ወሎ የኢትዮጵያ ውርስና ቅርስ ማኅበር

Wollo Ethiopian Heritage Society

P.O. BOX 918, OXON HILL, MD 20750 (USA) ፠ wollo.org

ነሓሴ 23፣ 2010 ዓ.ም. (August 28, 2018)

የራያ ሕዝብ በተዋረድ ከአማራ፣ኦሮሞ፣ አገው፣ ትግሬና አፋር የተዋለደ ዛሬ እንደ ሌላው ወሎየ ባህላዊ ማንነቱን አማራ ብሎ ያስመዘገበ ህዝብ ነው። በሰሜን እንደርታ፡በደቡብ የጁ፡በምስራቅ አፋር እንዲሁም በመዕራብ ላስታ ያዋሱኑታል። በታሪክም በትግሬ፣ በዋግሹምና በየጁ ባላባቶች መካካል የፉክቻ ማዕከል ሆኖ ቆይቷል፡፡

የራያ ሕዝብ የራሱ የሆነ ልዩ ባህል እና ወግ አለው፡፡ ከሚደነቅበትና ከሚያስደስት ባህሉ ሁሉም እምነት ተከታዮች በተለይም ሙስሊም-ክርስቲያን፡ደገኛ-ቆለኛ ሳይል ተከባበሮ የሚኖርበት እሴቶችን ማቀፉ ነው። ብዙሃን ቋንቋዎችን ያንጸባረቀ የራሱ አነጋገር፡ አለባበስ፡ አዘፋፈን፡ የሰርግና የለቅሶ ስነስርአት ያለው ኩሩ እና ጀግና ውሎየ ነው። «ወያኔ» ተብሎ የሚጠራውን የ «አንረሳ» አመጽ በጣሊያን ወረራ ዘመን ያነሳውም ይህ ሕዝብ ነው።

ራያ ከዚህ ወራሪ-መሰሉ ትሕነግ መስተዳደር በፊት መቼም ቢሆን ከወሎ ክፍለ ሀገር ዉጭ የተዳደረበት ወቅት የለም። ነገር ግን ለ27 አመታት ካለ ፈቃዱ የደቡብ ትግራይ ወረዳ ሆኖ እንደ ወልቃይት፡ ጠገዴና፡ ጠለምት ሕዝብ በትግሬ ወያኔዎች ጫማ እየተረገጠና እየተፈናቀለ የቆየ ሕዝብ ነው። የትግራይ ክልላዊ መንግስት የመገንጠል ማስፈራሪያውን እሙን ለማድረግ እጅግ ለም እና ሰፊ የእርሻና ሌሎች ጥሬ ሀብቶች መገኛ የሆነዉን የራያን መሬት በጉልበት በመጠቅለል የተቃወሙትን ሰዎች በገፍ በማሰር በመግደልና ከቀያቸው በማሳደድ ሀብቱን በተለያዩ ህገወጥ የፓርቲ ኩባንያዎቹ በመቆጣጠር የራያን ሕዝብ የበይ ተመልካች አድርጎታል። ከመሃል አገር በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ የማይታወቀውን የዝርፊያ ሃብት ወደ መቀሌ ለማሸሽ እንዲመቸውና ኮረምንና አለማጣን ለማቆርቆዝ መንገዶችንና ሀዲዶችን በባዶ በበረሃ እንዲያልፉ አድርጓል፤እያደረገም ነው።

ሰሞኑን በሀገራችን በተፈጠረዉ የለውጥ ጭላንጭል ምክንያት ልክ እንደሌሎቹ አካባቢዎች ራያም እጂግ ሰላማዊና ጨዋነት በተሞላበት ሁኔታ የመብታችን-ይከበር ጥያቄዉን ቢያቀርብም ከኮራጁ «ወያኔ» የገጠመዉ የተለመደዉ የጉልበት ምላሽ ነዉ። የአለማጣ ሕዝብ ጌታቸው አሰፋ የተባለውን የደህንነት ወንጀለኛ ከአሁን በኋላ አንተ አትወከለንም ብሎ ከስብሰባ አዳራሽ አባሮታል። የአለማጣ የዋጃና የኮረም ነዋሪዎች የለውጥ ሃይሎችን ለመደገፍ በተደጋጋሚ በሞከሩት የአደባባይ ድምፅ ማሰማት ታላቅ ድብደባዎች፣ጅምላ አፈናዎች፣ እስሮች፣ ግድያዎችና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች በመቀሌው የገዥ ቡድን ተደማምረውባቸዋል። በትሕነግ ጀነራሎች የተጠለፈው የአፋር ልዩ ፖሊስና የወያኔ አጋዚ ሚሊሽያ ወረዋቸው ይገኛሉ። ቀደም ብሎ በወልድያ፣ ቆቦና መርሳ እንዳደረጉት የኮረምንና የአለማጣን ወጣቶች ከየቤቱ እያደኑ ወደ ማረሚያ ካምፖችና ወደ በረሃ ጨው ማምረቻዎች እያጋዟቸው ይገኛሉ።

 

*** የራያ ሕዝብ የጠየቀዉ ራስን-በራስ የማስተዳደር መብቱን፣ የተረሳውን እድገቱንና፣ በተለይም በጉልበት የተቀማዉን የታሪክ ማንነቱን ነዉ!! ***

 

ወሎ ውርስና ቅርስ ከጎናችሁ መቆሙን በአጽንዖት እየገለጸ፦

(1) ጥልቅ ተሃድሶ አካሂዳለሁ የሚለው የኢሐዴግ አዲስ አመራር በአማራው ሕዝብ በተለይም በራያና በወልቃይት ነዋሪዎች ላይ ለረጅም ጊዜ የተነጣጠረውን የግፍ ስርዓት በጆሮ ዳባነት ወይንም ችግሩን በማቃለል እይታ ማፌዙን አቁሞ የዜጎችን እኩልነትና መብቶችን እንዲታደግ በጥብቅ እንጠይቀዋልን፤

(2) መላው የወሎ ሕዝብ ልጆችህ በተናጠል ሲመቱ በቁጭት ማየቱን አቁመህ ባለንላችሁ መንፈስና አንድ ግንባርነት ለነጻነትህ ካልታገልክ የጭቆና አገዛዝ በጫንቃህ ላይ እንደሚፈራረቅብህ አይቀሬነቱን ልናስግነዝብ እንወዳለን፤እንዲሁም

(3) የታመቀው የራያ ጉዳይ እየገነፈለ ይበልጥ ወደተወሳሰበ ደረጃ ከማደጉና በደቡብ ክፍለ-ሃገሮቻችን 3 ሚሊዮን ተፈናቃዮችን ወዳፈራው ሕዝብ-ለሕዝብ ግጭት ከማምራቱ በፊት የፌደራል መንግስት ተጠያቂነቱን በመገንዘብ ክልለ-መንግስታዊ ጽንፈኝነትን ባፋጣኝ እንዲያስቆም በአንክሮ እናሳስባለን።

ዘረኝነት፡ አግላይነት፡ ዘራፊነትና አምባገነንነት ያክትሙ!

የራያ ሕዝብ ጥያቄ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጥያቄ ነው!

ሰላምና ፍትህ ለመላው የኢትዬጵያ ሕዝብ!