በሐምሌ ወር የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያፀደቀውን መሠረት በማድረግ ‹ቪ ኤይት› መኪና ለመግዛት 5.5 ሚሊዩን ብር ወጪ በዶክተር አብይ አህመድ ካቢኔ መታገዱ መልካም ጅምርና ህዝብ ህዝብ የሸተተ እንምጃ ነው እንላለን፡፡

ከቂል ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል!!! በቀ.ኃ.ሥ ዘመን ለእድገት ሠራተኞች ቢሽክሌት፣ ቮክስዋገንና ላንድሮቨር መኪኖች ይሰጡ ነበር፡፡ በደርግ ዘመን ፓጃሮና ላድን ክሩዘር መኪኖች ተበረከቱላቸው፡፡ በወያኔ ዘመን ለአንድ ሹም ቪ ኤይትና ሁለት ሦስት  ፎር ዊል ድራይቨ መኪኖች በግብር ከፋዩ ህዝብ ኃብት ተቸራቸው፡፡ ይህ ሙስናና ሌብነት በደሃው ህዝብና ገበሬዎች ደም በውጪ ምንዛሪ የተገዙ መሆናቸው ያሳዝናል፡፡ የመንግሥት ሹማምንት ጥቅማ ጥቅም ሊበቃ ይገባል፡፡ ለግሉ ዘርፍ የህዝብ መገልገያ ውይይት ታክሲዎች ቀረጥ ተቀንሶላቸው እንዲያስገቡ ቢደረግ ዜጎች በፀሃይና በዝናብ ወደ ሥራና ትምህርት ቤት ለመሄድ ተሰልፈው ሲሰቃዩ በማየት የሚደሰቱ የሹሞቻችን ወራዳ ሥራን የህዝብ ዕንባ ማበሻና መካሻ የለውጥ ዘመን እንዲሆን ይታሰብበት እንላለን፡፡

በፊዴራል ደረጃ ካሉ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች መካከል 77 ቢሮዎች፣የራሳቸው ቢሮዎች/ህንፃ የሌላቸው ስለሆነ የግለሰብ ህንፃን እንደ ቢሮዎች ተከራይተው 380 ሚሊዩን ብር በዓመት ይከፍላሉ፡፡ ከ1983 አ.ም የህወሃት/ኢህአዲግ መንግስት፤ በከተማ ልማት፤ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር፤ የመንግስት ኪራይ ቤቶች ኤጀንሲ (የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ) በመቆጣጠር በአዲስ አበባና በሌሎች አገሪቱ ክልሎች የሚገኙ በድምሩ 17,549 ቤቶች ማስተዳደር ጀመረ፡፡ ለሚኒስትሮች፣ጀነራሎች፣የደህንነት ሹሞች፣ዲፕሎማቶች የመንግሥት ቤት ተከራይተው ቤት ሰርተው የሚያከራዩ የነቀዙ ሹመኞች በሙስና ያገኙትን የግብር ከፋዩን የደሃ ዜጋ ቤት ማስረከብ  በአዲሱ ለውጥ ይኖርባቸዋል እንላለን፡፡ ከነዚህም ቤቶች ውስጥ በመግባት በፊዴራል ደረጃ ያሉ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች  ቢሮዎች በማድረግ፣ለቢሮዎች ኪራይ የሚወጣው 380 ሚሊዩን ብር በዓመት ክፍያን ማዳን ይቻላል እንላለን፡፡ የህወኃት ኢህአዴግ ሹማምንት በሙስና ለቤት መሥሪያ የተሠጠ መሬትና ቤት በጥናት ተደግፎ ለህዝብ ይቅረብ፣ ከዚህ በኃላም ለሹማምንቶችና ካድሬዎች የሚሰጥ ቤሳ ቤስቲን መሬት መኖር የለበትም!!! መንግሥት የራሱን ቢሮዎች ሳይሰራ የግለሰብ መኖሪያ ቤቶች ተከራይቶ መኖር ለከፍተኛ ወጪና በግብር ከፋዩ ህዝብ ኃብት መቀለድ በመሆኑ መቆም አለበት፡፡

የኢፈርትና ሜድሮክ የከተማ ቤቶች ቅርምትበ1967 ዓም የኢትዮጵያ ወታደራዊ መንግስት (ደርግ) በሃገሪቱ ውስጥ የሚገኙ በግል ዘርፍ የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶችን በአዋጅ ቁጥር 20/1974 ወደ መንግስት ሃብትነት በማዘዋወርና በመውረስ ፋብሪካዎች፣ ባንኮችና ኢንሹራንሰ ኩባንያዋችን፣ የከተማ ትርፍ ቤቶችን፣ የገጠር መሬትን፣ እርሻዎችን ወዘተ በብሄራዊ ሃብትና እድገት ሚኒስትር (Ministry of National Resource Development) ስር የተወረሱትን ንብረቶች እንዲያስተዳድር ስልጣንና ሃላፊነት በአዋጅ ተሰጠው፡፡በዚህም መሠረት፣የከተማ ትርፍ ቤቶችን አዋጅ ለማስፈፀም የመንግስት ኪራይ ቤቶች ኤጀንሲ ተቆቁሞ የወር ኪራያቸው ከመቶ ብር በታች የሆኑትን ቤቶች በቀበሌ አስተዳደር ስር እንዲተዳደሩ ተወሰነ፡፡ የወር ኪራያቸው ከመቶ ብር በላይ የሆኑትን ቤቶች በመንግስት ኪራይ ቤቶች ኤጀንሲ እንዲተዳደሩ ተወሰነ፡፡ የደርግ ወታደራዊ ሹማምንቶችና ቢሮክራቶች፤ የኢሠፓ፤ መኢሶን፤ ወዝሊግ፤ ኢጭአት፤ ማልሪድ፤ ሰደድ ካድሬዎች የተወረሱትን ቤቶቹን በነፃ ኪራይ ተቀራመቶቸው፡፡ ከ1967 እስከ 1983 አ.ም ድረስም ቤቶቹን ለግል ጥቅማቸው ተጠቀሙባቸው፡፡ ብዙ ሽህ ህፃናት የጎዳና ተዳዳሪዎች በሚኖሩባት ሃገር እነዚህ ሰቀቀናም የነቀዙ የጦር አበጋዞችና የፖለቲካ ካድሬዎች አገሪቶን አቆረቆዙ፡፡ወታደራዊው መንግስት፤የገጠር መሬትንና የከተማ ትርፍ ቤቶችን በአዋጅ ቢወርስም ቅሉ መሬት በመሸጥ፣ ሊዝና ኮንትራት በማድረግ ተግባር ላይ አልተሰማራም፡፡ የመንግስት ገቢ ከህዝብ ከሚሰበስበው ግብር(ታክስ) እንጂ መሬት በመሸጥ ላይ አልነበረም፡፡

የህወሃት/ኢህአዲግ መንግስት፤ የከተማ መሬት በመሸጥ፤ የገጠር መሬት በሊዝና ኮንትራት ከ 60 እስከ 90 አመታት ለውጭ ሃገር ባለሃብቶች በመሸጥ የኢትዮጵያን ህዝብ የመንግስት ጭሰኛ ያደረገ በእውቀት የጨነገፈ የደደቢት ደደቦች መንግስት ነው፡፡ የኢትዮጵያን ህዝብ የግል ንብረት የማፍራት መብቱን ተነጥቆ በመሬቱ ላይ የመጠቀም መብት ብቻ እንዳለው በህወሃት/ኢህአዲግ መንግስት ህገመንግስት ተደንግጎል፡፡ ከ1983 አ.ም የህወሃት/ኢህአዲግ መንግስት፤ በከተማ ልማት፤ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር፤ የመንግስት ኪራይ ቤቶች ኤጀንሲ (የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ) በመቆጣጠር በአዲስ አበባና በሌሎች አገሪቱ ክልሎች የሚገኙ በድምሩ 17,549 ቤቶች ማስተዳደር ጀመረ፡፡ ከዚህ ውስጥ በአዲስ አበባና በድሬዳዋ አስተዳደሮች በድምሩ 1,242 መኖሪያ ቤቶችና 5,507 የድርጅት ቤቶች መኖራቸውን የግል ኩባንያው በጥናቱ መረጃ ያረጋግጣል፡፡ የህወሃት/ኢህአዲግ መንግስት ከ1983 አ.ም ጀምሮ እስከአሁን እነዚህን መኖሪያ ቤቶች ለህወሃት፣ ብአዴን፣ ኦህዴድ፣ ደህኢዴድ ወዘተ የፖለቲካ ካድሬዎችና የጦር አበጋዞች፣ የደርግ ሹማምንትና ካድሬዎችን ከቤታቸው እያስወጡ በነፃ ተቀራመቶቸው፡፡ የሚገርመው እነዚህ የክልል መንግስቶች በየክልላቸውና በአዲስ አበባ ውስጥ ሁለት የመኖሪያ ቤቶች እንደ ክረምትና በጋ ቤት ይዘው ይገኛሉ፡፡ የህወሃት/ኢህአዲግ መንግስት የፓርላማ ተመራጮች ሌሎች የቤት ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡ ተመራጮቹ ባለመናገራቸውና ቀኝ እጃቸውን ለድምፅ ቆጠራ ለአመታት በማውጣታቸው፤ በክረምቱ ወራት ፓርላማ ተዘግቶ ወደ ቤታቸው ሲሄዱ በሃገረ ባህል ሃኪም ‹ወጌሻ› በመታሸት ነው የተሰቀለው እጃቸው ወደታች የሚወርደው እያሉ የዲጂታል ዘመን ወጣቶች ይቀልዳሉ፣ ያማሉ፡፡

በደርግ ግዜ የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ ለኢንባሲዎች ከ40 እስከ 50 ሽህ በብርና በዶለር ለኢንባሲዎች ይከራዩ የነበሩ ቤቶች በህወሃት የጦር አበጋዞች፣ካድሬዎችና ደህንነቶች ተወርሰው ላለፉት 27 ዓመታት በነፃ መኖሪያነት ሲያገለግሉ፤ የታጣው የህዝብ ሃብት በትንሹ ለማሳየት፤ ለምሳሌ አንድ ቤት 40,000 ሽህ ብር ለኢንባሲ ይከራይ ከነበረ 40,000 ሲባዛ 12 ወራት ይሆናል 480,000 ሽህ ብር በአመት፤ ሲሆን በሃያ ሰባት  አመት ሲሰላ ደግሞ 12,960,000 ሚሊዬን ብር ከአንድ ቤት ብቻ በነዚህ የቀን ጅቦች የኢትዬጵያ ህዝብ ተመዝብሮል ማለት ነው፡፡ ከአጠቃላዩ 17,549 ቤቶች ስንት ቢሊዬን ብር እንደተዘረፈ ለማየት የሒሳብ ሊቅ መሆን አይጠይቅም:: ትላንት በቁምጣና ሸበጥ ጫማ አዲስ አበባ የገባው የህወሃት/ኢህአዲግ የጦር አበጋዞች፣ካድሬዎችና ደህንነቶች በአዲስ አበባ ከተማ 500 ሜ/ካ ቦታ ተሰጥቶቸው ፎቅ ሰርተው ያከራያሉ፣ዛሬም በተሰጣቸው ቤት ኪራይ ይኖራሉ፡፡ እነዚሁ ሹማምንቶች ከየመጡበት ክልል ተጨማሪ 500 ሜ/ካ ቦታ የአርበኝነት ሣይሆን የባንዳነት ሥጦታ ተደርጎላቸዋል፡፡ አበው ሲተርቱ ‹ድህነት ይለመዳል፤ሃብታምነት አይለመድም› የሚሉት ብሂል ለዚህ ነው፡፡ የደርግን ስርዓት ለመጣል ስንት ታጋዬች ወድቀዋል፤ አንዴ ለአፍታ ቀና ብለው የዛሬዎቹን ሃብታም ጅቦች፤ የትላንቱን የድሃ ልጆች ቢዩችሁ ምን ይሉ!!!

በቤቶቹ ቅርምት የደደቢት ህወሃት የጦር አበጋዞችና የፖለቲካ ካድሬዎች የአንበሳውን ድርሻ ሲደርሳቸው ቀጥሎ የብአዴን፣ የኦህዴድ፣ደህኢዴድ ወዘተ ከቤቶቹ ቅርምት ኩርማን፣ ሲሶና አስራት ቅርጫ ደርሶቸዋል፡፡ የህወሃት የጦር አበጋዞች አደዋ አደባባይ ሲግናልና ከተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ከፍ ብሎ ለ‹ኢትዬጵያ› መከላከያ ሰራዊት መኮንኖች መኖሪያነት ስም የተገነባውን ከ50 አስከ 100 የሚደርስ ምርጥ ኮንዶሚኒየም ቤቶች ለህወሃት የጦር አበጋዞች መኖሪያነት ተሰጥቶል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በአዲስ አበባ ከተማና በአጎራባች የኦሮሚያ ክልሎች የህወሃት የጦር አበጋዞች፤‹የህዝብ ደህንነት›ና የፖለቲካ ካድሬዎች ከአንድም ሁለት ሦስት መሬት እየተመሩና እየሸጡ የኢትዬጵያ ህዝብን ንብረት ለአለፉት 27 ዓመታት ዘርፈዋል፡፡በወርሃ ሚያዝያ 2006እስከ 2010 ዓ/ም፤ በዚህ ድርጊታቸው የተበሳጩ የሃገሪቱ ወጣቶች ተቃውሞና አመፅ  በማሰማታቸው ብዙ ሰዋች ህይወታቸውን ማጣታቸውንና አያሌ ዜጎች መቁሰላቸውን የዓለም ዓቀፍ ዜና ሆኖ ሰንብቶ ነበር፡፡ ይህ የተዘረፈ የኢትዬጵያ ደሃ ህዝብ ንብረት አንድ ቀን እንደሚመለስ ጆሮ ያለው ወያኔ ግን አልሰማም ነበር!!! የህወሃት የጦር አበጋዞችና ካድሬዎች የመሬት ቅርምትና የቤቶች ነጠቃ ለአንዴም ለሁሌም ያከትማል የዶክተር አብይ አህመድ  መንግስት በዚህ ዓይነት የሙስና ስርዓት የመንግስት ኪራይ ቤቶች ኤጀንሲ (የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ) የሙስና አሰራር በአዋጅ ይሽራል፡፡ ቤቶቹም ከመንግስት ወደግሉ ዘርፍ ሃብትነት ይተላለፋሉ፡፡ የመንግስት ሹማምንት ቤት፣ መሬትና መኪና የመሳሰሉትን ዓይነት ጥቅማ ጥቅሞችን አያገኙም፡፡ ህዝቡንም በቅንነትና በታማኝነት ብቻ ያገለግላሉ፡፡ የሳዑዲ ዓረቢያ ቢሊዬነር ሼክ መሃመድ አላ-አሙዲ በሜድሮክ ስም ከመንግስት ኪራይ ቤቶች ኤጀንሲ (የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ) ብዙ ቤቶችን በድርጅታቸው ስም በመቆጣጠር በተለይ ሲኤምሲ (ደርግ ለኢንባሲዎች መኖሪያነት ያሠራቸው ሕንፃዎች በዶለር የሚከፈልበትን 90 ከመቶውን በመቆጣጠር) ትልቁን ቅርጫ በመውስድ ለቤት ኪራይ በወር አስር ሚሊዬን ብር እንደተከራዩ ቢታወቅም ብዙ ግዜ የቤት ኪራይ እንደማይከፍሉ በኤጀንሲው ሠራተኞች ያታወቃል፡፡ የህወሃት/ኢህአዲግ መንግስትና የሼክ መሃመድ አላ-አሙዲ (ሜድሮክ) የሲሦ መንግስትነት ሺርክና በመንግስት ኪራይ ቤቶች ኤጀንሲ (የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ) ሹማምንት እስከ አጥንታቸው መቅኒ በሙሰኝነት በነቀዙ ባለስልጣናት የኢትዮጵያ ህዝብን ንብረት ተመዝብሮል፡፡ ይህንን የንቅዘት ግንኙነት ለማጋለጥ የሞከሩ ጋዜጠኛች ሁሉ ማስጠንቀቂያና ድብደባ ደርሶባቸዋል፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከመንግስት ኪራይ ቤቶች ኤጀንሲ በሚመለከት አዲስ የቤቶች ፖሊሲ በመተግበር ብዙ ሚሊዮን ብር ወጪ ማዳን ይቻላል፡፡ አዲሱ የመንግስት ኪራይ ቤቶች ኤጀንሲ (የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ) ሹማምንት ኤጀንሲውን የሙስና ተግባር ሲያጋልጡና ቀጣዮን ሥራቸውን ለህዝብና ለጋዜጠኞች መረጃ ሲሰጡ አልታዮም፡፡ በአዲሱ ለውጥ መሠረት ከኪራይ ቤቶች ቤት ተከራይተው እየኖሩ የእራሳቸውን ቤት የሚያከራዮ በሙስና ተግባር የተዘፈቁ ሹማምንትን ቤቶች የማስለቀቅ ህጋዊ እርምጃ መውሰድ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ጋዜጠኞች ዛሬ ባለው የፕሬስ ነፃነት እውነት ላይ በተመሠረተ መረጃ የሙስና ወንጀል  የማጋለጥ ተልዕኮቸውን ይወጣሉ!!!

ዲያስፖራና ሃገር በቀል ፖለቲከኞች ከሙስናና ሌብነት እንዲሁም ከልዩ ልዩ ጥቅማ ጥቅም  የነፁ፣ ህዝብን የሚያስቀድም ሥነምግባር ያላቸው መሆናቸውን ማሳያቸው የአዲሱ ለውጥ ጊዜ አሁን ነው እንላለን!!! ህወኃት ኢህአዴግ መንግስት የተጠላው በሙስና ተግባሩ መሆኑን ለቅንጣት አትጠራጠሩ!!! ሙስናን የሚጠየፍ ትውልድ በምላስ ሳይሆን በተግባር እንፍጠር!!!