፊው መንግሥት በሚያደርገው የደሞዝ ጭማሪ መሠረት ባለሙያዎቹ ተጠቃሚ ሲሆኑ እንደነበር ነገር ግን የ1 ሺህ በመቶ ጭማሬ ጉዳይ ሲነሳ ሲሰሙ የመጀመሪያ ጊዜ እንደሆነ ገልፀዋል።

«ምንም እንኳ መንግሥት አንድ ሺህ በመቶ (አስር እጥፍ) የሚለውን ኃሳብ ባይቀበለውም በተቋቋመው ኮሚቴ አማካይነት ጥናት እያካሄደ ነው»

የባለሙያዎቹ አድማ መምታት በረራ ላይ የፈጠረው ተፅዕኖ ካለ በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ኃላፊው «በአድማው ተሳታፊ ያልሆኑ ባለሙያዎች ፣ ከዚህ ቀደም የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪ የነበሩና በሌላ ስራ ላይ ተመድበው የነበሩ ሌሎች ሥልጠና እንዲወስዱ ተደርጎ እንዲሁም ባለሙያዎችን ከውጭ አገር አየር መንገዶች በማምጣት ሥራው ያለ አንዳች እንከን እንዲካሄድ እያደረግን ነው» በማለት መልስ ሰጥተዋል።

ይህ ዘላቂ መፍትሄ መሆን ይችላል ወይ ስንል ላቀረብንላቸው ጥያቄ «እንግዲህ ከመንግሥት አቅም በላይ የሆነ የደሞዝ ጭማሪ የጠየቀን ባለሙያ ሌላ የምንይዝበት መንገድ የለም፤ ሌላም አማራጭ የለም፤ ስለዚህ ይህ ብዙ ችግር አይሆንብንም» ይላሉ።

ቢቢሲ የኢትዮጵያ አየር ትራፊክ ተቆጣጣሪ ባለሙያዎች ማህበር አመራሮችን ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

SOURCE     –   BBC/AMHARIC