የቱሉ ሞዬ ጂኦተርማል ፕሮጀክት የገንዘብ ድጋፍ ስምምነት የፊርማ ሥነ ሥርዓት
ቢዝነስ
29 August 2018
ቃለየሱስ በቀለ
የአሜሪካ የንግድና ልማት ኤጀንሲ በኦሮሚያ ክልል ለሚካሄደው የቱሉ ሞዬ የጂኦተርማል ፕሮጀክት ጥናት የሚውል የ1.1 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አደረገ፡፡
በምሥራቅ አርሲ ዞን ኢተያ ከተማ አቅራቢያ ቱሉ ሞዬ በተባለ ሥፍራ የሚገነባው የጂኦተርማል የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በአራት ክፍሎች የሚገነባ ሲሆን፣ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ 520 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ይኖረዋል፡፡ የፕሮጀክቱ አጠቃላይ ወጪ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ይገመታል፡፡ የፕሮጀክቱ ባለቤት ቱሉ ሞዬ ጂኦተርማል ኢፕሬሽንስ የተሰኘ በኢትዮጵያ የተቋቋመ ኩባንያ ሲሆን፣ በፕሮጀክቱ ላይ ኢንቨስት የሚያደርጉት ሬካቪክ ጂኦተርማል የተባለ የአይስላንድ ኩባንያና ሜሪዲየም የተሰኘ የአሜሪካ ኩባንያ ናቸው፡፡
የአሜሪካ ንግድና ልማት ኤጀንሲ ለቱሉ ሞዬ ጂኦተርማል ፕሮጀክት የመጀመርያ ክፍል የአዋጭነት ጥናት የሚውል 1.1 ሚሊዮን ዶላር እንደለገሰ አስታውቋል፡፡ የመጀመርያው ክፍል 50 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም እንደሚኖረው ተገልጿል፡፡ ጥናቱን የሚሠራው ዴለሮስ ኢንተርናሽናል የተሰኘ የአሜሪካ ኩባንያ ነው፡፡
የገንዘብ ድጋፍ ስምምነቱ ሰኞ ነሐሴ 21 ቀን 2010 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ ተፈርሟል፡፡ ስምምነቱን የፈረሙት የአሜሪካ ንግድና ልማት ኤጀንሲ የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ኃላፊ ካትሪን ሂንዳርዴልና የቱሉ ሞዬ ጂኦተርማል ኦፕሬሽንስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዳሬል ቦይድ ናቸው፡፡
በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት በአዲስ አበባ የአሜሪካ ኤምባሲ ጉዳይ ፈጻሚ ትሮይ ፊትሬል ለኢትዮጵያ ልማት ዘላቂ፣ አስተማማኝና ተመጣጣኝ ዋጋ ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ወሳኝ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ በጂኦተርማል፣ በፀሐይ፣ በውኃና በንፋስ የኃይል ምንጮች የታደለች መሆኗን የገለጹት ፊትሬል፣ አሜሪካ ኢትዮጵያ ዕምቅ የኃይል ምንጮችን ለማልማት የምታደርገውን ጥረት እንደምትደግፍ አስረድተዋል፡፡
ሚስተር ቦይድ ኢትዮጵያ በክልሉ በጂኦተርማል ዕምቅ ሀብቷ ቀዳሚ እንደሆነች ገልጸው፣ የቱሉ ሞዬ ፕሮጀክት ይህን ዕምቅ ኃይል ጥቅም ላይ ለማዋል እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡ በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ዴኤታ ፍሬሕይወት ወልደ ሃና (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ሁለት ፈር ቀዳጅ የጂኦተርማል ፕሮጀክቶች በመካሄድ ላይ እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡ ኢትዮጵያ በስምጥ ሸለቆ ውስጥ ከፍተኛ ዕምቅ የእንፋሎት ኃይል ያላት ቢሆንም፣ እስካሁን ጥቅም ላይ ሳይውል መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ የጂኦተርማል ፕሮጀክት ጥናት ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ በመሆኑ፣ የአሜሪካ መንግሥት ያደረገው የገንዘብ ድጋፍ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡
‹‹በስምጥ ሸለቆ ውስጥ ያለውን ከፍተኛ ዕምቅ የጂኦተርማል ሀብት ለማልማት ሁለት ኩባንያ ብቻ በቂ ላይሆን ስለሚችል፣ ተጨማሪ ኩባንያዎች ይመጣሉ ብለን እየጠበቅን ነው፤›› ያሉት ፍሬሕይወት (ዶ/ር) ግልጽ በሆነ ጨረታ ፕሮጀክቶቹ ለግል አልሚዎች እንደሚሰጡ ተናግረዋል፡፡
ሚስስ ካትሪን በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግሥት ታዳሽ የኃይል ምንጮች ለማልማት ቁርጠኝነት ማሳየቱን ገልጸው፣ የአሜሪካ ንግድና ልማት ኤጀንሲ በኃይል፣ በትራንስፖርትና በኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ ልማት እገዛ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡ በኢትዮጵያ ገበያ ለሚሳተፉ የአሜሪካ ኩባንያዎች ኤጀንሲው ድጋፍ የመስጠት ፍላጎት እንዳለው ገልጸዋል፡፡
የቱሉ ሞዬና ሻሸመኔ ከተማ አቅራቢያ ኮርቤቲ በተባለ ሥፍራ የሚገነባው 500 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለው የኮርቤቲ ጂኦተርማል ፕሮጀክት ልማት ስምምነት፣ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር በታኅሳስ 2010 ዓ.ም. መፈረሙ ይታወሳል፡፡ በአጠቃላይ ሁለቱ የጂኦተርማል ኤሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጀክቶች 1,000 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ይኖራቸዋል፡፡ ፕሮጀክቶቹ በአሜሪካ ንግድና ልማት ኤጀንሲና ፓወር አፍሪካ እንደሚደገፍ ታውቋል፡፡
Reporter