ባሕር ዳር፡ነሀሴ 24/2010 ዓ.ም (አብመድ) የኢህዴን መስራች እና ሊቀመንበር በመሆን ለድርጅታቸው እና ለሀገራቸው ብዙ ትግል ያደረጉት አቶ ያሬድ ጥበቡ መንግስት ገና ባልተጠናከረበት ወቅት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን በመወከል በውጭ ሀገራት በርካታ ስራዎች ሠርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ እርዳታ ማስተባበሪያ ድርጅትን አቋቁመው ከለጋሽ ሀገራት በርካታ እርዳታ አስገኝተዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ጉልህ የዲፕሎማሲ ስራ ሲሰሩ የቆዩ ሰው ናቸው፡፡ 
ይሁን እንጂ በድርጅቱ ውስጥ በተፈጠረ አለመግባባት ሀገር ውስጥ መስራት ስላልቻሉ በስደት ወደ ውጭ ሄደው ለበርካታ ዓመታት በስደት ኖረዋል ፡፡አሁን የተፈጠረውን ለውጥ ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ጥሪ መሰረት ወደ ሀገራቸው ገብተዋል፡፡

አቶ ያሬድ ወደ ሀገሬ እንድመጣ ያደረገኝ በሀገሪቱ ያለው ለውጥ እና እሱን ተከትሎ በተደረገው ጥሪ ነው ፡፡ከአሁን በፊት የነበረው አሠራር የአማራ ብሔረተኝነት በልሂቃን እና በአመራሩ ተቀባይነት እንዳይኖረው እና በበጀት አመዳደብ ላይ ተፅእኖ እንዲኖረው አድርጓል ብለዋል፡፡

አሁን ግን እየታየ ያለው ለውጥ የአማራ ምሁር እና ህዝብ ወደቀልቡ ተመልሶ የአማራ ብሔረተኝነትን እንዲያጎለብት ትልቅ እድል ሰጥቶታል ሲሉ ለአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ተናግረዋል፡፡

አቶ ያሬድ በሀገሪቱ የተፈጠረውን የለውጥ እንቅስቃሴ ለመቀላቀል ዛሬ ወደ ባሕርዳር ሲገቡ የአማራ ክልል መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ.ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ንጉሱ ጥላሁንን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት ባሕርዳር አውሮፕላን ማረፊያ ተገኝተው አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ወንዳጥር መኮንን
አዘጋጅ፡- ደጀኔ በቀለ