30/08/2018

ሰፊ የህዝብ ድጋፍ ያለው መንግስት ጨቋኝ የመሆን እድሉ ሰፊ ነው!!!
ሳሙኤል ገዛህኝ
 
”መንቀል እንጅ መትከል አናውቅም” (የፕሮፍ መስፍን አባባል ነው) እርግጥ ነው ኢትዮጵያውያን ችለው ችለው አድፍጠው ጨቋኞችን መንቀል ይችላሉ:: እንችላለን:: በነቀልነው ክፉ መንግስት ፈንታ የህዝብ መንግስት ተክሎ ስር ስድዶ ለፍሬ እስኪበቃ መከታተል ግን አናውቅም::
ጨቋኙ ህወሃት ብሶት በወለደው ህዝብ ተነቅሏል:: የአብይ መንግስት የህዝብ መንግስት ነው:: በህዝብ ይሁንታ በህዝብ ፈቃድ የተተከለ::
የአብይ መንግስት ያልጠና ገና ለጋ መንግስት ነው:: በፍትህ: በእኩልነት እና በዴሞክራሲ የፀና ሆኖ ስር እንዲሰድድ የተከልነው እኛ የመከታተል የመንከባከብ ሃላፊነት አለብን::
ለመንቀል ከሚፈጀው ጊዜና ትእግስት ያላነሰ ተንከባክቦ ስር እንዲሰድድ በደምብ እንዲፀድቅ ማድረጉ ብዙ ጊዜ: ትእግስት: ዘዴም ይጠይቃል::
የተከልነውን የአብይ መንግስት ስር ስድዶ እንዲፀድቅ የሚከተሉትን ጥቂት ጉዳዮች አሁን ማድረግ እና መከታተል ያለብን ይመስለኛል::
– ለጨቋኙ መንግስት መነቀል ምክንያት የሆኑ እና ለአብይ መንግስት ይሁንታ የስጠንባቸው: ተስፋና ጥያቄዎች በፍጥነት በስርዓት እና በህግ እንዲ ደነገጉ መጠየቅ መከታተል::
– ተስፋ የተገቡ የህዝብ ጥያቄዎች መቼ በህጋዊ ማእቀፍ እንደሚመሰረቱ መጠየቅ መከታተል:: በዚህ ጊዜ ውስጥ ይህ ይደረጋል ሊባል ይገባል::
– የሚድያ ህግ: የህገ መንግስት አንቀፆች: የፀረ ሽብር ህግ: የመያዶች ህግ:… የመሳሰሉት መቼ እና እንዴት እንደሚሻሻሉ እንደሚፈፀም መጠየቅ::
– የህዝብን እና የአገር ሀብት በመዝረፍ የታወቁ ግለሰቦች እና ድርጅቶች እንዲመረመሩ ወይም ለፍርድ እንዲቀርቡ መጠየቅ:: ይህ በጊዜ ገደብ መታወቅ አለበት መቼ እንደሚፈፀም::
– የዜጎችን ሰብአዊ ምብት በመጣስ አሰቃቂ ወንጀል የፈፀሙ ግለሰቦችና ድርጅቶች በታወቀ ጊዜና ግልፅ በሆነ ሁኔታ ለፍርድ እንዲቀርቡ መጠየቅ:: ጥፍራቸው የተነቀለ: እግራቸው የተቆረጠ: እርቃናቸውን የተዋረዱ: የተደፈሩ: ቶርቸር የተደረጉ ወገኖች እንዲካሱ: ፍትህ እንዲያገኙ መጠየቅ::
– በመላው አገሪቱ በተለይ በሶማሌ ክልል ለዜጎች መፈናቀል እና ሞት ለሀብት ውድመት እና ዝርፊያ ተባባሪ እና ተሳታፊ እንደሆኑ የሚጠረጠሩ የጦሩ ጀነራሎች እና የህወሃት አባላት ለፍርድ እንዲቀርቡ መጠየቅ::
አደባባይ ወጥቶ ጨቋኙን ህወሃት የነቀለው ቄሮው: ፋኖው: ዘርማው: የሶማሌው: የደቡቡ: የመላው ኢትዮጵያ ወጣት አሁን ያለውን መንግስት በተደራጀና ግልፅ በሆኑ ጉዳዮች ከፍ ብለው የተጠቀሱትና ሌሎችም ጉዳዮች ባስቸኳይ ምላሽ እንዲያገኙ የአብይን መንግስት በአደባባይ ወጥቶ መጠየቅና ጫና ማሳደር ያስፈልጋል::
ክትትል እና ጥበቃ የማይደረግበት ከልክ በላይ የህዝብ ድጋፍና ይሁንታ ያለው መንግስት እጅግ ጨቋኝ የመሆን እድሉ ከፍተኛ ነውና ቁጥጥር ክትትል ሊደረግበት ይገባል: